የዝናብ እጥረት ወኔውን የሚሰልበው የግብርና ኢኮኖሚያችን

በይርጋ አበበ

… መለስ ዜናዊ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው በተሾሙ ማግስት ለአገሪቱ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቃል ከገቧቸው ንግግሮቻቸው መካከል “በአስር ዓመት ውስጥ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በቀን ሶስት ጊዜ በልተው እንዲያድሩ አደርጋለሁ” ሲሉ አሜሪካን አገር ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተናገሩት ቃላቸው ቀዳሚው ነው።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊትም ገና ታጋይ በነበሩበት ወቅት ከአንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ንግግር “እኔ የምታገልለት ሀዝብ በርሃብ እያለቀ ነው” ሲሉ መናገራቸው ደግሞ ወጣቱን ታጋይ በጉጉት የሚጠበቅ አዳኝ ተደርገው እንዲታዩ እንዳደረጋቸው ይታመናል።

ሆኖም ግን አቶ መለስ ቃል የገቡለት አስር ዓመት እንደ ደራሽ ውሃ ጅው ብሎ ከማለቁም በላይ እሳቸው ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን ቤተ መንግስት እንደተቆናጠጡ 21 ዓመት አልፏቸው በሞት ተለዩ።  የአገሪቱ ህዝብ የምግብ እጥረት ግን እንደ ድሮው ሆኖ ዘልቋል።  በእሳቸው የስልጣን ዘመን እንኳ ለሁለት ጊዜያት አገሪቱ በከፋ የምግብ እጥረት ችግር ተጋልጣ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።  ባለፈው የመኸር ዓመት (በ2007 ዓ.ም) ኤልኒኖ በፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የተነሳ ደግሞ 100 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ከሚገመተው የአገሪቱ ህዝብ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጋው የእለት ደራሽ ምግብ ፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።  በአገሪቱ በተደጋጋሚ የሚፈጠረው የምግብ እጥረት ምክንያቱ ምንድን ነው? ከዚህ አዙሪት ችግር ለመውጣትስ መደረግ ያለበት መፍትሔ ምንድን ነው? በአሁኑ ወቀትስ በአገሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ከዚህ በታች መልስ የሰጠንባቸው ጉዳዮች ናቸው።  ለጥያቄዎቹ የሚበጁ መልሶች ከቆዩ ሰነዶችና የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንዲሁም ከምሁራን ጸሁፍ የተወሰዱ ናቸው።

እንደገና ዛሬም እንደገና

በ2007 ዓ.ም የመኸር ወቅት ላይ በአገሪቱ ከተከሰተው ድርቅ በብዛት ያጠቃው የምስራቁንና የደቡቡን የአገሪቱ ክፍል ቢሆንም ሰሞኑን ወደ ምስራቅ አማራ እና በደቡባዊና ምስራቃዊ ትግራይ (በአገሪቱ ሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች) በተዘዋወርንበት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ የየአካባቢዎቹ አርሶ አደሮች የገለጹልን “ባለፈው ዓመት ሰማይ ጠሉን ከልክሎን የምናመርተውም ሆነ የምንበላው አልነበረንም።  ለእንስሳቶቻችንም ሆነ ለእኛ (ለሰዎቹ) የሚሆን ቀለብ ያገኘነው መንግስት በሚሰፍርልን እርዳታ ነበር” ሲሉ ነው የተናገሩት።  እንደ አሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪፖርት ከ100 ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብ እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከዓለም በርካታ የህዝብ ብዛት ካላቸው አገራት መካከል በ13ኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች ሲል ይገልጻል።  በዓለም 13ኛ የህዝብ ብዛት ያላት አገር ኢኮኖሚዋ የተገነባው በግብርና ላይ በተለይም በአርሶ አደር ማሳ ላይ በሚካሄድ እርሻ ነው።

አገሪቱ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እድገት እያስመዘገበች እንደሆነ መንግስትም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ገልጸዋል።  ይህ የኢኮኖሚ እድገት የተገኘው ደግሞ በግብርናው ሲሆን ይህ ዘርፍ አጠቃለይ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ 70 በመቶ ድርሻ እንዳለው በ2014 የዓለም የእርሻ ድርጅት የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ መረጃዎችን ዋቢ አደርጎ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።  የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ዓመታትን ያሳለፈው ግብርና ግን ዓመታት በተፈራረቁ ቁጥር የሚጋፈጣቸው ፈተናዎች እየበዙበት ይገኛሉ።  ከእነዚህ ፈተናዎቹ መካከል ደግሞ ድርቅ እና አርሶ አደሩ በዘመናዊ ቴከኖሎጂዎች ታግዞ ማምረት አለመቻሉ ይገኙበታል።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

በ2007 የመኸር ወቅት ላይ በደረሰ ድርቅ የተነሳ ከአገሪቱ ህዝብ ቁጥር 1/5 ያህሉ የእርዳታ ፈላጊ እንደነበር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የሂውማን ራየትስ ዎች እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም የመሳሰሉት) ተገልጿል።  በወቅቱ የነበረውን የችግሩን ጥልቀት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው መግለጫ ግን “ድርቁን ለመቋቋም ከመጠባበቂያ ክምችት በቂ ምግብ” መኖሩን ገልጾ ነበር።  የዕለት ምግብ እርዳታ ፈላጊው ዜጋ ቁጥርም ቢሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚገለጹት ሳይሆን አስር ሚሊዮን ብቻ እንደሆነ ነበር በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በኩል የተገለጸው።

በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ 400 ሺህ ዜጎች መሞታቸውን አሌክሳንደር  ዴ ዋል የተባሉት ጸሀፊ “Evil days: thirty years of war and Famine in Ethiopia” በሚለው መጽሃፋቸው የገለጹ ሲሆን ጸሃፊው ያን ያህል ህዝብ በርሃብ እያለቀ በመንግስቱ ኃይለማሪያም የሚመራው የደርግ መንግስት ግን ከ100 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር አወጥቶ አስረኛ ዓመት የአብዮታዊ በዓሉን ያከብር ነበር ብለዋል።

በንጉሱ ጊዜ 300 ሺህ ህዝብ በርሃብ በሚያለቅበት ዓመት ንጉሱ በ35 ሚሊዮን ዶላር 80ኛ ዓመት ልደታቸውን ሲያከብሩ የአገሪቱ ግብርና ሚኒስትር በበኩሉ በ1966 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት “በአገራችን ያለው የምርት እድገት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሰባት በመቶ ብቻ የቀነሰ ሲሆን የምግብ ዋጋም ቢሆን በተለይ በወሎ ክፍለሀገር (ረሃቡ የበረታበት አካባቢ ነበር) ከወትሮው በተለየ አልጨመረም” የሚል ነበር።

በዚህ ዘመን ደግሞ አገሪቱን የሚገዛት ኢህአዴግ እና አባል ፓርቲዎቹ የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ በከፍተኛ ወጪ የታጀበ መሆኑን የታዘበው የዚህ ጸሁፍ አቅራቢ የብአዴን 35ኛ ዓመት ልደት በሚከበርበተ ወቅት “የፓርቲዎቹ ልደት አከባበርና የአገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች” በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ጠቋሚ ጽሁፍ አዘጋጅቶ ነበር።  በወቀቱም “በዚህ ዓመት የሚከብረው የፓርቲው (የብአዴን) ልደት ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ በዓላቱ ለየት የሚለው ግን በአገሪቱ በየአስር ዓመቱ በሚነሳው ድርቅ ምክንያት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአማራ ክልል ምስራቃዊ ክፍል በርካታ ዜጎች በምግብ እጥረት ምክንያት በሞትና በህይወት መካከል ባሉበት ወቅት መከበሩ ነው።  በዚህ ምክንያትም በርካታ ወገኖች የፓርቲውን ድርጊት እያወገዙት ይገኛሉ” በማለት ጽፎ ነበር።

ለዚህ ጽሁፍ ማጠናከሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከልም የሰማያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ አቶ አበበ ከልካይ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ የብአዴንን የምስረታ በዓል ማክበር “ነውሩን የበላ” ሲሉ ይገልጸውት ነበር።  ሃሳባቸውን ያጠናከሩትም “በአማራ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በምግብ እጥረት ምክንያት እየሞቱ ባለበት በዚህ ወቅት ፓርቲው የምስረታ በዓሉን በዚህን ያህል ወጭ ማክበር ማለት ለህዝብ ያለውን ንቀት ያሳያል።  እኛም እንደ ፓርቲ የብአዴንን ድርጊት አውግዘን መግለጫ አውጥተናል” ሲሉ ተናግረዋል።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

