ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሳዑዲ ዓረቢያ እና ግብፅ፣ ለምን የሕዳሴውን ግድብ እንደ የፖለቲካ ካርድ መምዘዝ አስፈለጋቸው?

በግብፅ ታሪክ በሕዝብ የተመረጡ ብቸኛ መሪ መሆናቸው የሚነገርላቸው፤ የሆኑትም፤ ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲ ናቸው። ሙርሲን ከመንበረ ስልጣናቸው ለማውረድ የግብፅ ጦር ሰራዊት እና የሳዑዲ ዓረብያ ረብጣ ፔትሮ ዶላር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ይህ ማለት ግን ሙርሲ ከመንበረ ስልጣናቸው ለመውረድ የእሳቸው የፖለቲካ አመራር ውድቀት አስተዋፅዖ አልነበረውም ማለት አይደለም። በተለይ የግብፅ ሕገ-መንግስትን ከቁርዓን መፅሐፍ መነሻ በማድግ ለመቅረጽ መሞከራቸው፣ ከግብፅ የሊብራል አራማጆች እና ከግብፅ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተቃውሞ የገጠማቸው መሆኑ አይዘነጋም። ይህም ቢሆን በውይይት እና በድርድር ብቻ መፈታት እንደነበረበት አከራካሪ ነጥብ አይደለም።

በሕዝብ የተመረጡትን የግብፅ ፕሬዝደነት መሐመድ ሙርሲን ከመንበረ ስልጣናቸው አባረው በታክቲካል የፖለቲካ ፍቅር ብን ብለው የነበሩት፣ የግብፅ ጦር ሰራዊት መሪዎች እና የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ዛሬ እሳት እና ጭድ ሆነው ተገኝተዋል። ሁለቱም በየፊናቸው አንዱ ሌላው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እየሰሩ ይገኛሉ። አለፍ ብለውም በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ ሀገሮች ውስጣዊ ፖለቲካ ዘልቀው በመግባት ለማማሰል ደፋ ቃና እያሉ ነው። ሁለቱ ሀገሮች በግብፁ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ዋጋ የመሰረቱት ወቅታዊ የፖለቲካ ጋብቻ ምን አፈራረሰው? የመካከለኛው ምስራቅ አህጉራዊ የፖለቲካ ቁርሾን ወደ አፍሪካ ቀንድ ለማምጣት ለምን ተጣደፉ? እና ሌሎችም ጥያቄዎችን ማስቀመጥ ይቻላል። በዚህ ጽሁፍ የቻልነውን እንመለከታለን።

በግብፅ እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የተፈጠረው ቁርሾ   ማጠንጠኛዎቹ ምንድን ናቸው?

ማጣቀሻዎች እንደሚያሳዩት በግብፅ እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቁርሾ መነሻዎቹ፣ ሁለቱ ሀገሮች በዓረቡ ዓለም በሚገኙ የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ፓርቲዎች ወይም ተዋጊዎች ላይ ያላቸው ፖለቲካዊ አረዳድ፤ በየመን እና በሶሪያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ አፈታት ዙሪያ፤ ኢራን በመካከለኛ ምስራቅ ፖለቲካዊ ውስጥ ያላትን ሚና እያደገ መምጣቱን የሚረዱበት መንገድ ለመሰረታዊ ልዩነታቸው በምክንያትነት ይቀመጣል።

ከመጨረሻው ነጥብ ብንመለከተው፣ ኢራን በመካከለኛ ምስራቅ ፖለቲካዊ ውስጥ ያላትን ሚና እያደገ መምጣቱ ለሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች በቀላሉ የሚዋጥ አይደለም። ይህም በመሆኑ የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ለረጅም ዘመን ሲያወግዙት ሲዋጉት የነበሩትን በሱኒ እምነት ስር የተሰባሰቡትን የሙስሊም ወድማማቾች ሕብረት እንቅስቃሴን እንዲቀበሉት ተገደዋል። ምክንያታቸው ደግሞ፣ ኢራን የምትመራው የሺዓ ሙስሊሞች ሕብረትን ለመግታ፣ ለመመከት ያለመ ነው። በተለይ ኢራን ከዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ የቀረበውን የኒውክለር ቦምብ ማምረት ሒደቷን የሚገታውን (JCPOA_P5+1) ስምምነት መቀበሏ እና ከዓለም ዓቀፉ የንግድ ሕብረተሰብ መቀላቀሏ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እንቅልፍ የነሳት ያልተጠበቀ ፖለቲካዊ ክስተት ነበር።

ይህ ያልተጠበቀው የሳዑዲ ዓረቢያ የፖሊሲ ለውጥ ማለትም፣ በዓረቡ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን የሙስሊም ወድማማቾች ሕብረት እንቅስቃሴ መቀበል፤ በጀነራል አብዱል ፋታህ አልሲሲ የሚመራው የግብፅ ወታደራዊ መንግስት ፈጽሞ የማይቀበለው ሆኖ ተገኝቷል። ምክንያቱም በግብፅ ምድር ውስጥ የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ፓርቲ በአሸባሪነት ከመፈረጁም ባለፈ፣ ፓርቲው እንዲፈርስና የፓርቲው ንብረቶች ወደ መንግስት እንዲጠቃለሉ ውሳኔ ከተሰጠባቸው አመታት አስቆጥረዋል። የግብፅ ወታደራዊ መንግስት የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ፓርቲ የግብፅ ሥርዓት አደጋዎች አድርጎ ነው የሚወስዳቸው። ቱርክ እና ኳታር እንቅስቃሴውን በመደገፋቸው ከሁለቱ ሀገሮች ጋር የሻከረ ግንኙነት እስከ መመስረት ደርሰዋል። ሳዑዲ ዓረቢያ በበኩሏ ከቱርክ እና ከኳታር መንግስታት ጋር የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ፓርቲን በተመለከተ በጋራ ትሰራለች። ከዚህም ባለፈ በቀጣይ በሶሪያ እና በየመን የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ፓርቲ በአመራርነት ለማስቀመጥ ሳዑዲ እየሰራች ትገኛለች።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ግብፆች በበኩላቸው ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ሚናዋ ከፍ እያለ መምጣቱን እንደስጋት አይወስዱትም። ይህም በመሆኑ ግብፆች፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ኳታር በፈበረኩት “የሱኒ እና የሺዓት” የእምነት የክፍፍል ጦርነት ውስጥ መሳተፍ አይፈልጉም። ፅንሰ ሃሳቡንም አይቀበሉም። እንደውም ጀነራል አል-ሲሲ በኢራን ላይ የተጣለውን የንግድ ማዕቀብ በማንሳት በአዲስ መልኩ ከኢራን ጋር የንግድና የቱሪዝም ግንኙነት ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል። በርግጥ በኢራን እና በግብፅ መካከል በቀላሉ ሙሉ ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት እንደማይመሰረት ማጣቀሻዎች ያሳያሉ። ምክንያቱም የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝደነት በነበሩት አንዋር ሳዳት ግድያ ዙሪያ ኢራን እጇ አለበት የሚባል ክስ እስካሁን ስለሚቀርብ ከመተማመን ላይ አልደረሱም።

ወደ ሶሪያ ፖለቲካዊ ቀውስ ስንመለስም በሁለቱ ሀገሮች መካከል መሰረታዊ ልዩነቶች አሉ። ሳዑዲ ዓረቢያ የሶሪያ ቀውስ የሚፈታው ፕሬዝደነት በሽር አልአሳድ ከስልጣን ሲወገዱ ብቻ ነው የሚል አቋም አላት። ብዙ ተግባራዊ እርምጃዎችም ውስጥ ተሳትፋለች። ግብፅ በበኩሏ የሶሪያ ቀውስ ፖለቲካው መፍትሄ ነው የሚገባው የሚል አቋም ታራምዳለች። እንዲሁም ግብፆች፣ ከአሳድ መንግስት ጋር ድርድር በማድረግ የሶሪያ የሲቪል ተቋማት እና የሶሪያ አንድነት በተጠበቀ መልኩ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። የፕሬዝደነት በሽር አላሳድ እጣፈንታም በሶሪያዊያን መወሰን እንዳለበት ያምናሉ። የሳውዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ይህን የግብፅ አቋም በጣም ነው ያበሳጫቸው። አንደኛው፣ ኢራን ለመካከለኛው ምስራቅ ሱኒዎች ስጋት አደለችም የሚል እሳቤ መወሰዱ፤ ሁለተኛው፣ የግብፅ ወታደራዊ መንግስት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ከ10 ቢሊዮን ፔትሮ ዶላሮች አፍስሰውልት ለሳዑዲ ፖሊሲ አለመገዛቱ የእግር እሳት ነው የሆነባቸው።

