Skip to content

ኢትዮጵያን የሚበጃት ‘የጥልቅ ተሃድሶ’ አዋጪው የትግል ጎዳና የቱ ነው?

የመንግሥት ሥልጣን የዝርፊያ ማዕድ ከሆነም የዝርፊያ ተራ እኛም ይድረሰን ባይነት ምርጫን በጉቦና በተንኮል፣ በአምባጓሮና በጥይት ሁሉ መተናነቂያ ከማድረግ አይመለስም፡፡ እንዲህ ያለው የምዝበራ ሽሚያ “እኩልነት”ን፣ “የብሔረሰብ መብት”ን፣ በተፈጥሮ ሀብትና በብሔረሰባዊ የሕዝብ ቁጥር ማየልን፣ ከሌላው የበለጠ መስዋዕት “መክፈል”ን፣ . . .  ወዘተ ሁሉ ሕዝብን መጋለቢያ አድርጎ ከመጠቀም አይመለስም፡፡ እዚህ  አዙሪት ውስጥ እስከተገባ ድረስም ዘግናኝ የደም ግብር መምጣቱ አይቀርም፡፡

በቶላ ሊካሳ

ከ2008 ዓ.ም. ልምድ እንደተማርነው እስከ ዛሬ የነበረው፣ አሁንም ያለው ሥርዓተ መንግሥት ያለዴሞክራሲያዊ መሻሻል ቢቀጥል ለመቆጣጠር የሚያስቸግር አደጋ መጋበዝ መሆኑ ዛሬ የማያከራክር ነው፡፡ ውድመት፣ ቁጣና ጥላቻዎች የተለዋወሱበት ትግልም መውጫ ወደ ሌለው ምስቅልቅሎሽ ውስጥ ሊዘፍቅ እንደሚችል በሽውታው ታይቷል፡፡ እናም ከአደጋዎች አምልጦ በፖለቲካ ሰላም ውስጥ ወደፊት መገስገስ የሚቻለው በየት በኩል ነው? በሁላችንም አዕምሮ ተሰንቅሮ ሊነዘንዘን የሚገባው ጥያቄም ይኼ ነው፡፡ ይኼንን መመለስ፣ ሌላው ቢቀር መቃኘት ይቻል ዘንድ መነሻና መሠረት የሆኑ የማዕዘን ድንጋዮችን ላሳይ፡፡

  1. የማዕዘን ድንጋዮች

እስላማዊ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትና የበለፀጉት ታላላቅ አገሮች እየተተነኳኮሉ መመጋገባቸው ማለቂያ ማጣቱ፣ በአንድ ወገን፣ ቀውስ በጠለፋቸው አገሮች ውስጥ የማያባራ ጦርነትና ትርምስ እንዲኖር እንዳደረገ ሁሉ በሌላ ጎን፣ በምዕራብ አገሮችም ውስጥ የሽብር ጥቃትንና የስቀት ኑሮን የማይላቀቁት ጥላ አድርጎታል፡፡ ጭራሽ፣ አሸባሪነት በሰርጎ ገብ አሸባሪዎች ከመሥራት አልፎ በውስጥ ያሉ ሙስሊሞችንና ትኩስ ስደተኞችን በማገዶነት የመጠቀም ብርታትን ተቀዳጅቷል፡፡ ይኼ መፍቻ ያጣ ችግር በሌሎች የቀውስ ሰበዞች ታግዞ በምዕራብ አገሮች ሕዝብ ውስጥ የእስልምናን ጥላቻና ፍርኃት ከማስፋፋቱም በላይ ኑሮው ለተናጋ ሰብዓዊ ፍጡር የመድረስና መጠጊያ የመሆን በጎነትን ገዝግዟል፡፡ ዛሬ በምዕራብ አገሮች ውስጥ እየገጠጠ የመጣው ሙስሊም ስደተኛ ጠል ዝንባሌና ይኼንኑ የሚያቀነቅንና ደጋፊው የሞቀ (የበረከተ) የቀኝ አክራሪነት የዚሁ ውጤት ነው፡፡

ይህ አዝማሚያ እያመጣ ያለውም ድግስ መድረሻ ያጣ ስደተኛን መጠጊያ መንፈግ ብቻ ሳይሆን፣ ስደተኛን በተለይም ሙስሊም ስደተኛን መልሶ ማባረርና ምዕራባዊ አገሮችን ከእስላማዊ መስፋፋት ማፅዳት የሚል ተልዕኮን ጭምር ነው፡፡ ዶናልድ ትራምፕና የአውሮፓ ወግ አጥባቂዎች ላይ የሚንፀባረቀው አስደንጋጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ የዚሁ ትንቢት መጀማመሪያ ነው፡፡ የትንቢቱ አቀንቃኝነት በተለመደው የወግ አጥባቂዎች ሠፈር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ብዙ የፖለቲካ ሠፈሮችን አንድ ረድፍ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ “ሶሻሊስቱ” የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድ ሽብርተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፈን ሰው ዜግነት የሚገፍና የሚያባርር ሕግ የማስወጣት ሙከራ (ለጊዜው ከራሱ ፓርቲ በመጣ ቅዋሜ የተስተጓጎለው) የዚሁ የሠፈር ቅልቅሎሽ ምልክት ነው፡፡ እንኳን የተሰደደ ተመልሶ ተባርሮ፣ አዲስ ስደተኛ አናስገባም ባይነትና የዕርዳታ መመናመን በቀውሳም አገሮችና በአካባቢያቸው ውስጥ የሚፈጥረው የትርምስና የጉስቁልና መዛመት ፈንግልን በዶሮ ፊት እንደማውራት ያህል አስፈሪ ነው፡፡

