“Our true nationality is mankind.”H.G.

እነ ስዬ አብርሃ የበተኑት መግለጫ (ታሪካዊ ሰነድ) መጋቢት 1993፤ ዛሬስ?አብዮታዊ አንድነት ለድርጅታችን! ውድቀት ለአምባገነኖች! ሉዓላዊነታችን ለዘላለም ተከብሮ ይኑር!

የተከበራችሁ ታጋዮችና የሕወሓት አባላት

በአሁኑ ወቅት በድርጅታችን በተለይም ደግሞ የድርጅታችን አመራር በሆነው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እጅግ በጣም ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል። ምንም እንኳን ለሕሊናችን ቀላል ሆኖ ባይገኝም ሌላ አማራጭ ባለማግኘታችን በዚህ ጹሑፍ ልናወሳው ተገድደናል።

ይህንን ችግር ሳይውል ሳያድር ልናሳውቃችሁ ግዴታችን ከመሆኑ ባሻገር ሁኔታዎች በራሳቸው አስገድደውናል። ከምትጠብቁትና ከምትመኙት ውጭ በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የተፈጠረውና በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ችግር ዋንኛ መንስዔ ከሻዕቢያ ወረራና ምከታው ጋር የተዛመደ ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው ሻዕቢያ አገራችንን በግፍ ወረረ፡፡ የወረራውም ዓላማ በሃገራች ላይ እኩይ ፍላጎቱን ለመፈፀምና የአገራችንን ሃብት ለመዝረፍ እንቅፋት ናቸው ያላቸውን ሕወሓት/ኢህአዴግን ለማጥፋትና የትግራይን ሕዝብ ለማበሳበስ ነበር። ከወረራውም በኋላ የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ተነስቶ ወረራውን መመከት ጀመርን።

በዚህም ጊዜ ውስጥ የተያዘብን መሬት ሁሉ ሳይመለስና ሻዕቢያም መሬታችንን ለመልቀቅና ሰላምን ለመፍጠር ዝግጁ ባልነበረበት በ1991 ክረምት ላይ አሜሪካና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ያዘጋጁት የመፍትሔ ሰነድ ለኢህአዴግ ይቀርባል።

ይህ ሰነድ ሉዓላዊነታችንን የማያስከብር በሻዕቢያ የተደፈረው መሬታችንን በዝርዝር ተቆጥሮ የሚመለስ ለመሆኑ ዋስትና የማይሰጥ፤ ሚሊሺያዎቻችን ከነትጥቃቸው እንዳይመለሱ የሚያግድ፤ ድርጅታችንና አስተዳደራችን ሥራውን እንደድሮው ያለገደብ እንዳይሰራ የሚከለክል፤ የውጭ ዜጐችን የማባረር ሉዓላዊ መብታችንን የሚነፍግ መሬታችንን የሚመለስ መሆኑን ባላወቅንበትና ባላስመለስንበት አሜሪካ የምትቆጣጠረውና እስከመቼ ሊቆይ እንደሚችል እንኳን ያልታወቀ የሰላም አስከባሪ ኃይል ሻዕቢያ በሚለቀው መሬታችን ላይ እንዲሰፍር የሚያመላክት ሰነድ ነበር።

ፈፅሞ ሉዓላዊነታችንን የማያከብር ሰነድ ነበር። ይህን ሰነድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተወያይቶበት ውድቅ አደረገው። ሰነዱ በኢህአዴግ ስር ለተዋቀሩ ድርጅቶች ቀርቦ ስለነበር በሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥም ሰፊ ክርክር ተካሄድበት ያኔ ማዕከላዊው ኮሚቴው ለሁለት ተከፈለ።

በአንድ ወገን ይህን ሰነድ ሉዓላዊነታችንን ስለማያስከብር ውድቅ ልናደርገው ይገባል የሚል ሃሳብ ሲቀርብ በሌላኛው በኩል ደግሞ «የለም ይህ ሰነድ ሉዓላዊነታችንን አይፃረርምና ልንቀበለው ይገባል» የሚል ሃሳብ ቀረበ። ይህን ሰነድ እንቀበለው ከሚሉት ወገኖች መከራከሪያ ሆኖ ይቀርብ የነበረው አንዱ ሃሳብ «ይህን ሰነድ ካልተቀበልን ኃያላኑ ይደቁሱናል! ማናቸውም ዓይነት ማዕቀብ (የነዳጅ የንግድ፤ የአይሮፕላን፤ የእርዳታ) በላያችን ያርፋል» የሚል ለጉልበተኞች ተንበርክከን ሉዓላዊነታችንን ከማስከበር ወደኋላ እንድንል የሚገፋፋ እጅግ በጣም አሳፋሪ ሀሳብ ነበር።

ከሙግትና ክርክሩ በኋላ «ሰነዱን አንቀበልም» የሚለው ሃሳብ በድምፅ ብልጫ አሸነፈ። የድምፅ ልዩነቱ ግን አራት ብቻ ነበር። አንቀበልም የሚል 17 ድምፅ እንቀበል የሚል 13 ድምፅ ነበር። ሰነዱን አንቀበልም ከሚሉት ውስጥ ገብሩ አስራት፤ አባይ ፀሐዬ ስዬ አብርሃ፤ አለምሰገድ ገ/አምላክ. ተወልደ ወ/ማርያም አረጋሽ አዳነ አውአሎም ወልዱ ቢተው በላይ አብርሃ ማንጁስ ገ/መስቀል ኃይሉ ሃሰን ሽፋ ሰሎሞን ተስፋዬ ኪሮስ፤ ፀጋይ ቅዱሳን ጎብዛን፤ አባይ ወልዱ ነበሩ።

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

ሰነዱን እንቀበል ያሉት ደግሞ መለስ፤ ስብሓት ስዩም፤ ሙሉጌታ፤ አርከበ፤ አባዲ፤ ቴዎድሮስ፤ ሐዱሽዓለም፤ ብርሃነ፤ ትርፉ፤ ጌታቸው፤ ክንፈ፤ ጫልቱ ነበሩ።

ይህ እንዳለ ሆኖ ሰነዱን እንቀበል አንቀበል እንፈርም አንፈርም ከሚለው የማዕከላዊ ኮሚቴ ክርክርና መከፋፈል አስቀድሞ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና በሌሎችም ኮሚቴዎች ውስጥ ሕወሃትን ወክለው ይሳተፉ በነበሩ የፖሊት ቢሮ አባላት ውስጥም ልዩነት ተፈጥሮ ነበረ።

ይህን በሰነዱ ምክንያት የተፈጠረውን ልዩነትና አስቀድሞም ይስተዋል የነበረውን የፖሊት ቢሮ አባላት መከፋፈል ግምት ውስጥ ያስገባው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህ ችግር በፖሊት ቢሮ አንዲታይና መፍትሔም እንዲገኝለት መመሪያም ይሰጣል። የፖሊት ቢሮውም የውይይት አካሄድን ለመጀመር የሚያስችሉ አንዳንድ አጀንዳዎችን ማየት ይጀምራል። ይሁን እንጂ የፖሊት ቢሮው ስብሰባ ከመጠናቀቁ በፊት በኢትዮጵያ ሕዝብና በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ቁርጠኛ ትግል ጦርነቱ በድል ይጠናቀቃል።

ጦርነቱን እንዳበቃም ያን በአመራር ውስጥ የተከሰተውን ችግር በማዕከላዊ ኮሚቴው መድረክ ላይ እንድናየው ተስማምተንና ዝግጅትም ተደርጎበት በወርሃ ጥር 1993 ውይይት ጀመርን። ለአንድ ወር ያህልም በአንድ አጀንዳ ላይ ብቻ ተወያየን። ያን ውይይትም ስንጀምርም አንድነትና መግባባት ይፈጠራል። ውይይቱም በጥሩ መንፈስ ይካሄዳል የሚል እምነት ነበረን።

በሂደት የታየው ነገር ግን የማዕከላዊ ኮሚቴውን ተስፋ ያጨለመ ነበር። መድረክ ላይ የሚቀርቡትና የሚንፀባረቁት አመለካከቶች ሁሉ ከመድረክ ውጭ በሚነዙ አሉባልታ፤ በስማ በለው ከሚነገሩ ሃሜትና ሹክሽክታዎች ጋር ሲያያዙ ማስተዋል ጀመርን። የመጀመሪያው አጀንዳ ውሳኔም የዚሁ ጥላ ያረፈበት መሆኑን ተገነዘብን። ሰነዱን እንፈርም፤ አንፈርም በሚለው የክርክር ወቅት የጉልበተኛን ተፅዕኖ ፈርተን ሉዓላዊነታችንን የማያከብር ሰነድ እንድንፈርም ይገፋፋን ከነበረው ወገን አንዳንዱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እኛን ለማጨለም በሰፊው ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተረድተነዋል።

የእንቅስቃሴው ዓይነተኛ አካሄድ ደግሞ «ኮራፕሽንና ፀረ ዴሞክራሲ» የሚል ነበረ። በተለይም ደግሞ «ኮራፕሽን» በሚለው ላይ ያነጣጠረ ነበር። ለሃገር ሉዓላዊነት በፅናት የቆመን ወገን በዚህ ዓይነት ክስ ለመወንጀልና ለማጠየም ለማግለልና ለመነጠል ጥረት ያደርግ ነበር የሚል እምነት አለን።

በመጀመሪያው አጀንዳ ላይ ታይቶ እንደነበረው የማዕከላዊ ኮሚቴው ውይይት አንድነትና የሃሳብ መቀራረብ ሳይሆን የተፈጠረው የማዕከላዊ ኮሚቴውን ተስፋ በመጠኑም ቢሆን ያላሟላና መጎነታተሉንም እያጠናከረ የመጣ ሆነ። ውሳኔውም በሁለት የድምፅ ልዩነት ማለትም 15 የድጋፍ 13 የተቃውሞ ድምፅ ሆነ። ያ አካል ወደአለመደማመጡ ደረጃ ወረደ። የአንድነትና የሃሳብ መቀራረብ ፋይዳ ወደሌለው ውይይት ተቀየረ።

ከዚህም በላይ እየታገልንባቸው የመጣንባቸው ዓላማዎች በጥያቄ ምልክት ውስጥ እየገቡና በግልፅ እየተመቱ በአዲስ አመለካከት እየተተኩ ለንትርኩና ውዝግቡ መነሻ እየሆኑ መጡ። ሌላው በጹሑፍም ይሁን በክርክር የሰማነው ዲሞክራሲን የሚመለከት ነጥብ ነው። የድርጅታችን ዲሞክራሲያዊ አመለካከት ሰፊውን ሕዝብ ማለትም ሰርቶ አደርና ገበሬውን የሚጠቅም ሕዝባዊ ዴሞክራሲ የሚል ነው። ዛሬ ግን የቡርዧውን ዴሞክራሲ እየገነባን ወደ በለጠ ከፍተኛ ደረጃ እናድርሰው የሚል ሰማን።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

የቡርዧ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም ወደ ሕዝባዊ ዴሞክራሲ ሊለወጥ አይችልም። ሕዝባዊ ዴሞክራሲ የሚለውን የድርጅታችንን እምነትና አቋም ለምን ማጥላላት እንደተጀመረ ለኛ አይገባንም። የድርጅታችን ያልሆኑ ሌሎች የተለያዩ አመለካከቶችም ነበሩ። እነዚህ ሁሉ በድምሩ ወያኔያዊና ሕዝባዊ ድርጅታችንን የሚሸረሽሩና መሰረቱንም የሚቀይሩ አመለካከቶች ናቸው።

ሉዓላዊነታችንን የማስከበር ትግል ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ የድርጅታችንን ወያኔያዊ ዓላማ ለማጥፋት ዘመቻው ተጀምሮብናል።

የታገልንላቸውን አሁንም እንተገብራቸዋለን የምንላቸውን ዓላማዎች በዚህ ዓይነት መንገድ በጠባቡ የማዕከላዊ ኮሚቴ መድረክ በብርቱ ጥቃት ስር ሲወድቁ ዝም ብሎ ማየትን አልመረጥንም ሕሊናችንም አይፈቅድልንም።

ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ እንመለስ በስብሰባውም ሆነ ከስብሰባው ውጭ በነበረ መንፈስ ፋይዳ ያለው ለድርጅትም ይሁን ለሕዝብ የሚጠቅም ስብሰባ ሊካሄድ ይችላል የሚል እምነታችን እንደተሟጠጠ 12 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የፈረሙበትን ሰነድ ለማዕከላዊ ኮሚቴ አቀረብን።

ያቀረብነውም ሰነድ ሁለት ነጥቦችን የያዘ ነበር። ነጥቦቹም፦

የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በያዘው መንፈስ ቢቀጥል ፋይዳ ያለው ውጤት ስለማይኖረው አስቸኳይ ጉባዔ ተጠርቶ ጉዳዩን ጉባዔው እንዲመክርበትና ዕልባት እንዲያበጅለት የመጨረሻ ብይን እንዲሰጥበት፤

የስነምግባር ጉድለት ዘመድ መጥቀም የስልጣን ብልግና ይኼንና የመሳሰሉትን የሚያጣራ ኮሚቴም እንዲቋቋም. ይህ ደግሞ ለድርጅታችን ጥራት ይጠቅማል የሚል እምነት አለን። ሁሉም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በዚህ የማጣራት ሂደት ውስጥ አልፈው ሪፖርቱ ለጉባዔው እንዲቀርብና ጉባዔውም እንዲወስንበት የሚል እምነት አለን።

ይህም ልክ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ በጥቅም ላይ እየዋሉ ላሉ ሃሜታዎች መቋጫ ሊያስገኝ ይችላል። ይህን ያቀረብነውን ሰነድ እኚያ 15 እና 16 አባላት በተካሄደው የ4 ሰዓታት የውይይት ጊዜ ውስጥ ሊቀበሉት አልፈቀዱም ውይይቱ ይቋረጥና በነጋታው እንቀጥልበት ተባለ።

በነጋታውም ስብሰባው ይቆይና ያን ሰነድ በተወሰኑ አካላት እንወያይበት የሚል ሃሳብ አቅርበን ተቀባይነት አላገኘም። ከዚያ በኋላ ሰነዱን ካቀረብነው 12 የማዕካላዊ ኮሚቴ አባላት ውጭ የሆኑት 15 እና 16 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከድርጅታችን ሕገ ደንብ ውጭ «ኮረም» ወይም ምልዕተ ጉባዔው ባልተሟላበት ሁኔታ «የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ» በማለት ብቻቸውን ቀጠሉ። እንደማዕከላዊ ኮሚቴ ሆነውም ውሳኔዎችን ያሳልፉ ጀመር። በሕገ ደንባችን መሰረት ምልዕተ ጉባዔው ሞልቷል የሚባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ 20 አባላት ሲገኙ ብቻ እንደሆነ እነርሱም እኛም ጠቅላላው ድርጅታችንም የሚያውቀው ነው።

ከዚህም በላይ ደግሞ የድርጅታችንን ሕገ ደንብ በመጣስ አስር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን (ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ የፖሊት ቢሮ አባላት ናቸው) ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታችሁ አግደናችኋል ብለውናል። አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሚታገደው በ2/3ኛ የማዕከላዊ ኮሚቴ ድምፅ ብቻ እንደሆነ እነርሱም ያውቁታል። 20 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሲደግፍ ነው ይህ ዓይነቱ እርምጃ መውሰድ የሚቻለው። 15 ወይም 16 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተሰብስብሰው ይህን መሰል አስደማሚና ሕጋዊ እርምጃ በፍፁም መውሰድ አይችሉም።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

የድርጅታችን ሕገ ደንብ ብጣሽ ወረቀት አይደለም። የምንመራበት ሕጋችን ነው። ማንም አካል ሊጥሰው አይችልም። እኛ ድርጅታዊ ሕጋችንን መሰረት ያደረገ ፍትሕ እንዲመጣ እንፈልጋለን። በዚህም መሰረት ጉዳያችንን በድርጅት ኦዲት ኮሚሽን እንዲታይልን ሃሳባችንን በጹሑፍ አቅርበናል። ውጤቱንም እንጠብቃለን።

ጥያቄያችን አስቸኳይ ጉባዔ ይጠራልን ነው።

ጥያቄያችን ልዩነታችንን የሚያጣራ አካል ቆሞ ድርጅታችን ይፅዳ እውነቱ ይታወቅ ነው።
ይህን ጥያቄ በማቅረባችን በሕግ ሊያግደን በማይችል ቡድን ልንታገድ አይገባም። በእኛ እምነት ይህ አካል ወይም ቡድን ፍትሐዊ በሆነ አግባብ በተጠራ ጉባዔ ፊት ቀርቦ የጉባዔውን ውሳኔ ሊቀበል ዝግጁ አልሆነም።

ይህ ቡድን የሚፈልገው በሐሜትና አሉባልታ የቦካ ጉባዔ ነው። ይህ አካል እውነቱ እንዲጣራ አይፈልግም። እሱ የሚፈልገው በሐሜት በልጦ መታየትን ብቻ ነው።

የተከበራችሁ የሕወሓት ታጋዮች

ይህ በሻዕቢያ ወረራ ጊዜ ለአፄዎች ተንበርክኮ ሉዓላዊነታችንን የሚጥስ ሰነድ እንፈርም ያለ የማዕከላዊ ኮሚቴ ቡድን፤ ይህ መሰረታዊ ዓላማችንን ለይምሰል እጠብቃለሁ እያለ ነገር ግን ሊሸረሽር ካልሆነለትም ጨርሶ ሊያጠፋው የሚሯሯጠው የማዕከላዊ ኮሚቴ ቡድን፤

ይህ ድርጅታዊ መዋቅርና ሕጋችንን ያለምንም ማፈግፈግ እየጣሰ ያለ ቡድን፤ ይህ የአመራር አቅማችንን ለመበታተን ለመምታት በሉዓላዊነት ላይ ለምን አገራዊ መስመር ይዛችሁ በፅናት ተቃወማችሁኝ በማለት ለጥቃትና ለጥፋት የተነሳ ቡድን ድርጅታችንን ጨርሶ ከመቆጣጠሩና እሱ ወደሚፈልገው የጭቁን ሕዝብና የሃገር ጥቅምን ወደሚፃረር መንገድ ሳይመራውና ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ በፊት በጋራ እንታገለው።

የእኛ ፍላጎት አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራ ነው። ለሕዝቡ የሚጠቅም ቅን ዓላማ አለኝ የሚል ከሆነ ወደ ጉባዔ ይቅረብ ስለሆነም ደግሞ ሁሉም የድርጅት አባል በየአካሉ ሆኖ ለአስቸኳይ ጉባዔው መሰናዶ እንቅስቃሴ ይጀምር። ያ አንድ ወገን እያካሄደ ያለው ሕጋዊ ያልሆነ እንቅስቃሴም እንዲቆምና ድርጅታዊ መዋቅራችንን እንዲከበር በፅናት ታገሉ!!

አብዮታዊ አንድነት ለድርጅታችን!
ውድቀት ለአምባገነኖች!
ሉዓላዊነታችን ለዘላለም ተከብሮ ይኑር!

1. ተወልደ ወ/ማርያም (የሕወሓት የፖሊት ቢሮ አባል)
2. አባይ ፀሐዬ (የሕወሓት የፖሊት ቢሮ አባል)
3. ገብሩ አስራት (የሕወሓት የፖሊት ቢሮ አባል)
4. ስዬ አብርሃ (የሕወሓት የፖሊት ቢሮ አባል)
5. ዓለም ሰገድ ገ/አምላክ (የሕወሓት የፖሊት ቢሮ አባል)
6. አረጋሽ አዳነ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
7. አውአሎም ወልዱ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
8. ገ/መስቀል ኃይሉ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
9. ሐሰን ሽፋ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
10. ሰለሞን ተስፋዬ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
11. አብርሃ ካህሳይ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
12. ቢተው በላይ (የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
—-
ይህ መግለጫ በኢትኦጵ ጋዜጣ የመጋቢት 12 ቀን 1993 እትም ላይ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚያው ወር በታተመው ኢትኦጵ መጽሔትም ላይ ወጥቷል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0