እንዲሁም በየመን እየተደረገው ባለው ሰብዓዊ እልቂት እና ቁሳዊ ውድመት ላይ ያላቸው አረዳድ ሌላው የልዩነታቸው ማሳያ ነው። የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሳዊ ቤተሰቦች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትንታኒያቸው አስኳል፣ የኢራን በመካከለኛው ምስራቅ በምታደረገው እንቅስቃሴ ዙሪያ የማያጠነጥን ነው። በተለይ ኢራን በሊባኖስ፣ በኢራቅ እና በሶሪያ ያገኘችው ተቀባይነት እና የበላይነት ለንጉሳዊ ቤተሰቦቹ የቀን ቅዠት ሆኖባቸዋል። ይህንን መሰል የኢራን እንቅስቃሴን በሰነዓ-የመን እንዳይደገም፣ በሰብዓዊ እልቂትም ይሁን በቁሳዊ ውድመት በማንኛውም ዋጋ ለማረጋገጥ የሱኒ እምነት ተከታይ ሀገሮች አስተባብረው በየመን ጦርነት ከከፈቱ ሰንበት ብለዋል። ዓለም ዓቀፉ ሕረተሰብም በበኩሉ የሳዑዲ ዓረቢያን ፔትሮ ዶላር በመፍራት፣ የየመን ሕዝቦች እልቂትን አለየሁም አልሰማሁም በማለት እንደሰጎን በንፁሃን ደም በራሰው በየመን ምድር አሸዋ ውስጥ አንገቱን ቀብሮ ይገኛል።

እንደሚታወቀው ሳዑዲ ዓረቢያ እና ግብፅ “Operation Decisive Storm” በሚል ስያሜ የተሰጠውን በየመን ላይ የተከፈተውን ጦርነት በጋራ ለመስራት ተስማምተው ነበር። ሆኖም በግብፅ በሚገኘው በሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ የግብፅ ዜጎች በየመን ላይ የሚደረገውን ጦርነት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። በተንታኞች ዘንድ የግብፅ መንግስት በተዘዋዋሪ ተቃውሞውን የገለፀበት ተደርጎ ተወስዷል። ሆኖም የግብፅ ወታደራዊ መንግስት ከሳዑዲ ጋር የገባውን ስምምነት የሚያከብሩ ምልክቶች አሳይቶም ነበር። ይኽውም፣ የግብፅ አየር ሃይል እና ባሕር ሃይል ጦርነቱን ለመቀላቀል ተንቀሳቅሰው ነበር። ሆኖም በመጀመሪያ በሚደረገው የምድር ውጊያ የግብፅ ወታደሮች ሳይሳተፉ ቀሩ። በአንፃሩ ዓረብ ኤምሬት፣ ሱዳን እና ሞሪታንያ በምድር ውጊያው ተሳትፈዋል።  በዚህ ጊዜ ነበር በሁለቱ ሀገሮች ልዩነት መኖሩ በግልፅ የወጣ።

የግብፅ ወታደሮች የእግረኛ ውጊያ ያልተሳተፉበት በምክንያቶቹ መካከል፣ ከ50 ዓመታት በፊት ግብፅ በየመን ምድር የደረሰባት የጦርነት ኪሳራ በርካታ የግብፅ ወታደሮችን ሕይወት የቀጠፈ በመሆኑ፤ የግብፅ ጦር ሰራዊት ከአሸባሪው አይ.ሲ.አይ.ሲ ጋር ጦርነት ውስጥ በመሆኑ፤ ሳዑዲ ዓረቢያ በየመን የሚገኙትን የሁዚ እና ሳልህ ደጋፊዎችን በማስወገድ በየመን ውስጥ ባለው የሙስሊም ወድማማቾች ሕብረት ፓርቲ በአል-ኢስላህ ፓርቲ ለመተካት ያላትን እቅድ በመቃወም ጦር ሰራዊት አለማሰማረቷ ከቀረቡት በርካት ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከግብፆች በኩል የተሰማው ግን፣ እምነትን መሰረት ያደረገ ፓርቲን በሌላ እምነትን መሰረት ባደረገ ፓርቲ መተካት እኩል ስጋት አላቸው የሚል ነው። ይኽውም፣ የሺዓ እምነት አረማጅ የሆነውን የሁዚ የፖለቲካ ሃይልን አስወግዶ በሱኒ እምነት መሰረት ላይ የተመሰረተውን የአል-ኢስላህ ፓርቲን መተካት ለግብፅ እኩል ተደርጐ በመውሰድ ነው፣ ለሳዑዲ ዓረቢያ ግን የአል-ኢስላህ ፓርቲን ማንገስ ዓላማዋ ነው።

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል

በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የሳዑዲ ልዑካን በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለውን የሕዳሴውን የሃይል ማመንጫ ግድብ ጎብኝቷል። ይህንን ጉብኝት ተከትሎ በግብፅ ካይሮ ከተማ ከፍተኛ የተቃሞ ሰልፍ ተደርጓል። ሆኖም የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች በግብፅ ወታደራዊ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ተጠቅመውበታል። በኢትዮጵያ በኩል ከጉብኝቱ የተገኘ መኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም።

ጀነራል አል-ሲሲ በተፋሰሱ ሀገሮች…

የግብፅ ፕሬዝደነት ጀነራል አል-ሲሲ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ከፕሬዝደነት ሳልቫኪር ጋር በካይሮ ከተማ መወያየታቸውን ተከትሎ፣ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች አዲስ ውጥረት መጀመሩን የዘገቡ በርካቶች ናቸው። በተለይ የሳዑዲ ዓረቢያ የልዑካን ቡድን የሕዳሴውን የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን መጎብኘቱን አያይዘው መዘገባቸው የአል-ሲሲ እና የሳልቫኪር ውይይት የተለየ ትኩት እንዲያገኝ አድርጎታል። እንዲሁም ከዑጋንዳው ፕሬዚደነት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እና ከአስመራ አገዛዝ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታው የጉብኝታቸው ዓላማ ከኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ተደርጎ ለመዘገብ ቀሏል።

ዘገባዎቹን መሬት ካለው ተጨባጭ እውነታ ጋር ለማስታረቅ ግን በጣም እርቁ ነው። ይኽውም፣ የደቡብ ሱዳን እና የአስመራ መንግስታት አሁን ባለቸው መንግስታዊ ቁመና የጥፋት ተልኮን መሸከም በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ አይደሉም። በተለይ ደቡብ ሱዳን የኔሽን ሆነ የመንግስት ግንባታ ሒደቱን ያልጨረሰ በጎሳ ፖለቲካ ተቸንክሮ የቀረ ነው። ይህም በመሆኑ የግብፅን የጥፋት ተልዕኮ ፈፃሚ ለመሆን ቀርቶ፣ እንደሀገር ለመቀጠል ያላቸው ጊዜ የሚቆጠር መሆኑ በስፋት ይታመናል። የኢሳያስ አገዛዝም ቢሆን የግብፅን የጥፋት ተልዕኮ ለመሸከም ሊሞክር ቢችልም፣ ውጤቱ ግን ከአገዛዙ ሕልውና ጋር የተያያዘ የመሆኑ ይቀበላል ተብሎ አይጠበቅም።  የዑጋንዳው ፕሬዚደነት ዮዌሪ ሙሴቬኒ በኢንቴቤ የተፈረመውን የናይል ውሃን በፍትሃዊነት የመጠቀም መርህን የሚዘሉ አይደለም። እንደውም ኢትዮጵያ በናይል ውሃ የመጠቀም መብቷ ሊጠበቅላት ይገባል ብለው በአደባባይ የሚናገሩ ናቸው። ዑጋንዳም ብትሆን 200 ሜጋዋት ለማመንጨት ከቻይና መንግስት ጋር እየሰራች ነው የምትገኘው። እነዚህን ማሳያዎች ካስቀመጥን፣ የጀነራል አል-ሲሲ ጉብኝት ዓላማው ምንድን ነው?

አል ሲሲ የመሐመድ ሙሪስን መንግስት በሃይል በማስወገድ በተወሰኑ የግብፅ ማሕበረሰብ ቅቡልነታቸውን ማረጋገጥ ችለው የነበሩ ቢሆንም፣ ግብፅ ባጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ማሕራዊ መሰረታቸው እየተሸረሸረ መጥቷል። በተለይ ከፍተኛ መጠን ያለው የግብፅ ሕዝብ በመንግስት ድጎማ የሚኖር በመሆኑ የኢኮኖሚ ቀውሱን ተከትሎ ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተጋልጧል። የወደቀውን ኢኮኖሚ ለማንሳት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን የተቀበለው የአል-ሲሲ መንግስት አዲስ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል።

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

አል ሲሲ የግብፅ ማክሮ ኢኮኖሚን ለማሻሻል ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም ከአይ.ኤም.ኤፍ. ጋር ድርድር አድርገው ወደ ሥራ ገብተዋል። በተደረሰው የድርድር ስምምነት ግብፅ በሶስት ዓመታት ውስጥ 12 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአይ.ኤም.ኤፍ. ታገኛለች። ዶላሩ ግን በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የአል ሲሲን ማሕበራዊ መሰረቶች መሸርሸር ጀምረዋል።

ከተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የግብፅ የመገበያያ ፓውንድ በአርባ ስምንት በመቶ የገንዘብ ምንዛሪ ዋጋ ቅነሳ ይደረግበታል። የገንዘብ ምንዛሪ ዋጋ መቀነስ እንደአይ.ኤም.ኤፍ. ምክር የውጭ ንግድ የሚያስፋፋ መሆኑ ቢነገርም በተጓዳኝ የግብፅ የውጭ እዳን የሚጨምርና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባውን እቃዎች ዋጋ አንሮታል። የዋጋው መናር የቀረጥ መጨመርን በማስከተሉ የኑሮው ውድነት በግብፅ እየናረ መሆኑ እየተዘገበ ነው። ሌላው የግብፅ መንግስት ለሕዝቡ የሚያደርገውን ድጎማ እንዲቀንስ አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው። የነዳጅ የኤሌክትሪክ ድጎማ በጣም መቀነስ ወይም ሙሉ ለሙሉ ማንሳት ሌላው ቅድመ ሁኔታ ነው። የስኳር ዋጋ አርባ በመቶ በላይ ሆኗል። የቫት አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። የውጭ ምንዛሬ መገበያያ በገበያ እንዲወሰን ተደርጓል።

የአይ.ኤም.ኤፍ. ቦርድ መግለጫ እንደሚያሳየው፣ ግብፅ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማስተካከያ ፕሮግራሞች ቀርጻ እንደምትቀርብ ነው የሚያሳየው። በተለይ መስተካከል ያለባቸው የግብፅ ገንዘብ ከሚገባው በላይ የምንዛሪ መጠኑ መጨመር። የውጭ ምንዛሪ እጥረት መከሰቱን። የበጀት ጉድለት። ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር። ኢንቨሰትሮች በግብፅ ኢኮኖሚ አለመተማመን። እና ሌሎችንም ያነሳል።

የውጭ ምንዛሪውን ሊብራል ማድረግ። የውጭ ምንዛሪውን መቀነስ። የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን መጨመር። ጠንካራ ሞኒተሪ ፖሊሲ በማበጀት የዋጋ መናርን መቆጣጠር። ዓመታዊ የበጀት ጉድለትን መቀነስ። ስለዚህም ቫትን ወደ ሥራ ማስገባት። የሃይል አቅርቦት ድጎማን መቀነስ። የደመወዝ አከፋፋል ስርዓቱን ማመጣጠን። ቁጠባን በመጨመር ድሃውን ሕዝብ ማገዝ። አስር በመቶ የመንግስት እዳን ለመቀነስ አቅዶ መስራት።

መዋቅራዊ ለውጥ የሚያስፈልገው፣ እድገቱን ተከትሎ አዳዲስ ሥራዎችን መፍጠር። ለግል ባለሃቶች አመቺ የሥራ ከባባዊ ሁኔታዎችን መፍጠር። የንግድ ሥራ ፈቃድ አሰጣጥና ማስተካከል፣ የሕዝብ ሃብቶች ማስተዳደር፣ በመንግስት የተያዙ ድርጅቶችን በተገቢው ሁኔታ ማስተዳር፣ የሃይል አቅርቦት ዘርፍና ድጎማን ማስተካከል፤ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲሰራባቸው የሚጠበቁ ናቸው።

እነዚህ ከላይ በቅድመ ሁኔታ የተቀመጡት የአል ሲሲ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። አል ሲሲ የሚመሩት ወታደራዊ መንግስት በሕዝቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ከፍተኛ እምነት የተጣለበት ቢሆንም የግብፅ ሕዝብ ፍላጎትን ሊያሟላ አልቻለም። እነዚህን የግብፅ ሕዝብ ፍላጎት ማሟላት ያልቻለው የአል ሲሲ መንግስት እንደቀድሞዎቹ የግብፅ መሪዎች፣ ሕዝቡን በናይል ውሃ የብሔርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ በመክተት ሊያናውዙት እየሰሩ ናቸው።

በነገራችን ላይ እስካሁን ከነበሩት የግብፅ መንግስታ የተሻለ ሰይጣን እንምረጥ ከተባለ፣ ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ የተሻሉ ሰይጣን ናቸው። ምክንያቱም ቢያንስ በናይል ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ጠረጴዛ ስበበው እንወያይ ያሉ ብቸኛ መሪ ናቸው። ይህንን የአል ሲሲ አስተሳሰብ ለውስጥ የፖለቲካ መታገያ ያደረጉ ደግሞ በርካታ የግብፅ ፖለቲከኞችም አሉ።

ለዚህ ነው፣ የአል ሲሲ የወቅቱ የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ጉብኝት ዋናው መነሻ፣ ውስጣዊ የፖለቲካ ግለት እና የኑሮ ውድነት የፈጠሩትን ውጥረት ለማርገብ የታለመ፤ የማስቀየሻ ስልት ተደርጎ ነው የሚወሰደው።

sendeke news paper በሳምሶን ደሳለኝ