ባገራችን ፣በብሄረሰቦች ስያሜ ዙርያ በየጊዜው የሚያገረሽ ውዝግብ መነሻው ሁለት ነገር ነው:: የመጀመርያው አላዋቂነት ሲሆን ሁለተኛው ክፋት ነው::

ለምሳሌ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ተብለው እንዲጠሩ ይፈልጋሉ:: ይህን ፍላጎት ለማሙዋላት የሚጠይቀው ምን ውጣ ውረድ አለ? ቅንነት ብቻ በቂ ነው:: ይቺን ጠብታ ላብ የማትጠይቅ ነገር ሳይቀበሉ፤ ስለጋራቤታችን ተቆርቁዋሪ ነኝ እያሉ የሚመፃደቁ ሰዎች አያሳዝኑም??

አንዳንዱ ፣”እኔ አውቅልሃለሁ “ለማለት የሚሄድበት ርቀት እጅን ባፍ የሚያስጭን ነው:: ለምሳሌ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ያባ ባህርይ ድርሰቶች በተባለ መፅሃፉ” ጋላ”የሚለው ቃል ስድብ እንዳልሆነ ለማስረዳት አብዝቶ ደክሙዋል:: በጉዳዩ ላይ የፃፈውን ረጅም ሀተታ ያሳረገው እንዲህ በማለት ነው፤

“ዛሬ ጋላ ስድብ ነው የሚል እሰማለሁ እንጅ፤ ባደግሁበት አካባቢም ሆነ በማውቃቸው ምንጮች ዘንድ ቃሉ እንደማንኛውም የህዝብ ስም የገለልተኝነት መጠርያ እንጅ ስድብነት የለውም:: “

ይህ አባባል ከውነት የራቀ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ምርምር አይጠይቅም :: ጌታቸው ሃይሌ ካደገበት አካባቢ የመነጨው ፤ አለቃ ዘነብ “መፅሀፈ ጨዋታ ” በሚለው ስመጥር ስብከቱ” ሰውን አንተ ባርያ አንተ ጋላ ብለው ቢሰድቡት የአዳም ልጅ መሆኑን አይተውም “ብሎ ፅፉዋል:: ዘነብ፣ “ጋላ” የሚለው ቃል ስድብ መሆኑን ከመግልፅ አልፎ፣ ባርያ ከሚለው ቃል ተርታ እንዳሰለፈው ልብ እንበል::

ከጥቂት አመታት በፊት ፕሮፌሰር አለም እሸቴ መድረክ ላይ ወጥቶ ኦሮሞ የሚለውን ቃል ካብዮቱ ወዲህ የተፈጠረ ነው ብሎ ሲናገር ተሰምቱዋል:: የሚፈልግ ሰው ዩቲብ ውስጥ ገብቶ ቪድዮውን ማየት ይችላል:: ሰሞኑን ደሞ ፤ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ የተባለ ባለሳምንት ፤” ይህ ጋላ የሚባል ህዝብ ፤ አሁን ኦሮሞ ነው የሚባለው:: እኔ በዚህ መጠርያ አልስማማም”ይላል: : የወንድሙን ስም ለመቀበል የጎፈነነው ሰው ፤ ስለወንድማማችነት ለመስበክ ቴሌቪዝኑን ሲያጣብብ ማየት አይገርምም? ለመሆኑ ፣በዚህ ሰውየ የሰአት አቆጣጠር “አሁን ” ስንት ነው?

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

ኦሮሞ የሚለው ቃል ፕሮፌሰር ላሬቦ እንደሚለው “አሁን ” የመጣ ሳይሆን ፣ከጥንት ጀምሮ የህዝቡ ስም ነው:: ስያሜው በብዙ ቀዴምት ያውሮፓመንገደኞች መፃህፍት ውስጥ ተመዝግቦ መገኘቱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል:: ለምሳሌ እንጦኒዮስ ዳባዲ የተባለ መንገደኛ በ1888 ላሳተመው ጥናት የሰጠው ርእስ “ጋላ በሚል ስም ለስለሚጠሩት ኦሮሞች -ያፍሪካ ታላቅ ህዝብ “የሚል ነበር:: ወንድሙ ሚካኤልም ፤ ደጃዝማች ጎሹ ስላደረጉት ዘመቻ ሲፅፍ፣” ጋላ በሚባሉት ኦሮሞዎች ላይ የተካሄደ ዘመቻ”(campagne contre les ilmormas dits gallas “ይላል::
ቱቸር የተባለ የጀርመን ሊቅ ሁለት የኦሮሞ ተወላጆችን በ1844 ሙኒክ ላይ አግኝቶ ከነሱ እያጠያየቀ መዝገበቃላት አሰናዳ:: በመዝገበቃላቱ Oromo የሚለውን ቃል ሲፈታ “The name by which the Gallas call themselves in comparison with other nations .ይላል::

ጣልያናዊው ፕሮፌሰር ቪትርቦ በ1887፣ ያሳተሙት የሰዋስው መፅሀፍ ርእስ ” Grammmatica Della lingua Oromonica የሚል ነው::

ዛሬ ፤መረጃ እንደ ጠንቁዋይ ጠልሰም ፤በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ የሚገኝ ብርቅ ነገር አይደለም:: እድሜ ለኢንተርኔት ፣ጥንታዊ ሰነዶች ለብዙሃን እንዲደርሱ ሆነው ተነዝተዋል:: አፍ አመጣልኝ ተብሎ የወንድማማች ህዝቦችን ፍቅር የሚያደፈርስ ነገር መናገር ውሎ አድሮ ያስገምታል::

(በጨዋ ደንብ ለሚወያይ ሰው ቤቴ ክፍት ነው:: ለስድብ ደሞ ማርከሻው ፤ማርክ ዙከርበርግ ዘንድ አይጠፋም)

Related stories   የአውሮፓ ህብረት የይስሙላ ምርጫዎች ሲታዘብ ቆይቶ አሁን አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ

አስተያየቶች

Getatchew Haile እኔ ባደግሁበት አካባቢና በታሪክ ሰነዶች ውስጥ ቃሉ ስድብ አልነበረም። የገዳ ሥርዓትም በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ያልኩበትንም ምክንያት ሰጥቻለሁ። ስደመድምም ደግሞ እንዲህ ብያለሁ፤ “ያምሆነ ይህ፥ ዛሬ ኦሮምኛ ተናጋሮዎች ‘ጋላ’ ስድብ ነው፤ ስትጠሩን ኦሮሞ በሉን እንጂ ጋላ አትበሉን” ካሉ ፈቃዳቸው ይሁንላቸው” የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፥ ገጽ 103. ኦሮሞዎች ቃሉን መጥላታቸውን ከዐወቅሁ ጀምሮ፥ ሰነድ ስጠቅስ ካልሆነ በቀር ተጠቅሜበት አላውቅም። ሌሎችም እንዳይጠቀሙበት ሲያጋጥመኝ ሁሉ ተከላክያለሁ።ተቃቅሮ አብሮ መኖር አይቻልም። ሰላም መሰማማትን ይጠይቃል። ይኸም የኔ ነው፤ “ጡጤ ከቤታችን አጠገን ቁመቱ አጭር የሆነ ረጅም ካብ አለ። ነፍስ ሳውቅ ለምን እንደተካበ ብጠይቅ የተነገረኝ ሕዝቡ በዚያ ጊዜ ጋላ የሚላቸው ኦሮሞዎች ሲወርሩ እነሱን ለመመከት የተገነባ መሆኑን ነገሩኝ። እዚያ ቦታ አማሮቹና ኦሮሞቹ አሁን ጎረቤቶችና ጋብቾች ናቸው።” አንዳፍታ ላውጋችሁ ገጽ 26.

Abdulhaq Sirage Islam እውነትህን ነው እኔ በግሌ ኦሮሞም አማራም አይደለውም ፤የኦሮሞ ህዝብ እኔ መጠሪያዬ ኦሮሞ ነው እያለ አይደለህም እኔ ነኝ ያንተ መጠርያ የማውቀው ብሎ ክርክር ለምን ያስፈልጋል? እንዚ የታሪክ ሙህሮች ጊዜ እየጠበቅ ብቅ ብለው ኦሮሞን በመዝለፍ ለዚች ሀገርና ህዝብ ሊያስገኙት ያቀዱት ጥቅም ምን ይሆን ? እስኪ በቤታችን እንኳን ወንድማችን የሚጠላውን ካለከበርንለት ጠላታችን እንጂ ወንድማችን ሆኖ ይቀጥላል? ኦሮሞ ስሜ ኦሮሞ እንጂ ሌላ አይደለም ካለ አለቀ ኦሮሞ ነው ተንኩወል ያላነገበ ጤነኛ ሰው መከራከሪያ አጀንዳ ማንሳት አለበት ብዬ አላምንም።

Zerayakob Amdetsion በውቀቱ ስዪም ወደኋላ ሄጄ እራሴን ለማየት አስገደደኝ። በእውቀቱን በጣም ነበር የማደንቀው። እንዲያውም ‘ፀጋዬ ገብረመድህንን የሚተካው እሱ ነው’ እያልኩ ብዙ ጊዜ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተወያይቻለሁ(ተመሳሳይ ባይሆንም በስነጽሑፍ ዘርፍ ለማለት ነዉ)። ፀጋዬ ገብረመድህን ከሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦች የተገኘ ነው። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በውቀቱ ስዪምም ተመሳሳይ እንደሆነ በቅርቡ አበሰረን። መልካም ነው።
‘ለመሆኑ የበውቀቱ አድናቂ የሆንኩት ለምን ነበር?’ የሚል ጥያቄ መጣብኝ ። እራሴን ማየት ጀመርኩ አዎ ‘ለምን ይሆን?’ ምናልባትም ታሪክ ቀመስ መጣጥፎችን ስለሚያዘወትር ይሆን?! ግራ ገባኝ ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክን ማወቅ በጣም እወዳለሁ። እድሜ ፖለቲካና ታሪክን እየቀላቀሉ ለሚያወናብዱ ወመኔ ፖለቲከኞቻችን፤ እንጂማ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የሶሻልሳይንስ ተማሪ እንዳልሆን ያደረገኝ የታሪክ ትምህርት መጥላቴ ነበር። እውነት ለመናገር እጅግ በጣም ጠልቼው ሳይሆን በአንፃራዊነት ነበር። እናም ወደ በውቀቱ ስመለስ የወደድኩበት ምክንያት መጣጥፎቹ ልክ በማር እንደተጣለ ጠጅ ወይም ደግሞ በማር እንደተበረዘ ጠላ በታሪክ መቃኘታቸው ይመስለኛል። ከተወሰኑ ጊዚያት ወደዚህ ግን ልክ በፊት እጠላው የነበረውን ታሪክ ለመውደድ እንደተገደድኩ፤ በውቀቱ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ላይ ያለኝ አመለካከት በተቃራኒው እያደገ መጣ። ምክንያቱ ምን ይሆን? ይመስለኛል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድም በጽሁፎቹ ልክ እንዳልተገራ በቅሎ ኮትኩተው ያሳደጉትን መራገጡ ይሆናል፤ አለበለዚያም ከእውነት ይልቅ በሁሉም እወደድ ባይነት በጽሁፎቹ እያሳየ ይሆናል። እናም በዚሁ እርግጫው ከቀጠለ ‘የት ይደርሳል የተባለው.. ..’ እንዳይሆን ያሰጋል።

ከአዘጋጁ- ሙሉውን የአስተያየት ምልልስ ጽሁፉን ካገኛችህበት ከበእውቀቱ ስዩም የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ተመለከቱ፤ ይህንን አስመልክቶ ማንኛውም ጨዋነት የታከለበት አስተያየት እናስተናገዳለን

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *