የአንዲት ተማሪ ወላጅ ልጃቸውን ሊያስመዘግቡ ቃሊቲ አካባቢ ወደሚገኘው ኖላዊ አፀደ ህፃናትና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ይሄዳሉ፡፡ ከትምህርት ቤቱ ባለቤት አቶ ተስፋዬ አግዘው ጋርም ይገናኛሉ፡፡ ወላጅ በውስጣቸው የጨነቃቸውን ነገር ለትምህርት ቤቱ ባለቤት ይተነፍሳሉ፡- “እኔ በህይወት ብዙ መቆየት አልችልም፤ እባካችሁ ልጄን እንደ ልጃችሁ ተንከባክባችሁ አሳድጉልኝ” በማለትም ይማፀናሉ፡፡
የትምህርት ቤቱ ባለቤት በሁኔታው በመደናገጥ “ምን ሆነው ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ወላጅ ከእንባቸው ጋር እየታገሉ፤ “የኩላሊት በሽተኛ ነኝ፤ መዳን አልችልም” አሉ፤በተስፋ መቁረጥ ስሜት፡፡
የትምህርት ቤቱ ባለቤትም፤ “እንግዲያውስ ግዴለም እንዳሉት አደርጋለሁ” ሲሉ ቃል ገብተው ይሸኟቸዋል፡፡ እኚህ ወላጅ ዛሬም የአልጋ ቁራኛ ሆነው ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ይገኛሉ፡፡
አቶ ተስፋዬ ከዚያች ደቂቃ ጀምሮ የሰውየው ነገር እረፍት እንደነሳቸው ይናገራሉ፡፡ ሁለት ቀን እንቅልፍ አልተኛሁም ነበር የሚሉት የት/ቤቱ ባለቤት፤ወዲያው በኩላሊት በሽታ ለሚሰቃዩ ወገኖች ለምን የአቅሜን አላደርግም በማለት ከተማሪዎችና ከአካባቢው ማህበረሰብ መዋጮ ለማሰባሰብ መወሰናቸውን ይናገራሉ፡፡ የትምህርት ቤታቸው የዓመቱ መዝጊያ በዓል በተከበረበት ባለፈው እሁድ ከተማሪዎች 7 ሺህ ብር የተሰበሰበ ሲሆን ከኪሳቸው 20 ሺህ ብር በመጨመር ፣በአጠቃላይ 27 ሺ ብር በስፍራው ተገኝተው ለነበሩት የኩላሊት ህሙማን ማህበር መስራቾችና ሊቀመንበር አስረክበዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ የመዝጊያ ስነ ስርአት ላይ የታደሙት የተማሪ ቤተሰቦች በበኩላቸው 21 ሺህ ብር አዋጥተው ለኩላሊት ህሙማን ለግሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ባለቤት በቀጣይም ለኩላሊት ህሙማን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን መሰል ተቋማትም ለህሙማኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ገንዘቡን የተረከቡት የኩላሊት ህሙማን ማህበር አመራሮችም፣ገንዘቡ በቀጥታ ለህሙማኑ መታከሚያ እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅት በወር በአማካይ 23 ሰዎች ኩላሊታቸው ተጎድቶ ወደ ዳያሊስስ ህክምና እንደሚመጡ የገለፁት የማህበሩ አመራሮች፤ ከታማሚዎቹ ከ60 በመቶ በላይ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ16-30 የሚሆናቸው ወጣቶች ናቸው ብለዋል፡፡
“ህመሙ በአስጊ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው” ያሉት የማህበሩ ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን አሰፋ፤ በሁለት ወር ውስጥ በዘውዲቱ ሆስፒታል የተገነባው አዲሱ የህክምና ማዕከል ስራ እንደሚጀምር ጠቁመው፣ማዕከሉ አገልግሎቱን ሲጀምር አንድ ታማሚ ቀደም ሲል ለዳያሊስስ ህክምና በሳምንት የሚያወጣው እስከ 4 ሺህ ብር የሚደርስ ወጪ፣ ወደ 300 ብር ዝቅ ይላል ብለዋል፡፡ ለህሙማን ትልቅ ተስፋ ነው!!

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?

addisadmass news paper

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *