የጎንደር፣ የአኵስም፣ የላሊበላና የጃንሜዳ አብሕርተ ምጥማቃት በናሙናነት ተመርጠዋል
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የጥምቀት በዓል አከባበርን፣ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ባህላዊ የዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት ሊያካሒድ ነው፡፡
ሰነዱን ለማዘጋጀት በዘንድሮው የጥምቀት ክብረ በዓል፣ በድምፅና ምስል እንዲሁም በጽሑፍ መረጃዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን፤ በጎንደር፣ በአኵስም፣ በላሊበላና በጃንሜዳ የሚገኙና ታቦታት የሚያድሩባቸው አብሕርተ ምጥማቃት፣ በናሙናነት መመረጣቸው ተገልጿል፡፡
ጥምቀት በልዩ ገጽታ በሚከበርበት በጎንደር ከተማ፣ ሥነ በዓሉን በቪድዮ ካሜራ በመቅረፅ፣ ፎቶግራፍ በማንሣት፣ የጽሑፍ አስረጅዎችን በመሰብሰብና የሚመለከታቸውን የሥራ ሓላፊዎች በማነጋገር የመስክ ሥራ የሚያከናውን የባለሥልጣኑ የባለሞያዎች ቡድን ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ወደዚያው የተሰማራ ሲሆን እስከ ወሩ መጨረሻ በዚያው እንደሚቆይ ተጠቅሷል፡፡ በርካታ ታቦታት በሚያድሩበትና በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ በሚከበርበት የአዲስ አበባ ጃን ሜዳን ባሕረ ጥምቀት ጨምሮ በሰሜን ወሎ  ላሊበላና በማዕከላዊ ዞን ትግራይ  አኵስም፤ አከባበሩን በቪዲዮ በማስቀረፅና የፎቶግራፍ መረጃዎችን በመውሰድ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትብብር እንድታደርግ ባለሥልጣኑ መጠየቁን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ሓላፊ፣ ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሓላፊው ገለጻ፣ የድምፅ፣ የምስልና የጽሑፍ መረጃዎቹ፣ በዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በአግባቡ ከተሰበሰቡ በኋላ የሚዘጋጀውን የማስመረጫ ሰነድ በቀጣዩ ዓመት ለዩኔስኮ ለመላክ  መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
የማስመረጫ ሰነዱ፣ የጥምቀት በዓል አከባበርን፣ በዩኔስኮ በሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር  ውስጥ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማካተት የሚያስችል ዝግጅት እንደኾነ ተገልጧል።
የክርስቶስ ጥምቀት መታሰቢያ በማድረግ በየዓመቱ በዋዜማው ጥር 10 ቀን ታቦታት ወደ ውኃ ዳር በመወረድ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፤ በዩኔስኮ ከተመዘገበ፣ በክርስትና ሃይማኖት ከመስቀል በዓል በመቀጠል ሁለተኛው የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ይሆናል፤ ተብሏል፡፡

by Adissadmass news ናፍቆት ዮሴፍ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *