ይህ ጥያቄ የሚናቅ አይመስለኝም። የሚሊዮኖች ጉዳይ ነው። የኦሮሞ ትግልን በዳዴ ያስኬደ !! ለጣያቄዬ የምፈልገው ምላሽ ግልጽ ያለ ነው። ግራ ተጋብቼ ሳይሆን ፖለቲከኛ የሆናችሁት ከግራ መጋባት ነጻ እንድትሆኑ ጭምር በማዘን ነው።
በመጀመሪያ ማሳሰቢያ
በአሁኑ ወቅት የልመና ፖለቲካ እያየሁ ነው። ይህ የልመና ህብረትና መማማል ከጊዚያዊ ጫጫታ የዘለለ ውጤት እንደማያመጣ አምናለሁ። የልምምጥ ውህደት ዋጋ ይኖረዋል ብዬ ስለማላስብ እነዚህ ወገኖች መልስ ይሰጡኛል ብዬ እንደማላምን ከወዲሁ ማስታወቅ እፈልጋለሁ።
ማብራሪያ
እኔ ውልደቴ ሸዋሮቢት ሰላ ድንጋይ አካባቢ ነው። አባቴ እናቴን አግብቶ ነበር እዛ የወሰዳት። እሷ ከሙሉ ዘሮቿ ጋር አብራ ትኖር የነበረው ኢጃጂ ግድም ከሚገኝ አንድ ቀበሌ ሲሆን የተደባለቀች ናት። ሴት አያቷ የጉራጌ፣ ወድንድ አያቷ የአማራ ደም አለባቸው። ወደ ቅደም አያት ሲገባ ደግሞ ይሰፋል። እናቷ እና አባቷ እዛው ኢጃጂ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። የአባትና እናቶቻቸው ዘር ያሉበትን ከተማ፣ ቀበሌና ልዩ ቦታ ቀርቶ አቅጣጫውንም አያውቁትም።
እንግዲህ እናቴ ከእነሱ አብራክ ከወጣች በሁዋላ አባቴ ይዟት ወደ ሸዋ ሮቢት አቀና። በድምሩ ስድስት ልጆች የነበራቸው ሲሆን አራቱ የተወለዱት አዲስ አበባ ሲሆኑ ሁለት ደግሞ የተወለድነው እዛው ” አማራ አገር” ነው። አራቱ ልጆች አዲስ አበባ ቢወለዱም ወደ አባታችን አገር ሄደው አያውቁም። አባታችን ከሞተ በሁዋላ ሙሉ ግንኙነታችን ከእናታችን ወገኖች ጋር በመሆኑ ከአባቶቻችን ወገኖች ጋር ተለያይተናል። እናም ያደገነው በኦሮሞ ባህል፣ በኦሮሞ ልምድና ወግ ነበር ብል ማጋነን አይደለም። እንግዲህ ይህ የመዋለድ ነገር ወደ ልጆች፣ ልጅ ልጆች ሲሰፋ መቆሚያ አይኖረውም። እናም አፍንጫ ሲመታ ነውና ሊታሰብበትና አንድ ቁርጥ ያለ ነገር ቢይዛበት ምን አይሻልም።
ጥያቄዬ
አሁን ባለው አስተሳሰብ እኔ ምንድን ነኝ? ኦሮሞ? አማራ? ” ኦሮማራ?” ሊገባኝ አልቻለም። ለመሆኑ እንደኔ ያላችሁ ምን አስተያየት አላችሁ? ፖለቲከኞቻችን ለእንዲህ ያለው ጥያቄ ምን መልስና እቅድ አላችሁ? እናንተ “ዜግነት” ብትሰጡን፣ የፈለግነውን ሃሳብ ማራመድ እንችላለን? ወይስ? ካልሆነስ በእናንተ አስተሳሰብ የመጨረሻው እጣ ፈንታችን ምን ይሆን? እንደ እኔ ያሉ ብዙ ሚሊዮኖች እንደ ሆኑስ ታምናላችሁ? ውይስ ” ዲቃሎች ትንሽ ናቸው” ብላችሁ ነው የምታምኑት? ነው ” ክልስ ኦሮሞ” ተብለን ልዩ መተዳደሪያና አሁን አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት እንዳደረገው የምርጫ አጀንዳ እንሆናለን?
ወደ ግል ጉዳዬ ልመለስ፤ ሁሉም ነገር ቢጠራ መልካም ይመስለኛል። ስለሆነም እባካችሁን ግልጽ ያለውን ነገር ካሁኑ ንገሩኝ። ለእኔ መልስ ስትመልሱ እናንተም እግረ መንገዳችሁን ከግራ መጋባት ነጻ ትወጣላችሁ። እኔም ለልጆቼ ቁርጡን ነግሬ ከአያቶቻቸው ዘሮችና ከሚወዱት አካባቢ ጋር አንድ ቀን ከቶውንም ሊለያዩ እንደሚችሉ ከእነ ምክንያቱ አስረዳቸዋለሁ። ይህን ጉዳይ ከዚህ በላይ አስፍቼው እጽፍበታለሁ።
አድናቆት
በእናቴ ሰፈር፣ አጎራባች ቀበሌዎች፣ እንዲሁም ወደ እናቴ ዘሮች መንደር ስጓዝ ለተዋወኳችሁ በሙሉ ልባዊ ክብር አለኝ። የዋህነታችሁ፣ ቅን ልቦናችሁ፣ ሰው አክባሪነታችሁ፣ ጓዳችሁን ገልብጣችሁ ላበላችሁኝ፣ ላጠጣችሁኝ፣ ጎዝጉዛችሁ ላሳረፋችሁኝ፣ ላዘላችሁኝ፣ ላቀፋችሁኝ፣ ለጋትችሁኝ፣ ሽንቴን ለሸናሁባችሁ፣ ቅቤ ላዋጣችሁኝ፣ ጠጉሬን ለላጫችሁኝ፣ የምትችሉትን ወዳጅችሁ ላደረጋችሁልኝ፣ ዘሬን ቆጥራችሁ ስለማታውቁ … ዘርዝሬ አልጨርሰውም እስከ ለዘላለም ምስጋናዬ ትልቅ ነው።
ስም ያልተገለጸው ለቤተሰብ የሞራል ጥንቃቄ ተብሎ ብቻ ነው።
አዘጋጁ- ይህ መልዕክት የተላከው በፌስ ቡክ ሳጥናችን ነው። እንዳለ አቅርበነዋል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *