“….የማሕበራዊ መሰረቶቹን ጥቅም ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ፕሮግራም ቀርፆ የሚታገል ድርጅት የሚፈጽመው ስህተት መሰረታዊ ፕሮግራሙን የሚፃረር መሆን የለበትም። ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን ክህደት መሆኑን ታላቅ ጥፋት ተደርጎ ይወሰዳል። ድርጅቱ ወደዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መስተካከል ካልተቻለ የሰልፍ ለውጥ ይከተላል። እንደዚህ አይነት ጥፋት ወደ መስራት ከተገባ ደግሞ ተሃድሶ አያድነውም፣ ጥያቄውም የተሃድሶ ጉዳይ አይሆንም። አብዮታዊ ድርጅቶች ስትሆን በሚመልከት መሠረታዊና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ስህተት አለመስራት፣ መሰረታዊ ያልሆኑ ስህተቶች ሲፈጸሙም ፈጥኖ ማረም፣ አንዴ የተፈጸመና የታረመ ስህተት መልሶ የማይደገምበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ሦስት መርሆችን ይከተላሉ” 

“በየተቋሙ በሚመደቡ ካድሬዎች ዘበኝነት የሚረጋገጥ ተሃድሶ የለም”

ኢሕአዴግ መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለንባብ ባበቃው አዲስ ራዕይ መጽሔት በጠባብነት እና በትምክህት የፈረጃቸው ኃይሎች ውግንናቸው እና ሰልፋቸው ተፈጥሮያዊ ይዘቱን ሳይለቅ አጀንዳ በመቀያየር እየፈተኑት መሆኑን አስነብቧል።

ድርጅቱ በ1993 ዓ.ም. እና በ2008 ዓ.ም ያደረጋቸውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞ አጀንዳዎችን ከፋፍሎ አቅርቧል። የትምክህት እና የጠባብነት ኃይሎች በመጀመሪያዊ ተሃድሶ ለመታገያ ያነሷቸው ሃሳቦች፣ “በፌደራል የመንግስት የመሰረተ ልማት ስርጭት፣ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጎማ፣ በፌደራል ምክር ቤቶችና የካቢኔ አመራር ስምሪት እንዲሁም የቢሮክራሲው ተዋፅዖ ዙሪያ ብዥታ በመፍጠር ብሔር ብሔረሰቦች እራሳቸው የመሰረቱት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንዲጠራጠሩ ማድረግ ብሎም ስርዓቱን ማፍረስ ዋነኛው አለማቸው ነበር” ብሏል።

አሁን በተፈጠረው ቀውስ ውስጥ ይዘውት ብቅ ያሉት አጀንዳዎች ሲል ድርጅቱ የዘረዘራቸው፣ “ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍለ፣ የመከላከያ እና የፀጥታ ሃይላችን ብሔራዊ ተዋፅዖ” እንዲሁም በወሰን ማካለል የሚታዩ ናቸው። ያም ሆኖ አሁንም አላማቸው በፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ መፍጠር መሆኑ ላይ ለውጥ የላቸውም” ሲል አቋሙን አንፃባርቋል።

ድርጅቱ በጥልቅ መታደስ ካልቻልኩ ይደርስብኛል ሲል ስጋቱን በሰነዱ በዚህ መልክ አስቀምጧል፤ “የአንድ ድርጅት ብቃት የሚገለጸው ስህተት ባለመስራቱ ሳይሆን ምንም አይነት ሰህተት ፈጸመ የሚለውን ስህተቱን ያረመበት አግባብ ነው። የማሕበራዊ መሰረቶቹን ጥቅም ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ፕሮግራም ቀርፆ የሚታገል ድርጅት የሚፈጽመው ስህተት መሰረታዊ ፕሮግራሙን የሚፃረር መሆን የለበትም። ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን ክህደት መሆኑን ታላቅ ጥፋት ተደርጎ ይወሰዳል። ድርጅቱ ወደዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መስተካከል ካልተቻለ የሰልፍ ለውጥ ይከተላል። እንደዚህ አይነት ጥፋት ወደ መስራት ከተገባ ደግሞ ተሃድሶ አያድነውም፣ ጥያቄውም የተሃድሶ ጉዳይ አይሆንም። አብዮታዊ ድርጅቶች ስትሆን በሚመልከት መሠረታዊና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ስህተት አለመስራት፣ መሰረታዊ ያልሆኑ ስህተቶች ሲፈጸሙም ፈጥኖ ማረም፣ አንዴ የተፈጸመና የታረመ ስህተት መልሶ የማይደገምበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ሦስት መርሆችን ይከተላሉ” ብሏል።

የድርጅቱ ሰነድ ግን “ድርጅቱ ወደዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መስተካከል ካልተቻለ የሰልፍ ለውጥ ይከተላል።” ስላለው ነገር አላብራራም። አዲሱ ሰልፍ ከፓርቲው ውስጥ የሚወለድ ወይም ሌላ ሶስተኛ ተቀናቃኝ ኃይል የሚፈጥረው ሰልፉ ይሁን ወይም አይሁን ድርጅቱ ያለው ነገር የለም። አልያም ፓርቲው ለሁለት የመሰንጠቅ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል የሚል መላምትም አላስቀመጠም።

ድርጅቱ በአዲስ ራዕይ ካስነበበው ፍሬ ነገሮች መካከል በዚህ አምድ “የተሃድሶው አቅጣጫ ተስቷል” እየተባለ በድርጅቱም ውስጥ ከድርጅቱም ውጪ ስለሚናፈሱት ጉዳዮች ያነሳውን አቅርበነዋል። በተለይ በአንድም በሌላ ጉዳይ ትኩረት ውስጥ የገቡ የገዢው ፓርቲ ነባር አመራሮች ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ እንዴት በስልጣናቸው ሊቀጥሉ ቻሉ? በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ተጠያቂው ማንነው? ምሁራንን ወደ ኃላፊነት የመጡት በተወሰኑ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ፍላጎት ነው? መነሻ አስተሳሰቡስ ምንድን ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ድርጅቱ ከዚህ በታች ባስቀመጣቸው መከራከሪያዎች ይሞግታል። አንባቢያን የራሳችሁን ግንዛቤ እና መረዳት ከነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ አንፃር በመውሰድ መገምገም ትችላላችሁ።

Image result for eprdf conference

ተሃድሶው አቅጣጫውን ስቷል

በተጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ ላይ ከሚደመጡት የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ሌላው ከወዲሁ አቅጣጫውን እየሳተ ስለሆነ የሚፈይደው ነገር የለም የሚለው ነው። ይህ በከፊል የተለወጠ ነገር የለም ከሚለው ጋር የተያያዘ ሲሆን ሌሎች መገለጫዎችም አሉት። በዚህ ረገድ የሚነሱት ሃሳቦች በዋኛነት በቅርቡ በፌዴራልና በክልል መንግስታት ከተሰጠው የአስፈፃሚ አካላት ሹመት ጋር የተያያዘ ነው። ሹመቱን አስመልክቶ ከተሾሙት ግለሰቦች ብሄራዊና ፆታዊ ተዋፅኦ እንዲሁም ብቃት ጋር በተያያዘ የሚነሳው ተናጠል ትችት በየትኛውም ወቅት ሊነሳ እንደሚችል ጉዳይ የሚወሰድ በመሆኑ እዚህ ላይ ማተኮር አይገባንም። ነገር ግን ተሃድሶው አቅጣጫ ስቷል በሚል የሚነሱ ሶስት የተሳሳቱ ሃሳቦች ላይ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ ይሆናል።

የመጀመሪያው ባለፉት ዓመታት በፌዴራልም ሆነ በክልሎች በከፍተኛ አመራር ኃላፊነት ደረጃ የነበሩ ሰዎች በመልሶ መደራጀቱ በስልጣቸው ላይ መቀጠል አልነበረባቸውም የሚለው አመለካከት አንዱ ነው። ይህ አመለካከት ተሃድሶ ከተባለ ለውጥ መኖር አለበት። በኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ደግሞ ለውጥ የለም የሚል፣ ተሃድሶው ለውጡን ከግለሰቦች ጋር አስተሳስሮ የሚመለከት በመሆኑ የተሳሳተ ነው። በመሠረቱ ተሃድሶው እንደ ድርጅትና እንደ መንግስት ያጋጠሙትን ድክመቶች በማስወገድ አገራዊና ክልላዊ ለውጥ ለማምጣት እንጂ ግለሰቦችን መቀያየር አይደለም ዋናው አላማው። በጉልቻ መቀያየር የሚጣፍጥ ወጥ የለምና። የተለወጡ ሰዎች የተለወጠ ሁኔታ ውጤቶች በመሆናቸው ድርጅቱን እንደድርጅት ማደስና መለወጥ ከተቻለ ችግር በነበረበት ሁኔታ ሲመሩ የነበሩ ሰዎችም ከተለወጠው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ለውጠው ልምዳቸውንና አቅማቸውን በመጠቀም ድርጅቱን በለውጡ ጎዳና መምራት የማይችሉበት አምክንዮ የለም። በሌላም በኩል ደግሞ ደርጅቱ ከስህተቱ እንደሚታረመው፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አባላትም ሂስና ግለሂስ አድርገው ታርመው እንደሚቀጥሉት ሁሉ በከፍተኛ አመራር ኃላፊነትም ላይ የነበሩ ሰዎች በሰሩት ስህተት ላይ ሂስና ግለሂስ አካሂደው ታርመው በአመራር ኃላፊነታቸው የማይቀጥሉበት ምክንያት አይኖርም፣ ይህንን የሚከለክል የድርጅት መርህም የለም።

በመሆኑም በከፍተኛ የአመራር ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች የሚቀየሩትና መቀየርም ያለባቸው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብና በመንግስት ህግ መሰረት ከኃላፊነት እንዲነሱ የሚያደርግ ሁኔታ ሲኖር ነው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት ባገኘ የግል የመልቀቂያ ጥያቄና ለቦታው የተሻለ እጩ ሲገኝ እንዲሁም በኃላፊነት የማያስቀጥል ጥፋት መፈፀሙ ሲረጋገጥ የሚሉትን ያካትታል። ከዚህ ውጭ ግን እንደ ድርጅት የነበረውን ስህተትና ጉድለት ስለሚጋራ ወይም የተሟላ ግለሂስ ስላልወሰደ ወይም ደግሞ ብዙ ሂስ ስለቀረበበትና በአግባቡ ስላልተቀበለ. . . በመሳሰሉ መመዘኛዎች በየትኛውም አካል ላይ ያለን አመራር ከኃላፊነት ማውረድ ገንቢ አይደለም። መሰረታዊ የሆኑትን የአመራር ብቃት መለኪያዎች የሚያሟላና በድርጅቱ መተዳደሪያና በመንግስት መመሪያ ከኃላፊነት የሚያስነሱ ተብለው የተቀመጡት የማይመለከቱት እስከሆነ ድረስ ድክመቶቹን በሂደት እንዲያሻሽል ጊዜ መስጠትና በኃላፊነቱ እንዲቀጥል ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል። በፌዴራልና በክልል በተካሄደው መልሶ ማደራጀት የተከናወነው ሹመት በዚህ አግባብ መገምገም ይኖርበታል። በነበራቸው ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የተደረጉት በሙሉ ባለፉት የአመራር ዘመናቸው እንደ ድርጅት በተገመገሙት ድክመቶች ላይ የየራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። ሁሉም ግን ተመሳሳይና እኩል ስህተት ፈፅመዋል ማለት የሚቻል አይሆንም። እንደየስህተታቸው መጠንም የወሰዱት ሂስና ግለሂስ የተለያየ እንደሚሆን ይታመናል። በነበራቸው ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው ግን ድርጅቱን መንታ መንገድ ላይ እንዲደርስ ያበቃው የአመራር ችግር አካል እንደነበሩት ሁሉ ድርጅቱ በጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ የመፍትሄው አካል ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ብቃት ስላላቸው እንደሆነ መግባባት ያስፈልጋል።

በመልሶ መደራጀቱ በተደረገው ሹመት ላይ የሚነሳውና ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሁለተኛው የተዛባ አመለካከት ደግሞ ተጠያቂነት የሚመለከተው ይሆናል። በጥልቀት ወደመታደስ ንቅናቄ እንድንገባ ያስቻለን ግምገማ ላይ በግልጽ እንደቀረበው ላጋጠመን ችግር ተጠያቂው አመራሩ፣ በዋነኛነትም ከፍተኛ አመራሩ ነው። የአመራሩ ተጠያቂነት ሲባል እንደአካልና በግለሰብ ደረጃ ያለው ተለይቶ መታየት ይኖርበታል። የጋራና የግል ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በሚመለከትም ድርጅታችን ግልፅ መርህ አለው። ይህ የሚታወቅ ቢሆንም ተጠያቂነትን በሚመለከት ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች ይነሳሉ። የመጀመሪያው የጋራ ኃላፊነት በሆነ ተግባርና ስልጣን ላይ ግለሰብ ተነጥሎ መጠየቅ አለበት የሚለው ነው። በድርጅታችን መርህ መሰረት ለአንድ አካል የተሰጠ ስልጣንና ተግባር የጋራ ኃላፊነት ሲሆን የአካሉን ኃላፊነት ለአንድ ግለሰብ አሳልፎ መስጠት አይቻልም። አንድን ተግባር እንዲፈፅም ተልዕኮ የተሰጠው የአካሉ አባል ስህተት ፈፅሞ ቢገኝ እንኳ የአካሉ ኃላፊነት ስለሆነ አካሉ ተጠያቂ ነው። ከአካሉ የኃላፊነት ክልል ውጭ በመሄድ በግሉ ስህተት የፈፀመ ወይም ደግሞ በግል በተሰጠው ኃላፊነት ክልል የተፈፀመ ስህተት ሲኖር ግን ግለሰቡ ተጠያቂ ይሆናል። ከዚህ የድርጅታችን መርህ ያፈነገጠና ከአመራሩ የተወሰነ ግለሰብን ለይቶ ተጠያቂ የሚያደርግ አመለካከት ሊስተካከል የሚገባው ይሆናል።

ተጠያቂነትን የሚመለከተው ሌላው የተሳሳተ አመለካከት ደግሞ ከቅጣት ጋር ተያይዞ የሚቀርበው ነው። የኢህአዴግና የየብሔራዊ ድርጅቶቹ ስራአስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ባካሄዱዋቸው ግምገማዎች በነበሩ ድክመቶችና በተፈፀሙ ስህተቶች ላይ እንደአካል ግለሂስ ወስደዋል። ለተፈጠረው ችግርም እንደአካል ተጠያቂ መሆናቸውን ተቀብለዋል። በግል በነበራቸው ኃላፊነትም ግለሂስ የወሰዱና ሂስም የተደረጉ እንዲሁም ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን ተጠያቂነትን ከኃላፊነት በማውረድና መሰል ቅጣት ክልል ብቻ የሚመለከት የተሳሳተ አስተሳሰብ ይታያል። በድርጅታችን መተዳደሪያ ደንብ ለደረሰ ጥፋት የሚያሰጡ የተለያዩ የቅጣት አይነቶች – ከቀላል ማስጠንቀቂያ እስከ ማባረር አሉ። ስለሆነም ተጠያቂነትን አምኖ መቀበልና ራስን መውቀስ ለመታረምም ዝግጁነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በቀጣይ ኃላፊነቱን በትክክል እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት በተሰራው ስህተት ተጠያቂ የማድረግ እርምጃዎች እንደሆኑ መረዳት ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ በጥሞና ሊስተዋል የሚገባው ሌላ ጉዳይ ቢኖር ገና ተሃድሶው እየተጀመረ ባለበት ሁኔታ የታየው የከፍተኛ አመራሩ ከኃላፊነት መነሳትና ከተጠያቂነት አኳያ የመጨረሻ ነው ማለት እንዳልሆነ ነው። አሁን በተካሄደው ሂስና ግለሂስ እንደአካልም ሆነ እንደግለሰብ ብዙ ድክመቶች ተነስተዋል ማለት ይቻላል። ይሁንናም ያልተወሰዱ ግለሂሶችና ከቀረቡ ሂሶችም ተሸፋፍነው ያለፉ ወይም ደግሞ በቀጣይ የሚቀርቡ አይኖሩም ተብሎ አልተደመደመም። ንቅናቄው ወደ አባላትና ወደ ፐብሊክ ሰርቪሱ እንዲሁም ወደ ህዝቡ በገባ መጠን አዳዲስ ጉዳዮች ሊነሱና የተለወጠ ርምጃ ሊወሰድ የሚችልበት ሁኔታ ዝግ አይደለም። በበላይ አካላት የተካሄደው ሂስና ግለሂስ ወደ ታች በወረደ መጠን ከወዲሁ የታየውም ይህንን ያመለክታል። አሁን ገና ሁሉም ወደ ንቅናቄው ሜዳ እየወረደ ነው። በንቅናቄው ፈጥኖ የሚሮጠውና የሚያዘግመው ወይም ደግሞ የማይነቃነቀው በግልጽ ተለይቶ የሚታወቀው ወደፊት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ያኔ የሮጠው አዝጋሚውንም የቆመውንም እያለፈ መድረስ የሚገባው ቦታ ላይ ይደርሳል፤ የሚያዘግመው ደግሞ ማዝገም እስከሚፈቀድበት ደረጃ ድረስ እንዲያዘግም፤ የማይነቃነቀው ደግሞ ቦታ እንዲለቅ ይደረጋል።

ከሹመቱ ጋር በተያያዘ ተሃድሶው አቅጣጫ ስቷል በሚል የሚነሳው ሶስተኛው የተሳሳተ አስተሳሰብ ደግሞ የምሁራን ወደ ኃላፊነት መምጣትን የሚመለከተው ነው። በዚህ ዙሪያ የሚነሱት በድርጅቱ የአመራር ደረጃ ምደባ ከፍተኛ አመራር ያልሆኑ ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት መመደብ የለባቸውም፣ የድርጅት አባላት ያልሆኑ የመንግስት ኃላፊነቱን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ አይመሩትም ችግራችን የምሁራን በመንግስት ኃላፊነት ያለመመደብ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው። ምሁራንን ወደ አመራር ማምጣት መፍትሄ አይሆንም. . . የመሳሰሉ ናቸው። እነዚህ ሃሳቦች በአብዛኛው በድርጅት አባላት የሚነሱ ሲሆን በተወሰነ ደረጃም በፐብሊክ ሰርቪሱና በህዝቡም የሚነሱበት ሁኔታ አለ። የሃሳቦቹ ዋነኛ መነሻም እየተለመደ የመጣው የመንግስት ሹመት አሰጣጥ እንደሆነ ግልፅ ነው። ይሁንናም ከተሃድሶ ተልእኮዎች አንዱ ደግሞ በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ያሉ ድክመቶችን ማስተካከል፣ አዳዲስ አስተሳሰቦችንና ተግባራትንም ማስተዋወቅ ስለሆነ ይህ ያልተለመደ የሚመስል አሰራር ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።

በመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ መመደብ/ መሾም ያለባቸው የድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው የሚለው አስተሳሰብ በጥልቀት የመታደሱን ንቅናቄ የግድ ካሉት መሰረታዊ ጉድለቶቻችን ቁልፉ የሆነው በመንግስት ስልጣን ላይ ከተፈጠረው የተዛባ አተያያ የሚመነጭ ነው። ቁልፉ ችግራችን ድርጅቱ የስልጣን ምንጭ መሆኑ ነው ብለናል። በድርጅቱ ወደ ከፍተኛ አመራር በመጣህ መጠን ወደ መንግስት ከፍተኛ ስልጣን መሸጋገር እየተለመደ ትክክለኛ መርህም ተደርጎ እየተወሰደ የመጣበት ሁኔታ የጥፋታችን ሁሉ መንስኤ ሆኗል። ይህ አካሄድ ግን በአስከተለው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛ የድርጅትና የመንግስት ኃላፊነት አመዳደብ መርህ አኳያ ሲታይም ቀልጥፎ መታረም ያለበት ስህተት ነው። ድርጅትና መንግስት ሁለት የተለያዩ ፍጡሮች ናቸው። በየራሳቸው መተዳደሪያ ደንብና ህግ የሚመሩ፣ የየራሳቸውም ተልዕኮ ያላቸው ሁለት አካላት እንደሆኑ ይታወቃል። በምርጫ አሸንፎ የመንግስት ስልጣን የሚይዝ ድርጅት የሁለቱን ልዩነት በሚገባ ጠብቆ መምራት ካልቻለ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ እስከመፍር የሚዘልቅ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ድርጅቱ ለመንግስት ፖለቲካዊ አመራር ይሰጣል፣ መንግስት ደግሞ ከፓርቲው ፖለቲካዊ አመራር የሚመነጩ ፖሊሲዎችን መሰረት በማድረግ ይንቀሳቀሳል።ለስራው የሚኖረው ሙያዊና የአመራር ብቃት ሊሆን ይገባል። በልዩ ትኩረትም ሆነ በሙያዊና የአመራር ብቃታቸው የሚሾሙ የፓርቲ አባላት በሚኖሩበት ሁነታ ግን የግድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑ ብቻ የሚባል ባይሆንም በፓርቲው ከፍተኛ አመራር ኃላፊነት ላይ የደረሱ ሰዎች የተሻለ ብቃት ያላቸው እንደሚሆኑ ስለሚጠበቅ ባብዛኛው ቀዳሚ ተመራጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።

ትክክለኛው መርህ ይህ ሆኖ ሳለ የመንግስት አስፈፃሚ የኃላፊነት ቦታ ሁሉ በድርጅት አባላት ያውም ከፍተኛ አመራር በሆኑ ብቻ መያዝ አለበት የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው። የመንግስት ኃላፊነት የድርጅት አባላትና ከፍተኛ አመራር ባልሆኑ ከተሞላ በመንግስት መዋቅሩ ፖለቲካዊ አመራር ለመስጠትና የድርጅቱን ፖሊሲ ለማስፈፀም ያስቸግራል የሚል ምክንያትም አይሰራም። ድርጅት በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት ውስጥ ፖለቲካዊ አመራር የሚያረጋግው መዋቅራዊ አቅም ስለያዘ አይደለም። ፖለቲካዊ አመራር የሚረጋገጠው ድርጅቱ ፕሮግራሙን አቋሞቹን ለማስተዋወቅና ምልአተ ህዝቡ የሚደግፋቸው በሂደትም የኔ ብሎ የሚቀበላቸውና የሚመራባቸው የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ውጤታማ የፖለቲካ ስራ በመስራት ነው። ይህንን የመፈፀም ኃላፊነትም የድርጅት መዋቅር ይሆናል። የድርጅት መዋቅር ዋነኛ ተግባራት የፖለቲካና የድርጅት ስራዎች ሲሆኑ እነዚህም በአባላትና በህዝብ ውስጥ በሚሰሩ ሁለት ዘርፎች ተለይተው የሚከናወኑ ናቸው። የአባላት ፖለቲካዊ ስራ በውስጠ ድርጅት ልሳንና በየአደረጃጀቱ /መሰረታዊ ድርጅትን፣ ህዋስ/ እንደአስፈላጊነቱም በተለያዩ የውይይት መድረኮች አማካይነት የሚካሄደውን ስራ ይመለከታል። በህዝቡ ውስጥ የሚካሄድ ፖለቲካዊ ስራ ደግሞ በተለያየ ደረጃ በሚዘጋጁ የህዝብ መድረኮችና በልሳን አማካይነት እንዲካሄድ ይጠበቃል። ይሁንናም ድርጅታችን ለህዝብ ፖለቲካዊ ስራ የሚሰጠው ትኩረትና ራሱ በስራውም ላይ ያለው ግንዛቤ ተዳክሟል ማለት ይቻላል። የህዝብ ፖለቲካዊ ስራ የመንግስትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እቅዶች ማስፈጸም ብቻ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ወደህዝብ የሚወርድ ፖለቲካዊ ስራ ምናልባት ሽታው የሚታየው በምርጫ ሰሞን ብቻ እየሆነ መጥቷል።

በመንግስት መዋቅር ፖለቲካዊ አመራር ለማረጋገጥና ከድርጅቱ ፕሮግራም የተቀዱት የመንግስት ፖሊሲዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ቀዳሚው ጉዳይ የመንግስት ሰራተኞችም በድርጅቱ የፖለቲካ ስራ የሚሳቡበትና ደጋፊ ሊሆኑ የሚችሉበትን መፍጠር ይገባል። የድርጅት መዋቅር ተገቢ የፖለቲካ ስራ በማይሰራበት ሁኔታ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑ ግለሰብ የመንግስት ስራውን ለመምራት ስለተሾመ ፖለቲካዊ አመራር ተረጋግጧል ማለት አይቻልም። በሌላም በኩል በመንግስት ተቋማት የሚሰጠው ፖለቲካዊ አመራርና የፖሊሲ ተፈፃሚነት የሚረጋገጠው በተቋሙ ያሉት ሰራተኞች የመንግስትን ፖሊሲ አውቀው እንዲፈፅሙ፤ የማይደግፉት ቢሆንም እንኳ የመፈፀም ግዴታ እንዳላቸው ተረድተው የሚተገብሩበትን ሁኔታ በመፍጠር ነው። ይህ ደግሞ ኃላፊው የድርጅት አባል ቢሆንም ባይሆንም የግድ መፈፀም ያለበት ይሆናል። የዚህ አይነት ስርዓት ባልተገነባበት በየተቋሙ በሚመደቡ የድርጅት አባላት ዘበኛነት የፖለቲካ አመራርን ማረጋገጥ አይቻልም።

በተጀመረው የመልሶ ማደራጀት በከፍተኛ ተቋማትና በተለያዩ ቦታዎች ሲያገለግሉ ለነበሩ ምሁራን የተሰጠው ሹመት በዚህ መንፈስ መታየት ይኖርበታል። ምሁራኑ የተመረጡት በሹመት የተመደቡበትን ተቋም ለመምራት ሙያቸውና የስራ ልምዳቸው ብቁ ስለሚያደርጋቸው ነው። ውጤታማነቱ በተግባር የተረጋገጠ መስመር እያለው በማስፈፀም አቅም ድክመት የተነሳ ህዝቡ የሰጠውን መንግስትን የመምራት ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደተሳነው ለሚረዳው ኢህአዴግ የማስፈፀም አቅም ከፍተቱን የሚሞሉ ባለሙያዎችን መሾም ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ውሳኔው በርግጥም የመታደስ ርምጃ መጀመሩን የሚያመለክት፣ ፖለቲካዊ አመራርን በፖሊሲ ጥራትና ፖሊሲውን ተቀባይነት እንዲያገኝ በሚሰራ ፖለቲካዊ ስራ ብቃት፣ በድርጅት መዋቅሩ አማካይነት በሚሰራ የፖለቲካ ስራ እንጂ በየተቋሙ በሚመደቡ ካድሬዎች ዘበኝነት ማረጋገጥ እንደማይቻል፤ መንግስትና ድርጅት የተለያዩ መሆናቸውን፣ የድርጅት አባልነት የስልጣን ምንጭ መሆን እንደማይገባው የተገነዘበ ርምጃ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በርግጥ ምሁራኑ ስለመጡ ብቻ የመንግስት አመራር ችግር ይፈታል የሚባል እንዳልሆነ አያከራክርም። የምሁራኑ መምጣት በአጠቃላይ በመንግስት የአመራርና አሰራር ስርዓታችን መለወጥ ጋር ካልተዛመደ ሌላ በጉልቻ መቀያየር ወጥ የማጣፈጥ ከንቱ ምኞት ይሆናል።

ምንጭ – ሰንደቅ ጋዜጣ – ርዕስ ተቀይሯል

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *