Abraha Desta – ካልደፈረስ ኣይጠራም ይላሉ ኣበው! በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ማብዛት የሚፈይደው ነገር ባይኖርም ለዛሬ እንቅስቃሴያችን ደንቃራ ሆኖ ካስቸገረን ግን ልክ ልኩን መናገር ግድ ነው፡፡ የሃገራችን ፖለቲካ በዋናነት እየታመሰ ያለውና በቀላሉ እንዳንግባባ ካንሰር የሆነን የደቂቃነ ሚኒልክና ደቂቃነ መለስ ኣተካሮ ነው፡፡

ደቂቃነ ምኒልክ ሃፄ ሚኒልክን የሚነቅፍ ትንሽ ሀሳብ ካገኙ ትንሽ ትእግስት የላቸውም፡፡ ምኒልክን የተቸ እሰከ ዘሩ ይሰድቡታል፡፡ ደቂቃነ መለስም ምኒልክን የሚያወድስ ኣንድ መስመርም ካገኙ ይረባረባሉ፡፡ ደቂቃነ መለስ ሚኒልክ የኣማራ ወኪል ኣድርገው ያቀርቡታል፡፡ የምኒሊክ ስህተት የኣማራ ስህተት ነው እስከማለት ይዳዳቸዋል፡፡ ደቂቃነ ሚኒልክም መለስ በመለስነቱ ሳይሆን የትግራይ ወኪል ኣድርገው ይስሉና የትግራይ ህዝብ የመለስ ሃጥያት ተሸካሚ ያደርጉታል፡፡ መለስና ሚኒሊክ ግን ሁለቱም ህዝብ የማይፈልጋቸው ለራሳቸው ስልጣን ተንከሲስ ስራዎች ሲሰሩ የመሸባቸው እና የለየላቸው ኣምባገነኖች ነበሩ፡፡ ማንንም ህዝብ ኣይወክሉም፡፡ ኣምባገነን ህዝብ ኣይወክልምና፡፡

#መለስ ሲተች ትግራይ የተተቸ ስለሚመስለው የመለስ ጉድፍ ለመደበቅ የሚሯሯጥ ደቂቀ መለስ ኣለ፡፡ ሚኒልክ ሲተች ኣማራ ተተቸ፤ ኣማራ ተዋረደ ብሎ የኢትዮጵያ ማህፀን የሆነውን ጀግናው የትግራይ ህዝብ ባንዳ እያለ ህዝብን በጅምላ ይሳደባል፡፡ ደቂቃነ መለስ መለስ ዎርልድ ክላስ ማይንድ ነው ኣንተ ለመተቸት ሞራል የለህም እያለ ጆሮህ ላይ ይጮሃል፡፡ ደቂቃነ ምኒልክም ምኒሊክ የመጀመርያው ባንክ ባይከፍት፤ ባቡር ባያሰራ፤ የመጀመርያው ሆቴል ባይከፍት፤… ወዘተ እያሉ ነጋ ጠባ ያደነቁሩናል፡፡ እኔ የሚገርመኝ መለስ ወርልድ ክላስ ማይንድ ከሆነ የታለ የመለስ የተዋጣለት ቲኦሪ? የመለስ ጭንቅላት ለኢትዮጵያ ምን ጠቀመ? የመለስ ኣዋቂነት ፀረ ዴሞክራሲ ሆኖ ኣልተገኘም? ኢትዮጵያ በመለስ ኣመራር ኣይደለም እንዴ የዓለም ድሃ ሆና ዕየቀጠለች ያለችው? መለስ ኣይደለም እነ ማኦ ዘዱንግ በ30 ዓመት ቻይና ሲቀይሩና የዓልም ልዕለ ሓያል ለመሆን የምትታትር ሀገር መስርተውም እንኳ ዎርልድ ክላስ ማይንድ ኣልተባሉም፡፡ የመለስ ሚና ከቃላት የዘለለ በ25 ዓመት ውስጥ እንደነ ቻይና ይቅርና ከልመና መቼ ኣወጣን? ይሄ ጥሬ ሃቅ ነው ዋጠው፡፡

#ምኒልክ ሁሉም ነገር ባይጀምርልህ ኖሮ ይሄኔ ጠፍተ ነበር እያለ የትምክህት ልጋጉን የሚረጭብንስ የተቀረው የኣፍሪካ ኅዝብ በልማት ጥሎን የሄደው ምኒሊክ ስለ ጀመረላቸው ነው? ሚኒልክ ነው የኬኔያ መሰረተ ልማት ጣይ? ሚኒልክ ነው የደቡብ ኣፍሪካ፤ የናይጀርያና የግብፅ ኢኮኖሚ ፈር ያስያዘው? ሚኒልክ ባይኖር ባሉበት ይቆሙ ነበር? እኛም ምኒልክ ባይኖር ምንም ትምህርትቤትም ባንክም ኣንከፍትም ነበር? ወይስ ትምክህት ኣመልህ ስለሆነ ነው በየመድረኩ የምታደነቁረን? የውጭ ባለሙያዎች ጠርተህ ባቡር ማስጀመር፤ ቧንቧ ማስከፈት፤ ባንክ መክፈት ተኣምር ነው? ሌላ አገር ላይ የተፈጠረ ኮፒ ኣድርገህ ማስሰራት እንደዚህ ካስጮሀህ ምኒሊክ ለመጀመርያ ጊዜ የፈለሰፋቸው ኣዲስ ፈጠራዎች ቢሆኑ ኖሮ እኮ በደቂቃነ ሚኒልክ ጥሩንባ ነፊነት መኖር ኣንችልም ነበር ማለት ነው፡፡

ደቂቃነ መለስ መለስን የትግራይ ህዝብ ወኪል፤ ደቂቃነ ምኒልክ ደግሞ ሚኒልክን የኣማራ ህዝብ ወኪል ኣድርጋቹ የምታቀርቡት በምን ሂሳብ ነው? እኔ ትግራዋይ-ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በናንተ ኣስተሳሰብ መለስ ትግራዋይ ስለሆነ መለስን መቃወም የለብኝም ማለት ነው፡፡ ኣንድ ኣማራ ወንድሜ ኣማራ ስለሆነ ምኒልክን መቃወም የለበትም ማለት ነው፡፡ እኔ መለስን የምቃወመው በትግራዋይነቱ ሳይሆን የድርጅቱ ፖለቲካዊ እርምጃ ኣማባገነናዊና ኣገር በታኝ ስለሆነ እንዲሁም የሰማዕታት ኣደራ ክዶ የቤተሰብ ፓርቲ ላያችን ላይ ስለጫነብን ነው እንጂ ብሄሩን እያሰብኩ ኣይደለም፡፡ የደቂቃነ ምኒልክ ልጆች መለስን በጨፍጫፊነቱና በፀረ ዴሞክራሲያዊነቱ የምታምን ከሆነ ሚኒልክ ጨፍጫፊና የሰው ልጅ እንደ እቃ ይሸጥ ይለውጥ እንደነበረ መቀበል እንዴት ያቅትሃል? ችግሩ ይገባኛል፡፡ የመለስ ተከታዮች የመለስን ችግር የማይቀበሉት የትግራይ ወኪል ኣድርገው ሰለሚነሱና የሚኒልክ ተከታዮችም የምኒልክ ጉድፍ ሲወጣ ኣማራ ተዋረደ ብለው ስለሚያስቡና ሃሳዊና ኣስመሳይ የኣንድነት ጠበቃነት ለማሳየት ነው፡፡

ኣካፋውን ኣካፋ ማለት የማትችል ከሆነ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ካንሰር ተለክፈሃል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ! …ኢትዮጵያ! እያልክ የምትጮሆውም ክልብህ ለሁሉም እኩል ኣስበ ፤ አንተም ከማንም በላይ ኣለመሆንህ ከቃላት በዘለለ የምር ተቀብለህ ሳይሆን ያንተ ብሄር የበላይነት ያለበት ኢትዮጵያውነት እንዲኖር ስለምትፈልግ ነው፡፡ የዚህ ኋላ ቀር ሃሳብ ፈላስፎችና ኣራማጆች ደቂቃነ መለስ፤ ደቂቃነ ምኒልክ፤ ቤተ ኣማራና ኣግኣዝያን ናቸው፡፡ ትግላችን የነዚህን ሰይጣናዊና ኣገር ኣፍራሽ ፖለቲካ ከምክንታዊና አገር ወዳድ ፖለቲከኞች ጋር አገራዊ ፓርቲ ኣቋቁመን እናከሽፈዋለን፡፡
#ግልባጭ
ለደቂቃነ ምኒልክ – ለደቂቃነ መለስ በያላቹበትA!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *