የንስር መንገድ!
“ሦስት ነገር ይገርሙኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም። እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቆንጆ ጋር ናቸው” (ምሳ. 30:18-19)።
ባለፈው ሳምንት ያካፈልኳችሁና የብዕር ትሩፋት የተሰኘችው አነስተኛ ጥራዝ በሁለት ሳምንት ዕድሜ ታትማ ትናንት እጄ ገብታለች። ይበል ብያለሁ። ግን አንድ ቅር የተሰኘሁበት ነገር ስለነበረ ይህንኑ ለአታሚዬ ለማመልከት ወደ ሚሽጋን ስልክ መታሁ። ተነጋገርን። ልንለያይ ስንል ከትናንት ወዲያ እንዲያትም የላክሁለትን እና የንስር መንገድ ያልኩትን መጽሐፍ አስታውሼ ጀምሮት እንደሆነ ጠየቅሁት።
“ዛሬ ወይም ነገ እልክልሃለሁ!” አለኝ።
“ጨርሰኸው?”
“አዎ፤ 24 ሰዓት ነው የፈጀብኝ”
“ያክብርልኝ!”
ትናንት አምሽቼ ስገባ እሽጎቹን አገኘኋቸው። እነሆ የሁለቱም ሕትመት ተቀላጠፈ ማለት ነው። የሚቀረኝ ስርጭቱን መጀመርና ይልቁንም የምረቃ ሥርዓቱን ማቀድ ነው። እንግዲህ የሥራው ባለቤት ቢፈቅድና ብንኖር ግንቦት መጨረሻ ወይም ሰኔ መጀመሪያ ላይ ለምስጋና እጃችንን ለፍስሐ ጭማቂአችንን እናነሣለን። ክብር ልጆቼ ብሎ ሲጠራን ላላፈረብን አባታችን ይሁን!
አሜሪካ እንደመጣሁ ዙሪያ ገባውን ሳማትር ከመጻፍ ዘግይቼ ነበር። እናም አንድ መጽሐፍ የጨረስኩት በሦስተኛው ዓመት ነው። ኋላ ስረጋጋ ግን ፍጥነቴን ጨምሬ መሮጥ በመቻሌ በሙሉ ኃይሌ ወደ አገልግሎት ተመልሻለሁ። እናም በ16ኛው ዓመቴ 16ኛ መጽሓፍ መልቀቄን የሚያበሥረው ሥራዬ ይኸው። የንስር መንገድ እና ሌሎች መጣጥፎች የሚል ርእስ የሰጠሁት መድብል እሱ ነው።
መድብሉን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ እና ሁለገብ መጣጥፎች ብሎ ለሦስት መሸንሸን የሚቻል ይመስለኛል። የስድስቱ መጣጥፎች እና የአጫጭሮቹ ጽሑፎች አካሄድ እንዲያ ስለሆነ። የስደት ውበት፣ ያለኝ ይበቃኛል እና የንስር መንገድ የሚሉት ማኅበረሰባዊ ይዘት አላቸው። በአንፃሩ አባቶች ይኑሩ፣ መከራ ያልበገረው እናትነት እና የፍንዳታው ዘመን የሚሉት ደግሞ ቤተሰብን ይቀርባሉ። ቀሪዎቹ እዚህም እዚያም የሚሉ ሁለገብ ጽሑፎች ሆነው ክተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተለቀሙ ናቸው።
ያለፈውን የማስታወቂያ ጽሑፍ በማየት ማበረታቻ ለላካችሁልኝ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
አሁን ማዘዝ ይቻላል፤ በውስጥ መስመር ምላሽ ለመስጠትም ዝግጁ ነኝ። ከተቻለ መረጃውን በማካፈል ለወላጆቻችሁ አድርሱት…

ከስንዱ አበበ ፌስ ቡከ የተወሰደ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *