ስንቱን አፀድ አከሰምነው
(በውቀቱ ስዩም)

ያገራችን ቦለቲካ በሁለት ቃል ሲደመደም
ምኒልክ ይቅደም!
ምኒልክ ይውደም!
—-
መቸም ያዳም ልጅ መሆን ፣ የማይፈታ ጣጣ
ሁለመናው ሲዞርብን ፣የመኖር ሰበብ ስናጣ
ጉልበትና ስልጣን ኖሮን ንብረት መሬት ባንደለድል
እንዳባቶች ፣እንደናቶች ፣ዘምተን ታጥቀን ባንገድል
ለሱስ ያህል ያምረናል ጦር ፣ላመል ያህል ያምረናል ድል::
አልፎ ሂያጆች ሆነን ሳለ ፣ደማቅ ድንበር አስምረን
በመናኛ ድንኳን ዙርያ ፣ የኮረንቲ ቅፅር አጥረን
ያብሮ መኖር መላ ጠፍቶን ፣ያብሮ መሞት ዘዴ ፈጥረን
ከቤታችን ጠብ ቢጠፋ ፣ ከጎረቤት ተበድረን
በየሱስ ስም በማርያም ስም
በነ ሌኒን በማርክስም
ዛሬ ደሞ በምኒልክ
ባገኘነው ወዳጅ መጠን ፣ባፈራነው የጠላት ልክ
ዋጋችንን ስንተምነው
ስንቱን ቀትር ፣አጨለምነው
ስንቱን አፀድ ፣አወደምነው?!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *