የሚድሮክ ግሩፕ ባለቤት ሼኸ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በስማቸው የተመዘገበ የንግድ ድርጅት እንደሌለ በአሜሪካን ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ግርማ ብሩ አስታወቁ። ግርማ ብሩ ” በጣም፣ በጣም ጥቂት” ሲሉ የጠሯቸው ዳያስፖራዎች ካልሆኑ በቀር የተቀሩት አገር ወዳድ መሆናቸውንና በዚህም እንደሚደመቁ ተናግረዋል።
አቶ ግርማ ይህንን የተናገሩት ከኢትዮ ቲዩብ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ባደረጉት ቃለምልልስ ነው። ጠያቂው ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃብታቸው በሚያስገርም ፍጥነት እያጨመረ ያለውን ሼኽ መሐመድን አስመልክቶ ይገኝበታል። ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአክሲዮን የያዙትን ድርሻቸውን እንዲያስረከቡ ቀነ ገደብ ተቆርጦ የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ግርማ ጉዳዩን ከፋይናንስና ከባንኮች አዋጅን ጋር ነበር በቀጥታ ያያዙት። በዚሁ አዋጅ መሰረት በባንኮችና ኢንሹራንሶች ውስጥ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች እንዲስተናገዱ ህጉ አይፈቅድም አሉ።

ጠያቂው አከል አድርጎ ” ሼኽ መሐመድስ” ሲል በደፈናው ሳያበራራና በቂ መከራከሪያ ሳይዝ ለሰነዘረው ጥያቄ ” “ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በስማቸው የተመዘገበ የንግድ ድርጀት የላቸውም” ሲሉ አቶ ግርማ መልስ ሰጥተዋል። ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በፋይናንሱ ዘርፍ ውስጥ እንዳሻቸው የሚንቀሳቀሱ፣ የራሳቸው ባንክና ኢንሹራንስ ያላቸው መሆኑን እሳቸውም ቢሆን እንደማይከዱ፣ በቤተሰቦቻቸው ስም የተከፈቱ ቢሆኑም በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያላቸውን ሚናና የራሳቸው የፋይናንስ ተቋም እያላቸው ከመንግስት ባንኮች በስፋት እንደሚበደሩ አንስቶ ያልጠየቀው ጠያቂ ከአቶ ግርማ ሰፊ ማብራሪያ እንዳይቀርብ ምክንያት ሆኗል።
ሌላው አቶ ግርማ ያነሱት አነጋጋሪ የሆነው ” ጥቂት” ሲሉ የጠሩት፣ ዳግም ጠያቂው ፈገግ ብሎ ” ጥቂት ማለት በኢህአዴግ ስንት…” ሲላቸው፣ አቶ ግርማ መልሰው ” ጥቂት ሳይሆን በጣም ጥቂት ” ሲሉ ደግመው ደጋገመው እሳቸውም በፈገግታ መልስ የሰጡበት የዳያስፖራው ጉዳይ ነው። የስደት ፖለቲካ ስኬታማ እንደማይሆን በማውሳት መልሳቸውን ያሰፉት አቶ ግርማ፣ ህገ መንግስቱን አክበረው ወደ ንግግር ቢቀርቡ እንደሚሻል፣ ይህ አግባብ ሁል ጊዜም ቢሆን ክፍት እንደሆነ ጠቁመዋል።
” እንደ ኢትዮያ ዲያስፖራ አገሩን የሚወድ የለም። አንዳንዴም የሚይስደስተው ዲያስፖራው የሚሰራው ጥፋት አገሩን ስለሚወድ ነው” ሲሉ የተደመጡት አቶ ግርማ ” ዲያስፖራው አገሩን በትምህርትና በኢንቨስትመንት መርዳይ ይፈልጋል፣ እኛ ግን በሚፈለገው መጠን አልደረስንለትም” በማለት የዲያስፖራው ወዳጅ ሆነው መልስ ሰጥተዋል።
ይህንን አባባል የሰሙ በተለያዩ መድረኮች ክፉኛ ትችት የሰነዘሩ ሲሆን ” አይን ያወጣ ውሽት ” ያሉም አሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ” የህልውና ጉዳይ” ሲሉ አሞካሽተው መልስ የሰጡት አቶ ግርማ “ለመሆኑ ኦህዴድ አለ?” ለተባሉት ” አለ” ሲሉ በፈገግታ መልሰዋል። በአስር ሺህ የሚቆጠር የበታችና የመካከለኛ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያገደውና ያሰናበተው ኦህዴድ ” አለ” ሲባል እንዴትና በምን መመዘኛ እንደሆነ ግን አላብራሩም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *