…. እንዲያለሙ የሚጠበቀው 50ሺ ሄክታር ነው። የሁለቱ ድርጅቶች ከተጨመረ 55ሺ ሔክታር ነው እንዲለማ ሲጠበቅ የነበረው። ከዚህ ውስጥ 51 ነጥብ 4 ሔክታር መሬት በጥሩ ሁኔታ አልምተናል። በአንፃሩ የውጭ ባለሃብቶች በርግጥ የልማት ባንክ ተበዳሪ ቢኤችኦ ነው። ንግድ ባንክ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ሃብት ለውጭ ባለሃብቶች አንስቶ ሲያበድር የተባለ አንዳች ነገር የለም። ብድር የወሰዱ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ዶላር መንዝረው ከሀገር ወጥተው ሄደዋል” ሲሉ አስረድተዋል….. 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ከደንበኞቹ ጋር የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በውይይቱ የተሳተፉት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ናቸው። የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ሳይሆን ልማት ባንክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሳይመካከር በአናት ያጸደቀውን አዲሱን የብድር ፖሊሲ ያስተዋወቀበት መድረክ ነው።

ልማት ባንኩም አዲስ ዝርዝር ለኮሜርሻል እርሻ የተዘጋጀ በቅደም ተከተል የሚሰሩ ድርጊቶችን የያዘ ሰነድ በገለፃ መልክ አቅርቧል። መድረኩን የመሩት የልማት ባንክ ፕሬዝደንት አቶ ጌታሁን ናና ናቸው፡፡ በብድር ፖሊሲ ላይ መግለጫ ያቀረቡት የባንኩ ምክትል ፕሬዝደንት እና የሪጅኖች አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ዋቄ ናቸው፡፡ የብድር ፖሊሲው ሰነድ ከቀረበ በኋላም ተወያዮቹ የተለያየ ምልከታቸውን አንጸባርቀዋል። በቅሬታ የታጨቁ በርካታ ሃሳቦች ወደ መድረኩ ተወርውረዋል።

በብድር ፖሊሲው ሠነድ ከሰፈሩት ነጥቦች መካከል፤ ተበዳሪዎቹ በጥሬ ገንዘብ  7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለዋስትና እንዲያቀርቡ ያስገድዳል። ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ፒ ኤል ሲ) የተመዘገቡ ባለሃብቶች ከመካከላቸው ከአስር በመቶ በላይ ድርሻ ያላቸው ተጨማሪ የግል ንብረታቸውን በዋስትና ማስያዝ እንዳለባቸው ያስገድዳል። ከዚህ በፊት ባለሃብቶቹ ለልማት ያወጧቸው ማናቸውም አይነት ንብረቶች በዋስትና አይያዝላቸውም። ተበዳሪዎች የሚያቀርቡት ገንዘብ አለመታጠቡን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። የሚያመርቱት ምርት በባንኩ በኩል እንዲሸጥ ይደርጋል። የካምፕ ግንባታዎች ወጪ ለኮንትራክተሩ በቀጥታ ከልማት ባንክ ተከፋይ እንደሚሆን ተደንግጓል። ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ባለበት ቦታ ልማት ባንክ ብድር አልሰጥም ብሏል። በተበዳሪዎች የሚቀርበው የዋስትና ጥሬ ገንዘብ በሕጋዊ ባንክ ውስጥ ለአንድ አመት በቋት ውስጥ የተገላበጠ መሆን አለበት። ለኮሜርሻል እርሻ የሚሰጥ ብድር የክፍያው ጣሪያ ከስምንት አመታት ሊበልጥ አይገባም። የብድር ወለድ መጠኑ ከ8 ነጥብ 5 ወደ 9 ነጥብ 5 ከፍ ተደርጓል። ብድር ለመውሰድ በሒደት ላይ የሚገኙ ባለሃብቶችን ብድር ለመውሰድ በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት የክለሳ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

ከልማት ባንክ ኃላፊዎች ገለጻ በኋላ ሃሳባቸው ካቀረቡ ባለሃብቶቹ መካከል የተወሰኑትን በዚህ መልክ አቅርበነዋል።

የቤንሻንጉል ክልል ኢንቨስተሮች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አያን ተሻገር እንደተናገሩት፤ “ሁለት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሰዎች መሬታቸው ወደ መሬት ባንክ ይግባ ተብሏል። ይህ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከልማት ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ አይችሉም። ልማት ባንክ ገንዘብ የሚያገኘው ከሕብረተሰቡ ከሚሰበሰብ ግብር በመሆኑ፣ የሕዝብ ገንዘብ ባክኖ ይቀራል። ሌላው የውል ሕጉን ማየት ያስፈልጋል። እኛ ባጣራነው መሰረት በ2006 ዓ.ም መሬት የጠየቁ ሰዎች ናቸው መሬት የተነጠቁት። በ2006 ዓ.ም መሬት ወስደው ለልማት ዝግጅት እያደረጉ ሳለ ባንኩ የብድር አገልግሎት መስጠቱን ለሁለት ዓመታት አቋርጧል። መሬት መደራረብን በተመለከተ 18 ባለሙያዎች ተሰብስበን በሃምሳ ቀናቶች እንጨርሳለን ብለን እየሰራን ነው” ብለዋል።

አያይዘውም በሰነዱ ላይ “አልሚዎች የሥራ ልምዳቸው ይጠየቃል ተብሏል። ሆኖም አብዛኛው አርሶ አደራችን ኢትዮጵያን እየመገበ ያለው ዲግሪ ወይም ትምህርት ኖሮት አይደለም። አንድ ባለሃብት ባለሙያ ቀጥሮ ወደ ልማት ቢገባ አትችልም የሚለው ነጥብ አልታየኝም። በሀገራችንስ በቂ የግብርና ባለሙያ ቢፈለግ ማግኘት ይቻላል ወይ የሚለው ከግምት መግባት አለበት በማለት የባንኩን አዲስ ፖሊሲ ተቃውመዋል።

ሌላው የካምፕ ግንባታ ክፍያ በቀጥታ ለኮንትራክተሩ ይከፈል ለሚለው የሰጡት ምላሽ፤ “የኮንዶሚኒየም ግንባታ አጣርተው የማይሰሩ ኮትራክተሮች፣ ጫካ ገብተው፣ መሬት ላይ ተኝተው፣ የማሽላ ቂጣ በልተው ሥራዎችን ያከናውናሉ የሚል ተስፋ የለኝም። በአማራጭ መልክ ልታስቀምጡት ትችላላችሁ። እንዲሁም፤ የመሬት መደራረብን የተፈጠረው በጋምቤላ ክልል ውስጥ ሆኖ ሳለ፣ በአጠቃላይ በሀገሪቷ የግብርና ኢንቨስትመንት ቦታዎች የተከሰተ ይመስል፣ ባንኩ ብድር ሆነ ድጋፍ ሲጠየቅ የመሬት መደራረብ እንደሌለባችሁ መረጃ አቅርቡ የሚለው ተቀባይነት የለውም። ክረምቱ እየገባ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው” ብለዋል።

ለዋስትና የሚጠየቀው 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በንግድ ምዝገባ ተመዝግቦ ይምጣ የሚለው የባንኩ መመሪያ፣ አሉታዊ ጎኑን ግንዛቤ ውስጥ የከተተ አይመስልም። እያንዳንዱ ኢንቨስተር ባንክ ያለውን ተቀማጭ አሳይቶ ነው መጀመሪያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰደው። ፈቃድ የወሰደውም ከሦስትና አራት አመት በፊት ነው። ይህ የሚባለው 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ቢኖር ለተለያዩ ሥራዎች ጥቅም ላይ የዋለ ነው። እየዋለ ነው የሚገኘው። እኔ ምስክር ነኝ፣ ንግድ ሚኒስቴር ጋር ሄደን ስንጠይቅ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በባንክ ውስጥ ተቀማጭ እንዳለህ ከባንክ አጽፈህ ና ነው የተባልነው። እንደእኛ ማኅበር የምንጠይቀው፣ እንደኢንቨስትመንቱ ፈቃዱ በተሰጠበት አይነት የሚሰጡ ከሆነ በእናንተ በኩል ይጠየቅ። ካልሆነ ይህንን እንደቅደመ ሁኔታ ልንጠይቅበት አይገባም። ይህ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው። ባልሰጣችሁን ብድር፣ ባላተረፍነው ትርፍ፣ ወደባንክ ባልገባ ገንዘብ ሌላ ገንዘብ አውጥተን ወይም አራጣ ገብተን አናመጣም። አራጣ ደግሞ አንገባም። የሚወጡት ሕጎች ድርቅ ያሉ ብቻ ሳይሆን እንደአስፈላጊነቱ ሊለወጡ የሚችሉ መሆን አለባቸው። እንደእግዚአብሔር ቃል እንደወረደ መሆን የለበትም። ኢንቨስትመንት ፈቃዳችን ላይ እንዳለ እንጂ ልታጸድቁልን የሚገባው፤ በውላችን ላይ ንግድ ፈቃድ የሚወጣው ከምርት በኋላ ነው። ምርት ማምረት ሲጀምር ንግድ ፈቃድ ያወጣል ነው የሚለው” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በመጨረሻ ለባለሃብቱ የማስተላልፈው ከ2006 በኋላ መሬት በጋምቤላ የወሰዳችሁ የውል ግዴታችሁን ብትመለከቱት ጥሩ ነው። የውል ግዴታዉ ሦስትና አራት አመታት የሚል ከሆነ ከዚህ በፊት መሬታችሁ ሊወሰድ አይገባም። የውል ግዴታ አለ። ከዚህ ውጪ የፍርድ ቤት ጉዳይ ነው የሚሆነው። ሌላው ባንኩ ካስቆማችሁ ጊዜ ጀምሮ ያለውና ብድር ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ነው የውል ግዴታችሁ መታየት ያለበት። ዶክተር አርከበ እቁባይ ባሉበት ይህንኑ ጥያቄ አንስቼ ነበር። በአጠቃላይ ግን ለጉዳዩ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ስለሆነ፣ ኮሚቴውም በስፋት የተራመደበት በመሆኑ ልማት ባንኩ በሰጠው ማብራሪያ ልንደናገጥ አይገባም። ባንኩ የራሱን ፖሊሲ ነው ያወጣው። መንግስት ደግሞ ይህንን የባንኩን ፖሊሲ በርግጠኝነት ያጥፈዋል። አባላቶቻችን ሳትደናገጡ መንግስትን ማሳሰብ አለብን” ሲሉ ያላቸውን ተስፋቸውን አንፀባርቀዋል።

የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ማኅበር ም/ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሰለሞን ኃይሉ በበኩላቸው፤ “የቀረበውን ሪፖርት በደንብ ነው ያዳመጥነው። በጋምቤላ በኩል የተነሱት ችግሮች በሙሉ ወደ ባለሃብቱ ነው የተደፈደፉት። ይህ ደግሞ አስተማሪም ሆነ ለውሳኔ ይጠቅማል ብዬ አላስብም። ባለሃብቱ ገንዘቡን ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ፣ ይህቺ ሀገር ነገ ዳቦ ለልጆቻችን ታተርፋለች የሚል ራዕይ ሰንቆ ነው። ከዚህ በፊት ከተለመደው ውጪ ባለሃብቱ የሀገሪቷን የልማት ስትራቴጂዎችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው። ይህ በራሱ አንድ እሴት ነው። ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ ገብቶ ሲሰራ አይዞህ የሚል መንግስት አለ ብሎ ነው። ገንዘቡንም ይዞ ነው ወደ ሥራ የገባው። አሁን ያለውን ፖለቲካ ኢኮኖሚን በመተማመንም ነው። ይህም ሆኖ፤ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንሰራው። ትላንትና ታታሪና ሰራተኛ የሆነ ወንድማችን በታጣቂ በመገደሉ ነቀምት ቀብረን የመጣነው። ሕይወታችን እንደዚሁ ይቀጥላል። ባንኩ ደግሞ ገንዘቤ እየባከነ በመሆኑ፣ በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያክል መመሪያ አውጥቼ ማነቃነቂያ በሌለው ሁኔታ ውስጥ አስቀምጣችኋለሁ እያለ ነው። ረጋ ብሎ በሀገራዊ ስሜት መነጋገርና መደማመጥ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ።

ባንኩ ያወጣቸው እና በሪፖርት የቀረቡት ነገሮች የሚያሳዩት፣ “እናንተ በሥራችሁ ወድቃችኋል። ገንዘቡን ዘርፋችኋል። ስለዚሀም አደጋ ውስጥ ገብቻለሁ፤ ገንዘቤን ተዘርፌያለሁ እያለ ያለው። ለመረጃም እንዲጠቅማችሁ፣ ልማት ባንክ የሰጠው 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር (ለሁለት ድርጅቶች የሰጠውን 800 ሚሊዮን ብር ሳይጨምር) ለ192 ኢንቨስተሮች ነው። እንዲያለሙ የሚጠበቀው 50ሺ ሄክታር ነው። የሁለቱ ድርጅቶች ከተጨመረ 55ሺ ሔክታር ነው እንዲለማ ሲጠበቅ የነበረው። ከዚህ ውስጥ 51 ነጥብ 4 ሔክታር መሬት በጥሩ ሁኔታ አልምተናል። በአንፃሩ የውጭ ባለሃብቶች በርግጥ የልማት ባንክ ተበዳሪ ቢኤችኦ ነው። ንግድ ባንክ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ሃብት ለውጭ ባለሃብቶች አንስቶ ሲያበድር የተባለ አንዳች ነገር የለም። ብድር የወሰዱ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ዶላር መንዝረው ከሀገር ወጥተው ሄደዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

አያይዘውም፤ አቶ ሰለሞን “ቢያንስ ጥናት ተብየው (ባለፈው የቀረበው ሪፖርት) አንድ ያልካደው እውነት አለ። ይኸውም፣ ሰማንያ ሰባት በመቶ የተፈቀደው ብድር ለተገቢው ዓላማ ውሏል ሲል በጥናቱ አካቶ አቅርቧል። አቶ ጌታቸው በማብራሪያው እንዳለው፣ ብክነት ዝም ተብሎ አይታለፍም። እውነት ነው፤ ዝም ብላችሁ እንድታልፉ አንፈልግም።  በሀገር ውስጥ ባለሃብት የባከነ ገንዘብ ካለ፣ እባካችሁ ነቅሳችሁ አውጡና አብረናችሁ እንታገል። ተጨባጭ መረጃ ይቅረብ። አሁን ካለው የተንሸዋረረ አመለካከት እንውጣ። ከአሉታዊ አስተሳሰብ በመነሳት የሚመጣ ፖሊሲ ምን እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ያመጣችሁትን ፖሊሲ፣ እንደምታመጡት እንጠብቅ ነበር” ሲሉ አካሄዱን ነቅፈዋል።

“ይህ የግብርና ኢንቨስትመንት ለእኛም ለባንኩ ምን ማለት እንደሆነ በቀና ልቦና መነጋገር አለብን። በአንድ በኩል አበዳሪዎቻችን ናችሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የልማት አጋሮቻችን ናችሁ። መነሻችን ከዚህ አስተሳሰብ ነው መሆን ያለበት። አጋር መሆናችሁ ይጠቅመናል፤ ከአሉታዊ አስተሳሰብ መነሳታችሁ ግን፣ ውሳኔ አሰጣጣችሁን አሉታዊ የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው።

ሌላው፣ “የምናቀርበውን ማስያዣ በተመለከተ፣ ቀደም ተብሎ አስተማማኝ መሆኑ ተረጋግጧል። ባለሃብቱ ገንዘብ ማሽነሪ ይዞ ነው ወደ ግብርና የገባው። ባለሃብቱ በገንዘቡ ነው፣ መንጥሮ መሬቱን ያለማው። ያቀረበው ገንዘብ ማሽነሪ ያለማው መሬት ተገምቶ ነው፣ ለዋስትናነት በቂ ነው ተብሎ ተበድሮ ወደሥራ የገባው። በማጭበርበር የተፈጸመ ነገር የለም። በጊዜው በቂ አይደለም ብሎ መናገር ይቻል ነበር።”

ተገቢ የሆነ የገንዘብ አስተዳደር አይጠቀሙም ለተባለው ወቀሳ ምላሽ ሲሰጡ፣ “ማን የት ተከታትሎን ያውቃል? ፋይናሺያል ስቴትመንት የሚጠይቀን አለ? የባንኩ ባለሙያ በእርሻ ላይ ቀርቦ የሚጠይቅ አለ? በምርት ጊዜ፣ ሰሊጡ ምን ይመስላል? ጥጡስ ምን ይመስላል? ያልታረሰው መሬት እንዴት ነው ያለው? ለምን እንደዚህ ሆነ? ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? የፕሮጀክት አስተዳደሩ ትክክል ነው፣ አይደለም ለማለት ቀርባችሁ አነጋግራችሁን ታውቃላችሁ? ጋምቤላ ዋና መስሪያቤት ተለምናችሁ እንኳን አትመጡም። አቶ ኢሳያስ አንድ ጊዜ መጣ፣ ጥሩ ሥራ ነው ብሎን ሄደ። አቶ ተሾመ ተደብቀህ መጣህ፣ ሳታነጋግረን ተመልሰህ ሄድክ። አቶ ጌታነህ ናና እመጣለሁ አልክ፣ አልመጣህም። እኛ ደልቶን አይደለም ያለነው። የሕይወት ዋጋ ከፍለን ነው ያለነው። ግማሽ እንጀራ በቀይ ወጥ መብላት የሚያቅተን ሰዎች አይደለንም” ሲሉ ግልፅ ቅሬታቸውን አስቀምጠዋል።

ጋምቤላ ላይ በእንጨት እና በሳር ካምፕ የሰሩ አሉ ተብሎ ለቀረበው ክስ፤ “እባክህ አቶ ጌታቸው፣ እገሌ ነው የሰራው በለን? እኛ እስከምናውቀው ድረስ በእንጨት እና በሳር ካምፕ የሰራ ባለሃብት የለም” ብለዋል። 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የተከፈለ ማስያዣ ያላችሁት፣ “ይህን ያህል ገንዘብ ካለኝ መቶ ሔክታር ዘንድሮ አለማለሁ። በማገኘው ትርፍ በሚቀጥለው ዓመት መቶ ሔክታር ጨምሬ አለማለሁ። ስለዚሀም 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካለኝ ልማት ባንክ ምን ልሰራ እመጣለሁ? ስጋታችሁ መሬቱን ብንሸጠው ገንዘባችሁን አይመለስም ከሚል እንደሆነ ይገባናል። ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ፣ ያለማነው መሬት፣ የሰራነው ካምፕ፣ ያስገባነው ማሽነሪዎች ቢሸጡ ምን ያህል እንደሚያወጡ እኛም እናተም እናውቃለን። ከማንም የተሰወረ አይደለም። የሚከስረውም ባለሃብቱ እንጂ ባንኩ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ለእኛ የሚያስፈልገን፣ ሆን ብሎ ለማደናቀፍ የተጠና ፖሊሲ ሳይሆን፣ ድጋፍ ነው” ብለዋል።

ከጋምቤላ ክልል የዲማ ወረዳ ኢንቨስተሮች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ጽጌሕይወት መብራቱ በበኩላቸው፤ “በአሁን ሰዓት ጋምቤላ ለልማት መግባቴ ትክክል ነበር ወይ? ከልማት ባንክ ብድር መውሰዴስ አግባብ ነበረ ወይ? ብሎ የማይጠይቅ ባለሃብት የለም። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋምቤላ ከምን ተነስታ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያውቃል ብለን ነው የምናስበው። የባንኩ ኃላፊዎች በጋምቤላ ልማት ሥራዎች ላይ የተከፈለውን መስዋዕትነት የመጣውን እድገት እንዴት መግለጽ አቃታቸው? አንደበታቸው ለምን ተሳሰረ? የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለጋምቤላ ግብርና ኢንቨስትመንት ላደረገው አስተዋፅዖ በከፍተኛ ደረጃ መመስገን ሲገባው፤ በሀገር ውስጥ ሬዲዮ ፋና በውጭ ሀገር ኢሳት እየተቀባበሉ በሚነዙት ወሬ ልማት ባንኩ እንዴት ይሽመደመዳል? በጣም የሚገርመው ለውጭ ባለሃብቶች ብድር የሰጠው እና ከሀገር ገንዘቡን ሲያሸሹ ቆሞ ሲመለከት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ልማት ባንክን ለመተቸት ይሁን ለመናገር አንዳችም የሞራል አቅም የለውም” ሲሉ የልማት ባንክ አስተዋፅኦን ከፍ አድርገዋል።

“ቁምነገሩ ወደዚህ ነጥብ እንዴት መጣችሁ፣ በርግጥ አይፈረድባችሁም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ባንኩን መሣሪያ ሊያደርጉ ስለፈለጉ ነው። ወደ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም። ሆኖም ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ባለፈው ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረው ኮሚቴ ተብዬ ያጠናው ጥናት ነው። ኮሚቴው በአልቧልታ የተሞላ፤ በማጭበርበር ድርጊቶች የተሞላ፤ ተደብቆ ነበረ አሁን ያገኘነው፣ በጓሮ በር የተሰራ ባለድርሻ አካላትን ያላሳተፈ፣ ሃሳብ ያልተሰጠበት፣ በማይመለከታቸው በፌደራል ግብርና ሚኒስትር እና  በተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር የእርሻ ኢንቨስትመንት ዳሬክተር ሆን ተብሎ ለጠላቶቻችን በድብቅ ተላልፎ የተሰጠ ሰነድ ነው። ይህን ሰነድ መሰረት በማድረግ፣ እና ሰርተን እንዳልሰራን፤ አልምተን እንዳላለማን፤ ባዶ መሬት እንደተወረር፤ በአንድ ብሔር ተወላጆች እንደተዘረፈ ተደርጎ ነው የቀረበው።  አቶ ጌታነህም የጋምቤላ ሃብት መዘረፍ ውጤት ነዎት ብዬ ነው የምወስደው” ሲሉ አቶ ጽጌሕይወት ተናግረዋል።

አያይዘውም፤ “አቶ ጌታነህ በሀገሪቷ ውስጥ በፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ ሙያ ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ በመሆንም፣ አሁን በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን ሃላፊነት ተጠቅመው ችግሮቹን ተረድተው መፍትሄ ይስጡን ብለን አንድ ሁለቴ አግኝተንዎት የነበረ ቢሆንም፣ ተስፋ ነው የቆረጥነው። አሁንም ከወራት በኋላ አብረን ስንቀመጥ ተስፋ የለውም።

አሁን ያወጣችሁት ፖሊሲ መንግስት ከቀየረው ስልጣን አስረክበን እንሄዳለን ማለታችሁን ሰምተናል። ስለዚህም ከውይይቱ ምንም አትጠብቁ ብለውናል። በነገራችን ላይ የእናንት (የልማት ባንክ) ሚስጥር በአደባባይ ነው ያለው። ለሁለት ሆናችሁ የምትመክሩት ሁሉ ይስማል። የባንኩ ሠራተኞች የሥነምግባር ችግር ያለባቸው ናቸው። የባንካቸውን ሚስጥር አሰራር የማይጠብቁ ናቸው። በጉቦ እየተደለሉ ሕሊናቸው የሚሸጡ ናቸው። ይዛችሁት የመጣችሁትን ሪፖርት ከሰማነው አሉባልታና ወሬ በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የተጠና የተባለው ሰነድ ተጽዕኖ የመጣ በመሆኑ፣ ሀገር በዚህ መልኩ ተጭበርብራ ማለፍ የለባትም” ሲሉ አሳስበዋል።

በመጨረሻ የምጠይቀው ጥያቄ አሉ፣ “የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋምቤላ ላይ ባካሄደው ሥራ በከፈለው መስዋዕትነት ሃፍረት ይሰማዋል ወይንስ ይኮራል?” ሲሉ ጠይቀዋል።

“በጋምቤላ ከአንድ አካባቢ ብቻ ስለሚበደሩ፣ እነሱ ድርሻቸውን ከወሰዱ በኋላ ብድር አይኖርም ነው የተባለው። ከዚህም አልፎ ኮሎኔል፣ ጀነራሎች ናቸው የሚበደሩት ነው የሚባለው። ኮሎኔሎች እና ጀነራሎች ቢበደሩ ችግሩ ምንድን ነው? የደርግን መዋቅር ያፈራረስን፣ የሻብዕያን እብሪት ያስተነፈሰ ሰራዊት ነው። ማበደራችሁ አደጋው ምንድን ነው? ወይንስ የደርግ እና የግንቦት ሰባት ኮሎኔሎች ነው ማበደር የፈለጋችሁት? በአደባባይ ጀነራል እና ኮሎኔል ነው የሚበደሩት ስላላችሁ የምንሸማቀቅበት ጉዳይ የለንም። ዛሬም ነገም ነን። ተበዳሪውም የአንድ ክልል አይደለም። ከጋምቤላ፣ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይ፣ ከአማራም ክልል አሉ። ስለዚህም አፋችንን ቆጠብ አድርገን አብረን ብንሰራ መልካም ይሆናል” ሲሉ ገ/ሕይወት ገ/ሚካኤል የተባሉ ባለሃብት ተናግረዋል።

የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ የማነህ “በተደጋጋሚ ስለችግራችን አቤቱታ አቅርበናል። ሲፈቱ ግን አላየንም። አሁንም ስሜት ማስተንፈሻ ሳታደርጉት ልታዳምጡን ይገባል። ፖሊሲው ከመነሻ ገዳቢ ነው። ብድር የለም ነው የሚለው። አምልጠው ከተደበሩ እንዴት ቀለበት ውስጥ እንደምትከቱና ብራችሁን መሰብሳብ እንደምትችሉ ነው የቀመራችሁት። 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋስትና ለዛውም ጥሬ ገንዘብ ለሀገር ውስጥ ባለሃብት የሚቀመስ አይደለም። በተለይ ጋምቤላ እና አሶሳ ከፍተኛ ወጪያችን የፕሮጀክት ወጪ በመሆኑ ከልማት ውጪ እንሆናለን። ከአስር በመቶ በላይ በፒኤልሲ ሼር ያለው ተጨማሪ የግል ንብረቶችን በዋስትና እንዲያቀርብ ይገደዳል፤ ይህ የሚያሰራ አይደለም። ከሀገሪቷ ንግድ ሕግ ውጪ በመሆኑም ልማት ባንክ ለሀገሪቷ ሕግ ይገዛ እያልነው። መሬት ላይ ያፈሰስነው ሃብትም ይያዝልን። ፖሊሲው በአጠቃላይ ግን ገዳቢ ነው” ብለዋል።

ከጋምቤላ የመጣው ባለሃብት ኢትያንግ ኡቻ በበኩሉ፣ “የዛሬው ስብሰባ ከባንኩ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ ቀጣዩን ሥራ እንዴት እንስራ የሚል መስሎኝ ነበር። ሰነዱ ሲነበብ ግን፣ ከፍተኛ ስጋት ነው የፈጠረብኝ። የስጋቴ ምንጮች አንደኛ እኛ የጋምቤላ እና የአሶሳ ሕዝቦች በተለያዩ መንግስታት ጭቆና ሲደርስብን ከንግዱ ዓለም ተገለን በኢኮኖሚ ወደኋላ የቀረን ነን። አሁን ባለው መንግስትም ልዩትኩረት ከሚሰጣቸው ክልሎች ነው የተመደብነው። ይህ ሆኖ ሳለ በአዲሱ ፖሊሲ እኛን የሚያግዝ አንድም ነገር አላየንም” ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።

ኢትያንግ አያይዞም፤ “እኔ ብድር ለመበደር የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቼ ለባንኩ አቅርቤያለሁ። ሆኖም ሁለት ዓመት ሙሉ ምንም ብድር ሳይሰጠኝ እየተጠባበኩ ነው የምገኘው። ለሌላው መሬት ስለተደራረበ አይሰጠም ይላሉ። እኛ የምናለማው መሬት ከቤተሰቦቻችን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነው። የተደራረበ መሬት የለም። የሰራነው ሥራ የተመለከቱት ካለብድር ይህን መስራት ከቻላችሁ በርቱ ብለውን ነበር። ነገር ግን በክልሉ ውስጥ የተለየ ትኩረት አልተሰጠም ብለው ሪፖርት አቅርበው፣ ባለፈው ሳምንት የደረሰን ሰነድ ግን የመኪና አደጋ ነው የመሰለን። ብድር አንሰጣችሁም ብለው ወስነዋል። እስካሁን ለምን እንዲህ እንደሆነ አልገባኝም። ያለማሁትን መሬት ከግምት የማይገባ ከሆነ በዋስትናነት የማይያዝ ከሆነ ምን ማለት ነው። ለልማት ከማዋሌ በፊት ለባንኩ ያለኝን የገንዘብ መጠን አሳይቻለሁ። ብድሩ ሲዘገይ አለማሁበት። ዛሬ ላይ ለልማት ያዋልኩት ሃብት ብድር ለመበደር አይያዝም ከተባለ፣ ሌላ ገንዘብ ከየት ላመጣ እችላለሁ። ሌላው እንደሀገር አንድ ፖሊሲ ሊወጣ ይችላል። ኋላቀር ለሆኑ ክልሎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ መቀመጥ አለበት” በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ሰንደቅ ጋዜጣ 

ምስል  በዝግጅት ክፍሉ የተመረጠ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *