“Our true nationality is mankind.”H.G.

አጤ ዮሐንስን በሚያዩበት አይን አጤ ሚኒሊክን ቢያዩ መግባባት ይመጣ ነበር

ግርማ ካሳ (ምላሽ ለ አብርሃ ደስታ) – “ሚኒሊካዊ አስተሳሰብ የአንድነትና የልማት አስተሳሰብ ነው” በሚል ርእስ ለጦመርኩት ወንድም አብርሃ ደስታ(Abraha Desta) የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶኛል። ለዉይይትና ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ተጨማሪ አስተያየቶችን መስጠት ፈለኩ።

” ባነሳኸው ሐሳብ ላይ ቅሬታ የለኝም” ሲል የጀመረው አብርሃ እንዲህ ይላል ፡

” እኔ “ምኒልካዊ አስተሳሰብ” ያልኩት ተፅፏል። ምኒልካዊ አስተሳሰብ ፀረ እኩልነት የሆነ እምነት ማለቴ ነው። እነሱ ሌሎችን እንደፈለጉ እየተሳደቡ የኛ ነው የሚሉትን ጨቋኝ ገዢ ሲተች ግን ይጮሃሉ። ግን ሁሉም ብሄርና ሀይማኖት እኩል ነው። መለስ ዜናዊ ካጠፋና ከተሰደበ ምኒልክ ሲያጠፋ ቢሰደብ ምን ችግር አለው። ትግራይና ኦሮሞ ብቻ ነው መሰደብ ያለበት? ምኒሊክ ሲሰደብ ለምን ትንጫጫላቹ ነው። ሁሉም ሰው እኩል አይደለም ወይ? ምኒልክ ለኔ ከመለስ በላይ አረመኔ ነው። የመተቸት መብቴ ሊከበርልኝ ይገባል።”

አጼ ሚኒሊክ ላይ ችግር ያላቸው ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ። አጼ ሚኒሊክን የመተቸት፣ “ይሄን ሰርተዋል” ብሎ የመውቀስ መብት አላቸው። አጼ ሚኒሊክ የሰሩት ጥሩ ሥራ እንዳለም ያጠፉት ጥፋት አለ። አብርሃም ሆነ ሌሎች እኔ አጼ ሚኒሊክን እንደማያቸው ይይዋቸው ብዬ ለመናገር አልችልም። ማንም ሺህ አመት አጼ ሚኒሊክን እየጠላ መኖር ይችላል። እኔ ምን አገባኝ ?

ሆኖም ግን ለአብርሃ ደስታም ሆነ ለሌሎች ምላሽ የምንሰጠው፣ ለምን “አጼ ሚኒሊክን አልወደዱም” ብለን ሳይሆን በሚጽፉት ጽሁፍ ያስቀመጧቸውን አንዳንድ መሰረት የሌላቸውን ነጥቦች ቻሌንጅ ለማድረግና ለማረም ነው።

ወንድም አብርሃ “ሚኒሊካዊ አስተሳሰብ” ሲል የጸረ-እኩልነት አስተሳሰብ ማለቱ እንደሆነ ነው የገለጸው። አንድ በጣም bother ያደረገኝ ነገር አለ። የአጼ ሚኒሊክ አገዛዝ ከነ አጼ ቴዎድሮስ፣ ከነአጼ ዮሐንስ በምን እንደሚለይ ቢገልጽልን ጥሩ ነበር። ካልተለየስ “ሚኒሊካዊ አስተሳሰብ” እንዳለው “ዮሐንሳዊ አስተሳሰብ” ፣” ቴዎድሮሳዊ አስተሳሰብ” … ለምን አላለም ? ይሄ አንዱ ጥያቄዬ ነው።

Related stories   የተላላኪው ጠበቃዎች

“የኢህአዴግን ስርዓት እየተቃወምኩ ብዙ ዓመታትን ወደኋላ ተመልሼ ሰውን እንደ ሰው የማያይ የነበረውን ዘውዳዊ አገዛዝ የማወድስበት ህሊና የለኝም። መለስን የመሳደብ መብት ያለው የሚመስለው ሰው ምኒልክን የመተቸት መብቱ ለምን ይከለክላል? … No Double Standard.” ብሎም እንደጻፈው ለምን Double Standard ፣ ለምን አጼ ሚኒሊክን ብቻ ?ለምን አጼ ዮሐንስም አይተቹም ? ደግሜ እላለሁ። ለምን Double Standard ? ? ?

ምን አልባት አጼ ዮሐንስን ከተቸው የትግራይ ልጆችን አሳዝናለሁ ብሎ አስቦ ከሆነ ሴንሲቲቭ የሆነው ፣ ታዲያ አጼ ሚኒሊክንን ከልባቸው ለሚወዱ ወገኖችስ ሴንሲቲቪቲ ለምን ሊኖር አልቻለም ?

እኔ በግሌ አጼ ዮሐንስ ሆነ አጼ ሚኒሊክ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ ራስ አሉላ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ንጉስ ሚካኤል፣ አርበኛ ቡራዩ…ነጻነታችንን አስጠብቀው ያቆዩልንን አባቶቻችንን፣ እናቶቻችንን ናቸው። ድካም ቢኖራቸውም ክብር ነው ያለኝ። እነርሱ ማክበር እንጂ መተቸት አይሆንልኝም። ለምን ካጠፉት ጥፋት ይልቅ ለአገር ያበረከቱት እጅግ፣ እጅግ በጣም የላቀ ነው ብዬ ስለማምን። ወዳጄ ተክሌ በቀለ የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ ም/ሊቀመንበር በጥሩ ሁኔታ አሳቀምጦትታል። ” እንሆ ዛሬ እዚህ ደርሰናል፡፡በናንተ ኣጥንትና ደም ኢትዮጵያ ሉኣላዊነቷ ተክብሮ የነጮቹ ኮቴ ካልደፈጠጣቸዉ፤ ማንነታቸዉ ካልተቃወሰባቸዉ ህዝቦች መሃል እኛ እንገኝበታለን፡፡አሁንም ዘላለማዊ ክብር ለናንተ!!!” ይላል። በጣም ትክክል !!!!!!

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ይሄን ስጽፍ አብርሃ ደስታ፣ አጼ ዮሐንስ ላይ ትችት እንዲያቀርብ ለመገፋፋት ሳይሆን፣ አጼ ዮሐንስን ባየበት አይኑ፣ አጼ ሚኒሊክን ቢያይ የኛን አስተሳሰብ ሊረዳ ይችል ነበር፣ አጼ ዮሐንስን በመዘነበት ሚዛን አጼ ሚኒሊክን ቢመዝን ከስሜት፣ ምን አልባትም ሕወሃት ከረጨው ፖለቲካ ተጽኖ ነጻ በሆነ መልኩ ትክክለኛ መረዳት ይኖረው ነበር ከሚል እንጅ።

አብርሃ ደስታ “ሚኒሊካዊ አስተሳሰብ” ሲል፣ ባጠቃላይ ዘዉዳዊ አገዛዝ ማለቱ ከሆነ ደግሞ “ሚኒሊካዊ አስተሳሰብ” ከማለት ዘዉዳዊ ስርአት ወይም ዘዉዳዊ አስተሳሰብ” ቢል የበለጠ ይመረጥ ነበር።

አብርሃ ደስታ ዘዉዳዊ አገዛዝ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ እንዳልሆነ ያጠዋል ብዬ አላስብም። በዘዉዳዊ አገዛዝ ፈላጭ ቆራጩ ዘዉዱ ነው። በእንግሊዝም፣ በፈንሳይም፣ በጃፓን…በሁሉም absolute monarchy በነበረባቸው አገሮች የዴሞክራሲና የመብት መከበር፣ እኩልነት አልነበረም። ስለዚህ “በአጼ ሚኒሊክ ጊዜ ዴሞክራሲ አልነበረም፣ እኩልነት አልነበረም” መባሉ ስህተት የለውም። ትክክል ነው። አነጋጋሪም አይደለም። ግን እግዜር ያሳያችሁ በዚያን ዘመን ፣ ከመቶ አመት በፊት ዴሞክራሲ አልነበረምና ብለን አሁን በዘመኑ በነበረው አስተሳሰብ አገርን ያቀኑትን መጥላትና መወረፍ ምን ይባላል ?

በእንግሊዞች የሚከበሩት እነ ሄንሪ ስምንተኛ፣ እኔ ኤሊሳቤት አንደኛ፣ በፈረንሳይ የሚከበሩት እነ ሉዊስ 14ኛ እና ናፖሌዎን በአገዛዛቸው እኩልነት አልነበረም። ብዙ ጥፋት አጥፍተዋል። ግን በአገራቸው የተከበሩ ናቸው። እኛ ግን የራሳችንን ሰዎች እናሳንሳለን። አሳዛኝ ነን!!!

አብርሃ ደስታ እየደጋገመ “ትግሬና ኦሮሞ” የሚለዉም ብዙ ሊገባኝ አልቻለም። ከጥቂት ቀናት በፊት “የትግራይና የኦሮሞ ሰዎች ስጋትም ግልፅ ሆኖልኛል” ሲል ጽፏል። አሁን ደግሞ “ትግራይና ኦሮሞ ብቻ ነው መሰደብ ያለበትን?” ይላል።

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

አንደኛ ወንድም አብርሃ፣ ይሄ ዝም ብለው ሶሻል ሜዲያ ላይ በብእር ስም የሚጽፉትና የሚሳደቡት ፣ ምን አልባት ሆን ብለው በወገን እና በወገን መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ሕወሃት ያሰማራቸው ሰላዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ አጥትቶ ይሆን? የኢትዮጵያ ብሄረተኛ አክቲቪስቶች እኮ ብዙ አሉ በገሃድ የሚጽፉ። በስም ጠቅሶ ይሄ አክቲቪስት፣ ይሄ ጦማሪ እንዲህ ብሎ “ኦሮሞን ፣ ትግሬን ሰደበ” ብሎ ለምን መረጃ አያቀርብም ? በጅምላ ትግሬና ኦሮሞ ተሰደበ ብሎ ደካማ የ victimization ፖለቲካን ከሚያራምድ ? ለምን አብረን ሕዝብን የሚሳደቡትን በሰለጠነ መልኩ በጋራ እንድንታገል አይሰራም ?ለምን የሕወሃት ካድሬዎችን ጦማር እያነበበ በብዙ አጀንዳዎች ዙሪያ ከሚቀራረቡት ታጋዮች ጋር ይላተማል ?

ለወዳጄ አብርሃ ይሄ ብዬ አቆማለሁ። ምን አልባት በአጼ ሚኒሊክ ላይ ጠንከር ያለ አላስፈላጊ አስተያየትት መስጠቱ politically motivated ከሆነ፣ የትግራይና የኦሮሞ ብሄረተኞችን ድጋፍ ለማግኘት ብሎ አስቦ ማለቴ ነው ፣ ትልቅ የፖለቲክ ስህተት ነው የሰራው። ለምን ቢባል በአጼ ሚኒሊክ ላይ ከጥቂት የትግራይ ብሄረተኞችና ሚሺነሪዎች አይምርውቸውን ከጠመዘዟቸው ከጥቂት የኦሮሞ ልሂቃን ዉጭ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአጼ ሚኒሊክ ፍቅር ነው ያለው። ክብር ነው ያለው። ለመይሳው ካሳና ለመተማው ጀግና ፣ ለራስ አሉላ፣ ለደጃች ባልቻ ….ፍቅርና ክብር እንዳለው።   አበቃዉ !

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0