የዶ/ር ዳኛቸው የጅብ እርሻ የኢትዮጵያን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ጽሑፍ ነበር፤ ብዙ ሰዎች እንዲያነቡት ተስፋ አደርጋለሁ፤ ካላነበቡት ፈልገው ቢያነቡት ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ይጠቀማሉ፤ ዳኛቸው ከመንገድ ሊይ ያገኛትን የአነጋገር ፈሊጥ ለቁም-ነገር አበቃት፤ ጅብ በተፈጥሮ ባሕርዩ አያርስም፤ ፍሬም አይለቅምም፤ ድንገት ተሳስቶ ቢያርስም እስቲበቅል ለመጠበቅ ትእግስቱ የለውም፤ ዳኛቸውም የጅቡን እርሻ ”በአንድ በኩል የኢሕአዴግን አካሄድ በሌላ በኩሌ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መሀከል የሚካሄደውን ሁኔታ ሊያስረዳልኝ/ሊገልጽልኝ የሚችል…” ነው በማለት ይጠቀምበታል።

በኢትዮጵያ የነገሠው በምንም ዓይነትና በማናቸውም ጥያቄ ብቸኛ ‘መለስ አለኝ’ የሚል አባዜ የተጠናወተው ሥርዓት ለቤት እጥረት ጥያቄ መልሱ ኮንዶሚኒየም ነው፤ ለመሬት ጥያቄ መልሱ ሊዝ ነው፤ የብሔር የእኩልነት ጥያቄ መልሱ ፌዴራሊዝም ነው፤ የክህሎት ጥያቄ መልሱ ሥልጠና ነው፤ እያለ ሕዝቡን ያደነዝዘዋል፤ ስለዚህም በነጻነትና በእኩልነት፣ በሥልጠናና በትምህርት፣ በብዛትና በጥራት … መሀከል ያለውን ልዩነት ለመከራከር ወይም ለመሞገት ስለማይፈቅድ ዴሞክራሲያዊ ባሕርይ የለውም፤ ይኸው ባሕርዩ — ለክርክርና ለሙግት ክፍት አለመሆኑ — ለእውቀት እርምጃ የማይበጅ እንቅፋት ያደርገዋል፤ እንግዲህ አንድ ማኅበረሰብ በአንድ በኩሉ ለዴሞክራሲ ፋይዳዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለእውቀት ማስፋፋት ፋይዳዎች መንገዶቹና በሮቹ ሁለ ከተዘጉበት የመታደስና የመሻሻል ዕድሉ ታፍኖአል ማለት ነው፤ አፈናውን የሚያጠነክረውና ይበልጥ አስከፊ የሚያደርገው የዴሞክራሲው መንገድ መዘጋት በዴሞክራሲ አስመሳይ ብልጠት፣ የእውቀቱም በር መዘጋት እንደዚሁ በአስመሳይ ብልጠት መሆኑ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ዳኛቸው ያስተዋለው የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ምንጩ በሥልጣንና በእውቀት መሀከል የተፈጠረው የቁርባን ጋብቻ መሆኑን ነው፤ የሥልጣንና የፊደል እውቀት ዲቃላ ሥልጠና ይሆናሉ፤ ዲቃላው ሥልጠና እውቀትን ተክቶ ለማናቸውም ጥያቄ መልሱን የሚቀዳው ከአንድ የሥልጣን ምንጭ ብቻ መሆኑን ያውጃሌል፤ ዶር. ዳኛቸው ‹‹ሁሉንም በጠቅላላ ቋጠሮ ውሰጥ ከ(ት)ቶ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ወጥ በሆነ ፖሊቲካዊ አተያይ አንዲመራና መፍትሔውም ለሁለም አንድ ወጥ የሆነ መልስ ብቻ እንዳላቸው አድርጎ የማቅረብ አባዜ ነው፡፡›› (ፍትሕ የካቲት 2/2004) በማለት የገለጸው ይህንን ጸረ እውቀት የሆነ የሥልጠና ውጤት ነው፤ ሥልጡን አገልጋይ ወይም ሥልጡን አሽከር ትእዛዝ እየጠበቀ፣ ትእዛዝ እየተቀበለ በትእዛዝ የሚሠራና የሚያሠራ ነው፤ እንደዚህ ዓይነቱ ሥልጡን አባቱ ሥልጣን ሲሆን እናቱ ፊደልዋን ጨርሳ ንባብ የጀመረች ነች፣ ከመሃይምነት ለመውጣትዋ ዲፕሎማ ተሸልማለች፤ ስለዚህም ተምራለች፤ ስለዚህም ምሁር ነች፤ ስለዚህም የፊደል ችሎታዋን ለሥልጣን አገልጋይነት ማዋል ለሹመት ያበቃታል፤ እንዲህም እያለ ሥልጣንና ሥልጡን አገልጋይነት እየተደጋገፉና እየተባዙ ይቀጥላሉ።

የደርግ ሥልጡን አገልጋዮች እውቀትን በትክክለኛው መንገድ የማካበቱን የተመሰከረለት መንገድ ለመለወጥ ተወራጭተው ነበር፤ መጀመሪያ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያውን መመዘኛ በትምህርት መሆኑ ቀርቶ በ‹‹መደብ ጀርባ›› እንዲሆን አደረጉ፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ፈተናው የሚሰጠው የመደብ ጀርባ እየታየ ባለመሆኑ ብዙዎቹ በመደብ ጀርባቸው የገቡት ለገና ወደየቤታቸው ይመለሱ ጀመር ተማሪዎቹ Christmas Graduates ይሏቸው ነበር፤ በኋላም ሥልጡን አገልጋዮች ትምህርትን ለሰፊው ሕዝብ በአጭር ጊዜ ለማዳረስ በነበራቸው ጉጉት የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ጊዜ ከአራት ዓመታት ወደሦስት ለወጡት፤ የሦስት ዓመቱ ተመራቂዎች ሊጨርሱ ስድስት ወር ሲቀራቸው ተማሪዎች አጉረመረሙና ጥናት ተደረገ፤ ካልተሳሳትሁ ወደዘጠና ከመቶ የሚጠጉት ተማሪዎች መመረቁ እንዲተላለፍላቸውና አንድ ዓመት እንዲጨመርላቸው ጠየቁ፤ ጉዳዩ ወደዩኒቨርሲቲው የአመራር ጉባኤ ቀረበና የጦፈ ክርክር ተደረገ፤ በዶር. ዱሪ የሚመራው የዩኒቨርሲቲው አመራር የተማሪዎቹን ጥያቄ በመደገፍ አንድ ዓመት እንዲጨመር አጥብቆ ተከራከረ፤ ሌሎቻችን ደግሞ ቀደም ሲል ወደሦስት ዓመት ሲለወጥ በጣም ተቃውመን የነበርነው አንድ ዓመት ይጨመር የሚለውን በጣም ተቃወምን፤ ምክንያቱም አንደኛ ተማሪዎቹ በሦስት ዓመት እንደሚመረቁ ተነግሮአቸው የገቡ ናቸውና ውሉ መፈጸም ነበረበት፤ ሁለተኛ የሦስት ዓመቱ ትምህርት ከአራት ዓመቱ የተሻለ መሆኑንና አለመሆኑን ማወቅ የሚቻለው እነዚህ ‹‹በለብ-ለብ›› የተመረቁት በሥራ ሲፈተኑ ነው፤ በማለት ተከራክረን አሸነፍን፤ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ተንጫጩ።

የዛሬውን የ32 ዩኒቨርሲቲዎች ጥራት ዳኛቸው በአጠቃላይ ነካክቶታል፤ (አዱስ ጉዲይ፣ የካቲት 2004)፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ተሽሮ ስልጠና የሚሰበክበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤›› ይላል ዳኛቸው፤ ከዚያ በላይ ለማለት በበኩሌ አልችልም፤ ግን የምሰማው ሁሉ ለብ ለብ በጣም የተሻለ እንደነበረ ነው፤ ዓላማቸው ሥልጠና በመሆኑ ለድኅረ-ምረቃ የኢሕአዴግ አባል ያልሆነ አለመቀበላቸው ዩኒቨርሲቲ የሚለውን ስያሜ ያዋርደዋል፤ ነገሩ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ትምህርት ያልገራቸው ሰዎች ስለትምህርት አመራር ሲሰጡ ከባዱንና ውስብስቡን ጉዳይ በቀላሉ እንደሚመለከቱት ሳይታለም የተፈታ ነው።

በጣም ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸውን ሠላሳ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ወደስማቸው ለማስጠጋት ምን ማድረግ ያስፈልጋል? እንደምንም ብሎ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ የሚባለው በምርጥ አስተማሪዎች፣ በተሙዋላ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-ሙከራ፣ በተሙዋላ የኮምፕዩተር አገልግሎት የተደገፈ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መታጀብ አለበት፤ ሠላሳ ሁለት ጥሩ ጥሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው።

Posted on April 7, 2012 by መስፍን ወልደ-ማርያም (Mesfin Wolde-Mariam)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *