ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለስኳር ፕሮጀክቶች ውድቀ ተጠያቂዎችን ለመያዝ ፍርሃት ነግሷል

የስኳር ፕሮጀክቶች ብዙ የተባለላቸው፣ ተሰፋቸው ከተጋብራቸው ቀድሞ የገነነ፣ አገዳ መፍጨት ሳይጀምሩ ከፍተኛ ዶላርና ብር ያመነዠጉ ናቸው። የፕሮጀክቶቹ መንጠፍ ብ2008 መገባደጃ ላይ በይፋ በትወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ ሃላፊው ራሳቸውን እንደጠሉ ጭምር ነበር የተናገሩት። በወቅቱ ሰንደቅ ጋዜጣ እንዲህ ብሎ ነው የገለጸው

የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ለሕመማቸው በምክንያትነት ያስቀመጡት፣ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን ገንብቶና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ ዕዳውን የመክፈል ኃላፊነት የተጣለበትን ቢሆንም፤ ኮርፖሬሽኑ ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ ይቅርና የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት ሳይችል እንደተቋም ወድቆ፣ እንደሀገር እዳ ከምሮ በአደባባይ እምባውን ሲረጭ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተመልክተውታል። በተለይ ግንባታዎቹን ለማከናወን 77 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር መበደሩን አስታውቆ ነገር ግን አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ባልገባበት ሁኔታ ውስጥ 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመክፈል ኃላፊነት ከፊቱ ተጋርጧል ሲል የጦስ ዶሮ ፍለጋ እየማሰነ ይገኛል…”

ከላይ የተገለጸውን አሃዝ ገንዘብ በሸንኮራ አሳበው እነማን አመነዠጉት? የሚለው ቢያከራክርም ድብቅ ባለመሆኑ እስካሁን ለምን እርምጃ አልተወሰደም የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ መልስ እንደሚያሻው የብዙዎች ጥያቄ ነው። የህዝብ ብቻ ሳይሆን የራሱ የፓርቲው አባልት ጉምጉምታ ነው። በአመራር ደረጃም ቢሆን መስማማት የለም።

በዚህ መሃል ለስኳር ፕሮጀክቶች መዘግየት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነውየሚል ዜና ከምንግስት ሚዲያዎች ተሰምቷል።

ይህ የተሰማው ዛሬ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ሚቴ ማቅረቡን ተከትሎ ነው። ፕሮጀክቶቹ ሰፊ ችግር ያለባቸው መሆኑ አሁንም በስፋት ቀርቧል። የሰንደቅን ሪፖርት ያንበቡ

ለስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ውድቀት፣ ስኳር ኮርፖሬሽን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ ራሱን ለመደበቅ ለምን ፈለገ?

ባለፈው ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በ2008 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ሪፖርት የብዙሃኑን ባለድርሻ አካለት እንዲሁም የተራ ዜጐችን አትኩሮት የሰባ ነበር።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብቴና ሌሎች ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች ባቀረቡት ሪፖርታቸው ላይ ተስፋ መቁረጥ እንዳጋጠማቸው ይህንን ስሜታቸውን ተከትሎ ሕመም እየተሰማቸው እንደሆነ ለቋሚው ኮሚቴ ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ለሕመማቸው በምክንያትነት ያስቀመጡት፣ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን ገንብቶና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ ዕዳውን የመክፈል ኃላፊነት የተጣለበትን ቢሆንም፤ ኮርፖሬሽኑ ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ ይቅርና የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት ሳይችል እንደተቋም ወድቆ፣ እንደሀገር እዳ ከምሮ በአደባባይ እምባውን ሲረጭ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተመልክተውታል። በተለይ ግንባታዎቹን ለማከናወን 77 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር መበደሩን አስታውቆ ነገር ግን አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ባልገባበት ሁኔታ ውስጥ 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመክፈል ኃላፊነት ከፊቱ ተጋርጧል ሲል የጦስ ዶሮ ፍለጋ እየማሰነ ይገኛል።

የስኳር ኮርፖሬሽን እንደተቋም የወደቀበትን ለመፈተሸ በሶስት የተለያዩ አግባቦች መፈተሸ ተገቢ ነው። አንደኛው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ ግንባታዎች በተመለከተ፤ ሁለተኛው አስሩ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ በተመለከተ፤ ሶስተኛው በምርት ላይ የሚገኙትን መተሐራ ስኳር ፋብሪካ፣ ወንጂ ስኳር ፋብሪካና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎችን በተመለከተ በተናጠል እና በጋራ ሪፖርቶችን መፈተሸ አስፈላጊ ነው።

ከላይ በተቀመጠው አግባብ መሰረት ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ የስኳር ኮርፖሬሽኑ እንደተቋም ለምን ወደቀ? ለውድቀቱ ትልቅ ስፍራ ያላቸው አካላት እነማን ናቸው? ተቋሙ እራሱ ለውድቀቱ ምን ያህል ድርሻ ነበረው? የአዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ የዘገየው ለምንድን ነው? አስሩ ፋብሪካዎች በእነማን እየተገነቡ ነው? በግንባታው ሂደት ላይ ተሳታፊ የሆኑ ድርጅቶች ከአጠቃላይ የግንባታው ወጪ ምን ያህል ድርሻ አላቸው? እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማስቀመጥ ወደ ትክክልኛው ድምዳሜ መድረስ ይቻላል። ከተንዳሆ መነሳቱ የሚሻል ይሆናል።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ታሳቢዎች ምን ነበሩ?

የፋብሪካው ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በቀን 26ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት እና በዓመት ከ600ሺ ቶን ስኳር የማምረት አቅም ይኖረዋል። የስኳር ልማቱ ፕሮጀክት ከስኳር ምርት በተጨማሪ፤ በየዓመቱ 55.4 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖረዋል። በተጓዳኝም የተሰራው ግድብ ለመስኖ ስራዎች ልማት፣ ለእንስሳ፣ ለዓሣ እርባታ እና ከብቶች ለማድለብ አገልግሎት ላይ ይውላል። ከኃይል አቅርቦት አንፃር  120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሰው ኃይል አንፃር በመጀመሪያው የፋብሪካ ግንባታ 35ሺ ሠራተኞች፤ በሁለተኛው የፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ 35ሺ ሠራተኞች በአጠቃላይ በስኳር ልማቱ ዘርፍ 70ሺ ሠራተኞች እንደሚኖሩት ይጠበቃል። እነዚህን ከላይ የሰፈሩ የፕሮጀክቱ ዕቅዶችን በበላይነት ሲመሩ የነበሩት የቀድሞ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ግርማ ብሩ እና በቅርብ ፕሮጀክቱን ሲያስፈጽም የነበረው  በአቶ በላይ ደቻሳ  ዋና ዳሬክተርነት ይመራ የነበረው የቀድሞ የስኳር ድጋፍ ሰጪ ኤጀንሲ ነበር። ሁለቱም ተቋሞች በሕግ ሰውነታቸውን ያጡ ቢሆንም በስኳር ልማቱ ላይ ያሳረፉት አሉታዊ አሻራቸው ግን ለቀጣዩ ትውልድ ዕዳ ሆኖ ቀጥሏል።

ምዕራፍ አንድ፤ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የውድቀት ሂደቶች

የኢትዮጵያ መንግስት በቀድሞው የስኳር ድጋፍ ሰጪ ኤጀንሲ በኩል በአፋር ክልል ውስጥ አዲስ የስኳር ፋብሪካ ለመገንባት እንዲሁም በነባሮቹ ወንጂ እና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ስራዎች ለመገንባት ዓለም ዓቀፍ ጨረታ ያወጣው እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2006 ነበር።

መንግስት አዲስ ፋብሪካ ለመገንባት እና የማስፋፊያ ስራዎቹን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያገኘው ከሕንድ መንግስት ነው። በአጠቃላይ በብድር ስምምነቱ የሰነድ ውል ላይ የሰፈረው፣ ለተንዳሆ አዲስ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ እና ለወንጂ እና ለፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ማስፈፊያ 640 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተቀምጧል። ብድሩ አነስተኛ የወለድ እና የእፎይታ ጊዜ ያለው ብድር (የሶፍት ሎን) ሲሆን የወለድ መጠኑ በመቶኛ 1.75 ነው። በሁለቱ መንግስታት በኩል በተገባው ስምምነት መሰረትም፣ ከአጠቃላይ የፋብሪካው ግንባታ እና ከፋብሪካዎቹ ማስፋፊያ ሥራዎች ውስጥ ሰማኒያ አምስት በመቶ የሚሆነውን በሕንድ ኩባንያዎች እንደሚገነቡ በብድር ውሉ ላይ ሰፍሯል። ይህም በመሆኑ በወጣው ዓለም ዓቀፍ ጨረታ ላይ በወቅቱ ከሃያ የሚበልጡ የህንድ ኩባንያዎች በጨረታው ተሳታፊ ነበሩ።

አጠቃላይ የፕሮጀክቶቹ ጨረታ በሰባት ንዑስ የፕሮጀክቶች የተከፈለ ነበር። የጨረታዎቹ አይነቶች፣ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ፤ፕሮሰስ ሃውስ፤ጭማቂ ማውጫ፤ኃይል ማመንጫ፤ዲዝል ጀነሪሽን፤ ፉክተሪ ዎርክስ እና ፕላንት ዋተር ሲስተም ናቸው። ከእነዚህ ንዑስ ፕሮጀክቶች አብዛኛውን ማሸነፍ የቻለ ተወዳዳሪ የነጠላ ኢንጅነሪንግ ዲዛይን እና ግዢ እንዲሁም የግንባታ ስራዎች (EPC) ውል ስምምነትን እንዲወስድ በጨረታው ሰነድ ላይ ተቀምጧል። (EPC is a prominent forum of contracting agreement in the construction industry. The engineering and construction contractor will carry out the detailed engineering design of the project, procure all the equipment and materials necessary, and then construct to deliver a function facility or asset to their clients.)

 ከላይ በሰፈረው አግባብ በተከናወነው ጨረታ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል የአሸናፊ ድርጅቶች ሥም ይፋ የሆነው በእ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 10 ቀን 2008 ነበር። ይፋ በሆነው ውጤት ሳራስዋቲ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን፣ ኡታም ሱክሮቴክ ኢንተርናሽናል – የፕሮሰስ ሀውስ ፕሮጀክትን እንዲሁም ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ የስኳር ጭማቂ ማውጫ እና የኃይል ማመንጫን ፕሮጀክት አሸነፉ። ይህንን የአሸናፊነት ውጤታቸውን ተከትሎ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የኢንጅነሪንግ ዲዛይን እና ግዢ እንዲሁም የግንባታ ስራዎች ዋና ኮንትራክተር መሆኑ ይፋ ተደረገ። ኩባንያው የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላን ለማከናወን ያቀረበው የገንዘብ መጠን 345 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነበር።

እንዲሁም ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት አሸናፊ ሲሆን ኡታም ሱክሮቴክ ኢንተርናሽናል ደግሞ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አሸናፊ ሆነ። ውጤቶቹ በይፋ ከታወቁ በኋላ የሕንድ መንግስት ብድሩን መፍቀዱን ገልጿል። በወቅቱ በተፈቀደው ብድር ላይ ለመወያየት በቀድሞ የኢንዱስትሪና የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ብሩ የተመራ ልዑካን ቡድን ከሕንድ መንግስት የኤክስፖርት እና የኢምፖርት ባንክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ወደ ስፍራው መሄዱን ይታወሳል።

በውይይታቸው ማጠቃለያም፣ ለፕሮጀክቶቹ የተፈቀደው ብድር ከተለቀቀበት ቀን አንስቶ በቀጣይ ሰላሳ ስድስት ቀናቶች ውስጥ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ እንደሚጀመር ይፋ አደረጉ። የፋብሪካው ግንባታ ፕሮጀክት በሁለት ዙር ተከፍሎ እንደሚከናወንም ተነገረ። የፋብሪካው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሆኖ፤ የሁለተኛው የፋብሪካው ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ  የመጀመሪያው የፋብሪካው ግንባታ በተጠናቀቀ በቀጣዩ አንድ ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገለጸ።

ሆኖም ግን እ.ኤ.አ. በ2008 በይፋ የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ ለአሸናፊው ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ የተሰጠ ቢሆንም ማስረከብ በነበረበት እ.ኤ.አ. በ2010 አላስረከበም። ዛሬም ድረስ አላስረከበም።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ እነማን ናቸው?

ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተመሰረተው ከስራ ገበታቸው በጡረታ እና በሌሎች ምክንያቶች በተገለሉ በቀድሞ የህንድ ዲፕሎማቶች ነው። በዲፕሎማቶቹ የተቋቋመው ኩባንያ ትሬዲንግ ሃውስ ነው (Trading house serves as an intermediary. The trading house must mark up the price of the goods it sells to cover its cost and earn a profit)።

ሌላው በወቅቱ የኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኩባንያ በስኳር ልማት ውስጥ ይህን ነው የሚባል ዓለም ዓቀፍ ልምድ ሳይኖራቸው በጨረታው እንዲሳተፉ መፈቀድን ተከትሎ ጥያቄዎች ነበሩ። እንዲሁም ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ የሚሆኑ አንዳችም ቁስ የማያመርቱ ከመሆናቸውም በላይ የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ የኢንጅነሪንግ ዲዛይን እና ግዢ እንዲሁም የግንባታ ስራዎች ዋና ኮንትራክተር ሆነው በጨረታው መመረጣቸው ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ነበር። ኩባንያው በድረ ገጹ ላይ ፕሮጀክቶችን ተፈጻሚ የሚያደርገው ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር መሆኑን አስፍሯል። (implement projects on turnkey basis through our consortium partners of global repute and project track records.)

እዚህ መስመር ያለበት ፍሬ ነገር ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ መዘግየት ዋና ተጠያቂ የሚያደርገው የሚከተለው የአሰራር ሥርዓት መሆኑን ነው። ይህም ሲባል በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ ጨረታ ላይ የንዑስ ጨረታ አሸናፊ መሆናቸው የተገለፀላቸው ሳራስዋቲ ኢንዱስትሪያል ሳይንዲኬት ሊትድ (Saraswati industrial Syndicate) እና ኡታም ሱክሮቴክ ኢንተርናሽናል ፕራይቬይት ሊትድ (Uttam Sucrotech International Pvt. Ltd.) ድርጅቶችን በጨረታው ተሳታፊ ባልሆነ ሌላ ድርጅት ሊቀይራቸው የሔደበት መንገድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ወደ ሕንድ ፍርድ ቤት እንዲያመሩ ያደረጋቸው አጋጣሚ ለተንዳሆ ውድቀት አይነተኛ ሚና ነበረው። የፋብሪካው ተከላም በፍርድ ቤት ክርክሮች እና እገዳ እንዲዘገይ ተደርጓል።

በሕንድ የፍርድ ችሎት የሆነውን እንመልከተው?

ለውስን ግንዛቤ ይረዳ ዘንዳ በሕንድ ኩባያዎች መካከል የተደረገውን የፍርድ ቤት ክርክር ትርጉም በዚህ መልኩ በአጭሩ ጭብጡን ለማስቀመጥ ተሞክሯል። እንዲሁም ክርክሩ የጀመረው በ2008/2009 መሆኑ ከግምት ይገባል።

በህንድ ኒውደልሂ አራተኛ ከፍተኛ ፍ/ቤት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 10 ቀን 2010 በተንዳሆ፣ በወንጂና በፊንጫ ስኳር ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ ተደርጎ የነበረውን የጨረታ አወሳሰድ ሂደት ክርክር ጭብጥ የሚከተለውን ይመስላል።

1.  ይግባኝ ባይ ዋልቻንዲና ጋር ኢንዱስትሪስ ሊሚትድ (Walchandnagar Industries)

መልስ ሰጪ ሳራስዋቲ ኢንዱስትሪያል ሳይንዲኬት ሊትድ (Saraswati industrial Syndicate)

2.  ይግባኝ ባይ ኦቨርሲስ ኢንፍራንስትራክቸር አሊያንስ (Overseas Infrastructure Alliance)

መልስ ሰጪ ኡታም ሱክሮቴክ ኢንተርናሽናል ፕ/ቬት ሊትድ (Uttam Sucrotech International Pvt. Ltd.)

3.  ይግባኝ ባይ ኦቨርሲስ ኢንፍራንስትራክቸር አሊያንስ

መልስ ሰጪ– ሳራስዋቲ ኢንዱስትሪያል ሲንዲኬት

የክርክር ጉዳዩ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራውን የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት የተመለከተ ነው። ፈንዱ የተገኘው ከህንድ መንግስት ከኤግዚም ባንክ ነው። ፕሮጀክቱ በሰባት ንዑስ ፕሮጀክቶች የተከፈለ ሲሆን፤ ለዚህም ራሳቸውን የቻሉ ጨረታዎች ተካሂደዋል። የጨረታዎቹ አይነት፣ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ፤ ፕሮሰስ ሃውስ፤ ጭማቂ ማውጫ፤ ኃይል ማመንጫ፤ ዲዝል ጀነሪሽን፤ ፎክተሪ ዎርክስ እና ፕላንት ዋተር ሲስተም ናቸው።

አብዛኛውን ፕሮጀክቶች የሚይዘው ኩባንያ የነጠላ ኢንጂነሪንግ የግዢና የግንባታ ስራዎችንም ውል እንዲሰጠው ከስምምነት ተደረሰ። ሳራስዋቲ ለእንፋሎት ኃይል ማመንጫ አሸነፈ፤ ኡታም ሱክሮቴክ ኢንተርናሽናል – የፕሮሰስ ሀውስ ጨረታውን አሸነፈ፤ የስኳር ጭማቂ ማውጫና የኃይል ማመንጫ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ አሸነፈ። ይህም በመሆኑ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ እንደ ብቸኛ የኢንጅነሪንግ የቅጥር እና የግንባታ ስራ ተቀራጭ ሆኖ እንዲሰራ ተስማሙ።

የይግባኝ ባዮች ቅሬታ

ይግባኝ ባዮች፡- ሙሉ ኰንትራት በእኛ ስም ተገብቷል ሲሉ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ደግሞ ሳራስዋቲ እና ኡታም በጨረታ ስላሸነፉ በመካከላቸው ያለው ውል መፈፀም አለበት፤ ይህ አልተፈፀመም።

– ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ዋልቻንዲናጋር ኢንዱስትሪስን በሕገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ስኳር ፋብሪካው ፕሮጀክት አስገብቷል። ለዚህ የሰጠው አሳሳች ምክንያት ሳራስዋቲ እና ኡታም የተስማሙትን የ15 በመቶ የአድሚኒስትሬሽን ኮሚሽን ለመክፈል ቸልተኛ ሆነዋል የሚል ነው። ይህን በምክንያትነት በማስቀመጥ በጨረታ ተሳታፊ የነበሩትን ሁለቱን ከገቡበት ውሉ በማስወጣት በጨረታ ተሳታፊ ያልነበረውን ዋልቻንዲናጋር ኢንዱስትሪስን በሕገወጥ መንገድ እንዲገባ ሲደረግ፤ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ኃላፊዎች ይህን ይግባኝም ሆነ ሌሎቹን ክሶች አልተቃወሙም።

1. ሳራስዊት በስር ፍ/ቤት ያቀረበው ክስ

ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ውሉን ለማስፈፀም ባለመፍቀድ ከሳሽን አስወጥቶ በሙሉ ሦስተኛ ወገን ተክቷል፤

ዲሴምበር 2007 ተንዳሆ ለኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ በፃፈው ደብዳቤ የሌሎቹ ፓኬጆች አሸናፊዎች ባሉበት እንዳሉ ከንዑስ ኮንትራክተሮቹ የተደረገው ስምምነት ቴክኒካልና ፋይናንሻል ገፅታዎች ሳይለወጡ ከግለሰቦቹ ጋር ውሉ ተጠናቋል።

ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ የሰጠው መልስ፤ ንዑስ ተቋራጮችን የመመደብና መብትና ኃይሉ ያለው በተከሳሽ ስልጣን ስር ነው። ተከሳሹ በ10/01/08 እና በ21/02/06 ማሻሻያ ውሎች ከፈረመ በኋላ ከሳሽን በቃልና በፅሁፍ ፕሮጀክቱ እንዳይስተጓጐል በተቻለ መጠን ውሉን እንዲፈርሙ ጠይቋል። ሆኖም ከሳሽ ንዑስ ተቋራጭነት ውሉን በማጓተት እንዳይፈፀም አድርጓል። ይህንም ጉዳይ 2ኛ ተከሳሽ ጁን 13 ቀን 2008 እንዲያውቀው ተደርጎ ሌላ ግልፅ የሆነ ትዕዛዝ ለተከሳሽ ስራውን ከሁሉም ንዑስ ስራ ተቋራጮች ጋር እንዲያጠናቅቅ ሌላ መጓተትን ለማስወገድ እና ስራውን ለማስጀመር ተጠየቀ፤ ቃለ ጉባኤው ተያይዟል።

በዚህ ጥያቄ መሠረት ተከሳሽ ከሳሽን ኮንትራቱን እንዲፈፅም ቢጠይቀውም፤ ከሳሽ ኮንትራቱን ለመፈፀም ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ በዋጋ እና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የተነሳ ጁላይ 8 ቀን 2008 ላይ መስተጓጐለ እንዳይደርስበት ዋልቻንዲናጋር ኢንዱስትሪ ጋር ለተንዳሆ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈርሟል።

በተጨማሪ 1ኛ ተከሳሽ የተወሰነ ጊዜ ውል Messrs I ሙምባይ ጋር ንዑስ ተቋራጭነት ስራውን እንዲሰራ ተዋውሏል። በመሆኑም ተከሳሽ Messrs ሙምባይ ስም በንዑስ ተቋራጭነት ተጠቁሟል። ጁን 11 ቀን 2008 በተፃፈ ደብዳቤ ከዚህ አንፃር ከሳሽ የንዑስ ስራ ውሎቹ መፈፀም ጀምረዋል። በከሳሸና በ2ኛም ሆነ በ1ኛ ተከሳሽ መባሉ አለአግባብ ነው።

ኡታም ሱክሮቴክ – ሁሉንም ትብብር ከኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ጋር እያደረኩ እያለ ተከሳሽ፤ “በሕገወጥ መንገድ የውሉን መፈፀም በመተው ለራሱ ፍላጐት ሲል ያልተገባ መጓተት በመፍጠር ሙሉ በሙሉ ከውሉ ውጭ እንድሆን በማድረግ የራሱን ወገኖች በሕገወጥ መንገድ ተክቷል።

ከላይኛው ጋር ተመሳሳይ በሆነ ክስም ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ በምትካችን ሌላ ሦስተኛ ወገን ለማምጣት ዝቷል።

በእኔና በተንዳሆ መካከል ውል ተደርጓል ብሏል ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ በሰጠው መልስ። ከሳሽ በተቀመጠለት ቀነ ገደብ የውል ግዴታውን ባለመውጣቱ ተከሳሽ ከዋልቻንዳጋር ፕሮሰስ ሀውስ እንዲገነባ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል።

2ኛ. ተከሳሽም በ518/2008 በፃፈው ደብዳቤ ለኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ የፕሮሰስ ሀውሱን በምትክነት ለመገንባት የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎታል። ሁለቱም ከሳሾች የዋልቻንዲናጋር ውል ጊዜውን ቀደም በማድረግ በመ/ቁ 408/2009 የተሰጠውን ትዕዛዝ ለማደናቀፍ የተደረገ ነው። ከሳሽ ባቀረበው የችሎት መድፈር ክስ በመታየት ላይ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋርሳዋልቲ በፍ/ስ/ሕ/ ሴክሽን 181 መሠረት ዋልቻንዲናጋር እና ኤግዚም ባንክ በተከሳሽነት 3ኛና 4ኛ ሆነው እንዲገቡ ጠይቋል።

ዋልቻንዲናጋር እንዲገባ ተፈቀደ

ኡታም ባቀረበው ተመሳሳይ ማሻሻያ ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል

* 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽን ሳርሳዊቲን ለ2ኛ ተከሳሽ ለኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኮንትራቱን ለመፈፀም መዘግየቱን እንደሚያሳውቅ ዝተዋል። ከሳሽ ውል በማዘጋጀት ከሁሉም ወኖች ጋር ከተደረሰው ስምምነት ጋር የሚጣጣም ከ2ኛ ተከሳሽና በከሳሽ መካከለ አዘጋጅቶ ለ1ኛ ተከሳሽ ጁን 28 ቀን 2008 ልኰለታል።

በሁለቱ ተከሳሾች ወይም በከሳሽ በተደረገው ስምምነት 1ኛ ተከሳሽ ውል ለማፍረስ ዝቷል።

ሁሉም የጨረታው አሸናፊዎች ከኢትዮጵያ መንግስት በተላለፈው መመሪያ መሠረት TSFP & FSF አንድ ብቸኛ የቅጥርና የግንባታ ተቋራጭ ለመቅጠር ማሰባቸውን እና ሁሉም ተጫራቾች እንደ ንዑስ ተቋራጭ ከዋናው ተቋራጭ ጋር መስራት እንደሚችሉ ተገለፀ።

* በተመሳሳይ ውል የኢትዮጵያ መንግስት ለወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በሰጠው ውል ከባሸይ ለሸንኮራ አገዳ መጭመቂያ ፋብሪካ ግንባታ አሸንፏል። በዚህ ጊዜ የቅጥርና የግንባታ ስራው ኡታም ሱክሮቴች የሰጠ ሲሆን፤ ከከሳሽ ጋር ውል የፈረመው 15 በመቶ ክፍያ ሳይጠየቅ ነው። አሁን ከሳሽ እንዳወቀው 1ኛ ተከሳሽ የቅጥርና የግንባታ ተቋራጭ ለመሆን መብት የሌለው ሲሆን፤ ተከሳሾች በጋራ በመመሳጠር 1ኛ ተከሳሽ አርሲ ተቋራጭ እንዲሆን በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ ያልተጠቀሰ የውል ዋጋ ከክሱ ላይ መጠየቁ አለአግባብ ነው።

– 1ኛ. ተከሳሽ በሚስጥር በጨረታው ላይ እንኳን ያልተሳተፈ ንዑስ ስራ ተቋራጭ አስገብቷል። ከጨረታ ሕግጋት ውጭ ከመሆኑ እና ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ከመስጠቱ በተጨማሪ ተከሳሽ የሰብ ኮንትራክተርነት ውሉ ለመቋረጡ የደረሰው ማስጠንቀቂያ እስከዛሬ የለም የሚል ነበር ክሱ።

ከሳሽ ክሱን አሻሽሎ ኤግዚም ባንክና ሌሎች ተከሳሾች ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ጠይቋል። ፍ/ቤቱም ይህን ውድቅ ስላደረገበት ክስ የማሻሻል ጥያቄው ላይ ይግባኝ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፤ ይግባኙንም ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም። በዋናው ክርክር ላይ የተሰጠው ውሳኔ ግን በሰነዱ ላይ አልተጠቀሰም።

ክስ ለማሻሻልና ሌሎች ተከሳሾች ወደ ክርክር እንዲገቡ ያቀረበውን ጥያቄ ፍ/ቤቱ ባለመቀበሉ በዚያው ከፍተኛ ፍ/ቤት ለሁለት ዳኞች ይግባኝ ቀርቦ ፍ/ቤቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጐታል።

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል

የጨረታ አወሳሰድ ሂደቱ ክርክር ምን ክስረት አስከተለ?

ከ2008 እስከ 2010 ድረስ የተደረገው የፍርድ ቤት ክርክር በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከተለ። ይኽውም በ2008 የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ የብድር ስምምነት ሲደረግ የአንድ አሜሪካ ዶላር ምንዛሪ 9.50 ነበር። የብድር ስምምነቱ ከፍርድ ቤት ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሴፕቴምበር 1 ቀን በ2010 በሰጠው መግለጫ የገንዘብ ምንዛሪ ዋጋ ቅነሳ በመደረጉ የአንድ አሜሪካ ዶላር ምንዛሪ በ13.75 ብር እንደሚመነዘር  ይፋ አደረገ። የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ ዋጋም በከፍተኛ ዋጋ ናረ።

እንዲሁም ኢታም ከሕግ አግባብ ውጪ ስራ ተወስዶብኛል በማለት የወንጂ ስኳር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራዎችን በፍርድ ቤት ክርክር መነሻ ለሁለት ዓመታት አዘገየው።

በአንፃሩ ግን ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ እራሱ የፋብሪካ ፋሲሊቲዎች ማቅረብም ሆነ መስራት ስለማይችል ዋናው ስራው ሥራዎችን አውትሶርስ ማድረግ በመሆኑ ሊያገኝ የሚገባውን ኮሚሽን በየትኛውም ጊዜና ወቅት ይሰበሰባል።

በዚህ በምዕራፍ አንድ ውድቀት ውስጥ አይነትኛ ሚና የነበራቸው የቀድሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ ግርማ ብሩ፣ የስኳር ድጋፍ ሰጪ ዋና ዳሬክተር አቶ በላይ ደቻሳ እንዲሁም በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሶፊያን አህመድ መሆናቸውን ፀሐፊው ያምናል።

ምዕራፍ 2፡ ተንዳሆ ከእነነቀርሳው ከስኳር ኮርፖሬሽን ምስረታ ጋር

ተቀላቀለ

    በ2003 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን  ሲመሰረት 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች እና ነባር የፋብሪካ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እንዲመራ ኃላፊነት ተጥሎበት መሆኑ ይታወቃል። ከነባር ፕሮጀክቶች መካከል የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ነቀርሳን ለመሸከም ታሪካዊ ኃላፊነት ወስዷል። ለስኳር ልማት እድገት ከፍተኛውን ውድቀትና የስራ ተነሳሽነት ያጠፋው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ፣ በተቋሙ ኃላፊዎች በኩል ችግሮቹ ተለይተው ዳግም በሌሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ላይ እንዳይደገም ጥሩ ትምህርት ወስደናል ሲሉ በጊዜው ተደምጠዋል። ሲውል ሲያድር ግን ከተቋሙ ኃላፊዎች የሚሰማው ሪፖርት ለየቅል ሆኖ ተገኝቷል። የተቋሙ ሁለት ከፍተኛ ኃላፊዎች በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ስለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየቶችን እንመልከታቸው።

አቶ አስፋው ዲንጋሞ የቀድሞው የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አማካሪ እና የሕግና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ስለጉዳዩ በወቅቱ እንዳስረዱት፤ ስራችንን ከመጀመራችን በፊት በነባር ስኳር ፋብሪካዎች እና በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ያለው የስራ ሂደት መገምገም ነበር። የግምገማውን ውጤት መሰረት አድርገን አጠቃላይ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች እና የስኳር ፋብሪካዎቹን ግንባታና ምን መሆን እንዳለበት የወደፊት አቅጣጫ አስቀምጠን ነው ወደ ስራ የገባነው ሲሉ የተቋሙን ሥራ አጀማማር በጥናት ላይ የተመሠረተ መሆኑ አስረድተው ነበር።

አያይዘውም፤ በተንዳሆ እየተገነባ ባለው አዲስ የስኳር ፋብሪካ ላይ ባደረግነው ግምገማ ብዙ ችግሮች ለይተን አውጥተናል። ከእነዚህም ውስጥ፤ ከተቋራጩ ድርጅት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ መሠረታዊ የእቃ አቅርቦት አሰራር ሰንሰለት ማጣት እና የገንዘብ አቅርቦት እጥረት ዋነኞቹ ነበሩ። እነዚህን ችግሮች ከመሰረታቸው ደረጃ በደረጃ እየፈታን አሁን ወደ ተሻለ የስራ አፈፃፀም የገባንበት ሁኔታ ነው ያለው ሲሉ አሳውቀው ነበር።

“የብድር ገንዘብ የሚለቀቀው ደረጃ በደረጃ በሚታየው የአፈፃጸም ውጤት በመሆኑ ከሕንድ መንግስት በተገኘ ብድር የተጀመረ ፕሮጀክት እንዴት የገንዘብ እጥረት ገጠመው? ተቋራጭ ድርጅቱ የተለቀቀለትን ገንዘብ አለአግባብ የተጠቀመበት ሁኔታ መኖሩን በጥናታችሁ ጊዜ አግኝታችሁ ነበር ወይ? ወይንስ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጨረታ ሂደት ከጅምሩ ችግር ነበረበት ብላችሁ ታምናላችሁ?” የሚሉ ጥያቄዎች ለአቶ አስፋው ቀርቧላቸውም ነበር።

አቶ አሰፋው የሰጡት ምላሽ፤ “ጨረታው መቼ እንደተካሄደ በርግጠኝነት ለመናገር አልችልም። የጨረታውን ሂደት ማወቅ፣ አለማወቅ አሁን እየሰራንበት ላለው ሂደትም ምንም አይነት ተጨማሪ ዕሴት አይኖረውም። ወደ ስራ የገባነው የጨረታው ውል ከተፈፀመ ሶስት ዓመት በኋላ በመሆኑ እኛን አይመለከተንም። በተገባው ውል መሠረት የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታዎችን እየመራን ነው ያለነው። ከእኛ በፊት ለተፈጸመው አሠራር በወቅቱ ስላንነበረኩ ምንም ማለት አልችልም። ጨረታውን ያሸነፈው  ተቋራጩ ድርጅት የአፈፃፀም ችግር ነበረበት ለሚለው ግን፤ አዎ ነበረበት። የአፈፃጸሙ ችግር ግን ከጨረታ አሠጣጡ ጋር የተገናኘ ነው ለተባለው በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም እውቀቱ ስለሌለኝ ምንም ማለት አልችልም” ሲሉ ተቋማቸውን ተከላክለው ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ዳሬክተር አቶ አባይ ፀሃዬ የ2004 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርታቸውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ጊዜ እንደተናገሩት፤ “በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ኮንትራክተሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ኮንትራክተሮችን ማሰናበት እና እነርሱን ለመተካት ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ባሉበት ሁኔታ ጫና በመፍጠር ስራውን ከበፊቱ በተሻለ አካሄድ እንዲራመድ ለማድረግ በአማራጭነት ወስደናል” ብለዋል።

አቶ አባይ በወቅቱ በሪፖርታቸው አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት፤ ፕሮጀክቶቹ አስቀድሞ በነበራቸው ሥር የሰደደ ችግር የተነሳ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሠሌዳ አልተጠናቀቁም። በተለይ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት የሕንድ ኩባንያ በፈጠረው ችግር የተነሳ እጅግ የጎላ በመሆኑ ከታሰበው ጊዜ የተራዘመ ጊዜ እንደሚወስድ ተገምቷል ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የችግሮቹ ነቀርሳዎች ቀደም ብለው የተከወኑ መሆናቸውን አመላካች በሆነ መልኩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ነበር።

በወቅቱ በ2004 ዓ.ም የቀረበው የዋና ዳይሬክተሩ ሪፖርት እንደሚለው፤ የተንዳሆ ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ በ2004 የበጀት ዘመን ስለማይጠናቀቅ በታህሳስ 2005 በከፊል ተጠናቅቆ የማምረት ሥራ የሚጀምር ሲሆን፤ በጥር ወር 2005 መቶ በመቶ ተጠናቅቆና በየካቲት ወር ተፈትሾ፣ በመጋቢት ወር 2005 በተሟላ አቅም የማምረት ሥራ ይጀምራል ብለው ነበር። አያይዘውም፣ ለግብዓት የሚሆን 4ሺ 550 ሔክታር አገዳ ተከላ እስከ 2004 በጀት ዓመት ፍፃሜ ይከናወናል። የተንዳሆ ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ በታህሳስ 2005 ዓ.ም. በምርት ዘመኑ መጀመሪያ ላይ በከፊል ተጠናቆ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን 6 ሺ 929 ሔክታር በሸንኮራ አገዳ ተሸፍኗል ብለው ነበር።

የዋና ዳይሬክተሩ ሪፖርት መቋጫ የነበረው በአምስት ዓመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተቀመጠውን ግብ ለመምታት  2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን ስኳር ማግኘት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ አስቀድመው የተጀመሩት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እና ተንዳሆ መጠናቀቃቸው ወሣኝ መሆኑ አስታውቀው ነበር። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታዎች የፊንጫና የወንጂ ስኳር ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ከነችግራቸው ወደ ስኳር ምርት ተሸጋግረዋል።

በአንፃሩ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ በሚያያዛዝን ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ የሙከራ ሥራዎች ለማከናወን ኮርፖሬሽኑ ጥረት ቢያደርገም አልተሳካለትም። በተለይ ፋብሪካው የሙከራ ምርት እንዲጀምር ፍተሻ በሚደረግበት ወቅት የገጠሙ ችግሮች፣ በስኳር ፋብሪካ ታሪክ በጣም አስገራሚና እንደሀገር ከፍተኛ ውድቀትና መጭበርበር መፈፀሙን አመላካች ነበሩ።

ይኽውም፣ ለፋብሪካው ኃይል የሚያቀርበው ቦይለር እየተሞከረ ባለበት ጊዜ የፋብሪካዎቹ ሁለት ተርባይኖች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል። የአንዱ ዋጋ ከአስር ሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል። እንዲሁም የሸንኮራ አገዳውን ወደ ወፍጮ መፍጫው የሚገለብጠው ክፍል፣ ሸንኮራ አገዳውን ለመገልበጥ በተጫነለት ሰንሰለት ከፍ ለማድረግ ሲሞክር ድጋፍ ይሰጠው የነበረው የሲቪል ዎርኩ ከስር ተነስቶ ተገንጥሎ ወድቋል።

ሌላው በጣም የሚገርመው የፋብሪካው ተከላ ባለማለቁ በ25ሺ ሔክታር መሬት ላይ የለማው የሸንኮራ አገዳ ማሳ በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው። በአሁን ሰአት በኮርፖሬሽኑ በኩል የፋብሪካው ተከላ 96 በመቶ ተጠናቋል የሚል ሪፖርት ቢወጣም በተገቢ ሁኔታ የተያዘ የሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት ስለገጠመው ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ ነው።

ምዕራፍ 3፣ ለተንዳሆ 2ተኛ ምዕራፍ ክፍያ ለምን ተፈጸመ?

የስኳር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች ጥቅት 19/03/07 ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል። በዚህ ሪፖርት የ2007 የነባር ፕሮጀክቶች ፊሲካል እቅዶች የቀረቡ ሲሆን አንዱ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክትን የተመለከተ ነበር።

በሰነዱ ላይ እንደሰፈረው፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ (13,000 ቶን በቀን) በነሐሴ ወር ጀምሮ ማምረት እንዲጀምር ይደረጋል። የስኳር ፋብሪካው ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ማናቸውም አስፈላጊ ቅደመ ክፍያዎች ለዋናው ኮንትራክተር የተከፈሉ በመሆኑ እና በመጀመሪያው ምዕራፍ ወቅት ለቀጣዩ ምዕራፍ ግንባታ አስፈላጊው ዝግጅት በመደረጉ ሥራው በ2007 ዓ.ም የካቲት ወር ተጠናቆ መጋቢት ምርት እንዲጀምር ይደረጋል።

እንዲሁም የመስኖ ግንባታና አገዳ ተከላ በተመለከተየተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ 13,000 ቶን በቀን የመፍጨት አቅም ስላለው ይህን የሚመጥን 25,000 ሔክታር ላይ በመስኖ የሚለማ አገዳ ተክል ሽፋን ስለሚጠይቅ፣ ኮንትራክተሩ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በ2007 የልማት ዘመን የመጀመሪያውን ምዕራፍ 25,000 ሔክታር ያላለቁ የመስኖ መሰረተ ልማት አጠናቆ ያቀርባል። በተጨማሪም የ18,000 ሔክታር የጥናትና ዲዛይን ስራ ይሰራል።

በተያያዘም አገዳ ተከላ በተመለከተ የ2006 ተከላ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ሽፋኑ 18ሺ479 ሔክታር ደርሷል ይላል። እንዲሁም የአገዳ ተከላ በበጀት ዓመቱ (በ2007 ዓም.) 10ሺ 521 ሔክታር አገዳ ይተከላል ሲል ሰነዱ ያትታል።

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

እዚህ ላይ ስኳር ኮርፖሬሽኑ ሊመልሰው የሚገባው ጥያቄ፣ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኩባንያ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላን እጅግ በወረደ አፈፃጸም እያከናወነ መሆኑ እየታወቀ ሁለተኛው የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ ግንባታ እንዲያከናውን ማን ፈቀደለት? ክፍያውስ እንዴት ተፈጸመ? ሌላ የህንድ ኩባንያ ሁለተኛውን ምዕራፍ የተንዳሆ ፋብሪካን ተከላ እንዲያከናውን በአማራጭነት ለምን አልታየም? ከላይ የሰፈረው 18ሺ 479 ሔክታር አገዳ የት ደረሰ? ተጨማሪ 10ሺ 521 ሔክታር አገዳውስ ምን በላው?

በአጠቃላይ ስኳር ኮርፖሬሽን ከነነቀርሳው ተንዳሆን ተርክቦ ወደ ስራ የገባ ቢሆነም በቀጣይነት በነበሩ አፈፃፀሞች በዚህ ጸሃፊ እምነት አቶ አባይ ፀሐዬ እና አቶ ሽፈራው ጃርሶ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው ብሎ ያምናል።

የሕንድ ፓርላማ ልዑካን ትዝብት

የሰንደቅ ምንጮች እንደገለጹልን ይህ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ የህንድ የፓርላማ ቡድን ልዑካን ጎብኝቶት ነበር። የፓርላማው ቡድን ባቀረበው ሪፖርት የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ የስራ አፈፃፀም ከሚጠበቀው በታች የወረደ በመሆኑ የተሰማቸውን ቅሬታ በሪፖርታቸው ላይ አስፍረውታል። በተለይ የፓርላማው ቡድን ሕንድ አፍሪካ ውስጥ ከቻይና ጋር ለምታደርገው የኢኮኖሚ ፉክክር በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ የታየው የአፈፃፀም ደካማነት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያላቸውን ከፍተኛ ስጋት ለመንግስታቸው አስታውቀዋል።

አስሩ ስኳር ፋብሪካዎችና የኮርፖሬሽኑ ለቅሶ

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንበደቡብ ኦሞ ዞን ኩራዝ አንድ፣ ኩራዝ ሁለት፣ ኩራዝ ሦስት፤ በአማራ ክልል በለስ አንድ፣ በለስ ሁለት፤ በአፋር ክልል ተንዳሆ አንድና ሁለት እንዲሁም፣ ከሰም፤ በትግራይ ክልል ወልቃይት፤ በኦሮሚያ ክልል በአርጆ ደዴሳ የስኳር ፕሮጀክቶችን እየሰራ ይገኛል።

በጥቅምት 19/02/07 ኮርፖሬሽኑ ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ስለ ፋብሪካዎቹ ግንባታዎች ዝርዝር መረጃዎች አስፍሯል። እንደቀረበው ሰነድ፣ የፋብሪካ ግንባታ የ2007 በጀት ዓመት ከስኳር ልማት ፈንድ እና ከአገር ውስጥ ብድር የተያዘ በጀትን በሚመለከት በሜቴክ እየተሰሩ ላሉት የበለስ አንድ እና ሁለት ብር 4.26 ቢሊዮን፣ ለኩራዝ አንድ ብር 2.30 ቢሊዮን በድምሩ ብር 6.56 ቢሊዮን እንዲሁም ለተንዳሆ ምዕራፍ ሁለት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ብር 290.76 ሚሊዮን፣ ለከሰም ብር 562.5 ሚሊዮን፣ ለወንጂ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ቀሪ ክፍያ ብር 608.33 ሚሊዮን እና በውለታ መሰረት የሚከፈል ለመለዋወጫ የሚከፈል ብር 1756 (15.6 USD) ሚሊዮን ብር 7.2 ቢሊዮን የተጠየቀ ሲሆን፤ ብር 1.94 ቢሊዮን በበጀት ዓመቱ መያዙን ገልጿል።

በዚህም መሰረት ለበለስ አንድ እና ሁለት ብር 792 ሚሊዮን፣ ለኩራዝ አንድ 300 ሚሊዮን፣ ለተንዳሆ ብር 290.76 ሚሊዮን እንዲሁም ለከሰም ብር 562 ሚሊዮን ብር እንዲያዝ ተደርጓል። እንዲሁም በውጭ ብድር ለሚገነቡት ለወልቃይት ብር 4.4 ቢሊዮን፣ ለኩራዝ 2 እና 3 ብር 4.3 ቢሊዮን እና ለተንዳሆ ምዕራፍ ሁለት ፋብሪካ ግንባታ ብር 2.2 ቢሊዮን ጨምሮ በድምሩ ብር 12.9 ቢሊዮን ለፋብሪካ ግንባታ ተይዟል።

የነባር ፋብሪካዎች እና አዳዲስ ለሚገነቡ ፋብሪካዎች ለአማካሪ የሚከፈል ክፍያን በተመለከተ ለነባር ፋብሪካዎች የውጭ አማካሪዎች ብር 97.7 (4.89 USD) ሚሊዮን፣ አዳዲስ ለሚገነቡ ፋብሪካዎች ብር 120.98 (6.04 USD) ሚሊዮን እንዲሁም ለአገር ውስጥ አማካሪዎች ብር 6.11 ሚሊዮን በድምሩ ብር 208.12 ሚሊዮን ብር ለውጭ እና ለአገር ውስጥ አማካሪዎች የተፈቀደ ሲሆን፤ ይህም ከስኳር ልማት ፈንድ ከሚገኝ ገቢ እንደሚሸፈን ታሳቢ ተደርጎ የተያዘ መሆኑን ጠቁሞ በጀቱ በዋና መ/ቤት በኩል እንዲያዝ ተደርጓል ይላል።

እንዲሁም በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት የሚገነባው የኦሞ-ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ መስከረም ላይ ተጠናቆ ህዳር 2007 ምርት ማምረት ይጀምራል፣ የኦሞ ኩራዝ 2 ፋብሪካ የፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ፋይናንስ ከቻይና ልማት ባንክ በብድር effective ሆኖ የመጀመሪያው ቅድመ ክፍያ በ2006 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የተፈፀመ ስለሆነ በዚህ አግባብ ሁለቱም ፋብሪካዎች በ24 ወራት እንዲጠናቀቁ የታቀደ ስለሆነ በበጀት ዓመቱ 49 በመቶ ሥራ ይከናወናል ብሎ ኮርፖሬሽኑ እንደሚጠብቅ በሰነዱ ላይ አስፍሯል። አያይዞም በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት የሚገነቡት ሁለት 12,000 ቶን በቀን የመፍጨት አቅም ያላቸው ፋብሪካዎች ጣና በለስ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ታህሳስ ወር 2007 መጨረሻ እና በመጋቢት 2007 መጨረሻ እንደ ቅደም ተከተላቸው ተጠናቅቀው አገዳ ለመፍጨት ይዘጋጃሉ፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በመገንባት ላይ ላለው ስኳር ፋብሪካ የውሃ አቅርቦት እየተሰሩ ካሉት ካናሎች በመስመር ተገንጥሎ ይገነባል ይላል።

በአንፃሩ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የ2008 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡ ጊዜ ተስፋ መቁረጥና ሕመም እየተሰማን ነው ብለዋል። ከአጠቃላይ የተቋሙ ሥራ አፈፃጸም አንፃር ተስፋ ባይቆርጡ ነበር የሚገርመው። ለአብነት ማሳያ የሚሆነው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ምዕራፍ አንድን ማስረከብ ላቀተው ለኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኩባንያ ተንዳሆ ምዕራፍ ሁለት ፋብሪካ እንዲገነባ ብር 2.2 ቢሊዮን በጀት የያዘ ስኳር ኮርፖሬሽን በምን በመመዘኛ በአደባባይ እምባ እያነባ ከሕዝብ ቅቡልነት ለማግኘት እንደሚዳክር ለማንም የማይገባ አቀራረብ ነው።

የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች በገዛ አንደበታቸው ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ “ከሰባት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ስኳር ማምረት ቢጀምርም ጥራቱ የተጓደለ የእንፋሎት አቅርቦት፣ የፋብሪካው ፊልተር በቆሻሻ በመዝጋቱና በተርባይን ላይ ጉዳት በማድረሱ እንዲቆም መደረጉን” ገልጸዋል። በጣም በሚያሳፍር መልኩ ደግሞ ጥገና ከተደረገ በኋላ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ለፋብሪካውና ለመስኖ የሚሆን የውኃ አቅርቦት ችግር ወደ ምርት እንዳይገባ እንዳደረገው መናገራቸው ነው። ዛሬ ላይ በተንዳሆ የውሃ ግድብ ሥራ ማስጀመር የሚችል ውሃ ወደ ግድቡ ገብቷል። ፋብሪካው ፍተሻ እንዳይደረግበት ዋናው እንቅፋት የሆነው የሸንኮራ አገዳ አቅርቦት ነው። ምክንያቱም ሸንኮራ አገዳው ለምርት ዝግጁ በነበረበት ሰዓት ፋብሪካውን ሕንዶቹ ይቀልዱበት ስለነበረ ነው። እውነቱ ይህ ነው።

ሌላው የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንትና ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ ለቋሚው ኮሚቴ በሰጡት አስተያየት፣ የአሥሩም አዳዲስ ፋብሪካዎች ኮንትራት የተሰጠው ለአገር በቀሉ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ነው። ሆኖም በተፈለገው ጊዜ ፋብሪካዎቹን መገንባት አልቻሉም። እንዲሁም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አመራሮች ከሜቴክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በቢዝነስ ኮንትራት ሕግ አይመሩም ነበር ማለታቸው ይታወቃል።

አቶ አብርሃም እዚህ ድረስ ርቀው መናገራቸው ካልቀረ ገዢው ፓርቲ የሚከተለውን ፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳስረው ማስረዳት ቢችሉ ጥሩ ነበር። የገዢው ፓርቲ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ዋነኛው ሞተር መንግስት እራሱ ነው። ከዚህ አንፃር ሜቴክ ሲፈጠር መንግስት በነፃ ገቢያ ኢኮኖሚ ውስጥ የግል ባለሃብቶች ሊሰማሩባቸው በማይችሉ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ለመሳተፍ ከዘረጋው የኢኮኖሚ አውታር አንዱ ነው። በአቅም በገንዘብም ከዜሮ የጀመረ ተቋም ነው። ዋና ዓላማ ተደርጎ የተነደፈው ግን የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር ወደ ሀገር በቀል አቅሞች በቀየር አስተማማኝ ውስጣዊ አቅም መፍጠር ነው።

ይህ ማለት ግን ሜቴክ የፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታዎችን ላዘገየበት ተጠያቂ አይሆንም ከሚል መደምደሚያ አያደርሰንም። ይህም ሆኖ በሜቴክ በኩል ያለውንም ማድመጥ እና ለህዝብ ይፋ ማድረግ ከተቋሙ ይጠበቃል፡፡ አከራካሪ የሚሆነው ነጥብ ግን ከብር 77 ቢሊዮን የሜቴክ ድርሻ ምን ያህል ነው የሚለው ነው። ዝግጅት ክፍላችን ባለው መረጃ መሰረት የፋብሪካዎቹ ግንባታ ከ200 እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ወጪ እንደሚደረግባቸው ነው። እንደኮርፖሬሽኑ መረጃ መሰረት በአሁን ሰዓት ሜቴክ በሶስት ፋብሪካ ግንባታዎች ላይ ብቻ ተሳታፊ መሆኑን ነው። የመጨረሻውን የፋብሪካ ተከላ ወጪን ታሳቢ አድርገን ብንወስድ እንኳን ሜቴክ ለሚተክላቸው ሶስቱ ፋብሪካዎች 750 ሚሊዮን ዶላር ውጪ የሚደረግባቸው ነው የሚሆኑት። ይህ ማለት ብር 15 ቢሊዮን ነው የሚሆነው። በተጠቀምነው ስሌት እንኳን ብናሰላው ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድረው 77 ቢሊዮን ብር አንፃር የሜቴክ ድርሻ ቢሰላ ከአንድ አምስተኛ በታች ነው የሚሆነው።

ይህ ማለት ለስኳር ኮርፖሬሽኑ እንደተቋም መውደቅ ሜቴክ የአንበሳውን ድርሻ አለው የሚለው የስኳር ኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች መከራከሪያ ውሃ የሚያነሳ አይመስልም። ለዚህም ነው፣ ለስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ውድቀት ስኳር ኮርፖሬሽን እንደሰጎን አሸዋ ውስጥ ራሱን ለመደበቅ ለምን ፈለገ? የሚል ጥያቄ ያነሳሁት። እውነቱን ተቀብለው ከመጋፈጥ፣ እውነቱን መሸሽን ኮርፖሬሽኑ በአማራጭነት  ወስዶታል፡፡ ለውድቀቱ ዋናው መንስኤ፣ ስኳር ኮርፖሬሽኑ እንደተቋም የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም የሚያስችል ውስጣዊ አቅምም ሆነ አደረጃጀት የለውም። አልነበረውም። ይህንን ጥሬ ሃቅ “እንሸማቀቃለን” በሚል የብልጥ አቀራረብ፣ ሕልውናን ለማስቀጠል ብቻ መሞከር ሲጨልም ዋጋው ምትክ አልባ መሆኑ አይቀርም።

የስኳር ልማቱን ወደተግባር ለመቀየር የስኳር ኮርፖሬሽን አጠቃላይ አመለካከት መቀየር አለበት። ይኸውም፣ ስኳር የፖለቲካ ሸቀጥ አይደለም። ስኳር እድሜ ጠገብ የምርምር ውጤት ነው። ስኳር ለማምረት ምንም የተለየ ሚስጥር የለውም። ብቸኛው አማራጭ ተቋሙን ለእውቀት ብቻ መተው ነው።

 ሰንደቅ ጋዜጣ Wednesday, 18 May 2016 13:5 ያተመወና ፋኑኤል ክንፉ ያዘጋጀው ሪፖርት