በፓርቲዎቹ የልደት አከባበር ላይ የህዝቡ ቅሬታ ጎልቶ መውጣቱን ተከትሎም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከሪፖርተር ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “በዓላቱ ሲከበሩ የተጋነነ ወጪ አልወጣም ቢበዛ ውሃ ብንጠጣ ነው” ሲሉ ነበር የተናገሩት።

በኤልኒኖ ምክንያት በደረሰው ድርቅ የተነሳ የአርሶ አደሩ ምርት መቀነሱንም ሆነ የአርብቶ አደሩ የቁም እንስሳት መሞትና ዋጋቸውም መውረዱ ይታወቃል።  በዚህ ዓመትስ ምን ይመስል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ባሳለፍነው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባላት ለተነሱላቸው ጠያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት “በመኸር ወቅት ብቻ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ12 በመቶ ብልጫ ያለው የግብርና ምርት አግኝተናል።  ይህ በመስኖ የሚሰበሰበውን ሳይጨምር ነው።  የመስኖው ሲሰበሰብ ልዩነቱ ይጨምራል።  የመኸሩ በራሱ ጥሩ ለውጥ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል” ሲሉ ተናገረዋል።

በቅርቡ ወደ ምሰራቅ አማራ እና ደቡብና ምስራቅ ትግራይ የገጠር ቀበሌዎች ተዘዋውሮ የአርሶ አደሮቹን ኑሮ ተመልክቶ የተመለሰ የጋዜጠኞች ቡድን ነበር።  በዚህ ጉዞ ከተመለከትናቸው እና መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች የሚያመለከቱትም ሆነ አስተያየታቸውን ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ከሰጡት አርሶ አደሮች መረዳት የተቻለው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ የተሻለ ምርት ቢገኝም በዚህ ዓመትም ተጨማሪ የርሃብ ስጋት ያንዠበበባቸው መሆኑን ነው።  ለዚህ ቸግር ትልቁ ምክንያት ያሉትን ሲገልጹም “የእርሻ መሬት ችግር” እንዳለባቸው ደጋግመው ተናገረዋል።

ርሃብና ድርቅ ለምን ይበረታብናል?

 ቆየት ብሎ በወጣ አንድ ጥናት ላይ “በ20ኛው ክፍለ ዘመን 30 የርሃብና የድርቅ ጊዜያት ተፈጥረዋል።  ርሃቡና ድርቁ የተከሰተባቸው አገራት ሁሉም በአንባገነን መንግስታት በሚመሩ ወይም በጦርነት በሚታመሱ አገራት ላይ ነው።  ከ30ዎቹ የርሃብና የድርቅ ክስተቶች መካከል አራቱ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ናቸው” ሲል ይገልጻል።  በሌላ በኩል ደግሞ አልጄዚራ ባለፈው ዓመት ባሰራጨው ዘገባ “ኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ በታሪኳ አይታው የማታውቀው ድርቅ ተከስቶባታል” ሲል ዘግቦ ነበር።  የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተወካዩ ባሪ ኬም በበኩሉ የርሃቡን መጠን ሲገልጽ “በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል የሚቀርበው ምግብ እንኳን በቂ አይደለም” ሲል ዘጋቢው ገልጾለታል።

በሌላ በኩል ቢቢሲ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን የድርቅ መጠን ሲገልጹ ከ30 ዓመት በኋላ የተፈጠረ አስከፊ ድርቅ እንደሆነ ገልጸውት ነበር።  የእነዚህ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት መረጃ በአኃዝ ቢለያይም የድርቁን መጠን በተመለከተ የተሰማሙበት ነጥብ ግን ከባድ ድርቅ በአገራቸን መከሰቱን ነው።

በኢትዮጵያ ላይ ድርቅ እና ርሃብ ለምን ይበረታል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ስንሻ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ያስቀመጧቸውን የምክንያት ሃሳቦች (ሎጂክ) እናገኛለን።  ወርልድ ፕሬስ ዶት ኮም ከተባለ ድረገጽ ላይ የተለያዩ ምሁራን ያስቀመጡትን ሃሳብ ሰንመለከት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚነሳው ድርቅ እና ጥሎት ለሚሄደው የረሃብ ችግር ምክንያቶቹ አራት ናቸው።  “አገሪቱ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ ግብርና (በተለይም የእርሻ ግብርና) መከተሏ” ቀዳሚው የችግሩ ምክንያት እንደሆነ ተቀምጣል።  ዝናብ ላይ መሰረቱን በጣለው እርሻ ላይ ኢኮኖሚዋን የገነባችው ኢትዮጵያ ችግሩ ይበልጥ እንዲጠነክርባት ያደረገው ሌላው ምክንያት ደግሞ “በአነስተኛ የገበሬ ማሳ ላይ የሚካሄድ እርሻ መከተሏ” እንደሆነ ይገልጻል።  የህዝብ ቁጥሩ በየጊዜው እየጨመረ መሄዱ እና የእርሻ መሬት በበቂ መጠን አለመገኘቱ ሌላው ምክንያት ሲሆን የመሰረተ ልማት አለመሟላት ደግሞ ቀሪው የችግሩ ምክንያት እንደሆነ ተቀምጧል።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ከአርሶ አደሮቹ ጋር ባደረኩት ቃለ ምልልስ የሰጡኝ መረጃ የሚያመለክተውም “የዝናብ እጥረት በመፈጠሩ፣ የእርሻ መሬት ስላጠረን እና በመጠኑም ቢሆን መስኖ ተጠቅመን ያመረትነውን ምርት የሚገዛን በማጣታችን ችግራችን በየጊዜው እየጨመረ ሂዷል” የሚል ነበር።

ህንዳዊው የኖቤል ተሸላሚ ኢኮኖሚስት አማርትያ ኩማር ሴን በበኩላቸው “Development as a freedom” በሚለው መጽሃፋቸው  መንግስታት ይበልጥ ጨቋኝ በሆኑ ቁጥር ርሃብ ይበልጥ እየበረታ ይሄዳል በማለት በዓለም ላይ የሚፈጠሩ ድርቆች ተፈጥሯዊ ቢሆኑም ርሃብ እንዲበረታ የሚያደርገው ግን የአገዛዞቹ ስራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከተከሰቱት የድርቅ ወቅቶች መካከል ብንመለከት እንኳ በንጉሱ ጊዜ የተከሰተው የ1966 ድርቅ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዳይገለጽ ተደርጎ መቆየቱ ርሃቡ እንዲበረታ ምክንያት ሆናል።  በተመሳሳይ ባለፈው የመኸር ወቅት የደረሰው ድርቅ ያሰከተለውን ጉዳት በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግስት ሲሸፋፈን ቆይቶ በመጨረሻ ነው ያመነው።  ይህንም ቢቢሲ የኢትዮጵያን የአደጋ መከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ምትኩ ካሳን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዘገባ በኢትዮጵያ ያለው የተረጂዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው በለውኛል ሲል ዘቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን በርሃብ ምክንያት ሞተ የተባለ የሰው ህይወት ባይሰማም በርካታ እንስሳት መሞታቸውን ግን መንግስትም ይፋ አድርጓል።  ይህ ደግሞ ተፈጥሮ በሚጥልበት ጦስ የተጎዳውን አርሶ አደር በእርዳታ ከሞትና ከርሃብ እንዲተርፍ ለማድረግ ከመንግስት የሚጠበቅ ስራ ነው።

ከችግሩ እንዴት እንውጣ

በዚህ ዙሪያ የምሁራንና የባለሙያዎች እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው።  የአገሪቱ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ በመመስረቱ እና መንግስት አሳካዋለሁ ብሎ ከያዘው የእድገትና ትራንስፎርሽን እቅድ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ነው።  ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ ቀጥተኛ የገቢ ምንጩ ግብርና መሆኑም ግልጽ ነው።  በዚህም ምክንያት ይህን ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እና የአርሶ አደሮቹን የዘመናት ችግር ለይቶ በማውጣት በየጊዜው በሚከሰት ድርቅ ከሚንኮታኮት ኢኮኖሚ መዳን ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።

በመስክ ጉብኝት እንደታዘብነውም ሆነ መንግስት በይፋ እንደገለጸው በዚህ ዓመትም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊዎች ናቸው።

sendekenewspaper

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *