ስመ ገናናው ናፖሊዎን አንድ ወቅት ወታደሮቹን መጎብኘት ፈለገና ዝግጅቱ እንዲከናወን ለበታች  ሹማምንቱ ትዕዛዝ ያስተላልፋል ። የሚጎበኝበት ስዓት ከመድረሱ በፊት ወታደሮቹ በታዘዙት መሰረት ሰልፋቸውን ይዘው ይጠባበቃሉ፤ ናፖሊዎን  በቦታው እንደደረሰ አንድ እንግዳ ነገር ትኩረቱን ይሰበዋል ያ ትኩረቱን የሳበው ጉዳይ ከሰልፈኛው መካከል አንዱ ወታደር ከመሰመር አፈንግጦ ወጥቶ መቆሙ ነው። ናፖሊዎን በቀጥታ ወደዚሁ ሰው ይሄድና  “ስምህ ማን ነው?”  ብሎ ይጠይቀዋል። ወታደሩም መልሶ  “ስሜ ናፖሊዎን ይባላል” አለው  ናፖሊዎንም መልሶ “ወይ ስምህን ቀይር ወይም አሰላለፍህን አስተካክል” አለው።

ይህንን ምሳሌ እንደ መንደርደሪያ መጠቀም የፈለግሁት ህዝብ እንደ ህዝብ የፖለቲካ መሪዎችን፤የፖለቲካ ድርጅቶችንና ማህበራዊ ሚዲያዎችን የመፈተሽ ሃላፊነት እንዳለበትና ሲያልፍም ለህዝብ ወገንተኝነት መቆማቸውን በማረጋገጥ የተጣመሙትን በማቃናት የሳቱትን በመመለስ ጉልህ ሚናውን ሊጫወት ይገባዋል ለማለት ነው። በመስመራቸው ገብተው የማይጥበጥቡትንም ባለ ንስር ዓይን እንደሆነው እንደ ናፖሊዎን ወይ ስማችሁን ቀይሩ ወይ አሰላለፋችሁን አስተካክሉ ሊላቸው ይገባል።

ህዝብ በተፈጥሮ የተቸረውና በፖለቲካው መድረክ በመሪ ተዋናይነት የሚጫወቱትን እውነተኞቹንና ውሸተኞቹን የሚለይበት አስደናቂ መነጽር አለው። ግራ ተጋብተን ግራ እያጋባን ያለን ኩርንችቶችና ተሰግስገን ያለቦታችን የምንንደፋደፍ ዘባተሌዎች ወይም በቅጥረኝነት በበግ ለምድ የቆምን ተኩላዎች አቅም አሳጥተነው እንጅ ህዝብ ማን በየትኛው ስፍራ መቀመጥ እንዳለበት የሚመዝንበት ልዮ ተፈጥሮአዊ ዕውቀት አለው። ህዝብ እንደ ህዝብ ይህንን ተፈጥሮአዊ የሆነ ልዪ ስጦታውንና በታሪክ ተንሰላሰሎ ያካበተውን እምቅ ዕውቀት በመጠቀም ግራ አጋቢዎቹን እያንጓለለ ከትግሉ ሰልፍ ዘወር ሊያደርጋቸው ይገባል። ይህን በማድርጉም ህዝብ ራሱን ከታላቅ ጥፋት፤ ሃገርን ከአሰቃቂ አደጋ ከመታደጉም በላይ ዛሬ ሳይገባቸው የመርገም ሃዋርያ የሆኑ የጥፋት መልዕክተኞችንም በማዳን በአስተማሪነቱ አቻ የማይገኝለት ታሪክን ከትቦ ማለፍ ይቻለዋል ብዬ አምናለሁ።

በናሽናል ጅኦግራፊ የዱር ዓራዊት ጥናታዊ  የቴሌቪዥን ፕሮግራማቸው ውስጥ በአንድ በኩል የጅቦቹ በሌላ በኩል የጎሹ፤ የሜዳ አህያውና … ትዕይንት ያስደንቀኛል። ጅቦቹ ከመንጋው አንድ መጥለፍ ሲፈልጉ ከወዲያ ወዲህ እየተራወጡ መንጋውን ግራ ያጋቡታል ከዚያ ወዲያ የሚፈልጉትን ግዳይ ይጥላሉ። ግንሳ ያ መንጋ ከመራወጥ ይልቅ አስተውሎና ባንድ ላይ ቆሞ ቢያፈጥባቸው ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? ያስገርማል። እኛም ቀስ ብለን እናስተውል እስኪ ዛሬ በየፌስቡኩና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ተሰማርተው በተገቢው የትግል ስልት ተሰልፎ ጠላቶቹን እንዳያበራይ ህዝብን ግራ የሚያጋቡ የደደቢት የመንፈስ ጅቦች አይታዬአችሁም? ህዝብስ ቢሆን በሚያራውጡት በነዚህ የመንፈስ ጅቦች ነው መበርገግ ያለበት ወይስ አስተውሎ መመልከትና እነርሱን ልክ ማስገባት?። ህዝብ እንደህዝብ የመለኪያ ሚዛኑን ለመጠበቅ በዘመን መካከል የገነባውን እምቅ ዕውቀት መጠቀም አለበት ነው እምነቴ። በሌላ በኩል ደግሞ ግራ የተጋባ ተልዕኮ ይዛችሁ ከሆድ በቀር ለህሊናቸሁ ቦታ ያለሰጣችሁ በአሳማ መንፈስ የምትነዱና  ህዝብን ግራ የምታጋቡ ሰው መስል ሰዎች ቆም በሉና አስቡ የደደቢቶቹ አለቆቻችሁ ለጭንቀታቸው ማስታገሻ እንዲሆን  እናንተን ለተልዕኮ ያሰማሯችሁ እንጅ እነርሱ ራሳቸው ግራ እንደተጋቡ፤ የሚይዙት የሚጨብጡት እንዳጡ በየመድረኩ እየለፈለፉ ነው ኧር ወሽሽሽ…..!!

ዛሬ ዓለምን ለመምራት በፊተኛው ረድፍ ላይ ከሚገኙት ህዝቦች መሃከል አይሁዶች ተጠቃሾች ናቸው። የአይሁዶች እምነት፤ፍልስፍና፤ኢኮኖሚክስ አርክቴክትና የመሰል ስልጣኔዎቻቸው መነሻና መሰረት ደግሞ የሙሴ መጻህፍት ናቸው የሙሴ መምህር ደግሞ ኢትዬጵያዊው ዬቶር ነው። የኢትዬጵያ ህዝብ እንደህዝብ መነሻ ነጥቡ ትልቅ ስፍራ የሆነ ትልቅ ህዝብ ነው ለማለት ነው። “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳው አይሸከምለትም” እንዲሉ ሆኖብን እንጅ እኛ ኢትዬጵያውያን በዚህ ታላቅና ታሪካዊ ህዝብ እጅ ውስጥ የሚገኙ በዘመናት ምጥ የተወለዱ ለሌላው ዓለም ልናበረክታቸው የምንችላቸው ታላላቅ የፈጠራ ወጤቶች የሆኑ ድርሳናት፤ቅርሶች ፤ታሪክና  የአስደናቂ ማህበራዊ መስተጋብር ባለቤቶች ነን።

በትህትናውና ለሰው ልጅ በሚሰጠው ዋጋ ሁልጊዜ ቀልቤን የሚገዛው ዶ/ር አበበ ገላጋይ አንድ ወቅት አንድን ጠንካራ የሆነ ተቋም ለመገንባት ምን ምን ዓይነት አላባውያን እንደሚያስፈልጉ ለመግለጥ  የአባቶቻችንን የረቀቀ አዕምሮና የፈረጠመ አካላዊ ብቃት በምሳሌነት ተጠቅሞ በአንድ ቦታ ሲያስተምር እድሉ ገጠመኝ። በአርአያነት የተጠቀመበት ምሳሌና ያስተማረውም ሰለፋሲል ግንብ ግንባታ ነበር። የጎንደሩ ፋሲል ግንብ ሲገነባ በማህበረሰቡ ውስጥ በዕውቀታቸው አንቱ የተሰኙ ሃምሳ ቸንካሪ /አርክቴክት/፤ሃምሳ ማጋሪ / የነጠሩ ግንበኞች/ ፤ እና ሃምሳ አነዋሪ / ክሪቲክ/ ተመርጠው ነው ብሎ አስተማረን። አዎ ያን የመሰለ የሃገር ኩራት የስነ-ህንጻ ጥበብ እንድናይ ድንጋዬች እንዲሁ በራሳቸው አልተከመሩም በብዙ የነጠሩና የተቀመሩ ቀመሮች ፤ የሃሳቦች መቀባበል እና የብዙ ጉልበት  ውጤት እንጅ፤ተመልከቱ እንዲህ ዓይነት ጥበቦችን የማቀናጀት ብቃት ያለን ህዝቦች ነን። ዛሬ ላይ እንኳንስ ሌላኛውን ወገን ለማዳመጥ እራሳችንን እንኳን በአግባቡ የምናዳምጥበት አቅል አጥተናል ቆም ብለን እናስብ።

በእጅጉ እየቆዘምኩ የምገረምበት ነገር ቢኖር በዓለማችን ከፍተኛ ተጽዕኖን በፈጠሩት በመጀመሪያዎቹ ቅዱሳት መጽሃፍት በመጽሓፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን ሰፊ ሥፍራን የያዘ ሃገርና ሕዝብ፤ በቅኔው ጥልቀትና ውበት ዓለምን ያስደመመው ታላቅ ደራሲ ሆሜር “በጠባያቸውና ውስጥ ነቀፌታ የማይገኝባቸው ኢትዬጵያውያን” ብሉ የመሰከረለትና ያወደሰው ሕዝብ ከደለበው ታሪኩና ከገዘፈው ስሙ ጋር የት ነው ያለው? በረጅም ታሪኩ ዝናን ያተረፈው ታላቅ ሕዝብ ብዙ ርቀትን ተጉዞ በዚህ ባለንበት ዘመን ታላቅ መሪን ያለማግኘቱ ዕንቆቅልሽ ምን ይሆን? ከቀላል መልሶች ስንነሳና ራሳችንን ስንመረምር  ግን የአንክሮ ጊዜ የሌለን የግርግር ሰዎችና የውቂው ደብልቂው ጉዶች የመሆናችንን ጉዳይ ነው!። መቼም ጭዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ነውና አንድ ጊዜ እውቁ የኪነጥበብ ሰው ሳህሌ ደጋጎ፤ ዛሬ በህይወት ከሌለውና የምኒሊክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ መምህር የነበረው ትሁቱ፤እውነተኛውና ለህሊናው የሚጠነቀቀው አስተማሪዬ፤ ጓደኛዬ ተስፋዬ ታደሰ /በአጋጣሚውም የወገኖቻችንን ነፍስ ይማር  /። ወቅቱ ደርግ እንዲህ እንደዛሬው ተረኞች ሊወድቅ እየተንደፋደፈ የነበረበት ጊዜ ነው ታዲያ አንዲት ቦታ ላይ ቁጭ ብለን ስንጫወት ጋሽ ሳህሌ ሙያውን በተመለከተ ምን ያክል ከሰዋዊ ማንነታችን እየወረድን ወደ እንሰሳነት እየገሰገስን እንደሆነ ሲነግረን “ወገኖቼ ነገሩ ነጥቀህ ሩጥ ነው” ብሎ ቋጠራት። ለትውልድ የሚተርፍ እርሾ ሳይጠርቱ ለራስ ኖሮ ማለፍ፤ በራስ ወዳድነት የተለከፈ ማንነት እግዜኦ……!!!

መቼም ኪነጥበብ ሙያዬ ነው በሙያዬ ዘርፍ ደግሞ ዘና ብዬ የመናገር መብትም አቅምም አለኝ ብዬ አምናለሁ። አስተዋዮቹ አባቶቻችን የሰርግ ዘፈኖች፤የፍቅር ዘፈኖች የጦርነት ፉከራና ሽለላ፤ የሃዘን እንጉርጉሮ፤ የመንፈሳዊ ዜማዎች የመሳሰሉትን በወግ በወጉ ሰድረውልን ነው ያለፉት ምግቡንም እንዲሁ!። በሃዘን ጊዜ የሰርግ ዘፈን አይዘፈንም ከወቅቱ ድባብ ጋር ይላተማል ነውር ነው። ቆሎ ለመክሰስ እንጅ ለቁርስ እንደማይቀርበው ሁሉ ማለት ነው። ሁላችንንም አንድ የሚያስማማን ነገር አለ ብዬ አምናለሁ ይህ ዘመን ለኢትዬጵያና ለኢትዬጵያውያን የሃዘን ዘመን  ነው ይህ ደግሞ ከወያኔዎቹ ጎራ ውጭ ላለነው ወገኖች የተገለጠ ዕውነት ነው።  ዘመን የሰጣቸው የአንድ ዘመን ወጠጤ ጎረምሶች ተጠራረተው ሃገር ለማፍረስ ዶልተው ተሳካላቸው መልካም። መሳካት እንዲህ ከሆነ ሌባም ሰርቆ ይሳካለታል ያ አይደለም ጥያቄው ዋናው ነገር በእኛ በኩል ግን  ዓላማውን በመደገፍ ረገድ  የህሊናችንን የብጽዕና ወይም የእድፈት ደረጃ እንድንፈትሽ ያስገድደናል። ግን እኮ እኛም ራሳችን ሳይቀር እንዴት ግራ እንደተጋባን እናስተውል። ሃገር በእነዚህ ጎጠኛ ዱሩጌዎች እጅ ወድቃ እየተበጠበጠች ምድሪቱ የዕንባ ቋት ሆና እያለች ሚዲያዎቻችን በዘፈን አስረሽ ምችው ሲሉ ድባብ የማይገባን ደንጉሎች መሆናችን አይደለም ወይ? ምን ዓይነት ዜማ በምን ጊዜ መጠቀም እንዳለብን እንኳን ለመለየት አቅም ያጣን ስንኩሎች ሆነናል የዕውን ዓለም አብሱርድ!!!።

ጩኽቴ ሰው የመሆን መለኪያ ነባር ቅርሳችንን እንምዘዝ እንጠቀምበትም ነው የምለው። በሃገራችን  እንደዛሬው የባንክ አገልግሎት ባልነበረበትና ባልተስፋፋበት ዘመን የሃገሬ ሰው ገንዘብ በአደራ ሲያስቀምጥ ከግራ ከቀኝ አይቶ፤የመመዘኛ አቅሙን ጥግ ድረስ ተጠቅሞ በመለኪያው በገጠሙለትና  በታመኑ ሰዎች እጅ ነው። ታዲያ ሁለቱም አደራ ሰጭም ተቀባይም የመለኪያ ሚዛናቸው የረቀቀ ነው። ሰጭ ንብረቱን የት እንደሚጥለው ያውቃል ዝምድና ወይም ቀረቤታ አይደለም መለኪያው ስዕብና ነው እውነተኛውን ሰው ሆኖ መገኘት!። ተቀባይም ገንዘብ ስለተገኘ እጁን ቶሎ አይሰድም ከገንዘብ በላይ የሚጠነቀቅለት በማህበረሰቡ መሃከል የገነባው ስም አላ!። “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም አይደል የሚለው” መጽሃፉ።  ተቀባዪ አደራ አስቀማጭን በጥያቄ ይይዛል ከእኔ ይልቅ እገሌ አይቀርብህም ወይ? ፤እገሌም  ከኔ የተሻለ የከበረ ሰው አይደለም ወይ? ይላል። ይህንንና መሰል ነባር ማህበረሰባዊ የመለኪያ እሴቶቻችንን በመጠቀም  ፖለቲከኞችን፤የፖለቲካ ድርጅቶችንና  የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ልንፈትሻቸው ይገባል። እንደ እስስት ቀለማቸውን እየቀያየሩ፤ እንደ እባብ ገላቸውን እየገለበጡ በህዝብ ደም የሚቀልዱትን ሰው መሰል ሸልመጥማጦች የደረቡትን የአስመሳይነት ካባ አስወልቀን ከሰልፉ ልናባርራቸው ይገባል።

እያልኩ ያለሁት መሪዎቹን ፈትሾ፤ በትክክለኛው መንገድ ቀርፆ ማሳደግና ለተገቢው ሥልጣን የማብቃቱ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የሕዝብ ነው ባይ ነኝ። ሕዝብ መሪውን መዝኖና በርብሮ ሊፈጥረው ይቻለዋል ። በአንፃሩም በህዝብ እጅ ለተቀረፀውና ለተፈጠረው መሪም የሕዝብ ወኪል መሆኑን አምኖ የመቀበልና የመገዛት ኃላፊነት አሁንም የሕዝብ ነው። እርግጥ ነው  በሃገራችን ይሁን በዓለማችን ዙሪያ የሞራልን ሕግ በውስጣ ቸው ያዳበሩ ወደ መንፈሳዊ ልዕልና ገስግሰው ብፅዕናን የተላበሱ መሪዎችን ማግኘት ሕልም እየሆነ  እየከበደም ነው። የኛው ቤት ጉድ ግን በእጅጉ የተለየ ነው ሃገራችን የምንዱባንን የማያቋርጥ እንባ የምታፈልቅ የሴኦል ዋና መዲና አደርጓታል። ይሁን እንጂ ለእግዜሩም ለሰይጣንም ያልደቆኑ ነገር ግን መሃልተኛ የሆኑና በህሊና እውነት የሚኖሩ መሪዎችን ማፍራት ግን እንችላለን ባይ ነ ኝ።

ምንም እንኳን በሕዝብ ፈቃድ የወጣ በሕዝብ ፈቃድ የወረደ መሪ በዘመናችን እስካሁን ለማየት ባንታደልም በምናልፍበትና በዚህ ውሽንፍር በበዛበት አስቸጋሪ የትግል ታሪካችን ሂደት ግን መውጫው ላይ የተላቆጥንበትን የመከራ ዘመን የሚመጥን ጥሪት ለመጨበጥ ከወዲሁ ከድንዛዜ፤ ከማናለብኝነትና ከአድርባይነት ጋር ተሞሻልቀን በሚወጣው ደምና ላብ መጭው ዘመናችንን ከሩቅ ሩቅ በሚታይ ብሩህ ቀለም ሰቆቃወ ብሄርን ልንከተብ ፤የመጣንበትን ኮረኮንች ለቅመንም ኤቨንኤዜር ብለን ልንደረድር ግድ ይለናል። መጣ ሄደት እያለ ዳግመኛ የሌላን ትውልድ ስጋና ነፍስ ሰርቆ ዋጋ ሳያስከፍልብን እኛው በእኛው ጣጣችንን በንስሃም በግብርም ልንጨርስ ያስፈልጋል ። በመሆኑም መሪዎቻችን የምንላቸውን ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሚዲያ ተቋማትን በመፈተሽ ዙሪያ ላይ ከደለበው ታሪካችን ዘግነንና እንደ ሕዝብ ራሳችንን መርምረን ልምዳችንን እንድንጠቀም  የሚያስገድዱን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉብን ላማሳሰብ ነው አለበለዚያ ዙሪያው ገደል ነው ።

– ነጋ አባተ – ዋሽንግተን ዲሲ- ቸር ያገናኘን።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *