ዛጎል ዜና- በተደጋጋሚ ኢህአዴግ ከመጋረጃው በስተጀርባ ሲሞገት ነበር። በይፋ የሙገታው ፍሬ ጉዳይ ባይነገርም በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ኢህአዴግ ጠቅልሎ በያዘው ስልጣን ዙሪያ ቅድመ ሁኔታ ያለበት ንግግር ስለመደረጉ ስምምነት አለ። ከዚያም በላይ የሰብአዊ መብት ጉዳይና የፕሬስ ነጻነት ከተቀፈደደበት ሰንሰለት እንዲወጣ ማሳሰቢያ መሰጠቱም በይፋ ተሰምቷል። በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ኢህአዴግ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱም ከሚመለክታቸው ወገኖች ማረጋገጫ ተሰጥቶበታል።
ከዓመት ተኩል በፊት ለተመሳሳይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ሄደው እንደነበር ያወሱት በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሥራ ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪና ” አገሪቱ አሁን ያለችበት ሂደት በእሳት ላይ ተጥዶ እንደሚንተከተክ ማሰሮ ይመስላል። እናም እንዲህ የሚንተከተክ ማሰሮ ለማስተንፈስ ያለው ምርጫ ክዳኑን ማንሳት ብቻ ነው፤ ያ ካልተደረገ መንተከተኩ አያቆምም። በዛ ከቀጠለ ደግሞ መገንፈሉ አይቀርም። ከዚያ በሁዋላ የሆነው ሁላችንም እናውቀዋለን” ሲሉ በወቅቱ የሰጡትን ምክርና ማሳሰቢያ በማስቀደም በቅርቡ ድፍን ግን ግልጽ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።
ቀደም ሲል ከነበሩት የተቃውሞ አካሄዶች በተለየ መልኩ ቅርጹን ቀይሮ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በስፋት የተነሳው ተቃውሞ ኢህአዴግ “መቶ በመቶ ህዝብ መረጠኝ” ብሎ በፎከረበት ማግስት መሆኑ የፈጠረው ድንጋጤ አሁን ድረስ የረገበ አይመስልም። ይልቁኑም አመጹን ተከትሎ የተወሰዱ እርምጃዎች በየቤቱ የዘለቁና ሰፊ የሃዘን ስሜት የፈጠሩ መሆናቸው ቁስሉ በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነ በየአቅጣጭው የሚሰማ ነው። ለዚህም ይመስላል ኢህአዴግ ከፖለቲካ ድርድር ጋር በተዛማጅ የሃይማኖት መሪዎች “ችግሩን ሁሉ በእርቅ እናትመው፣ እንዝጋው” ለማለት ሲነሱ ተባባሪነቱን የገለጸው።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቶም ማሊኖ ውስኪ ሲናገሩ መንግስት በአስቸኳይ አዋጁ ነገሮች የተረጋጉ ያህል ሊሰማው እንደሚችል ይጠቀሳሉ። አያይዘውም ” ይዞት የሚመጣው አደጋ አለ” ይላሉ። የኦሮሚያና የአማራ ህዝብ ካነሷቸው ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የተወሰዱት እርምጃዎች የበለጠ ቅሬታ መፈጠራቸውን ያሰምሩበታል። በሌላ አነጋገር ኢህአዴግ ወደሚፈለገው የመፍትሄ መንገድ በአስቸኳይ ካልገባ አደጋው የከፋ ሆኖ እንደሚሰማቸው ነው የጠቀሱት። ይህም ብቻ አይደለም ለአገሪቱ የፖለቲካ ድባበ የሚያመቸውን ሁኔታ በመፈለግ የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ደጋፊዎችንና አስቸኳይ አዋጁ ያሰራቸውን እንዲፈቱና በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ውይይት በሚደረግበት ሁኔታ ስምምነት መደረሱን ይፋ አድርገዋል።
በጉትጎታም ይሁን በሁኔታዎች አስገዳጀንት ኢህአዴግ የጠራውን የድርድር ስብሰባ ጅማሮ የሚበረታታ ቢሆንም ፣ ሙሉ በሙሉ የሚያደንቁ ክፍሎች አልተሰሙም። ይልቁኑም መገረም የታየባቸው ነው የሚመስሉት። ” ወደፊት የሚሆነውን እናያለን” ከሚሉት ጀምሩ ” እንደ ጅምሩ ከቀጠለ” ሲሉ ባዩት የመጀመሪያ ቀን ያልተለመደ የኢህአዴግ ባህሪ የደነገጡ ስለመኖራቸው አነጋገራቸው ይመሰክራል። በቅርቡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ “ኢህአዴግ ካለፈው ተምሮ የእውነት ውይይት የሚያደርግ ከሆነ ትንሽ መፈትሄ ይገኝ ይሆናል። ካልሆነም እዳው የእሱ ነው” ሲሉ ለጀርመን ሬዲዮ አስተያየታቸውን አካፍለዋል። በነገራችን ላይ ኢንጂነር ይልቃልና አንድ አጋራቸው ሰማያዊ ፓርቲን ወከለው ስብሰባውን ከተካፈሉ በሁዋላ በመካከሉ ስብሰባውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተሰምቷል። ይሁን እንጂ ስብሰባውን ከተካፈሉት ወገኖች በይፋ አለተገለጸም።
አመራሮቹ የታሰሩብት መድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ጅምሩን መልካም ካሉት ውስጥ አንዱ ናቸው። ለመጀመሪያ ቀን የተካሄደው የቅድመ ድርድር ውይይት አራት ዋና የተባሉ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ ደርሷል። የመድረክ መሪ አሰያየም፣ የውጪና የአገር ውስጥ ታዛቢዎችን በተመለከተ፣ የፕሬስ አካሄድና ማን መገለጫዎችን ይስጥ፣ የስብሰባ ስነ ስርዓትና አጀንዳ ቀረጻ በተመለከተ መግባባት ላይ መድረሳቸውን የገለጹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም የቤት ስራቸውን ሰርተው ለቀጣዩ ስብሰባ ቀጠሮ መያዛቸውን አስታውቀዋል።
ጉዳዩን የሚከታተሉ እንዳሉት ለድርድር የተጠሩ ፓርቲዎች አሁን ባዩት የመጀመሪያ ስብሰባ በዙም ጮቤ መርገጥ እንደሌለባቸው ይመከራሉ። አሁን ስምምነት ላይ ተደረሱ የተባሉት ጉዳዮች ገና መንገድ ጠራጊ ጉዳዮችና ወደ ድርድር ለመግባት መንደርደሪያዎች በመሆናቸው የትክክለኛ ለውጥ ፈላጊነት ማረጋገጫ አይሆኑም። በሌላ በኩል የተቀናቃኝ ፓርቲዎች በዙ ከመለፍለፍ እንዲቆጠቡ የሚመከሩ አሉ። በድርድሩ ላይ ሚዲያዎች አላስፈላጊ ጫና እንዳያሳድሩ ቁጥብ በመሆን እንዲራመዱ ያሳሰቡም አሉ።
ለድርድር ከተቀመጡት ፓርቲዎች ውስጥ ኢህአዴግ ያቋቋማቸውና የሚረዳቸው በመኖራቸው የታማኝነት ችግር አካሄዳቸውን እንዳያበላሸውና በስተመጨረሻ ” ለምዕራቡ ፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ” እንዳይውሉ ሁሉንም ርምጃቸውን በማስተዋልና ከጊዜ ጋር እንዲያደርጉ ሃሳብ የሚሰጡ ክፍሎች የሁሉም ፓርቲዎች ” የፖለቲካ እስረኞችና መሪዎች” ከእስር መፈታት ጉዳይ የመጀመሪያ አጀንዳ እንዲሆን መስማማት እንዳለባቸው ያምናሉ። አቶ የሺዋስ ለጀርመን ሬዲዮ እንዳሉት ቀድሚያ የሚያነሱት ጥያቄ የታሰሩ የፓርቲያቸው አመራሮች፣ ደጋፊዎችና አባሎቻቸው ጉዳይ ነው። ይህ ግን በተናጠል ከሚሆን በጋራ ቢቀርብ የተሻለ ይሆናል ተብሏል።
ወደ ድርድሩ ሲገባ ዋና መከራከሪያ የሚሆነውና ኢህአዴግ የሚፈተንበት የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ነው። ነጻ የምርጫ ቦርድ እንዲሰየም መጠየቁ ግድ በመሆኑ ድርድሩ እድሜው ረጅም ይሁን ውይም አጭር ከወዲሁ ለማወቅ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ፈርሶ በአዲስ እንዲቋቋምና ገለልተኛ እንዲሆን ከወዲሁ መጠየቅና ድርድሩ በእርግጥ አገርና ህዝብን ነጻ ስለማድረግ ታስቦ መሆኑንን ሲያረጋግጡ ለማየት የጓጉ በርካቶች ናቸው።
ከዚህ ውጪ ኢህአዴግ ወደ ድርድርና እርቅ ሃስበ መምጣቱ እንደ አንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ ሊታይለት እንደሚገባ የሚናገሩም አሉ።

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

ቀደም ሲል – በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሥራ ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመሩት የሁለቱ ሃገሮች ቡድኖች ያደረጓቸው ውይይቶች የኢትዮጵያ መንግሥት የሃገሪቱን የምርጫ አያያዝ ለማሻሻል የገባውን ቃል እንዲገፋበት ማሳሰብን ጨምሮ ስፋት ባላቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ኤምባሲው አክሎ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ለውይይት ሁኔታዎች አንዲመቻቹ፣ ጠንካራ መገናኛ ብዙኃን እንዲኖሩም ውይይቱ ትኩረት አድርጎ መነጋገሩን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
መሠረታዊ ነፃነቶች እንዲከበሩ በማድረግ የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠር እንዲቻል፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አስፈላጊ ጫና ለመልካም አስተዳደርና ለዓመታዊው የዩናይትድ ስቴትስ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት ያለውን ጥቅም አንስተው የሁለቱ ሀገሮች ቡድኖች መክረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመዴነህና በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ጉዳይ ፈፃሚ ፒተር ቨርማን ተባባሪ ሊቀመንበርነት የተመራው ይህ ሰባተኛው የሥራ ቡድን ስብስባ ወደፊት በሚያደርጓቸው ውይይቶች በግልፅነት ለመነጋገር መስማማታቸውን የኤምባሲው መግለጫ አመልክቷል፡፡ ሲል ቪኦኤ መዘገቡ ይታወሳል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *