በኦሮሚያ ክልል ከሶስት ሺህ አራት መቶ በላይ አመራሮች በህግ ሊጠየቁ ነው። ከወረዳን መዋቅር አራት ሺህ ስድስት መቶ፣ በቀበሌ ደረጃ ከአስራ ሶስት ሺህ አምስት መቶ በላይ  አመራሮች ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገለጸ። ኢዜአ የክልሉን ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ስዲሱ አረጋን ጠቅሶ እንደዘገበው ከኪራይ ስብሳቢነት፣ ከብልሹ አሰራርና፣ ሕዝቡን ያማረሩና ለቀሬታ የዳረጉ አመራሮችን የመለየት ስራ ተሰርቷል። እንዲሁም ” የስርዓቱ አደጋ የሆኑት ጠባብነት፣ አክራሪነትና ጎሰኝነት በአመለካከትና በተግባር መኖራቸውንም ተረጋግጧል” ከማእከላዊ ኮሚቴ የታገዱ ከፍተኛ አመራሮች አሉ ስማቸው ግን አልተጠቀሰም።

በክልሉ ሕዝባዊ አመጽ በተነሳበት ወቅት ” ኦህዴድ መዋቅሩ ፈርሷል። የበታች አመራሩ ከድቷል። የታች አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ ተናግቷል” የሚሉና የተለያዩ ዜናዎች ሲሰሙ ነበር። የኮማንድ ፖስት የተቋቋመበትና አገሪቱን በወታደራዊ  እዝ ስር ለማስተዳደር የተፈለገውም ለዚሁ እንደሆነ ሲጠቆም ነበር። ዜናው ይህንን እንደ ምክንያት ባያቀርብም ከሃላፊነታቸው የተነሱት የበታች አመራሮች ብዛት ይህንኑ ቀደም ሲል ሲሰጥ የነበረውን አስተያየት የሚያረጋግጥ እንደሆነ አስተያየት የሚሰጡ ይናገራሉ። ከሕዝባዊ አመጹ መነሳት በሁዋላ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦህዴድ አባላት መታገዳቸው፣ በቁትትር ስር መዋላቸውና ማጣራት እየተካሄደባቸው እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።

Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

የኢዜአን ሙሉ ዜናው የሚከተለው ነው።

ato-adisu-oromya-comunication-head

አዲስ አበባ የካቲት 8/2009 በኦሮሚያ ክልል በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በኪራይ ሰብሳቢነት የተጠረጠሩ ከ3 ሺህ 400 በላይ አመራሮችን በሕግ ለመጠየቅ ማስረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ ገለጸ። በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው ሕዝቡን ያማረሩና ለቅሬታ የዳረጉ ዋና ዋና ችግሮችን መለየት እንደቻለም ተነግሯል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በክልሉ የተካሄደውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥልቅ የተሃድሶ ጉዞ መጠናቀቅ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በጥልቅ ተሃድሶው የተነሱ ችግሮች ባለቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ በተለዩ አካላት ላይ ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ማስረጃዎች እየተሰባሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተወሰዱ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ሁለት አመራሮች ከስራ አስፈጻሚ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሸጋሸጉ የተወሰነ ሲሆን ሶስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መታገዳቸውን ተናግረዋል። ከክልል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር 4 ሺህ 660 አመራሮች ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን በቀበሌ ደረጃም ከ13 ሺህ 500 በላይ አመራሮች እንዲነሱ ተደርጓል።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

የአመራር አባላቱ የታገዱት በአቅም ማነስ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በስነ ምግባር ጉድለትና በሌሎች ምክንያቶች መሆኑንም ጠቅሰዋል። በሕግ አግባብ በተወሰዱ እርምጃዎችም ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ 946 አመራሮች በኪራይ ሰብሳቢነት ተጠርጥረው ማስረጃ እየተሰባሰበ መሆኑንና 260 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታውቀዋል።

በቀበሌ ደረጃ የተጠረጠሩ 2 ሺህ 470 የአመራር አባላትን ለሕግ ለማቅረብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ፣ አራት ተሽከርካሪዎች፣ 40 መኖሪያ ቤቶችና ከ244 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት በህግ እገዳ ተጥሎባቸው ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የክልሉ ሕዝብ ፍላጎትና አቅርቦት ባለመጣጣሙ ከፍተኛ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር። በመሆኑም የክልሉ መንግስት ይህንና ሌሎች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዘው ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ገብቷል።

በጥልቅ ተሃድሶው ከማዕከላዊ ኮሚቴ እስከ ቀበሌ ባለው እርከን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተካተው በድምሩ ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተሳትፎበታል ነው ያሉት። በመጨረሻም ከክልሉ 20 ዞኖችና 10 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 20 ሺህ ሰዎች የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞው ሂደት ላይ ተወያይተዋል።

Related stories   የትህነግ "ውሮ ወሸባዬ" - የመንግስት ሩጫ - የሃላኑ የኢትዮጵያን ቋንጃ የመበጠስ የእባብ አካሄድና ባንዳዎች!

ሕብረተሰቡ በተለይም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭና ተግባራት በሆኑት የመሬት አስተዳደር፣ የግዥና ኮንትራት አስተዳርና ገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ከፍተኛ ችግር መኖሩን አንስተዋል። የስርዓቱ አደጋ የሆኑት ጠባብነት፣ አክራሪነትና ጎሰኝነት በአመለካከትና በተግባር መኖራቸውንም ገልጸዋል። “በተሃድሶ ሂደቱ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ትክከለኛ መስመር መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል” ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

አመራሩ በበኩሉ ችግሮቹን ለማስወገድና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ቃል የገባበት ነው ብለዋል። በተለይም በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ፤ የመንግስት ሰራተኛውም በለውጥ መሳሪያዎች የተቃኘ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆኑበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ከክልሉ ካቢኔ ጀምሮ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ የአመራር ለውጥ መደረጉን ነው ያስታወቁት። “ህዝቡ ጥልቅ ተሃድሶው በሂደት ላይ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ አለበት” ያሉት ኃላፊው የክልሉ ሕዝብ ለተሃድሶው ስኬት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚያስመሰግነው መሆኑን አክለዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *