ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነው የአሜሪካ ኤምባሲ በተለይ ለፋና እንዳስታወቀው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የሚገኙ በርካታ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የሚሰጡትን የቪዛ መጠን ” ቀንሰዋል” በሚል የሚናፈሰው መረጃ ሀሰት ነው።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ካሳለፉት ውሳኔ ጋር በተያያዘ ዋሽንግተን ለኢትዮጵያ ዜጎች በምትሰጠው ቪዛ ቁጥር ላይ የተቀመጠ ገደብ እንደሌላ ኤምባሲው ማረጋገጫ ሰጥቷል። “ኢትዮጵያ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ በፕሬዚዳንቱ እገዳ ከተጣለባቸው ሀገራት ውስጥ አትገኝም” ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ፥ ማንኛውም ቪዛ የተሰጠው ኢትዮጵያዊ ወደ አሜሪካ መግባት እንደሚችል አመልክቷል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ቪዛ ኖሯቸው ነገር ግን ገደቡ ካለፈባቸው እስከ አራት ዓመት የሆኑ ሰዎች ያለ ቃለ መጠይቅ በፖስታ ቪዛ የሚያገኙባቸው እድል ነበር። አሁን በተደረገው ለውጥ ግን የቪዛ ገደባቸው ከተጠናቀቀ ከአንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ቪዛ እንደሚጠይቁ ሰዎች ይስተናገዳሉ ብሏል።

ነገር ግን ከ79 አመት በላይ እድሜ ያላቸው አዛውንቶች፣ ከ14 አመት በታች ታዳጊዎች እና የተሰጣቸው ቪዛ የጊዜ ገደብ ካበቃ ከ12 ወር በታች የሆኑ ሰዎች የቪዛ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ሳይጠበቅባቸው ቪዛ እንደሚሰጣቸውም ነው ኤምባሲው የገለፀው።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የሀገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል የሶሪያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል። ይህ ውሳኔያቸውም በበርካታ አሜሪካውያን እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ሰንብቷል።

ባለፈው ሃሙስ በሲያትል የሚገኝው የፌደራል ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንቱን የስደተኞች የጉዞ እገዳ ውድቅ አድርጎታል። ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቃውመው ለፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አቤት ቢሉም ፍርድ ቤቱ በሲያትል ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ አፅንቶታል።

አሜሪካን ከሽብር ስጋት ነጻ ለማድረግ በሚል ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ያሳለፉት ውሳኔ ውድቅ የተደረገባቸው ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው “የሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ነው” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ትራምፕ በቀጣይ በሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለመጠየቅ ስለመዘጋጀታቸው ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *