(ዳንኤል ክብረት) ወዳጆቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት?!
እነሆ ታክሲ ይዤ ከሲ ኤም ሲ ወደ መገናኛ ለመሄድ መንገድ ዳር ቆሜ ነው፡፡ እንዳጋጣሚ አንዲት ዲ ኤክስ መኪና ከፊቴ ቆመች፡፡ የምታሽከረክረው ልጅ በእጇ እንድገባ ጠቆመችኝ፡፡ «ስታስተምር ስለማውቅህ ነው» አለችኝ፡፡ አመስግኜ ጋቢና ተቀመጥኩ፡፡ የተቀመጥኩበት ወንበር ላይ በመስተዋት የተለበጠ ጥቅስ ነበረበት፡፡ መስተዋቱ የተያያዘበት ፍሬሙ በአበባ ያጌጠ ነው፡፡ ምናልባት ለሰው ልትሰጠው ያዘጋጀችው መሆን አለበት፡፡ እንዳጋጣሚ ጥቅሱን አንሥቼ ከኋላ ወንበር ላይ ሳደርገው «ስላላደረግክልኝ ነገር ሁሉ አመሰግንሃለሁ» ይላል፡፡
የጻፈው ሰው ስሕተት ሠርቷል፡፡ መሆን የነበረበት «ስላደረግክልኝ ሁሉ» ነው፡፡ በስሕተት አንድ ተጨማሪ «ላ» አስገብቶበታል፡፡ ልንገራት ወይስ ልተወው እያልኩ አመነታሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን ስሕተት ላታስተውለው ትችላለች ብዬ ስላሰብኩ መንገሩን መረጥኩ፡፡ «ጥቅሱን የጻፈልሽ ሰው ሳይሳሳት አይቀርም» አልኳት ቀስ ብዬ፡፡ «እውነትክን ነው» አለችና አንድ እጇን ወደ ኋላ ልካ ጥቅሱን ወደ እሷ አምጥታ አየችው፡፡ «የቱ ጋ ነው ባክህ የተሳሳተው» አለችኝ፡፡ «ስላደረግክልኝ ለማለት ፈልጎ ስላላደረግክልኝ ብሎታል» አልኳት በጣቴ ፊደሉን እያሳየሁ፡፡ «እርሱን ነው እንዴ ፤ አይ ፈልጌው ነው» አለች ጥቅሱን ወደ ቦታው እየመለሰች፡፡
«ስላላደረግክልኝ የሚለውን ነው የፈለግሽው?»
«አዎ ፤ አይባልም እንዴ»
«ሰምቼ አላውቅም»
«ለሌላ ሰው ላይሠራ ይችላል፡፡ ለኔ ግን ይሠራል»
«እንደዚህ የሚል ጥቅስ ግን ያለ አይመስለኝም»
«ይህ ከሕይወት መጽሐፍ የተገኘ ጥቅስ ነው» አለችና ፈገግ አለች፡፡
«የቱ ነው ደግሞ የሕይወት መጽሐፍ?»
«እያንዳንዱ ሰው የየራሱ የሕይወት መጽሐፍ አለው፡፡ በዚያ መጽሐፍም በሕይወቱ ያገኛቸው ነገሮች ተመዝግበዋል፡፡ በዚያ መጽሐፍ በሕይወት ተፈትነው የነጠሩ ምርጥ ምርጥ ጥቅሶች ይገኛሉ»
«ፈላስፋ ነገር ሳትሆኚ አትቀሪም»
«አንተም የሕይወት መጽሐፍህን ካነበብከው ፤ ፈላስፋ መሆንህ አይቀርም፡፡»
«ግን ለምንድን ነው ስላላደረግክልኝ ሁሉ አመሰግንሃለሁ ያልሽው»
‹‹አየህ እያንዳንዱ ጥቅስ ከጀርባው የሚጠቀስ ታሪክ አለው፡፡ ታሪኩን ካላወቅከው ጥቅሱ በደንብ አይገባህም»
«እስኪ በደንብ እንዲገባኝ ታሪኩን ንገሪኝ»
«እንዲህ በቀላሉ ያልቃል ብለህ ነው»
«አንድ ቦታ አቁመን ለምን አትነግሪኝም»
«ይህንን ያህል ያስፈልግሃል?»
«በጣም አጓጓኛ ፤ ስላላደረግክልኝ ሁሉ አመሰግንሃለሁ የሚል ሰምቼ አላውቅማ»
መገናኛ ስንደርስ ወደ አንድ ጥግ አቆመች፡፡ እናም እንዲህ ነገረችኝ፡፡
እንደ እኔ ውጭ ሀገር መሄድ የሚወድ ሰው አልነበረም፡፡ ከቻልኩ እንደ ሰው ቪዛ አግኝቼ ካልቻልኩም እንደ በርበሬ እና ሽሮ ተፈጭቼ አሜሪካ መሄድ አለብኝ ብዬ ቁርጥ ሃሳብ ነበረኝ፡፡ ያውም ደግሞ አሜሪካ ገብቼ ዜጋ መሆን ነው የምፈልገው፡፡ እዚህ ሀገር መማር፣ መሥራት፣ መኖር ፈጽሞ አልቻልኩም፡፡ ሕልሜም እውኔም አሜሪካ ነው፡፡ ስለ ጤንነቴ ከሚጠይቀኝ ሰው ይልቅ ስለ አሜሪካ የሚነግረኝን ሰው ነበር የምወድደው፡፡ ያ በጣም የሚወድደኝ እና የምወድደው አጎቴን እንኳን አስቀይሜዋለሁ፡፡ እርሱ ዜግነቱን የሚለውጥ ሰው ደመኛው ነው፡፡ ከወንድሞቼ እና እኅቶቼ ጋር ምነው ምንስ ቢሆን እንዴት ዜግነት ይቀየራል? እያለ ይጣላል፡፡ እኔ ደግሞ ካልቀየርኩ ሞቼ እገኛለሁ ብዬ ተነሣሁ፡፡
ቤተሰቦቼ ቢሉኝ ቢሠሩኝ ይህንን ሕልም መተው ስላልቻልኩ አለ በሚባለው መንገድ ሁሉ እኔን አሜሪካ ለመላክ ሞከሩ፡፡ ከአጎቴ በቀር፡፡ አንድን ነገር ሙጭጭ ስትልበት ጥምም ነው የሚልብህ፡፡ ለጓደኞቼ የተሳካው መንገድ ሁሉ ለእኔ ጠመመ፡፡ ሌላው ቀርቶ ኬንያ ሄጄ ፕሮሰስ ጥበቃ ሦስት ዓመት ተቀመጥኩ፡፡ ጠብ የሚል ነገር አልነበረም፡፡
የኬንያው አልሳካ ሲል ዑጋንዳ ገባሁ፡፡ እዚያ እንዲያውም የተሻለ ነገር ማየት ችዬ ነበር፡፡ አንድ ፕሮሰስ ገዝቼ አንድ ስድስት ወር ጠበቅኩና ተሳካ፡፡ ለኢንተርቪው ተጠርቼ ስገባ ሰውነቴ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ የማውቀውን ነገር እንኳን መናገር አቃተኝ፡፡ የኔ መውደቅ ሳያንስ ባለ ፕሮሰሱንም አዘጋሁበት፤
እንደገና አገሬ ገብቼ ሌላ ነገር ጀመርኩ፡፡ ዲቪ ገዝቻለሁ ፤ ፎርጂድ ፓስፖርት ለማሠራት ሞክሬያለሁ ፤ ለባዛር እና ለኤግዚቢሽን በሚል ቪዛ ለማሠራት ገንዘብ ከሰክሻለሁ፡፡ ብቻ ተወው ፤ ጓደኞቼ «ዋልያ» እያሉ ይቀልዱብኛል፡፡ እንደ ዋልያ ከሀገሬ ውጭ እንድኖር አልተፈቀደልኝማ፡፡ ያልተሳልኩት ታቦት ፤ ያልሄድኩበት ጠበል ፣ ያላማከርኩት ባሕታዊ ፣ ያልከፈልኩበት ኤምባሲ የለም፡፡ ሁሉም ጭጭ ምጭጭ አሉ፡፡
ሲጨንቀኝ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላሁ፡፡ ባይኖር ነው እንጂ ቢኖርማ እንዴት ይህንን ሁሉ ጸሎት ፤ ይህንን ሁሉ ሥዕለት አይሰማም ፤ ቢያዳላ ነው እንጂ ባያዳላማ ለሌሎች ያደረገውን ለእኔ ማድረግ እንዴት ያቅተዋል ብዬ ተቀየምኩት፡፡
ቀና ብዬ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ
አላህን ሠፈራ ወሰዱት መሰለኝ
ያለውን ወሎዬ ታስታውሰዋለህ፡፡ በ1977 ከድርቁ በኋላ ነበር እንዲህ ያለው፡፡ እኔም እንዲያ ነው የሆነብኝ፡፡
አንዷ እንደኔ የጨነቃትም
‹‹አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል›› ብላለች አሉ፡፡
በመጨረሻ በኑሮዬ ተስፋ ቆረጥኩና ከማይሆኑ ልጆች ጋር ገጠምኩ፡፡ የሕይወቴ መመርያ መቃም ፣መጠጣት ፣ መጨፈር ሆነ፡፡ ተያይዘን ከከተማ እንወጣለን፡፡ እንቅማለን እንጠጣለን፡፡ ከዚያም ሊደረግ የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ላይፍ እንቀጫለን፡፡
እናቴ አዘነችብኝ፡፡ ውጭ ያሉት ወንድሞቼ እና እኅቶቼም እየደወሉ ሊመክሩኝ ሞከሩ፡፡ ማን ሊሰማቸው፡፡ አጎቴማ ዘወትር ኀዘን ብቻ ሆነ ሥራው፡፡ ዘመዶቼ ሁሉ ለምክር ተሰለፉ፡፡ እነርሱ ሊመክሩኝ ባሰቡ ቁጥር እኔ ከእነርሱ ራቅሁ፡፡ በኋላ ላይ አጎቴን «እንደዚያ ስሆን እያየኸኝ ለምን ነበር እንደ ሌሎቹ ያልመከርከኝ» ብዬ ጠይቄው ነበር፡፡ ያለኝን አልረሳውም፡፡ «ሰው በኑሮው ተስፋ በቆረጠበት ሰዓት ፣ ሰው ጥፋትን እያወቀ በሚሠራበት ሰዓት ፣ ጸሎት እንጂ ምክር አይመልሰውም» ነበር ያለኝ፡፡
አንድ ሁለት ዓመት በዚህ ሁኔታ ከቀጠልኩ በኋላ ደግሞ እርሱም ሰለቸኝ፡፡ ጓደኞቼን ሁሉ ዘጋኋቸው በሬን ዘግቼ ቤቴ መዋል ጀመርኩ፡፡ አሁን እናቴ ይበልጥ ጨነቃት፡፡ ልጄን ምን አስነኩብኝ ማለት ጀመረች፡፡ ውጭ መውጣት አስጠላኝ፡፡ ሙዚቃ እና ፊልም ከፍቼ ቤት ውስጥ መዋል ፣ ማደር ጀመርኩ፡፡
አንድ ቀን ምን እንደነካኝ አላውቅም በድንገት ተነሥቼ እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ሄድኩ፡፡ ተሳለምኩና እዚያው ቁጭ አልኩ፡፡ የተቀመጥኩት ከዋናው የግቢው በር አጠገብ ነበር፡፡ አንድ መንፈሳዊ ትምህርት ይሰማኛል፡፡ ድምፁን ወደምሰማበት ዘወር ስል አንድ ልጅ በትንሽ ቴፕ ነበር የሚያሰማው፡፡ ሄጄ ጠየቅኩትና በአሥር ብር ሸጠልኝ፡፡ የሕይወቴ ለውጥ ያኔ ተጀመረ፡፡
ቤቴ ገብቼ እየደጋገምኩ አዳመጥኩት፡፡ ውስጤን ነበር የነካው፡፡ በነጋታው ወደ እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ሄጄ ሌሎች ሁለት ካሴቶች ከልጁ ገዛሁ፡፡ ልጁ ሌላ ካሴት ከፈለግሽ ብሎ አንድ ሱቅ ጠቆመኝ፡፡ እዚያ ሄጄ ሌሎች ሁለት ጨመርኩ፡፡
በትምህርቱ ውስጥ ራሴን ነበር የማየው፡፡ ውስጤን ነበር የምመረምረው፡፡ መንገዴን ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ፡፡ እናም ከፈጣሪ ጋር መሟገቴን ተውኩ፡፡ ውጭ ስለመሄድ ማለሜን ተውኩ፡፡ ለብዙ ሰዓታት ከራሴ ጋር ከተሟገትኩ በኋላ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ተውኩት ትምህርቴ ተመለስኩ፡፡ ያኔ ቢዝነስ አስተዳደር የሚባል ትምህርት ጀምሬ አንድ ሴሚስተር እንደተማርኩ ነበር ውጭ ውጭ የሚል ዛር ለክፎኝ ያቋረጥኩት
እናቴ ማመን አልቻለችም፡፡ ቤተሰቦቼ ሁሉ ተገረሙ ፤ ግን ደግሞ ይመለስባታል ብለው ፈርተው የምላቸውን ከመፈጸም ውጭ ሊናገሩኝ አልደፈሩም፡፡
ላሳጥርለህና ትምህርቴን ላጠናቅቅ አንድ ወር ያህል ሲቀረኝ አጎቴ አስጠራኝ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ በጣም ነበር የሚወደኝ፡፡ እንዲያውም እናቴ ቤት ከኖርኩበት ዘመን እርሱ ቤት የኖርኩበት ዘመን ይበልጥ ነበር፡፡ ልጅ ስላልነበረው በእርሱ ስም ነበር የምጠራው፡፡ የእኔ ሕይወት በጣም ነበር የሚያሳስበው፡፡ በዚያ ላይ የደም ብዛት በሽታ አለበት፡፡ የኔን እንደዚያ መሆን ሰምቶ ለብዙ ቀናት አልጋ ላይ መዋሉን ሰምቻለሁ፡፡ ርግጠኛ ነኝ የመለሰኝ የርሱ ጸሎት ነው፡፡
እግዚአብሔር ሲወድድህ የሆነ ቦታ ስለአንተ የሚጨነቁ ሰዎች ይሰጥሃል፡፡ ጸሎታቸው የሚደርስላቸው ፣ ጩኸታቸው የሚሰማላቸው ሰዎች ያዘጋጅልሃል፡፡ ላታውቃቸው ወይንም ላትገምታቸው ትችል ይሆናል፡፡ ግን ስለሚወድድህ ያዘጋጅልሃል፡፡
እቤቱ ስደርስ እናቴ ፣ አባቴ ፣ ሌላው አጎቴ እና ሁለት አክስቶቼ ፣ ከውጭ የመጡ ሁለት ወንድሞቼ እና የአጎቴ የንስሐ አባት ሳሎን ተቀምጠዋል፡፡ ሊመክሩኝ ነው ብዬ ፈራሁ፡፡ ይገርምሃል አንዳች የሕይወትክን መሥመር በተስፋ መቁረጥ ስትስት ምክር ትጠላለህ፡፡ እኔም እንደዚያ ሆኜ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተለውጫለሁ ምን ፈልገው ነው? እያልኩ ገባሁ፡፡
የሁሉም ዓይን እኔ ጋ ማረፉን ሲቆጠቁጠኝ ይታወቀኛል፡፡ ካህኑ ጸሎት አደረሱ፡፡ ከዚያም አጎቴ ከተቀመጠበት ተደላደለ፡፡ «እንደምታውቁት እኔ ልጅ የለኝም፤ ባለቤቴም ከሞተች ሦስት ዓመት አለፋት፡፡ እንግዲህ የሚቀረኝ ሞቴን መጠበቅ ነው» እንዲህ ሲናገር ሳላስበው እንባዬ ከዓይኔ ይፈስ ነበር፡፡ «አሁን የጠራኋችሁ ሀብቴን ሁሉ ለልጄ ማውረሴን ለመንገር ነው፡፡ ያለችኝ ልጅ እርሷ ብቻ ናት፡፡» አልቻልኩም ተነሥቼ ተጠመጠምኩበት፡፡ ተያይዘን ተላቀስን፡፡ ካህኑ ነበር ያላቀቁን፡፡
«እንደምታውቁት አንድ ቃል ነበረኝ፡፡ የእኔን ሀብት የሚወርሰው ሀገሩን ለቅቆ ያልሄደው ኢትዮጵያዊው ልጅ ነው፡፡ ከድሮ ጀምሮ ቦታችሁን እንጂ ዜግነታችሁን አትለውጡ እላችሁ ነበር፡፡ መቼም የእኛ እና የእናንተ አስተሳሰብ ይለያያል፡፡ ከእርሷ በቀር ሁላችሁም ሄዳችሁ፡፡ ሁሉም ልጆች ዜግነታቸውን ቀየሩ፡፡ ነገሩ በዚህ ጉዳይ ከልጆቼ ብቻ ሳይሆን ከወንድሞቼም ጋር አልተስማማሁም፡፡
እንደኔ ቃል ከዚህ ሀገር ያልወጣችው ብቸኛ ተስፋዬ እርሷ ናት፡፡ እርሷንም የእናንተ ዛር ለክፏት ካልሄድኩ ብላ ነበር፡፡ የእግዜር ነገር አሥሮ ያዘልኝ እንጂ»
የአጎቴን ፋብሪካ እና ሱፐር ማርኬት ወረስኩ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ወደ አንድ ገዳም ሄድኩና የእግዚአብሔርን ሥራ ለብቻዬ አስብ ነበር፡፡ እኔ ልሄድበት የፈለግኩትን እና እግዚአብሔር የመረጠልኝን መንገድ እያሰላሰልኩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ንግግር የማይገልጠው ምስጋና አጋጥሞህ ያውቃል? ዝምታ ብቻ የሚገልጠው፡፡ እኔ እግዚአብሔርን ለማመስገን ንግግር አለቀብኝና ዝምታን መረጥኩ፡፡ አንድ ገዳም ሄጄ ቀኑን በሙሉ ዝም ብዬ እውል ነበር፡፡ እይውልህ ትናንት በመከራ ያላገኘኋቸውን ቪዛዎች ዛሬ በክብር ሄጄ እወስዳቸዋለሁ፡፡ ዛሬ አሜሪካ ካልኖርኩ አልልም፡፡ የምሄደው ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሀገሬ እንድሠራ፣ እንድከበር፣ ፈለገ፡፡ እኔ ደግሞ በሰው አገር መከራ ካልተቀበልኩ አልኩት፡፡ በግድ ጠምዝዞ ወደ ተሻለው መንገድ ወሰደኝ፡፡
ዮሴፍን ታስታውሰዋለህ፡፡ የእግዚአብሔር ዕቅድ ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ እንዲሆን ነው፡፡ የዮሴፍ ፍላጎት ደግሞ ቶሎ ከእሥር ቤት ለመውጣት ነው፡፡ ዮሴፍ በሰው በኩል ከእሥር ሊወጣ ሞከረ፡፡ እግዚአብሔር ግን በእሥራቱ ላይ ሁለት ዓመት ጨመረበት፡፡ አሁን ለዮሴፍ ከእሥራቱ ራሱ በመረጠው መንገድ መውጣቱ ነበር ጥሩ? የዚያን ጊዜ ፍላጎቱን እግዚአብሔር ቢፈጽምለት ነበር ጥሩ? እንኳንም አላደረገው፡፡ እንኳንም አልፈጸመለት፡፡ የዮሴፍ ዕቅድ ቢፈጸም ኖሮ ያንን የመሰለ ተአምር፣ ያንን የመሰለ ታሪክ የት ይገኝ ነበር፡፡
አንዳንድ ጊዜ በቀላሉ በመዶሻ የሚፈረከስ ድንጋይ አለ፡፡ እምቢ ካለ ግን በድማሚት ይመታል፡፡ የኔ ልብ እምቢ አለ፡፡ ስለዚህ በድማሚት ተመትቶም ቢሆን ተመለሰ፡፡ ርግጠኛ ነኝ በሄድኩበት የኃጢአት መንገድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጥበቃው ነበር፡፡ ፍላጎቴን አልከለከለኝም፤ ነገር ግን ለክፉ አልሰጠኝም፡፡ እግዚአብሔር እና አጎቴ ተግባብተዋል፡፡ እኔ እና እግዚአብሔር ግን አልተግባባንም ነበር፡፡ እኔ ከእግዚአብሔር ጋር ለመግባባት ይህንን ሁሉ መንገድ መሄድ ነበረብኝ፡፡
እስኪ አስበው፡፡ የለመንኩትን ቢያደርገው ኖሮ፤ አሜሪካ ሄጄ አንድ ሱፐር ማርኬት እቀጠር ነበር፤ ወይንም የአንድ ፓርኪንግ ሠራተኛ እሆን ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ በራሱ መጥፎ ባይሆንም እግዚአብሔር ግን ይህንን አልፈለገም፡፡ ከእኛ ይልቅ ለኛ ያውቃልና፡፡ እኛ ከመረጥነው እርሱ የመረጠው ይበልጣልና፡፡ የጠየቅኩትን ከለከለና የመረጠልኝን ሰጠኝ፡፡ እኛ የሚያምረንን፣ እርሱ ግን የሚያምርብንን፤ እኛ የምንፈልገውን፣ እርሱ ግን የሚያስፈልገንን ያደርግልናል፡፡
ለዚህ ነው «ስላላደረግልኝ ሁሉ አመሰግንሃለሁ» የሚል ጥቅስ ያስጻፍኩት፡፡ ዛሬ ላይ እቆምና «እንኳንም የጠየቅኩህን አልሰጠህኝ ፤ እንኳንም የለመኩህን አላደረግከው ፤ እንኳንም እምቢ አልከኝ ፤» እለዋለሁ፡፡
ስለያት
«ለርእስዬ እም ርእስዬ እስመ አንተ ትቀርቦ» አልኩ፡፡ «ለእራሴ ከእራሴ ይልቅ አንተ ትቀርበዋለህ» ማለት ነው፡፡
ይህ የእርሷ ታሪክ ግን ከስድስት ዓመታት በፊት የተፈጸመ ሌላ ታሪክ አስታወሰኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *