negasso-gidadda-2

ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ በማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ  እና ሌሎች ጉዳዮች ብሎም ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እና በቀጣይ መደረግ ስላለበት የመፍትሄ አቅጣጫ ከቀድሞ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ!

አዲስ ዘመን፡- በሕገ መግስቱ ሦስተኛው ገፅ ላይ የእርስዎ ስም ይነበባል፡፡ ይህን ሲያዩት ምን ይሰማዎታል?

ዶክተር ነጋሶ ፡- የህገ መንግስቱ ጉዳይ ሲነሳ ከማርቀቅ ጀምሮ በጉባዔ አስኪፀድቅ ድረስ ተሳትፌያለሁ፡፡ የአርቃቂ ኮሚሽን አባል ነበርኩኝ፡፡ ያኔ የሽግግር መንግስት ወቅት ነበር፡፡ በማርቀቁ ረገድ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፓርላማ ውጭ ከሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም ከማህበራት ጋር ነው የተረቀቀው፡፡ ከሽግግር መንግስቱ ተወካይ በፓርላማ ሰባት ሰዎች ብቻ ነበርን፡፡ 29 ሰዎች በአርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ ነበሩበት፡፡ ከውጭ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ለመሳተፍ በጋዜጣና ሬዲዮ ጥሪ ተደርጎ ፈቃደኛ የሆኑ ሰባት ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤት፣ የሴቶች፣ የማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችም እንዲሁ በሂደቱ ተሳትፈዋል ፡፡

 ከኢህአዴግ አባላት ሆነው ግን በኢህአዴግ ስም ሳይሆን  ግለሰብ ደረጃ የተሳተፍነው አቶ ዳዊት ዮሐንስ እና (ኢህዴን) እና ከ(ኦህዴድ) እኔ ነበርኩ፡፡ ከሁለቱ የኢህአዴግ አባላት (ህወሃት) እና (ደህዴን) ማንም አልነበረም፡፡ ለማንኛውም ህገ መግስቱ ከተረቀቀ በኋላ ወደ ሽግግር ተወካዮች ምክር ቤት ከተወያየ በኋላ ወደ ጉባኤ ተላለፈ፡፡ ስድስት ሳምንት ተመክሮበታል፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ ሊቀመንበር፣ አዲሱ ለገሰ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም አባተ ኪሾ ፀሀፊ ነበርን፡፡ በርካታ የኮሚቴ መሪዎችም ነበሩ፡፡ ትልቅ ስራ ነው የሰራነው፡፡ በጣም ከልቤ የተሳተፍኩበት ነው፡፡ አንዳንድ ድክመቶችና እና ችግሮች ቢኖሩበትም ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ነው ያፀደቅነው፡፡ የህገ መንግስቱ ጉዳይ ሲነሳ ኩራት እና ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ትዝታውም አብሮ ይመጣል፡፡ በእርግጥ ማንሳት የምፈልገው ነገር ብዙ ሰዎች ይሳሳታሉ፡፡ ‹‹ይህ ህገ መንግስት የኢህአዴግ ነው››ይላሉ፡፡ ይህ ስህተት በመሆኑ መታረም አለበት፡፡  ፈርሜበታለሁና  ኩራት ይሰማኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ህገ መንግስቱ ሲጠነሰስ እርስዎ ነበሩ፡፡ እርስዎ አሁን 73 ዓመት ሆኖዎታል፡፡ ስለ ህገ መንግስቱ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት  ምን ይላሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ሕገ መንግስቱ ሀገሪቱ የምትተዳደርበት የበላይ ህግ ነው፡፡ በግለሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በህዝብና መንግስት መካከል የተደረገ የጋራ ውል ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ህልውና እና ህዝብ ጥቅም መዋል አለበት፡፡ ይዘቱም ለሀገር ጥቅም እስከሆነ ድረስ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ላይ የተመሰረተና ከጊዜው ጋርም መጣጣም አለበት፡፡ የህግ የበላይነትም ሊከበር ይገባል፡፡ በህገ መንግስቱ የሚመሰረት መንግስትም ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፡፡

በብዙዎቻችን ዘንድ ህገ መንግስቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል እንላለን፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ምክንያቶች ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ህግ መንግስቱን ከማርቀቁ እስከ ማፅደቁ ባለው ሂደት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና የህብረተሰብ ክፍል አሳታፊነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በወቅቱ አንዳንድ ተቀባይነት የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አልተሳተፉበትም፡፡ ኦነግ እና አንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች ፣ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ፣ ሚኤሶን በወቅቱ ብዙ ተቀባይነት ያላቸው ሆነው አልተሳተፉም፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት እነዚህ ድርጅቶች በውል ባይኖሩም አባሎቻቸው እና አመራሮቻቸው እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው ህገ መንግስቱ ‹‹የኢህአዴግ እንጂ የእኛ አይለም›› በሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በወቅቱ ከተሳታፊነት አኳያ ያደረግነው 73 ጥያቄዎች አዘጋጅተን ለ23ሺህ ቀበሌዎች በምርጫ መልክ ጥያቄ በትነን መልስ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በተፈለገው መጠን ፓርቲዎች አልተሳተፉም፡፡  ህዝበ ውሳኔ ቢደረግ መልካም ነበር፡፡ ይህ አልተደረገም፡፡

በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ግን እስካሁንም ድረስ ተቀባይነት ያላገኙ በርካቶች ናቸው፡፡ ለአብነት አናሳዎች በተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ይህ አለ? የኦሮሚያ እና አዲስ አበባን ግንኙነት በተመለከተ እስከአሁን ህግ አልወጣም፡፡ በእኔ እይታ ደግሞ አንቀፅ 29፣ 30፣ 31፣ 38 ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት ተግባራዊ አልሆኑም፡፡

ከ22 ዓመት በፊት ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ የነበረው እና በወቅቱ ያልተገነዘብነው የምርጫ ስርዓትም ሊፈተሸ ይገባል፡፡ በአንድ ቀበሌ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ሰው ይመረጣል፡፡ ከዚያም 547 ሰው ፓርላማ ይገባል፡፡ አሸናፊ ሁሉን ነገር ያጠቃልላል፡፡ ይህ ስርዓት ትክክል ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ስለዚህ የዜጎችን ድምጽ እኩል ለመስማት ያስችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ በርካታ ብሄርና ብሄረሰቦች ባሉበት ሲታይ ድክመት ነው፡፡ በክልልም ሆነ በፌደራል ምክርቤቶች አሸናፊ ናቸው የሚቀመጡት፡፡ ስለዚህ የህገ መንግስት ክርክር በሚነሳበት ወቅት የሚወስነው አንድ ፓርቲ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህም ኢህአዴግ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሌላም ፓርቲ ዕድሉን ካገኘ በዚሁ ነው የሚመራው፡፡ ስለዚህ ይህን የሚመራ ነፃ ፍርድ ቤት እንዲኖር ብንከራከር ጥሩ ነበር፡፡ በወቅቱ አላሰብንበትም፡፡

አዲስ ዘመን፡-  የተማሩ ሰዎች ያከተተ ብቻ ነበር ማለት ነው፡፡ ሁሉም ከዳር ዳር ተሳትፈዋል? ርቀት ቦታ ላይ ያሉትስ ተሳታፊ ነበሩ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ጥያቄውን ይዘው የሄዱት አወያዮች ለህዝቡ በደንብ ይገልፃሉ፡፡ የእኛ ህዝብ ብዙ ሰዎች እንደሚሉት አይደለም፡፡ የተማረ ባይሆንም ስለ መብቱ ያውቃል፡፡ ከህዝቡ ንቃተ ህሊና አኳያ መብቱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ በወቅቱ ለማወያየት የሄዱት ከብሄር ብሄረሰብ ተወከለው ነበር፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ  23ሺህ ቀበሌዎች ተሳትፈውበታል። ግን ያን ጊዜ ስንት ቀበሌዎች እንደነበሩ አላውቅም። በሁሉም ቀበሌዎች ተዳርሷል ወይስ አልተዳረሰም የሚለውን ምናልባት ይሄ ቴክኒካል ጉዳይ ነው፡፡ የትራንስፖርት ችግር አለ፤ ሄደው የሚያወያዩ ሰዎች ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተጠርተው፤ ስልጠና ተሰጥቷቸው አማርኛ ይሰማሉ ወይ? የሚለው ታይቷል፡፡ የእኔ ጥያቄ አብዛኛው ህዝብ አልተሳተፈበትም። መጨረሻም ላይ ከጸደቀ በኋላ ይሄ የጸደቀው ህገ መንግስት እናንተን ይወክላል፤ አይወክልም? ተብሎ ተጠይቆ ይወክለናል ብሎ ህዝበ ውሳኔ አልተሰጠበትም የሚል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴሬሽን ምክርቤት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚወከሉበትና የተለያየ አስተሳሰብ  የሚራመድበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል ስለሆነም ጫና መፍጠር አይችሉም ነበር?

ዶክተር ነጋሶ፡- ልክ ነህ፡፡ ግን እዚህ የሚገቡት ከየትኛው ፓርቲ ነው? ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተመጣጣኝ ድምፅ ቢኖር መልካም ነበር፡፡ ግን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቢወከሉም የተለየ ሃሳብ የማራመድ እድል የላቸውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአንድ ስርዓት ውስጥ ቢሆኑስ የተለያየ አስተሳሰብ ለማራመድ ህገ መንግስቱ ይከለክላልን?

ዶክተር ነጋሶ፡- ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ድርጅታዊ አሰራር የለም፡፡  ከፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ አባል ከወረደ በኋላ ማፈንገጥ አይቻልም፡፡ የፓርላማ አባላት የፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ ከፓርቲው አፈንግጦ ምንም ማምጣት አይችሉም፡፡ ከፓርቲው ካፈነገጡ ይገመገማሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ርዕሰ ብሔር የነበሩትና አብዛናው ህዝብ ተሳትፏል ብለው የፈረሙት እርስዎ ነዎት፤ ይህ ነገር እርስ በእርሱ አይቀራንም?

ዶክተር ነጋሶ፡- ከዚህ በፊትም ተናግሬያለሁ፡፡ ሁሉም ህዝብ ተሳትፎበታል፤ ስኬታማም ነበር ብዬ መናገሬ ስህተት ነው፡፡ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቄያለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ህገመንግስቱ ዛሬ ላይ ምን መሆን አለበት ይላሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- መጀመሪያ ላይ የጠቀስኳቸው ጥያቄ የሚነሳባቸው ያልተተገበሩ ድክመቶች አሉ። እነዚህ አንቀጾች እንደገና አሳታፊ የሆኑ መድረኮች ተከፍተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ የማሻሻያ አንቀጾች ተዘጋጅተውና ገብተውበት፤ ተቀባይነት አላቸው ወይስ የላቸውም? ተብሎ ህዝቡ ተጠይቆ  ህገ መንግስቱን ማሻሻል ይገባል፡፡ ህገ መንግስቱ አይሻሻልም የሚሉትንም ሆነ የእኛ አይደለም የሚሉት ትክክል አይደሉም።

በሌላ መንገድ ደግሞ ህገ መንግስቶች በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚሄዱ ናቸው እንጂ፤  እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቁጭ ብለው የሚቀሩ አይደለም። አዲስ መንግስት እየተመሰረተ ሌላ አዲስ ህገ መንግስት የሚወጣበት አካሄድ ትክክል አይደለም፡፡ በየጊዜው እየተሻሻለ መሄድ አለበት ብዬ ነው የምገምተው። ለአብነት አንቀፅ 39 ተግባራዊ አልሆነም፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ከላይ የተጠቀሷቸው ፓርቲዎችን መንግስት ተዳክመዋል ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጎላ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ ብለው ያስባሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- እነርሱ የሚፅፉትን እና የሚናገሩትን እየተከታተልኩ አይደለም፡፡ ግን ጥያቄዎች እየተነሱ አይደለም? እነዚህ ፓርቲዎች በወቅቱ ነበሩ፡፡ በህዝቡ ውስጥ ደጋፊዎች ነበሯቸው፡፡ ከዚያም በሂደት እንዲዳከሙ አልተደረገምን? በዚህ 25 ዓመት ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ እና ሲደራጁ ምን ዓይነት እርምጃ በፓርቲዎች ላይ እንደሚወሰድም አይተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለ አንቀፅ 39 ገዢው ፓርቲ ጥያቄ አልቀረበም እንጂ ተገቢ ከሆነ እውቅና እሰጣለሁ ይላል? የእርስዎ መከራከሪያ ነጥብ ምንድን ነው?

ዶክተር ነጋሶ፡- የእኔ ሃሳብ አሁንም በተለይ ከአንቀጽ 29 እና 31 ጋር ነው የሚያያዘው። የአመለካካት፣ የሃሳብ ነጻነት መኖር አለበት፤ መከበር አለበት። የተለያዩ ሃሳቦችን የሚይዙ፤ የተለያየም አይነት ሃሳብ ያላቸው ሰዎች በያዙት አመለካከታቸውና እምነታቸው የመደራጀት መብት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ከሆነ በተለያዩ ምክንያቶች «እኔ መገንጠል እፈልጋለሁ» የሚል ግለሰብ ካለ ሀሳቡን በነጻ መግለጽ አለበት ብዬ ነው የምገምተው። ሃሳቡን በነጻነት ገልፆ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ መደራጀት መብቱ ነው። ያንን የሚደራጅበትን ዓላማ የሚደግፉ ሰዎችን አሰባስቦ ማስተማር የራሱ መብት ነው። ስለዚህ በአንቀጽ 39 መሰረት ያለገደብ እስከ መገንጠል መብት ከተከበረ በዚያ የመገንጠል ሀሳብ ያላቸው ሰዎች መደራጀት መብታቸው ነው። መገንጠል የለብንም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ እንደዚሁ የመንቀሳቀስና የመደራጀት መብት ሊኖራቸው ይገባል። የለም ጥያቄው የብሔር ጥያቄ ነው የመገንጠልና ያለመገንጠል ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ በፌዴራላዊ ስርዓት መተዳደር አለብን የሚሉ ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በኮንፌዴሬሽን ነው የምንተዳደረው የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ እና የመደራጀት መብታቸው መከበር አለበት። ይሄ በትክክል ተግባራዊ ሆኗል ወይ? መብታቸው ተከብሯል ወይስ አልተከበረም? አንድ ጥያቄ ነው።

ስለዚህ እኔ አንቀጽ 39 ተግባራዊ አልሆነም ብዬ የማስብበት ምክንያት አለኝ፡፡ በእርግጥ መገንጠልን በጣም ነው የምቃወመው፡፡ ግን ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛ የነጻነት ጉዳይ ነው፡፡ የአመለካከት፣ የመደራጀት ነጻነቶች እና በዚያም ላይ ተመስርቶ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድበት ሁኔታ ተመቻችቷል ወይ? ከሚለው አኳያ ነው። እነዚህ ሁለቱ ተግባራዊ አልሆኑም። ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ተደራጅተው ሃሳባቸውን ከገለጹ በኋላ ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጡ ሁኔታው አልተመቻቸም።

ለምሳሌ ‹‹ኦነግ›› እኔ መገንጠል እፈልጋለሁ ይላል፤ የድሮው፤ የአሁኑን አላውቅም። ካልሆነ በመሣሪያ ኃይል ነው ተግባራዊ የማደርገው ይላል። ህዝቡ ይደግፋል ወይስ አይደግፍም የሚለው በምንድን ነው የሚታወቀው? ኢህአዴግ ኦነግ የሚለው ትክክል አይደለም፤ እኔ የምለው ነው ትክክለኛ ይላል፡፡ ክልሎች ተቋቁመዋል ቋንቋ፤ ተከብሯል ይሄ ይበቃል ይላል። ህዝቡ ራሱ የፈለገውን እየመረጠ ነው፤ ራሱን እያስተዳደረ ነው ይባላል፡፡ የትኛው ፓርቲ ነው በትክክለኛው መንገድ እነዚህ የተለያዩ ሀሳቦችን እየያዘ እየተወዳደረ ወደ ምርጫ የገባው? በምንድን ነው የምናውቀው?

አዲስ ዘመን፡- የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባልም ሆነው ነበር፡፡ ለአብነት የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ አንዱ ነበር፡፡ ለምን እራስዎን አገለሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ከፖለቲካ ፓርቲ ራሴን ያገለልኩበት በፕሮግራማቸው ያለመስማማት ነበር። ወደ ፓርቲው በምገባበት ጊዜ የውይይት መድረክ ነው እንጂ ፓርቲ አልነበረም። ከዚያ የውይይት መድረኩ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄዶ መመዝገብ ነበረበት እንደ ጥምረት። በወቅቱ ወደ ስድስት ፓርቲዎች ነበሩ። በውይይቱ ላይ ሁለት ሰዎች ነበርን እኔና ስዬ አብርሃ። እኛ የድርጅቶቹ አባላት ሳንሆን በውይይት እንሳተፍ ነበር። መድረኩ ወደ ምርጫ ቦርድ ሲመዘገብ አንዱን መምረጥ ነበረብን። ምክንያቱም እንደ ግለሰብ አባል መሆን አንችልም። ስለዚህ የትኛው ውስጥ ብገባ ይሻለኛል? ብሎ መምረጥ ነበረብኝ። አረና ትግራይ የትግራይ ሰዎች ፓርቲ ነው። እኔ ደግሞ የትግራይ አይደለሁም። የደቡብ ህብረትም ነበር። እኔ ግን ደቡብ አልነበርኩም። የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ (ኦብኮ) ነበር። ከእሱም ጋር የኦሮሞም ቢሆን በአስተሳሰብ በተለይም በሶሻል ኢኮኖሚና በብሔር ጥያቄ ላይ ልዩነት ነበረን። እኔ የምደግፈው ብሔር ብሔረሰቦች እስከመገንጠል አንቀፅ 39 በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ነው። የኦፌዴን እና የኦብኮ የሁለቱ ድርጅቶች አንቀፅ 39 ላይ ያላቸው አቋም ከእኔ ጋር የሚስማማ አልነበረም። አንቀፅ 39 እንዲከበር ይህም የሚከበረው የህዝብ ውሳኔ መሰረት ተደርጎ ነው። እነርሱ እዚህ ላይ ጥያቄዎች ነበራቸው አልተስማሙም።

ሌላው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ነው። አንድነት ደግሞ አንቀፅ 39 በሙሉ ይቃወማል። ስማቸውን መጥቀስ የማልፈልገው ሁለት ሰዎች እዚህ መጥተው «እባክህን የአንድነት ፓርቲ አባል ሁን» ብለው ጠየቁኝ። እነዚህም የኢትዮጵያ አንድነት እንጂ አንቀፅ 39 እንቃወማለን የሚሉ ናቸው። የእናንተን ፓርቲ መቀላቀል አልችልም አልኳቸው። እነርሱም በጣም ታስፈልገናለህ እባክህ አባል ሁነን አሉኝ። ይሄማ ከሆነ ፕሮግራማችሁን ማሻሻል አለባችሁ ስለዚህ አሻሽላችሁ አምጡ ብላቸው «አንተ የምትፈልገውን አንቀፅ ፅፈህ አምጣልን፤  ጉባዔውን እንዳካሄድን እዛ ውስጥ አስገብተን እናፀድቃለን» አሉ። እሺ አልኩና አንቀፅ 39ን በቀጥታ አልጠቀስኩም። የእነሱ አንቀፅ ሶስት አንድ አምስት ነው የምትባለው።

የፃፍኩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚፈቱት በዴሞክራሲ መንገድ በውይይትና በድርድር ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ ተቀባይነት ካላገኘ ጥያቄው ወደ ህዝብ ይወርድና ህዝብ ይወስንበታል የሚል አስቀመጥኩ። አንቀፅ 39 አላልኩም። የህዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። ስለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች በዚህ ዓይነት በዴሞክራሲ መንገድ በውይይትና በድርድር ካልተፈቱ ወደ ህዝብ ይወርዱና በህዝቡ ውሳኔ ይፈታሉ በሚል አስቀመጥኩና ሰጠሁ።

በፕሮግራም አስገብተው በጉባዔ አፀደቁት። ያን ጊዜ እሺ አልኩና ወደ ፓርቲው ገባሁ። ምክያቱም በእኔ እምነት ፖለቲካ በሃይል አይፈታም በውይይት እንጂ፡፡ አብረን በጥሩ ሁኔታ እየሰራን እያለ ታህሳስ 2006ዓ.ም ጉባዔ አካሄድን፡፡ ለጉባኤው ከሚነሱ ሃሳቦች አንዱ አንቀፅ ሶስት አምስት አንድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በምን አይነት መንገድ ነው ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ማሻሻያው «ሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ከተመለከተ በስተቀር» የሚል ሐረግ ገባ፡፡ በዚህ መሻሻል አለበት ተባለ፡፡ ይህ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ይጨፈልቃል ብዬ ተከራከርኩ፡፡ ወደ ጉባዔ ቀርቦ ፀደቀ፡፡ በማግስቱ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲካሄድ ንግግር አደረኩ እና እኔ አልስማም ብዬ ወጣሁ፡፡ በመሃል ሌላ ችግር ተፈጥሮ ፓርቲው አራት ቦታ ላይ ተካፈለ መሰለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለመዳከሙ  የእርስዎ እጅ አለበት ይባላል፡፡ ምን ይላሉ? ከፖለቲካ ውጭ ከሆኑስ በቀጣይስ እንዴት ነው ሀገሪቱን ለማገልገል ያቀዱት?

ዶክተር ነጋሶ፡- አንድ ግለሰብ ከፓርቲ በላይ ምን ያክል አቅም አለው፡፡ ሌላ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ይህን ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ እውነታው ግን እኔ በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጄ የለበትም፡፡ አሁን ማገልገል የምፈልገው ለተለያዩ የህትመትና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ሃሳቤን በመግለፅ ለማስተማር እሞክራለሁ፡፡ የፓርቲ አባል ባልሆንም ከተጋበዝኩ ለማዳመጥ እሄዳለሁ፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይም እሳተፋለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ውይይቶች ላይ ሲጋብዙኝ እሳተፋለሁ ሃሳቤንም እሰጣለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም፡፡ የሚስማማኝ ፓርቲ የለም፡፡ ቢኖርም በእድሜና በጤና ጉዳይ አልሳተፍም፡፡

አዲስ ዘመን፡-  የጋራ ሰነድ የሆነውን ህገመንግስት ከማርቀቅ ጀምሮ ሌሎች ለሰሯቸው ተግባራት ተገቢ ጥቅም እና ክብር አግኝተው ይሆን?

ዶክተር ነጋሶ፡- ታሪኩን ታውቀዋለህ መሰለኝ፡፡ ትፅፈዋለህ ወይስ አትፅፈውም? ብትጽፈው ደስ ይለኛል፡፡ አሁን ካለሁበት ቤት ውጣ ተብዬ ሁለቴ ተፅፏል፡፡ ለቤት ውስጥ እና ለኑሮ የማወጣውን ገንዘብ ተከልክያለሁ፡፡ የምኖረው በ1ሺህ 700 ብር የፓርላማ ደመወዝ ነው፡፡ መኪናም ተቀምቻለሁ፡፡ ይህን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቢያውቁት ጥሩ ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ ባለቤቴ ናት የቀጠረችው፡፡ ጥበቃም በትንሽ ገንዘብ ቀጥሬ ነው። ለህክምና የባለቤቴ ጓደኞች መደሃኒት ገዝተው ባይልኩልኝ  ከባድ ነበር የሚሆንብኝ፡፡ ጠዋት እና ማታ አምስት ኪኒን ነው የምወስደው፡፡ የደም ስሮቼ ይዘጋጋሉ፡፡ ለህክምና እና ምርምራ ከሄድኩኝ ሁለት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ የስኳር እና የልብ በሽታ አለብኝ፡፡ ለመመርመር እና ውድ መደሃኒቶች ለመግዛት ገንዘብ የለኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ፕሬዚዳንቱ ጋር በታክሲ ነው የሄድኩት፡፡  የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን ክብር እና ጥቅም ይገባኝ ነበር። ይህ ለእኔ ተከልክሏል፡፡ ጥሩ ባለቤት እና የሰው ፍቅር ስላለኝ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ይህ አገር እና መንግስት የሚገባኝን ጥቅምና ክብር አልሰጠኝም፡፡ ለወደፊትም ይህን ታሪክ ይፈርደዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ?

ዶከተር ነጋሶ፡- ወገንተኛ ሆነሃል ተብዬ ነው፡፡ እውነቱን ከተናገርን እኔ የ1997 ዓ.ም ምርጫ በግል ነው የተሳተፍኩት፡፡ በግል ተሳትፌ ፓርላማ ከገባሁ በኋላም በምን ጉዳይ ላይ ወገንተኛ እንደሆንኩ መረጃ የለም፡፡ አዋጅ 255/94 አንቀፅ 7 ጥሷል ነው የተባልኩት፡፡ በአንቀፅ 13 መሰረትም መቀጣት አለበት ተባለ፡፡ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ ሄጄ ፍርድ በትክክል አልተሰጠኝም፡፡ ግን የመጀመሪያው ፍርድ ቤትም በግል በምርጫ መሳተፉ ችግር የለውም ብሏል፡፡ «ርዕሰ ብሄሩ ለህገ መንግስቱ፣ ለአገሪቱ እና ለህሊናው ታማኝ መሆን አለበት» ይላል ህገ መንግስቱ፡፡ ይህ እያለ ነው ኢ- ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቅማ ጥቅም የተከለከልኩት፡፡ አሁን ካለሁበትም ቤት በማንኛውም ሰዓት በፖሊስ ያስወጡኛል ብዬ ነው በፍርሃት የምኖረው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከአንድነት ብቻ ሳይሆን ከኢህአዴግም ተለያይተዋል፡፡  እንዴት ተለያዩ?

 ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፡- በመሰረቱ ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል እና የሃብት ክፍፍል ተፈጥሮ ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ የሚፈጠረው በእውነተኛ ሶሻሊዝም ነው፡፡ እስካሁን በዓለም ይህ የተፈጠረበት አላየሁም፡፡ የሩሲያ እና የቻይና ፍልስፍናም በሚለው መንገድ እንዲፈጠር አላዳረጉም፡፡ እኔ ግን እውነተኛ ሶሻሊዝም ተፈጥሮ ፍትሃዊ የስልጣን እና ሃብት ክፍፍል እንዲኖረ ነው የምፈልገው፡፡ ዛሬም እምነቴ ይህ ነው፡፡

እኔ ኢህአዴግን ስቀላቀል «አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የምንከተለው» ነበር የተባለው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሶሻሊዝም እንደርሳለን የሚል ነበር አስተሳሰቡ፡፡ በዚህ እምነት ነው የገባሁበት፡፡ ለዚህ ዓላማም ብዙ ሺህ ታጋዮች ተሰውተዋል፡፡ ግን በ1993ዓ.ም ላይ ተሃድሶ ተባለ፡፡ የዱሮው ቀርቶ ወደ ካፒታሊዝም ነው የምናመራው ተባለ፡፡ የሶሻሊዝም ነገር አይነሳም፡፡ ይህ መቼ እንደሚሆን አናውቅም ተብሎ ተነገረ፡፡ ያኔ ተሃድሶ ስብሰባው ላይ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ግን ይህ 1983ዓ.ም ጀምሮ እየተሠራበት ነበር፡፡ እስከዚህ ድረስ ምንም መረጃው አልነበረኝም፡፡ በወቅቱ የጦፈ ክርክር ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የቄስ ልጅ ስለሆንኩ ውሸት አልወድም፡፡ ሌላው እኔ ታጋይ እንጂ ዲፕሎማት አይደለሁም፡፡ በዚህ ላይ ጉዳዩ ሚስጥር ተደርጎ በመያዙ የሃሳብ ልዩነት ተፈጠረ፡፡ በአንድም በሌላም የህዝቡ ጥያቄ አልተመለሰም የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ ከዚህ ፓርቲውን ትቼ ወጣሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋርም በሐሳብ አለመግባትም ነበር ይባላል፡፡ እውነት ነው?meles

negasso_gidada_-3ዶክተር ነጋሶ፡- እኔ አቶ መለስን አድነቃለሁ፤ ሳደንቅም ነበር፡፡ የመከራከርና የመናገር አቅም አለው፡፡ በዚህ ላይ ችግር የለብኝም፡፡ በህውሃት መካከል በነበረው 1992 እና 1993 ዓ.ም ክፍፍል በነበረበት ወቅት አፈታቱ ላይ ነው የተለያየነው፡፡ መለስ እና ግብረ አበሮቻቸው የሄዱበት መንገድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የህወሃት አመራሮችን አባሮ ይህ የፀደቀው በመቀሌ ካድሬዎች ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስታዊ አይደለም፡፡ የድርጅቱ ህገ ደንብም ይከለክላል፡፡ ይህ ጠቅላላ ጉባዔ ሳይወስን ነው የተባረሩት፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት ነበርን፡፡ሁለተኛው የኢህአዴግ ማዕከላዊ ጉባዔ ሲደረግ አቶ መለስ ስለ አካሄዱ ሲገልፅ አንዳንድ የማይመቹ ቃላት ተናገረ፡፡ እኔም እጄን አውጥቼ ‹‹አነጋገርህ አላማረኝም አሁንስ መንግስቱን መሰልከኝ›› አልኩኝ፡፡  የአይዲዮሎጂ ልዩነትም ነበረን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ደጋግመው ዴሞክራሲ ስለመቀጨጩ ነግረውኛል፡፡ ግን ሁለት ጊዜ ተወዳድረው ፓርላማ ገብተዋል፡፡ ታዲያ ዴሞክራሲ የለም ማለት ይችላል?

ዶክተር ነጋሶ፡- በወቅቱ ስብሰባ ለማካሄድ፣ ሰልፍ ስንጠራ ተከልክለናል፡፡ ሚዲያው ምን ዓይነት ነፃነት አለው? 1997 ዓ.ም ምርጫ በተመለከተ አይተናል፡፡ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ተቃዋሚዎች ውጤታማ ነበሩ፡፡ ሚዲያውም ክፍት ነበር፡፡ በምርጫ ወቅትም ብዙ ጣልቃ ገብነት አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ የወጡትን አዋጆች አይተናል፡፡ በወቅቱ ጥሩ ነገር ተሰርቶ ነበር፡፡ ለካድሬዎች መመሪያ ተሰጥቶ ነበር፡፡ የምርጫ መመሪያ ለአባሎቹ በትኗል፡፡ ያም ሆኖ ደንቢዶሎ በምወዳደርበት ወቅት ፈተና ነበር፡፡ ካድሬ ሲረብሽ ህዝቡ ነበር ሥርዓት የሚያሲዘው፡፡ የምርጫ ቅስቀሳውም በዚያው ልክ ፈተና ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ውስጥ ናት፡፡ መሆን ነበረበት?

ዶክተር ነጋሶ፡- ባለፈው ጊዜ በተለያዩ ምክንያች ችግሮች ተፈጥረው ነበር፡፡ በእኔ እይታ በጊዜ ቢፈቱ ኖሮ ሁሉም ችግሮች አይከሰቱም ነበር፡፡ ሄዶ ሄዶ በእነዚህ ‹‹ውሃ መልስ ውሃ ቅዳ›› በሚባሉ ሁኔታዎች ነገሮች ተባብስው መጥፎ ውድመቶች ተካሂደዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ በኢሬቻ በዓል ላይ በተፈጠረው ችግር በተቀሰቀሰ ቁጣ በአንድ ሳምንት 130 ፕሮጀክቶች ሲወድሙ ያሳዝናል፡፡ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን አዋጁ ታወጀ፡፡

በዚህን ጊዜ ምን ታደርጋለህ? ከቁጥጥር የወጣውን ለማስቆም ሌላ ዘዴ ነበር? ጥያቄው ቶሎ ብሎ ወደ መደበኛ ሁኔታ መልሶ ህዝቡም መንግስትም ከሚመለከታቸው ጋር ተወያይቶ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ነው፡፡ እኔም ብኖርበት ወይ መልቀቅ ካልሆነ ግን ይህን አይነት እርምጃ መውሰድ አለብኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሌላው ጥልቅ ተሃድሶ ተደርጎ የአመራር ለውጥም እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

 ዶክተር ነጋሶ፡-  የነበረው «መሃይምም ሆኖ በድርጅት የሚያምን» የሚለው አባባል ተለውጦ ምሁራን ሲሳተፉበት በእውቀት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ማስፈፀም ሁኔታ እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የድርጅት አባል ያልሆኑ አሉ ይህም ጥሩ ነው፡፡ ግን ይህ ሁሉ መሰረታዊ የፖለቲካ፣ መልካም አስተዳደር፣ የሙስና ጉዳይ፣ ከህገ መንግስቱ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች በትክክል ተግባራዊ እስካልሆኑ ድረስ የሰዎች መለዋወጥ ችግሮችን ያራዝማል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአገር ርዕሰ ብሄር ሆነው ስንት ዲፕሎማቶችን እንደሸኙ እና እንደተቀበሉ ያስታውሳሉ?

ዶክተር ነጋሶ፡- ስንት ዲፕሎማቶች እንደተቀበልኩና እና ሽኝት እንዳደርኩላቸው በቁጥር አላስታውስም፡፡ ግን በርካቶች ናቸው፡፡

(አዲስ ዘመን) የካቲት 6/2009ዓ.ም.

ተጨማሪ የውስጥ ምስሎች ከዝግጅት ክፍሉ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *