Skip to content

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ብሔራዊ ባንክንና የፋይናንስ ድርጅቶችን ከሰሱ-አክሲዮኖቾቻቸው ባሉበት እንዲቆይ ፍርድ ቤት ዕግድ ሰጠ- ከ276.6 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝበር የተጠረጠሩ ኃላፊዎች ታሰሩ

በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በንግድ ባንኮችም ሆነ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የአክሲዮኖች ባለቤት መሆን እንደማይችሉ በወጣው መመርያ ምክንያት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷብሔራዊ ባንክን፣ ኅብረት ባንክንና ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያን ከሰሱ፡፡

በካሊፎርኒያ ነዋሪ የሆኑትና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወ/ሪት ሶፊያ በቀለ በጠበቃቸው አቶ ዮሴፍ ኪሮስ አማካይነት ብሔራዊ ባንክን፣ ኅብረት ባንክንና ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያን በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ከሰዋል፡፡

ግለሰቧ ብሔራዊ ባንክን የከሰሱት ባወጣው መመርያ ኅብረት ባንክና ኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ያላቸውን አክሲዮን እንዲመልሱ፣ ካልመለሱ ግን መንግሥት እንደሚወርሰው በመግለጽ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ማድረጉን በመቃወም ነው፡፡

ከሳሽ የኅብረት ኢንሹራንስ መሥራች የነበሩት አባታቸው እያንዳንዳቸው 1,000 ዋጋ ያላቸው 288 አክሲዮኖችንና እንዲሁም ከኅብረት ባንክ (መሥራች ናቸው) 4,066 አክሲዮኖችን በውርስ እንደተላለፈላቸው በክሳቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ የአክሲዮኖቹን ድርሻ ያገኙት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካላቸው አባታቸው መሆኑን የገለጹት ከሳሽ፣ ማንኛውም ሰው በስሙ ተመዝግቦ የሚገኝን ንብረት የመጠቀምና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ለፈለገው ሰው ያለክፍያና ያለምንም ገደብ የማስተላለፍ መብት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(1) እና በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1205(2) መደንገጉንም አስረድተዋል፡፡

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን መሠረታዊ መብት የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መመርያው ከመውጣቱ በፊት በውርስና በተለያዩ መንገዶች የተላለፉና በከሳሽ ስም የተዘዋወሩ አክሲዮኖች ወደ ኋላ ተመልሰው ሊፈጸሙ እንደማይገባቸውም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘው የአክሲዮን ድርሻ ላይ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም እንዲባልላቸው፣ በጠበቃቸው በኩል ክሳቸውን አቅርበዋል፡፡ በሕግ የተከበሩላቸውን አክሲዮኖች ለፈለጉት ሰው የማስተላለፍ መብታቸውን ተጠቅመው፣ አክሲዮኖቻቸውን ማስተላለፍ እንዲችሉ እንዲወሰንላቸውም አመልክተዋል፡፡

Related stories   የ80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን በአዲስ አበባ ተከበረ

ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ብሔራዊ ባንክ፣ ኅብረት ባንክና ኅብረት ኢንሹራንስ መልስ እንዲሰጡና በከሳሽ ስም የሚታወቁ አክሲዮኖች ባሉበት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ክስ ለመስማት ለየካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በርካታ ባለድርሻዎች በተለያዩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ ክስ መመሥረታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሌላ ዜና በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የፋይናንስ የሥራ ሒደት ዳይሬክተርና የደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር የሥራ ሒደት ዳይሬክተር፣ ባንኩን ከ276.6 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝበር ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የባንኩ ኃላፊዎች አቶ ሳሙኤል ግርማ ደሴና አቶ በለጠ ዋቅቤካ ሂርጳ ናቸው፡፡ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው በባንኩ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ላይ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡

Related stories   ምርጫውን ለማደናቀፍ ያሴሩ አካላት ህልማቸው አይሳካም – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በቅርንጫፉ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት በቅርንጫፉ ‹አካውንት ሪሲቨብል›፣ ‹ኤክስፖርት ሴትልመንት አካውንት› የሚባል ሒሳብ ከባንኩ ዕውቅና ውጪ በመክፈትና ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር፣ 276,675,572 ብር ባንኩ እንዲመዘበር ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመራቸው እንደሚገኝ ፖሊስ በማስረዳት፣ የወንጀል አፈጻጸሙ ውስብስብና አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

ዜናው የሪፖርተር ነው፣ ታምሩ ጽጌ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
አዲስ አበባ አታብድም፤ ግን ምላጭ ውጣለች

...ያበደው " እመኑኝ" ይላል። አዲስ አበባን የሚመቻት በልኳ የሚሰፋ ፖለቲካና ፍልስፍና ከልተበጀ  አትነቃነቅም። ሁሉን ስላቀፈች ለሁሉም ቤት እንዳትሆን ለሚጎትቷት መልስ...

Close