  • አዝማሚያ ጉም እያሰባሰበ እንደመሆኑና ሽብርተኛነትና ጦርነት በሚሽከረከርበት የአፍሪካ ቀንድ እምብርት እንደመገኘታችን፣ ራሳችንን ማትረፍና ለዙሪያችን መትረፍ የምንችለው በውስጣችን የተጀማመረውን የሽምቅ ውጊያ እሳት ካጠፋን፣ በውድመት የተሞላ የምሬት አመፅን ማርገዝ ካቆምን፣ ዓለም አቀፋዊ ሽብርተኝነትንና መዘዙን በደንብ አጢነንና አስጢነን ለሽብርተኛነት የሚጠቅሙ ሰበቦችን ካመከንንና ከቤታችን ባሻገር በጎረቤቶቻችን ያለ የሽብርና የትርምስ ወላፈን እንዲጠፋ የሚበጅ ሚና መጫወት ከቻልን ብቻ ነው፡፡ በቤት ውስጥ ስንትረከረክ የአካባቢያችንን ችግር ብንረሳ ከአካባቢያችን የመጣ ቀውስ ይጠልፈናል፡፡ የውስጣችንን አለባብሰን የደጅ ደጁን ወግ ብናሳምርም ሳናስበው ቀውስ ከውስጣችን ይፈነዳል፡፡ የውስጥና የአካባቢ ሰላም የተደጋገፉበት ሁኔታ መፈጠሩ ለህልውና ግድ የሚያሻ ሆኗል፡፡

ኢሕአዴግ በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ አዕምሮ ሙሽት ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አሻራውን አሳርፏል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መልክዓ ምድር ቀይሯል፡፡ የብሔረሰብ መብትን አነሰም በዛ የተመረኮዘ የአስተዳደር ይዞታ አሸናሽነን፣ የፓርቲ አደረጃጀትንና የሥልጣን አያያዝን ያመጣ ሕገ መንግሥት ተክሏል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአገሪቱ የልማት ግስጋሴ ጀማሪም ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ተቃውሞና ድጋፍ እንዳፈራ ሁሉ ሕገ መንግሥቱም ደጋፊና ተቃዋሚ አፍርቷል፡፡ እንዲያውም የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩትንና “ሕገ መንግሥቱ ሊያሠራ ይችላል፣ ተግባራዊ የሚያደርገው ታጣ እንጂ” የሚሉትን የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ወስደን፣ “ለሰላማችን ጠንቅ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ነው” ከሚሉት የተቃዋሚ ክንፎች ጋር ስናነፃፅር እነዚህኞቹ በቁጥር የሚያንሱ ናቸው፡፡ ወይም የሚያንሱ ይመስላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በራሱ ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ወደ ጎን የማይባሉ አስፈላጊ ሰበዞች ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም፣ የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ዴሞክራሲን ተጋግዞ የመገንባት ዕድል ዕውን የመሆን ተስፋ የሚኖው “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” በሚል ጥያቄ በኩል ሳይሆን፣ ያለውን ሕገ መንግሥት የጋራ መገናኛ በማድረግ በኩል እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ እናም በሽግግር መንግሥት ጥያቄ አማካይነት ካለው ሕገ መንግሥት ለማምለጥ መሞከር ለተከፋፈለ የፖለቲካ ንጠት በር መክፈት ነው፡፡

      ኢሕዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርጋቸው ሌላም ሰበዝ አለ፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን አወጣጡና “በአዲስ” አገዛዝ ግንባታው የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ ኃይል ከነርዕዮተ ዓለሙ በዋናነት የተጠቀመ መሆኑ አውታረ አገዛዙን ገለልተኛ እነፃ ገና የጎደለው መንታ ተፈጥሮ በጨነቀ ጊዜ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችል ኢሕአዴጋዊ ቡጥ ከውጭ ደግሞ “የዴሞክራሲ” ቅርፊት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችን ተግባራዊ ሕይወት ከሲታ እንዲሆን ያደረገው፣ የኢሕአዴግንም በሥልጣን ላይ መቆየት በሕዝብ ድምፅ ብቻ የማይወሰን እንዲሆን ያደረገው ይኸው የቡጥና የቅርፊት አለመጣጣም (የቡጡ ቅርፊቱን ለመጫን መቻሉ) ነው፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫ ድምፅ ቢሸነፍና ሽንፈቱን ተቀብሎ ከሥልጣን ለመውረድ የተስማማበት ሁኔታ ቢከሰት እንኳ፣ ከአገዛዙ የሥልጣን ኃይል ውስጥ ‹ዘራፍ› ብሎ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ምናልባት ሁሉ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በአጭሩ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የኢሕአዴግ ሰበዝ (ፋክተር) ለበጎም ለክፉም ውጤት መዋል ይችላል፣ እንዳያያዛችን፡፡

  • ዕድል እስካለ ድረስ የሚፈለገው ቡጡ ቅርፊቱን እየመሰለ እንዲመጣ፣ መልካዊውን “ዴሞክራሲ” ወደ ሥጋነት የሚቀይር ግንባታ እንዲካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ተግባር የዴሞክራት ተቃዋሚዎቹን ያህል የኢሕአዴግ ዴሞክራቶች ሚና አስፈላጊ ነው፡፡ በምርጫ ጨዋታ ዴሞክራሲን የማደላደል ቀዳዳ ኢሕአዴግ አይሰጥም የሚል መከራከሪያ አይረታም፡፡ ከዚህ በፊት በ1997 ዓ.ም. ቀዳዳው ተገኝቶ ገና ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በተቃዋሚ በኩል የታየው ጅልና ጀብደኛ አቅራሪነት ሳይጀመር አበላሽቶታል፡፡ አሁንም ኢሕአዴግ በአስደንጋጭ ቅዋሜ ተገፍቶ ዴሞክራሲን አጠልቃለሁ እያለ ነው፡፡ ደጋፊም ተቃዋሚም እዚህ የማጥለቅ ሒደት ላይ አፍጧል፡፡ በዚህ “ዴሞክራሲን በማጥለቅ” ሒደት ውስጥ ተቃዋሚዎች ብልህ ፖለቲከኛነትን አውቀውበት ከኢሕአዴግ ያነሰ ግን ጉልህ የሕዝብ ድምፅ ቢያገኙ እንኳ ትልቅ ድል ነው፡፡ ምክንያቱም የድምፁ ውጤት ፋይዳ ለዴሞክራሲ ናፋቂዎች ዴሞክራሲን ሥጋና መልክ፣ እንዲሁም የሕዝብ ባህል አድርጎ በመገንባት ረገድ ተግባብቶ ለመሥራት ጥሩ ዕድል በማስገኘቱ እንጂ በቡድኖች የሥልጣን ትርፍና ኪሳራ አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግን በድምፅ ቢበልጡ እንኳ ከጠቀስነው የዴሞክራሲ ጥንቁቅ (የትግግዝ) ግንባታ የራቀ ስኬት አይኖርም፡፡ የድምፅ ብልጫው የሚያመጣው አዲስ ዕድል ቢኖር የፖለቲካ እርቅ እንቅስቃሴን የበለጠ ሰሚ እንዲያገኝ ማድረጉ ነው፡፡ በድምፅ አሸንፎም የፖለቲካ እርቅ አቀንቃኝ መሆን ለምንድነው? ኢሕዴግን ለማቄል ነው ወይስ ለፅድቅ ነው? ይኼ ያልተገለጠላቸው ይኖሩ ይሆናል፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ኢሕአዴግን ማታለልም አይደለም፡፡ የፃድቅ ቸርነትም አይደለም፡፡ የዴሞክራሲን ዕድል ላለማስቀጨት፣ ደም አፋሳሽ የእሳት መንገድን ለማምለጥ የሚያስፈልግ ክፍያ ነው፡፡
Related stories   በሳሊቫኪርና በሪክ ማቻር መካከል እያገረሸ ያለውን ቅራኔ እየተባባሰ በመምጣቱ በደቡብ ሱዳን አዲስ ግጭት እንዳያገረሽ ተሰግቷል

ከሃያ ዓመታት በላይ የገዛውና ከወታደሩ የወጣው የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜ በ2009 ዓ.ም. ጥቅምት በተካሄደ ምርጫ መሸነፉን ከመቀበል ባሻገር፣ “ያካሄድነው ምርጫ ለማጭበርበር የማይመች በመሆን ዓለምን ያስናቀ ነበር” ብሎ ለማሞገስ ደፍሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በሥልጣን ዘመኑ ለሠራው በደል በሕግ ስለመጠየቁ አይቀሬነት ከተቃዋሚ አካባቢ መነገሩ አቋም አስቀይሮ፣ በ‹‹ምርጫው አልተሸነፍኩም፣ ምርጫው ተጭበርብሯልና ሌላ ምርጫ መካሄድ አለበት. . . ሠራዊቱም ለዚህ ከጎኔ እንደሚቆም እርግጠኛ ነኝ” የሚል ጣጣን አመጣ፡፡ እንግዲህ ለተቃዋሚ የማይረባ አቅራሪነት ለተሸናፊው እምቢ ባይነት የጋምቢያ ሕዝብ ምን ያህል የፍዳ ዋጋ ለመክፈል  እንደተጋለጠ መረዳት አያዳግትም፡፡ ለጋምቢያ ሕዝብ የሚበጀው ነባር ገዢውን አባብሎና ከተጠያቂነት ነፃ አድርጎ መገላገል ወይስ በአካባቢ ጣልቃ ገብነት ታግዞ ማውረድና ለፍርድ ማቅረብ? ለኛዎቹ ተቃዋሚዎች ይህ የጋምቢያ ፈተና የ1997 ዓ.ም.  ጀብደኝነት እንዲያስታውሱ፣ አሁንም የቆሙበት መሬት አሸዋማ መሆኑን እንዲያስተውሉ፣ እርቅና አብሮ መሥራት ከብልጣ ብልጥነት በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፖለቲካ ሰላም የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን እንዲረዱ ያስችላቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

  • ሕዝብ በሞላ የሰው ልጅ የተከበረበትን የነፃነት ኑሮ አግኝቶ ‹‹ተመስገን . . . ›› ማለትን ተጠምቷል፡፡ ይኼንን ነፃነት ግን ካልተነጠልኩ፣ ካልተገነጠልኩ ሞቴ ወይም ግዛቴ ከተሸረፈ ሞቴ የሚሉ የጦርነት መንገዶች ድል አያቀዳጁም፡፡ ነፃነት የጦርነትና የፍዳ ወጥመዶችንና ዕድሎች አምልጦ በመብት ዋስትናና ኃላፊነት ውስጥ መገስገስ ነው፡፡
  • ጊዜ ስሙን የምናነሳውና የምንናፍቀው ዴሞክራሲም በራሱ ነፃነትን አያጎናፅፈንም፡፡ ዴሞክራሲ የማጓጓቱን ያህል የሚፈራና ጥንቁቅ አጠቃቀምን የሚፈልግ ነው፡፡ ‹መብቴ ነው› ባይነት ‹ኃላፊነቴ› ነው ከማለት ጋር ካልተጣጣመ፣ ዴሞክራሲ የጥላቻና የርኩቻ ማምረቻ፣ ብሎም የፍጅት መደገሻ መድረክ መሆን ይችላል፡፡ በአሜሪካ እንግዳ ያልሆነውና በ2009 ዓ.ም. የፕሬዚዳንት ምርጫ ውስጥ ደግሞ ጎልቶ ያስተዋልነው መዘራጠጥና ልቅ አፍነት የሚያስቀና ‹የመብት ሀብታምነት› ሳይሆን ከሩቁ ልንሸሸው የሚገባ ነውር ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የዝርፊያ ማዕድ ከሆነም የዝርፊያ ተራ እኛም ይድረሰን ባይነት ምርጫን በጉቦና በተንኮል፣ በአምባጓሮና በጥይት ሁሉ መተናነቂያ ከማድረግ አይመለስም፡፡ እንዲህ ያለው የምዝበራ ሽሚያ “እኩልነት”ን፣ “የብሔረሰብ መብት”ን፣ በተፈጥሮ ሀብትና በብሔረሰባዊ የሕዝብ ቁጥር ማየልን፣ ከሌላው የበለጠ መስዋዕት “መክፈል”ን፣ . . .  ወዘተ ሁሉ ሕዝብን መጋለቢያ አድርጎ ከመጠቀም አይመለስም፡፡ እዚህ  አዙሪት ውስጥ እስከተገባ ድረስም ዘግናኝ የደም ግብር መምጣቱ አይቀርም፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝብ ለረዥም ጊዜ የአኗኗራቸው አንዱ የሌላውን ጥፋትና ስህተት የማሳለፍ/ይቅር የማለት ልምምድና በነገረኛ ቅስቀሳ ለመንተግተግ አለመቸኮል፣ በዴሞክራሲ ውስጥ ተቻችሎ ለመኖር የሚበጅ ትልቅ ጥሪቱ ነው፡፡ በ1960ዎቹ ወጣቶች ዘንድ የታየው አለመቻቻል ለራሳቸውም ለሕዝብም የተረፈ መከራ እንዳስከተለ ሁሉ፣ በዛሬዎቹ ወጣት ፖለቲከኞች አካባቢም ከዴሞክራሲ ጋር የማይኳኋን ጭራሽ ለሌላ ፍጅት ሊዳርግ የሚችል (ስለመስከንና እርጋታ የሚያወሩ አዛውንት ፖለቲከኞችን ዘመን ያለፈባቸው አድርጎ በሚቆጥር ግብዝነት ጆሮና ልቦናውን የደፈነ፣ አቋሙን ጥያቄ  ምልክት ውስጥ ማስገባት የማይሻና ግንፍልነትን እንደ ጠመንጃ የታጠቀ) አስፈሪ ዝንባሌ አለ፡፡ ይህንን ዝንባሌ ከወዲህም ከወዲያም የመግራት ጥረት ውጤት እያሳየ ስለመሆኑ ተስፋ የሚሞላ ነገር ገና አላየንም፡፡ በአገር ውስጥ በጥሞና ለመነጋገር የሚያስችለው የመንፈስ መቀራረብ ድልድዩ ገና አልተዘረጋም፡፡

2. የዴሞክራሲን ጭራ አለመልቀቅ

  የማዕዘን ድንጋዮቻችንን በትክክል ካስቀመጥን የትግል ኃይላችንን የት ሥፍራ ላይ ማዋል እንዳለብን የመለየቱ ሥራ ቀላል ነው፡፡ ዴሞክራሲን ብዙዎች እንሻለን፡፡ በፌዴራላዊ ሥርዓት መፍትሔነትም ላይ አጠቃላይ ስምምነት አለ (በአወቃቀር ዓይነት ላይ ከመለያየት በቀር)፡፡ ኢሕአዴግ አሻራውን ባሳረፈባት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሁለቱም ጅምር አለ፡፡ ይኼ እስከሆነ ድረስ ዋናው የትግል ተግባር የተጀመረውን ከሕዝብ ፍላጎትና ከአዋጪነቱ ጋር አገናዝቦ ማቃናትና ሙሉ ማድረግ  ነው፡፡

የተግባሩ ክንዋኔ ኢሕአዴግን በማባባል ብቻ የሚገሩ አይደለም፡፡ አሁንም የዴሞክራሲን መሠረት በአግባቡ የማንጠፍ ፍላጎት ያለው መሆኑ በትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የወደቀ ነው (የኢሕአዴግ የትንታኔ መጽሔት በሆነው ‹አዲስ ራዕይ› ከመስከረም እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም.፣ 11ኛ ዓመት፣ ቅጽ 5፣ ቁ. 6) ላይ ያለውን ‹‹እንደገና በጥልቀት የመታደስ›› ንቅናቄያችን ጽሑፍን ይመለከታል)፡፡ የዴሞክራሲ ሙከራችን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ (የይስሙላ) ከመሆን አላለፈም የሚል ቆራጥ ትችት በራሱ ላይ ኢሕአዴግ እንዲያደርግ አንጠብቅም፡፡ ከዴሞክራሲ ያልተነጠለ እውነተኛው ተሃድሶ ውስጥ የመግባት ለውጥም የሥርዓቱን ‹የቆየ ገመና› በይፋ ማመንን የግድ አይጠይቅም፡፡ ይሁን እንጂ በሥልጣን ለመቀጠል ይበጀኛል የተባለው ማድበስበስም ሆነ ሽምጠጣ ተደርጎም ቢሆን ግን ነፍስን ከማዳን ያለፈ ተሃድሶ ውስጥ ለመግባት የምር ተፈልጎ ከሆነ፣ በእስከ ዛሬው ሁኔታ ግለሰቦች መንግሥታዊ ሥልጣንን ለግል መበልፀጊያነት እንዲሻሙበት ጥሩ ዋሻ የሆናቸው ከገዢነት እስከ ሥራ ቅጥርና የደረጃ ዕድገት ድረስ ሳይቀር፣ ሁሉ ነገር በአንድ ፓርቲ መዋጡ እንደነበር ነው፡፡ ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው የመንግሥት አዕማድ ከማንኛውም ፓርቲ ጋር ያልተሳከረ/ ያልተወራረሰ ነፃ ህልውና የሚያገኝበት ለውጥ ሲካሄድ፣ የመንግሥት አስተዳደርና ሌሎች ክንዋኔዎቹ በሕዝብና እውነትን በሚሻ ጋዜጠኝነት ዓይን ውስጥ መሆን ሲጀምሩ መሆኑን ሳያቅማሙ መቀበል ግድ ነው፡፡

እዚህ ሁኔታ ውስጥ ከተገባ፣ ለየትኛውም ፓርቲ በሥልጣን የመቆየቱም ሆነ ወደ ሥልጣን የመምጣቱ ዕድል በፖለቲካ አቋሙ ውጤታማነትና ማራኪነት ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል፡፡ እናም የገዢው ፓርቲ አባልነትን የሥራ ማግኛና የመዝረፊያ አቋራጭ መንገድ አድርጎ የመጠቀም ቀዳዳ ይደፈናል፡፡ የሙያ ብቃትና የሙያ ውድድር የሚሹ ሥራዎችን ፖለቲከኞች መፈትፈታቸው ይቋረጣል፡፡ ማንኛውም ዜጋና ሠራተኛ የካድሬና የሹም ፊት ሳያይና በእጅ አዙር እደቆሳለሁ በሚል ፍርኃት ሳይገነዝ ጥፋቶችንና አጥፊዎችን ለማጋለጥ፣ ጥቃትን ለመመከትና ለመብት ለመቆም ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብርታት ያገኛል፡፡ ምክንያቱም ዕውናዊ መተማመኛ አለው፡፡ ጥፋትን ያጋለጠንና ለመብት የተቆረቆረን ሰው ላጥቃ የሚል ቢመጣ፣ ከበላዩ ጌታ የሌለው ሕግ አለሁልህ ይለዋል፡፡ የሕጉ አለሁልህ ባይነት ቢፈዝና ቢጓደል ደግሞ፣ ሥር የያዘው ዴሞክራሲ እየተከታተለ ለሕጉ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ለውጥ ጋር የተላላሰ ተሃድሶም ሹማምንት ከነቀዙ በኋላ የመባነን፣ የደራሽ ግምገማና የሹም ሽር ጋጋታ፣ እንዲሁም አውጋዦቼን ለመመከት በኢንተርኔት ማኅበራዊ መድረኮች ላይ በቡድንና በግል የሚሳተፍ ሠራዊት ላነቃንቅ የሚሉ ዕዳ አይኖርበትም፡፡ የለውጡ ሒደት ራሱ የመጠማመድና የውግዘት ውጥረትን ይበትናል፣ እንዳይከማችም ያደርጋል፡፡ ለውጡ ራሱ ሰዎችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥልጡን አስተሳሰብና ባህል በውዴታ እየሳበ ያስገባቸዋል፡፡ ማለትም ራሱን በራሱ የሚያዛምት የመለወጥ አብዮት ዕውን ይሆናል፡፡ የለውጡ ግለት ከበረደ በኋላም ቢሆን ግለሰቦች ጨዋነታቸውን እንዲጠብቁ የዴሞክራሲያዊ ሱታፌው ንቁ ዓይን መሳጣትንና ተጠያቂ መሆንን እያስታወሰ ያግዛቸዋል፡፡ በአጭሩ የዚህ ዓይነቱ የዴሞክራሲ ለውጥ አካል ሆኖ ያልመጣ ተሃድሶ በእንቅልፍ ልብ የመጓዝ ዓይነት ለመላተም የተጋለጠ፣ ምን ቢሰብኩና ግለሒስ ቢያደርጉ፣ ምን ሰው ቢቀያይሩ፣ ጠርቶ የማይጠራ የተመልሶ ጭቃ ኑሮ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

Related stories   “በአጣዬ እና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ኮማንድ ፖስቱ

ኢሕአዴግ ከዚህ ዓይነቱ ብዙም የማያራምድ የዘመቻ ዘይቤ ለመውጣት የቆረጠ ስለመሆኑ የሚያስተማምን ነገር እያየን አይደለም፡፡ ሕጋዊ ተቃዋሚዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት እንኳ በተቸገሩበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ፣ ከኢሕአዴግ ሹማምንት አባላት አልፎ ወደ መንግሥት ሠራተኞችና ወደ ኅብረተሰቡ እየዘለቀ ነው የተባለለት “የተሃድሶ ንቅናቄ” ማካሄድ፣ ተቀናቃኝና ኮሽታ በሌለበት ሁኔታ “የመሪነት” ሚናን የማሟላት፣ የተሰበረ ድጋፍን የመጠገን (ከእኔ ሥልጣን በታች የሚበድልህ ቢኖር ከእንግዲህ ጆሮ ዳባ ሳልል አለሁልህና ሁሌም እየተከታተልክ ሳትፈራ ንገረኝ የሚል፣ ምሬትና ትዝብት ትርተራን ከቁጥጥር ባልወጣ ሁኔታ የፈቀደ “ሥልጠና” የመስጠት) እንቅስቃሴ ነው፡፡ “ፌስቡክን” እና “ቲዊተርን” በመሳሰሉ ማኅበራዊ መድረኮች ውስጥ የአባላትና የደጋፊ ተሳትፎን አስመንድጎ ተፃራሪዎቹን የመመከት ተግባር ውስጥ እየተትረከረከ መሆኑም አዛላቂው የለውጥ መንገድ እንዳልተጨበጠ ምስክር ነው፡፡ በጠቀስነው በአዲስ ራዕይ መጽሔት ውስጥም በማያሻማ አኳኋን ዛሬም ከዱሮ መንገድ ዘወር እንዳላለ እንዲህ ሲል ይነግረናል፡፡

‹‹በተሃድሶ መስመራችን እንደተቀመጠው በአገራችን የሚካሄደው ለውጥ በዋነኛት ሦስት የለውጥ አቅሞች በከፍተኛ ትስስር የሚያከናውኑት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች የለውጥ ሐሳቦች ያመነጨው ድርጅታችን፣ ይኼንኑ ሐሳብ ሕጋዊ ባህሪ አላብሶ የሚያስፈጽመው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታችንና የለውጡን ሐሳብ በተሳካ ሁኔታ የሚፈጽመው ሕዝባችን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሦስት ወሳኝ የለውጥ አቅሞች መካከል ትልቁ የመሪነት ሚና በድርጅታችን ትከሻ ላይ ያረፈ . . . ››

ከዚህ አባባል ኢሕአዴግ ከመንግሥትነት ራሱን ነጥሎና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እኩል አድርጎ ማየት ውስጥ ገና እንዳልገባ፣ የእሱን ከሥልጣን መውረድ የሕዝቡና የልማቱ መሪ ማጣትና መሰናከል እንደሆነ አድርጎ እንደሚያስብ ለመገንዘብ አያስቸግርም፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ አመለካከቱ እስከ ፀናበትና የአገሪቱ የፖለቲካ ሚዛንም ባለበት ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ፣ ምርጫ የ‹‹አውራ›› ፓርቲ መዋቢያ፣ ሌሎች ፓርቲዎችም አጫፋሪ መሆናቸው ይቀጥላል፡፡ በአንድ ፓርቲ የተዋጠው አገዛዝም የሙስናና የማን አለብኝነት ዋሻ አበረታችና አራቢ ሆኖ የማገልገሉ ችግር አይወገድም፡፡

ይኼንን ተገንዝበን፣ ከዚህ ችግር ወደ ተላቀቀ ለውጥ እንዴት መግባት እንደሚቻል ስናሰላስል ኢሕአዴግን በብልህ ትግል ማሯሯጥ ግድ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ያሁኑ ዴሞክራሲን አጠልቃለሁ፣ የፓርላማ አወካከልን አሻሽላለሁ ባይነቱና ሥራ አጥነትንና የበደል ክምችትን የማቅለል ደፋ ቀናው ሁሉ የመጣው ከትግል ግፊት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በውድመት የቀለመ የትንንቅ መንገድን መለወጥ (የትግል አቅምን የሚያጠነክር፣ ገዢውን ቡድን ወደ አዎንታዊ መደፋፈር የሚስብ፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የዴሞክራሲ ዝንባሌ እንዲፋፋ የሚያግዝ፣ በምርጫ የመሸነፍና ከሥልጣን ወርዶ የመወዳደርን አስፈሪነት የሚገፍ የትግል ዘዴ ላይ መሰማራት) ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ እውነትን የሚሻና የሕዝብ ድምፅ መሆን የተዋጣለት ጋዜጠኝነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ በመገናኛ መድረክነታቸው ይህንን ክብር የነገቡ ገና ባይኖሩንም፣ ጭልጭልታዎች አሉ፡፡ ከጊዜ ጊዜም አፍ የሚያስከፍቱ እንጎቻዎች ይነጎቱልናል፡፡ በዚህ በኩል የሪፖርተር ጋዜጣ፣ የሸገርና የዛሚ ሬድዮ መድረኮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ የመረጃ እጥረትና የክርን ፍርኃት ብቻ ስለሚገድቡ በአብዛኛው ሁኔታ የሚቀርቡልን ደፋር እንጎቻዎች እንደ እስክስታ ግጥሚያ ‹‹ያዝ/ያዢ! እንዲህ!›› ያሉ ትከሻ ለትከሻ እንደመነካካት እየቃጡ መለስ የሚሉ ወይም ጥቅልነት የሚያጠቃቸው ዓይነት ናቸው፡፡

በዛሚ ሬድዮ ውስጥ የምናገኘው ‹‹ቆይታ ከሚሚ ስብሃቱ ጋር›› የተሰኘ ዝግጅት ለኢሕአዴግ መንግሥት ወገናዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሌሎቹ መገናኛዎች ከሚያነጉቱልን የዘለዓለም ሰበከት አለው፡፡ ዜጎች/ባለጉዳዮች አለኝታዬ ብለው መፍትሔ ያጣ ብሶታቸውን የሚያሰሙበት መድረክ ነው፡፡ በሚደርሱት መረጃዎች መሠረት በደሎችንና ሕገወጥ ሥራዎችን ሲያጋልጥና ሹሞችን ሲያፋጥጥ አድምጠናል፡፡ ቢሮክራሲያዊ ጨለማንና መብት ረጋጭነትን እየታገለ የእንባ ጠባቂነትንም ተግባር ሲፈጽም አስተውለናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመልካም አስተዳደር ችግር በጥናት ላይ የተንተራሰ የቴሌቪዥን ውይይት ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ካደረጉ ጊዜ አንስቶ፣ ‹‹ሥልጣንን ለግል መጠቀሚያ የማዋል ችግር ውስጥ ገብተናል . . ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልገናል. . . ጥልቅ ተሃድሶ እያካሄድን ነው . . . ›› እስከተባለበት እስከ ዛሬ ድረስም በቅጥልጥል ስብሰባዎችና ሹም ሽሮች ረካሁ ሳይል ጥፋተኞች እስከ ከፍተኛ ቅርንጫፋቸው ድረስ ተገልጠው እንዲጠየቁ መወትወቱን እንደቀጠለ ነው፡፡

በተለይ በጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የቀረበው የቆይታ ዝግጅት እጅግ  ልዩ (የአድማጭ ምስጋና የጎረፈበት፣ ‹‹ለክብራችሁ ቆሜ ነው የማዳምጣችሁ›› ሁሉ የተባለለት) ነበር፡፡ በእስክስታ ግጥሚያ የትክኪያ ሄድ መለስ ብልኃት ተሃድሶው ገና እንዳልጠለቀ፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ዘንድ ፈርጦ ያልወጣ ነገር እንዳለ፣ ስለዝርፊያ መረብ ጉዳይም በመንግሥት እጅ መረጃ ስለመኖሩ፣ የሸሹና ያሸሹ ስለመኖራቸው ጨረፍረፍ ተደርጎልናል፡፡ በተጨማሪ ተሃድሶው ከዴሞክራሲው መጥለቅ ጋር በቅርብ መያያዙ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ  ውስጥ ስላሉ ችግሮችና ስለመቃኛቸው ሁሉ ተጠቋቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ‹‹ሥልጣን ለግል መጠቀሚያ ውሏል ከተባለ ይህንን ያደረጉ ይገለጡና ይጠየቁ›› በሚል ድፍንፍን ጥያቄ ዙሪያ ከመሽከርከር ፈቀቅ ማለት ያልቻለ ትግል ለጓዳ የመንግሥት ፍንቀላ ሌማት ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ትግሉ አቅጣጫውን እንዳይስት ለመከላከል የሚቻለው የሁሉም ነገር ቁልፍ በሆነው ዴሞክራሲን የማጥለቅ ጥያቄ ላይ ትኩረትን በማሰባሰብ ነው፡፡ ሙሰኞችና ዘራፊዎች መከናነቢያቸውና መሹለክለኪያቸው እየተቦዳደሰ የመንግሥት አውታራት መፅዳት የሚችሉት፣ ክትርና ድብስብስ ድርጅታዊ ህልውናዎች እየተነቃነቁ በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች ዘንድ ዴሞክራቶች ጎልብተው መውጣት የሚችሉት ዴሞክራሲው መጥለቅና መስፋት ከቻለ ብቻ ነው፡፡ የኢሕአዴግንና የተቃዋሚዎቹ ድርድር ትልቁ ፋዳም ለዴሞክራሲው መጥለቅ በር መሆን ነው፡፡ ለሕዝብ ልዕልና፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለሰላም የምንጨነቅ ሁሉ ይህ እንዲቃና ኢሕአዴጋዊ፣ ተቃዋሚ፣ ገለልተኛ፣ ቅብጥርጥሮስ እየተባባልን የጎሪጥ ከመተያየት ፈንታ ተደጋግፈን ዴሞክራሲን ማራመድ ኃላፊነታችን ነው፡፡ በጥር አምስቱ የዛሚ ሬድዮ ‹‹የቆይታ›› ዝግጅት ላይ የነበሩ የእንግዶችና የአድማጭ ተሳታፊዎች ጥንቅርም ይህንኑ ትግግዝ በአርዓያነት የሚወክሉ ነበሩ፡፡

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

በዚህ ጎዳና ውስጥ ከተጓዝን በነፃ መደራጀትን በየፈርጁ ማጎልበት፣ የሐሳብ ነፃነትንና የሰላማዊ ሠልፍ መብቶችን ከመተናነቂያነት ይልቅ የሚብሱ ጥያቄዎችን፣ ጠንቀኛ ጥፋቶችንና መፍትሔዎችን አጉልቶ ለማሳየት የመገልገል አርቆ አስተዋይነት ይመጣል፡፡ ከዚህ ሌላ የፓርቲዎች ተፎካካሪነት መዳበር፣ የምርጫ ውጤት ከሚያስገኘው መሸናነፍ በበለጠም ጤናማ የምርጫ ዘመቻን መለማመድ፣ እንዲሁም ከሸፍጥና ከኃይል ተግባር የፀዳ የምርጫ አስፈጻሚነትንና ታዛቢነትን ለማካሄድ መብቃት ዴሞክራሲን ሥር ማስያዝ መሆኑን አውቆ ማሳወቅና ወደ ተግባር መቀየር በራሱ ለዴሞክራሲ ድል ነው፡፡ ይህ ድል ዕውን መሆንና መፅናት የሚችለው ግን፣ በፓርቲዎችና በሕዝብ ውስጥ (በተለይም በወጣቱ ዘንድ) ኩርፊያን፣ ጥላቻን፣ መፈራራትንና ግትርነትን የማሸነፍ መሠረታዊ ድልን ተቆናጦ እስከ መጣ ድረስ ነው፡፡ አለዚያ ጥረታችን ሁሉ ፈሳሽን በእጅ ጭብጦ ለመያዝ ወይም ባልተሟሸ ምጣድ እንጀራ ለመጋገር እንደ መሞከር ድካም ማብዛት ይሆናል፡፡

ይኼን ሁሉ ስናወራ ውስጥ ለውስጥ የሚሹለከለኩ ነገር ሠሪዎችና አለቅላቂዎች እንደሚያወላክፉ አጥተነው አይደለም፡፡ ግን በሕዝብ የእርስ በርስ የግንኙነት ውስጥ የገባንና የተጠራቀመን መርዝ የሚነቅለው ይህ ትልቁ የእርቅ ሥራ መንግሥትን ደጅ የማያስጠናና አዋጅን የማያስጠብቅ፣ በራስ ቁርጠኝነት ብቻ ተፋፍሞ ለንቀትም ለእብሪትም የማይመች ትልቅ የኅብረት ጉልበትን የሚያቀዳጅ ሒደት ነው፡፡ ጥላቻንና መፈራራትን ከነዝባዝንኬያቸው መበጣጠስ በሌላ ገጽታው ሰንሰለት እየበጣጠሱ ነፃ መውጣት ነው፡፡ ሰንሰለትን ለመበጣጠስ መቻልም በራሱ ራስንና ኅብረተሰብን ለዴሞክራሲ ማሟሸት  ነው፡፡

የእርስ በርስ እርቅ ይህን ያህል ፈርጀ ብዙ ፍሬ የሚሰጠን በመሆኑ ከተግባባን፣ ባለፈው እንደታየው ሞትና እዬዬ፣ መቁሰልና አካል መጉደል ለነበረበት የቅዋሜ ትግል ያንን ያህል የእልህና የወኔ ነዳጅ ያመነጨ ማኅበራዊ አቅም ከአደጋ ይልቅ በረከት ያለበትን የእርቅ ማዕበል ለመፍጠር ወኔና እልህ እንዴት ሊቸግረው ይችላል!? መከራከሪያችንና የተስፋ ማዕዘናችን ይኸው ነው፡፡

ወጣቶቻችን በአመለካከት መለያየትን ከጠላትነት ጋር ከማምታታት ሲወጡ፣ የተሰነዘረ ሐሳብን “ሞላጫ ሐሳብ! እሱ ሰውዬ የሚለው ሁሌም አይጥመኝም! … ወዳጅ መስሎ ጠላት/የጭቃ እሾህ!…” እያሉ ከመግፋት ፈንታ፣ “እዚህ ላይ የተባለው አሳማኝ ነው/ትክክል ይመስላል… ይህ ግን የተሳሳተ ነው … በቂ ማስረጃና መከራከሪያ ባይኖረኝም እዚህ ላይ የተባለው አልተዋጠልኝም፣ ለማንኛውም ቀስ ብዬ በአዕምሮዬ ላጉላላውና/ላጥናውና…” እያሉ መነጋገር ሲጀምሩ፣ የሚያስማሟቸውን እያበራከቱም አንድ ላይ ሲተምሙ የምናይበትን ቀን እንናፍቃለን፡፡ ተቃዋሚዎችም እስከ 2012 ዓ.ም. ምርጫ በአገሪቱ የፖለቲካ አየር ንብረት ላይ አዎንታዊ ኩትኮታ የሚያመጣ መርሐ ግብር ነድፈው ከወዲሁ ሲንቀሳቀሱ ለማየት እንጓጓለን፡፡

ከፓርቲዎች የመሸናነፍ ውጤት ይበልጥ ሸፍጥና ጠብ የለሽ ነፃና ፍትሐዊ የውድድር ምኅዳርና የምርጫ አፈጻጸም በኢትዮጵያ መጀመሩ ዋናው የዴሞክራሲ ፋይዳ መሆኑ እንዲጨበጥና እንዲሳካ፣ ለማንኛውም ፓርቲ አጫፋሪ ያልሆኑ ነፃ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት እንዲፈጠሩ የሚታገል፣ ከዚሁ ጋር በሸፍጥ ያልጎደፈ ምርጫ የመከናወኑ ጉዳይ ለዴሞክራሲ ያለውን እርባና የየትኛውም ፓርቲ ደጋፊና ገለልተኛ ዜጎች ሁሉ እንዲያጤኑና ይህንኑ አመለካከት የተቆናጠጠ የምርጫ አስፈጻሚነትና ታዛቢነት እንዲፈጠር የሚታገል፣ ለተከባበረ የፖለቲካ ተፎካካሪነት የተግባር ምሳሌ የሆነ፣ እስካሁን ከነበረው የኢሕአዴግ የመንግሥት፣ የማኅበራዊ ኢኮኖሚና የልማት እንቅስቃሴ ልምድ ውስጥ መቀጠልና መጎልበት ያለባቸውን ጥንካሬዎች ይዞ ጉድለቶቹን የሚሞላና ችግሮቹን የሚያስወግድ ዝርዝር ፕሮግራም የቀመረ፣ መንግሥትን ለመምራት የሚያስችል የሕዝብ ድምፅ ቢያገኝ እንኳን ሥልጣን ማጋራትን በጨመረ የጋራ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ መርሐ ግብር ከኢሕአዴግ ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስቀድሞ ያወጀ፣ በምርጫ ሰዓትም የሕዝብ ድምፅን በተናጠል ከመቃረጥ ጠባብነት ወጥቶ ዕጩዎችን በኅብረት ለማቅረብ የተሰናዳ ጠንካራ የተቃዋሚዎች ኅብረት መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚከተሉት ነጥቦችም በጋራ መርሀ ግብር ተጋግዞ መሥራት እንደሚቻልና ይህንኑ የሚፈልጉ ሁነኛ ጉዳዮች እንዳሉን የሚጠቁሙ ይመስለኛል፡፡ ከዴሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብቶች በአግባቡ መረጋገጥ ጋር የመብቶቹ ህያውነት እንዲረዝም የሚያስችል፣ የተንከባካቢነት ኅብረተሰባዊ ንቃትን ማጎልመስና ይኸው ንቃት ባልተጓደለበት ሁኔታ መንግሥታዊ ዓምዶችን ከየትኛውም ፓርቲያዊ ወገናዊነት አላቆ የመላው ሕዝብ ንብረት ማድረግ፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል አስተዳደሮች ደረጃ ዜጎች በእኩልነት የሚስተናገዱበትን፣ በልዩ ልዩ ዕድሎች ውስጥ የመሳተፍ ጉዳይ በፖለቲካ፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በሥውር ጥቅም፣ ወዘተ ላይ በተመሠረተ መድሎ የማይቃኝበትን ባህል መገንባት፣ ዜጎች ከግለሰብ አድራጊ ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት አድራጊ ፈጣሪነት የሚጠበቁበት (የመንግሥት ሕግ አስከባሪነት፣ የመንግሥት ከሳሽነትና የዓቃቤ ሕግ ለሕግ ተከራካሪነት ወደ ዜጎች መብት ድፍጠጣ የማይንሸራተትበት) ሚዛኑን ያልሳተ አገዛዝ መገንባት፤ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግሥትን ሃይማኖታዊ አለመሆንንና በሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ አለመግባትን ወይም በእጅ አዙር ከመቆጣጠር መራቅን፣ ከዚያው እኩል የሃይማኖቶችን ከፖለቲካ አራማጅነትና መንግሥትን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከመቃኘት መራቅን ፅኑ መሠረት ማስያዝ፣ በኃይል የትግል መስክ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዲደርቁና አስተማማኝ የፖለቲካ ሰላም ሥር እንዲይዝ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በኦኮኖሚ ልማቱ ረገድም በአጠቃላይ የተመጋገበ፣ ጤናማነቱ (በንግድ ሚዛን፣ በብድር አወሳሰድ፣ ወዘተ) የተጠበቀ አረንጓዴ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ በመገንባት ትልም ውስጥ የሁሉንም አካባቢዎች እምቅ ሀብት አትብቶ ወደ ተመጣጠነ የኢኮኖሚ የጥበብና የሰው ልማት መቀየር፣ ከፖለቲካ ሰላም መፈጠር ጋር የመንግሥትን የሕዝብ ተቀባይነት በማሳካት በውጪ ካሉ የአገሪቱ ተወላጆች በኩል ሊገኝ የሚችለውን የውጪ ምንዛሪ፣ የጥበብ፣ የእውቀትና የሐሳብ አመንጪነት አቅም አስመንድጎና በአገር ውስጥ ካለው አቅም ጋር አላልሶ የግስጋሴ እመርታ ማምጣት፣ የውስጥ ሥራ ፈጠራና ሥራ መክፈትን በልዩ ልዩ ዘዴዎች ከማነቃቃት ጎን፣ አዋጪና አስፈላጊ በሆነበት ሥፍራና ጊዜ ኢኮኖሚው ላይ በወረርሽኝ ጉዳት የሚያደርሱ የገቢ ዕቃዎችን በታሪፍ መመከት፣

የውጭ ኢንቨስትመንትን ከአጠቃላዩ የልማት ትልም አኳያ ካለው ቀዳዳ ሞይነትና የጥበብ ሽግግር እርባናው ጋር አዛምዶ መመዘን፣ መሬት የሕዝብ ይዞታ በመሆኑ ላይ ሊኖር የሚችል የአቋም ልዩነትን አሳድሮ፣ መሬት የዝርፊያ መሻሚያ በማይሆንበት ሁኔታ ግልጽ አሠራር ይዞ፣ አስቀድሞ በታወቀ የመሬቶች የአገልግሎት ድልድል እንዲመራ ማድረግ፣ የመንግሥት የኢኮኖሚ ልማት ተሳትፎ ዓብይና መሠረት ጣይ በሆኑ ዒላማዎች ላይ አትኩሮ በዚሁ ሒደት ውስጥ የግሉ ዘርፍ በምሕንድስና፣ በቴክኖሎጂ አመንጪነትና በሥራ ተቋራጭነት ረገድ የአቅምና የታማኝነት ብቃት እንዲያጎለብት ማገዝ፡፡

 ከአዘጋጁ– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ፎቶ ጎልጉል

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
እነ አቶ መላኩ ፈንታ ነፃ በተባሉባቸው የሙስና ክሶች ላይ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠየቀ

  በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል በሦስት መዝገቦች ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ መላኩ ፈንታ፣ በመዝገብ ቁጥር 141352 ከቀረቡባቸው 93 ክሶች ውስጥ...

Close