በሃላባ ልዩ ወረዳ ያዩ በተባለ ስፍራ ባለፈው አርብ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአንድ ቤተሰብ ሙሉ አባላት ህይወታቸው አለፈ። ከሀዋሳ ወደ ሆሳዕና እየተጓዘ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ከሃላባ ወደ ሃዋሳ ሲጓዝ ከነበረ ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭተው ነው አሳዛኙ የትራፊክ አደጋ የደረሰው።

በአደጋው ሶስቱ ወንድማማቾች ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል። የሟቾቹ ሁለት ልጆች ደግሞ ሀዋሳ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸውን አጥተዋል። በጣም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ከነበሩ ስድስት ሰዎችም የአንደኛው ህይወቱ ማለፉን ከደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮማንደር ዘሪሁን መላኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤ ሲኖትራክ ተሽከርካሪው ያለመስመሩ ገብቶ የህዝብ ማመላለሻ (ዶልፊን) ተሽከርካሪውን ገጭቶ ከመንገድ ማስወጣቱ ነው። የሲኖትራኩ አሽከርካሪ በሀዋሳ ከተማ ለፖሊስ እጁን ሰጥቷል። በተመሳሳይ ዜና በወገራ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል።

ከጎንደር ወደ ደባርቅ ከልክ በላይ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ (ሚኒባስ) ባለፈው ቅዳሜ አምባ ጊዮርጊስ ከተማ አቅራቢያ ወይላሆ በተባለ አካባቢ በመገልበጡ ነው የሰባት ዜጎች ህይወት የተጠቀፈው። የወገራ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ኢንስፔክተር ደርሶ ስንታየሁ እንደገለጹት፥ በፍጥነት ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ ሊገለበጥ የቻለው አሽከርካሪው መንገድ ላይ የገባበትን አህያ ለማዳን ሲሞክር ነው።

ከሟቾቹ በተጨማሪ 14 ተሳፋሪዎችም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፥ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል። ከሟቾቹ ውስጥ ሁለቱ ህፃናት ሲሆኑ፥ ከቆሰሉት መካከልም ሶስት ህፃናት ይገኙበታል።  ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ሲጓዙ የነበሩ እናትም ልጆቻቸውን በሞት ሲያጡ እርሳቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል።

 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በነብዩ ዩሃንስ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *