“Our true nationality is mankind.”H.G.

የ “ኢህአዲግ ዋንጫ” ተሳታፊዎች ድልድል ይፋ ሆነ!!

የ ”ኢህአዲግ ዋናጫ” አንድ ውድድር ነው። በዚህ ውድድር የተሳታፊዎች ገደብ የሚጣለው አንዳንዴ ነው። ሲደምን ህገ ደንብ ይነሳል። ቅድመ ሁኔታ ይሰረዛል። ደመናው ሲገፍ ህግ ባይኖርም ” አለ” ተብሎ እግድ ይጣላል። ይህ ውድድር ታሪካዊ አሻራና መነሻ ይኑረው አይኑረው አዘጋጆቹ ራሳቸው አያውቁትም። ዋናው ፌዴሬሽኑ ግን አዲስ አበባ ቢሮ እንጂ ወኪል የለውም። የውድድሩ የጊዜ ሰሌዳም ውሱን አይደለም። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው የሚዘጋጀው። የውድድር ኤክስፐርቶች እንደሚሉት ውድድሩን መዝግቦ ዓለም አቀፍ እውቅና ለመስጠት የሚችል የታመነ አካልና ቋሚ ህገ ደንብ  እስካሁን የለም።
የተጀመረው የዛሬ 26 ዓመት ግድም ነበር። የዚያን ጊዜ የተሳታፊዎች ቁጥር አይታወቅም ነበር። እጣ ለማውጣት ሲሰበሰቡ ወንበር አንሶ ነበር። የምድብ ድልድል ሲወጣ አግዳሚ ላይ እንዲቀመጡ የተደረጉ ነበሩ። አጨዋወታቸው ፈጣንና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑ መረጃ የወጣባቸው ወዲያው በመታገዳቸው ፉክክሩ ” እንቅልፋም ነበር ” ተብሎ ነበር። ያበደው የሚናገረው ” ነበር”ን  ነው። “ነበር ” ለትምህርት ቢሆን ጥሩ ነበር። “ነበር” ን በ “ነበር” እያጀቡ መንጎድ!! ያበደው ሳቀ!!
በጥቅማ ጥቅም አንድ ቡድን የበላይነት የነበርበት ፉክክር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ አቶ ኢሳያስ የክቡር እንግዳ ነበሩ። ግን ከክብር እንግዳነት አልፈው ተጨዋቾችን አሳትፈው እንደ ነበር ጌዜ ቆጥረው እራሳቸው አምነዋል። ውድድሩ ይግባኝ ሰሚ ስለሌለው ጥፋት እንደ ጥፋት አይቆጠርም። እንደውም ‘እውነት’ ተብሎ ነው የሚወሰደው። አሁንም ያበደው ሳቀ!! ሌሎች ተፎካካሪዎችን ደግሞ በስልት አዳክመዋል የሚሏቸው ነበሩ። አቶ ኢሳያስ ‘ውድድር’ ባይወዱም ይህንን ውድድር ግን ከጥንሱ እስከ ፍጻሜው ተከታትለውታል። በውድድሩ ወቅትና ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የምክር አገልግሎት ሰጥተው እንደነበር ትዝታ አላቸው።
በውድድሩ የራስን መለያ መልበስ አይቻልም ነበር። መለያ የሚመርጠው አዘጋጁ ነው። በግድ የራሳቸውን መለያ መረጡ የተባሉት ከውስጥ የአዘጋጁ ምርጫ የሆነውን መለያ ይለብሱ ነበር። ተመልካቾች ግን የላይኛውን ሳይሆን የውስጠኛውን መለያ ለማየት አልተቸገሩም ነበር። እናም ሁሌም ውድድሩ በአዘጋጆቹ የበላይነት ቢጠናቀቅም ይፌዝበታል እንጂ እንደ ድል አይታሰብም ነበር። ውጤቱ አስቀድሞ ስለሚታወቅ!!
ዳኞችን የሚመድበው አዘጋጁ ብቻ ነበር። ዳኞቹ ስለሚዳኙበት “ህግ” ተፎካካሪዎች አያውቁም። መስፈርቱና መመዘኛው አልተቀመጠምና ለመከራከርና አቤት ለማለት አያስችልም። ዳኞቹ የፊሽካ አነፋፍና የካርድ አመዛዝ የሰለጠኑት ” ከባለ ራእዩ” እንደነበር ተፎካካሪዎች ያውቃሉ። አራጋቢዎች፣ ታዛቢ ዳኞችና እንግዶች የሚመደቡት ከአዘጋጁ ነው። አዘጋጁ ካበጃቸው ተፎካካሪዎች በቀር ዋናዎች ቡድኖች ሁሉን አውቀው፣ እንደማይረቱ ቢረዱም ከውድድሩ አይቀሩም ነበር። አውቀው  ገብተው አማረው ይወጣሉ። አዘጋጆቹ የራሳቸው የውስጥ ውድድር ሲኖርባቸው ለዋናው ተሳታፊዎች ክብር ይሰጣሉ። አጀብ ትላለች ቦሰና። ደጎል ይህን ውድድር ተከታትሎ አይውቅም። ደጎል ባያያውም ተመለካች አልባ ሆኖ አያውቅም። እንደዚህ ሆኖ የሚካሄደው ውድድር በህዝብ አስገዳጅነት ዛሬ አዲስ ስም ተሰጠው። ድርድር!! ወገኖቼ ለካ እርቅም አለ። ቦሰና ቀልቧን የሳበው እርቅ የሚለው ነው።
ሰላም!! እንዴት ከረማችሁ?እንደ ኢህአዴግ ፖለቲካ የወበቃችሁ፣ እንደ እምዬ ኢትዮጵያ ድብርት በቤታችሁና በፍቅራቹህ መካከል የገባባችሁም ተደራደሩ። ለመታረቅ ውጤት ላይ ሳይሆን፣ ምክንያት ላይ አተኩሩ። ውጤት የምክንያት ባርያ ነውና ስለውጤቱ ማሰብ አስቀድሞ ነው። ውጤት ከተበላሸ በሁዋላ ምክንያት እንጂ ውጤት የመስማሚያ መንገድን አያጸዳም። ውጤት ያስተምራል። ቦሰና አባብሉን ባትወደውም ልክ ተናገሮ አናጋሪ እንደሚባለው!!
ቦሰና አስተዋይ ናት። ጸሎቷ አጭር ነው። ሁሉን ከሚያውቀው አምላክ ጋር በረባ ባልረባው አትነታረክም። ” ከተናግሮ አናጋሪ ሰውረኝ” ብላ ከንቱ ጸሎት አታደርግም። “ሰው” ሳይነካ ሌላውን እንደማይነካ ስለምትረዳ፣ አምላኳን በቅንጥብጣቢ ጥያቄዎች አታሰለችም። “የልምድ ጸሎቶች ድሮ ይሰሩ ነበር” ትላለች። ምሳሌ አላት። ” አሁን ሰው አምላኩን እርዱኝ እረዳችኋለሁ ብሏል” ትልና አፏን ታጣምማለች። ” አሁን እሱ በምን የሆን የሚረዳው? ምን አጥቶ?” ትጠይቃለች።  ድሮ ታላላቆች ሁሉም ነገር በየዋህነት ያደርጉ  ስለነበር። እሱም ይረዳቸው ነበር።  አሁን ግን የዋሆች የሚጸልዩት ጸሎት … የቦሰና አካሄድ የተለየ ነው። ያበደው ወደ ጉዳዩ ተመለሰ።

ቦሰና ” እሱ ይቅር ይበልሽ” ሲሏትም አትወድም። እሱ ከላይ ወርዶ ጥንት ይቅር እንዳላት ታምናለች። ሰው ራሱ ይቅር እንዳይል ደረሶ ” አማላጅ” ይሆናል። የወደደ እሱ ብግልጥ እንዳለውና አድርጎ እንዳሳየው ” ይቅር ማድረግ እንጂ ይቅር ይበልህ ብሎ የአሰታራቂነት ሚና…” ቦሰና ትፈላሰፋለች። ይቅርታ ከፖለቲካው ሰፈር መሰማቱ ልቧን እንደነካው ግን አትደብቅም። ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል። ይቅርታ ካልሆነ የኢትዮጵያን የክፋት ቂጢኝ የሚነቅል መድሃኒት የለም። ያበደው ከቦሰና ጋር ይስማማል። ቂም ያፈረሳል። ቂም ቋጥረው የተነሱ አልጠቀሙንም። በጊዜ መሰናበታቸው አንዳንዴም ለበጎ እንዳይሆነ… ለመታረቅና ሰላም ለማውረድ ወንጌልን መሸምደድ፣ ኦሪት ላይ መላከክ አያስፈልግም። ሰው መሆን ብቻ ይበቃል። ያበደው ” ሰው” ሲል ሁሌም ደጎል እንዳይሰማ በመጠንቀቅ ነው። ደጎል ውሻው!!

የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልቅ ” የኢህአዲግ ዋንጫ” ቀድሞ ቢጀመርም አልተጠናቀቀም። አሁን በሚወጡ መረጃዎች አራት ምድቦች ይፋ ሆነዋል። አየለ ጫሚሶ ተነጥቆ የተሰጣታቸው/ የቅንጅት/ ቡድን በስሩ ያካተታቸውን 11 ተጠባባቂ ቅጥቅጥ ክለቦችን በረዳትነት ይመራሉ። ኢዴፓ የቡድን አባት የሆነበት ሌላው ምድብ እነ ሰማያዊን፣ መኢአድን አካቷል። ህብረት አሰላለፉን ሚስጢር አድርጎ እየተጠበቀ ነው። ኢህአዲግ አሰላለፉን እንደ ተጋጣሚዎች የመቀያየር ልዩ መብት ስላለው አስቀድሞ የሚታወቅ አቋም የለውም። ኢህአዴግ ይቅርታ ህወሃት ግን በምርጫ ቦርድና በአንቀጽ 39 ቀልድ አያውቅም።
የውድድሩ አዘጋጆች ለያበደው በላኩት መረጃ አቶ ልደቱ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እንደሚሆኑ ከወዲሁ አስታውቀዋል። በመረጃው ላይ የውድድሩ የጊዜ ሰሌዳ አልተገለጸም። አቶ አየለ ጫሚሶ ለሞራል ማስጠበቂያ 11 ቀጥቅጥ ክለቦቻቸውን አሰባስበው የገመድ ጉተታ ውድድር እንደሚያደርጉ የጠቆመው መረጃው የዚህን ዋንጫ አየለ ጫሚሶ ከቀዳማይ እመቤት እጅ እንዲወስዱ ይደረጋል። ከዚህ ውድድር በሁዋላ አሸናፊዎች ” በታዛቢዎች ፊት በድምጽ ይለያሉ።
ጊዜው ባይገለጽም የመዝናኛ ትዕይንት የሚያሳዩ ተወዳዳሪዎች አሉ። ያበደው ፈገግ ብሎ ያነበበው መረጃ በዚህ የመዝናኛ ትርኢት ላይ የሚቀርቡ ዝግጅቶችን ነው። አስመስሎ መሳቅ፣ ፊትን በተለያዩ ቀለማት በመቀያየር በሥሥ ልብሶች ሰርከስ ማሳየት ፣ ሌላ ሰው ወይም አውሬ መስሎ መታየት፣ ጅብ መምስል፣ ተኩላ መምሰል፣ አሳማ መምሰል፣ ተዘጋጅተው የቀረቡ ጭምብሎችን በመልበስ የተጠኑ መነባንቦችን ማቅረብ፣ የምግብ ማግበስበስ ውድድር፣  የብሄር ብሄረሰቦችን ጭፈራ ማሳየት…. ” እስከመገንጠል ” የሚለውን አንቀጽ ሆን ብሎ መቃወም…
አዎ!! እንዲህ እያሉ ለድርድር ቀንድና ጭራ የሚቀጥሉ አሉ። እንዚህ “ጸረ ልማታዊ አስተሳሰብ” ያላቸውን አታዳምጡ። ሃሃሃሃሃሃ……አሁን ያበደው ነቃ። ድርድር ግድ ነው። አሁን ጊዜው የአሽሙር አይደለም። አገራችንን እናስብ። ችግሯና ጠላቶቿ ብዙ ኢትዮጵያ!! ያበደው አምላክን ዘወትር ለኢትዮጵያ ብቻ የሚያስብ አድርገው የሚመለከቱትን ይታዘባል። አምላክ ዩጋንዳን፣ ኬናያን፣ አሜሪካን፣ እንግሊዝን፣ ናይጀሪያን፣ ብራዚልን… ሁሉን ረስቶ ኢትዮጵያን ብቻ ሲጠብቅ ውሎ፣ ሲጠብቅ የሚያድር የሚመስላቸው…. አሁን ጊዜ የማሰቢያ ነው። ያበደው ድምጹን ከፍ አድርጎ መጮህ ቃጣው!!
ተደራዳሪዎች ዋስትና ይፈልጋሉ። እንደራደር ያሉ ደግሞ ይበልጥ ዋስትና ይሻሉ። በቂምና በጥላቻ የሚሆን ነገር የለም። መጪውን ትውልድ ማሰብ፣ አገርን ማስቀደም ግድ ነው። ተከባብሮ ወደ ሚጠቀመው መንገድ ማምራት የወቅቱ ጥያቄ ነው። ደጎል ምክር አለው። ማስጠንቀቂያም!!
ደጎል ” እኛ ውሾች ብዙ ዘር አለን። እባቶቻችንን እንኳን ጠንቀቀን ባለማወቃችን ጥርጣሬ ጤና አይነሳንም።  ዘረኞች አይደለንም። ከየትኛውም ዓለም ስንገናኝ ስለ ዘር አናወራም። ጠረናችንን እንቀያየራለን። ሰዎች ይህን ስናደርግ ሰላምታ እንደምንቀያየርና ግንኙነት እንደምናደርግ አይገባቸውም። በርግጥ አንዳንድ ተናካሽ ውሾች አሉ። መናከስ ተፈጥሯችን አይደለም። አሳዳጊ የሚያስተምረን ችግር ነው። አሳዳጊዎች መርዝ እየጋቱ እናንተን እንደሚያባሉዋችሁ ሁሉ ተናካሽ እንድንሆን ጉድጓድ ቆፍረው ጉድጓድ ውስጥ የሚያሳድጉን አሉ።…. መታመን ልዩ ባህሪያችን ነው። ኮተት የለንም። ለሆዳችን ብለን ወዳጃችንን አሳልፈን አንሰጥም። ፍቅር መቀበልና መስጠት እናውቃለን። በቤታችን ቀልድ አናውቅም…” ደጎል አይጨርስም። ደጎል ማብራሪያው ብዙ ነው። ” ግን ሰው ለምን ውሻን ስድብ አድርጎ ቃሉን ይጠቀምበታል” ይላል። አዎ!! አለአግባብ መለጠፍ እንወዳለን። መልካም የኢህአዴግ ዋንጫ ውድድር። ይቅርታ ድርድር !! እርቅ!! አንዱ አምላክ ስለ መጪው ትውልድ ሲል እርቅ እንዲመጣ ይርዳን!! ሌላው መንገድ ….. ተግባብተናል… ሰላም ሰለም… አሁን ወደ ቦሰና!! ቸር ያሰማን!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0