“…እንደ ጥናቱ ድምዳሜ ሁለት አበይት ጉዳዮች ተገኝተዋል። አሁን ሕዝባችን የሚበላውና የሚሸምተው ልክ እንደ አገሪቱ ኢኮኖሚ ስላደገ የሚጣለው ቆሻሻ ብዛት አድጓል። ጭብጨባ…. ሕዝባችን በቀን ሶስቴ ይበቃሃል ቢባልም ባለመስማቱና ከዚያ በላይ በመመገቡ የቆሻሻሻው መጠን በዝቷል።  ስለዚህ ይህ የእድገታቸን ማሳያ ዋናው ምልክት በመሆኑ በበጎ ጎኑ የታየ ሆኗል። ጭብጨባ… በሌላ በኩል የተገኘው ግኝት ሕዝባችን የሚመገበውና የሚጥለው በመበርከቱ ቆሻሻው አካባቢ በመኖር ተረፈ ምግቡን ለመጣል የሚያወጣውን ጉልበት ለመቆጠብ መወሰኑ ነው። ስለዚህ ካሁን በሁዋላ የሲሚንቶ ችግርን ስላንበረከክነው ቆሻሻውን ሲጥሉ ሲሚንቶ እየቀላቀሉ በማሰወገድ  ናዳውንና የአካባቢውን ብክለት  እንዲከላከሉ ቢደረግ ….” የቆሼ አጣሪ ኮሚቴ

ብክለት – ያው መበከል ነው። የተበከለ ሁሉ ንጹህ አይደለም። መበከል ሲያድግ መመረዝን ያመጣል። የተመረዘ መዳኛ የለውም። መዳን የማይችል ብክለቱን ለሌላው፤ ለቤተሰቡ ጭምር ያራባል። ከዛ ሁሉም ይበከላሉ። እናም ይመረዛሉ… የተመረዙ እየበዙ ሲሄዱ ንጹሃንም የተበከሉ ስለሚመስሉ ለመለየት ያስቸግራል። ይህ ሁሉም ጋር ነው። ቄሱም፣ ዲያቆኑም፣ ደብተራውም፣ ተወዛዋዡም፣ ፓስተሩም፣ ሽማግሌዎችም፣ ነቢይ የሚባሉትም… ሃጂውም፣ ሼካውም፣ ወልዩም….. መሪውም፣ ጀሌውም፣ ገዢውም፣ ተቃዋሚውም… ከራስ እንስከ እግር…. ጉድ እኮ ነው!! ከሁሉም ወገን ንጹሃን አሉ፤ ግን ለዛሬ እነሱን ልለፋቸው። ግን ቀናዎች ራሳችሁን መግለጽና ” አያገባናል” በማለት …..

ያበደው ከቆሼ ሰለባዎች ጋር ተሰውሮ ከርሟል። እንደምን ሰነበታችሁ? ቆሻሻ ሆይ የእለት ጉርስ፣ የመኖሪያ ሚስጢር፣ መሸሸጊያ ያደረጉህን በላሃቸው። ያላቸው የሌላቸው ላይ ቆሻሻ ከምረው፣ ከምረው፣ ከምረው….. ግን ለመሆኑ መከመር ጥበብ የለውም? ” ዝም ብለህ ከምር” የሚሉ መሃነዲሶች አዲስ አበባን እንዴት እያነጿት ይሆን? እውነት እንነጋገር ከተባለ ክምር እንደሚናድ የማይረዳ መሃንዲስ ቢገመገም፣ ቢታደስ፣ እስከ ጥልቁ ቢመረመር ምን ዋጋ አለው? ጥልቅ ነገር የምንመኘው እኮ ሜዳ ላይ ያለውን ስናየው ነው።

ቆይ ወገኖቼ፣ ቆሼ ሰፈር አጥር የለውም። በነገራችን ላይ አጥር እንኳን ቢኖረው አደጋው አይደርስም ወይም ይቀል ነበር። ቆሼ ሰፈር አላፊ አግዳሚ አፍንጫውን ጠቅጥቆ የሚመላለስበት ነው። እድሜውም ቀላል አይደለም። “ነዋሪዎች” አቤት ባይሉም ሲሚንቶና አሸዋ የሌለውን ቁልል፣ “ክምር” የሚሉት ክፍሎች፣ ክምር ለዚያውም የቆሻሻ እንደሚናድ እንዴት አያውቁም? አጣሪ ኮሚቴው ምን ይል ይሆን? ልክ እንደ ኦሮሚያ ማጣራት ” መንግስት ከልክ ያለፈ ሃይል አልተጠቀመም” እንዳለው? ባዶ እጁን የሚጮህ ህዝብ ላይ ጥይት ከማዝነብ ውጪ ምን ሊመጣ…. ያበደው ቀባጠረ። አሁንም ቆሼ…… ሲጣራ ” … ባለፉት 25 ዓመታት የተከመረው ሳይሆን የድሮው ነው” ሊባል? ወይስ ” አሁን ዜጎች የሚጥሉት ተረፈ ምርት ኢኮኖሚው እንዳደገው ሁሉ በመጨመሩ አደጋው የእድገቱ አመላካች ነው” ሊሉ?  የማዘጋጃ ቤት መሃንዲሶች ስለ ሬሾ አያውቁም እንዴ? ቦሰናም አሽሟጣለች። የተቆፈረ አፈር እንኳ ሲጋዝ የሚከመርበት የቁመት መጠን አለው። አጥር አፍራሽ መሃንዲሶች ካልሆኑ በስተቀር … እስኪ ለሁሉም ነብስ ይማር።

ቦሰና ቆቅ ናት። ነገሯ ይከብዳል። ስለ አየር መበከል፣ ስለተፈጥሮ መዛባትና የዓለም ሙቀት መጨመር መሪዎቻችን ሲናገሩ ትስቃለች። ” እኛ ተበክለናል” ትላለች። ” እንደውም ተመርዘናል” ስትል ግምገማዋን ታሰፋዋለች። ያበደው ስለመበከል አሰበ። የእምነት ቤቶች ስብከቱን ድህነት ተኮር አድርገውታል። ስብከታቸው ሁሉ ” ማድጋሽ ይሞላል፤ ትዳርሽ ይቃናል፣ ህዘንሽ ከዚች ሰዓት ጀምሮ ተወግዷል፤ ቀንበርሽ ተሰብሯል…” የሚል ነው። ከስብከቱ በሁዋላ ሁሉም ቤታቸው ሲመለሱ ሁሉም እነደነበረው ነው። ያሳዝናል። ትልቁን አምላክ ያሳንሱትና ….. ይህ መበከል ነው።

ሃብታም የበሽታ ጎሬ ስለሆነ  በህመሙ ይሰብኩታል። በፈውስ ያማልሉታል። በልጆቹ ይገቡበታል። ሰው እንዲያስብ፣ እንዲመራመርን የጌታውን ቃል በማጥናት ተረድቶ ” ከእለት ደራሽ የተራ ተሰፋ ስብከት እንዳይወጣ” በጉድለቱ እየሰበኩት ታላቁን የጌታውን ስጦታ እንዳይቀበል ይጎትቱታል። አንዱ ፓስተር በፈገግታ ” እኔ ሰው እያዳንኩ ገንዘብ ብሰበስብ ምን አለበት፣ ቅሪላ/ ኳስ የሚያለፉ ገንዘብ ይዝቁ አይደል ” እንዳለው፤ አዎ!! ብክለት ቀስ እያለ ያድጋል። ቀስ እያለ መርዝ ይሆናል። መርዙ በፍጥነት እየተራባ ዛሬ ሁሉም ግቢውን እያጠረ … በፈውስ ስም ብር ይለቅማል!! አንዱ ከሌላው እየተገነጠለ አባላትን ለማስኮበለል ሰራዊት ያሰማራል። የገባቸውን ግራ ያጋቡዋቸዋል። ያልገባቸውን ከወዲያ ወዲህ ያወዛውዟቸዋል። ” እምነት በስራ ካልተገለጠ እየሉ እየሰበኩ ….” ጎበዝ ቦሰና እንዳለችው ተበክለናል። ንጽሃና ጎሎናል። ከእውነት ጋር ተጣልተናል። 60 ለማይሞላ እድሜ እግዜሩ ቤት ሆነን ለከርስ እንባላለን።

መንግስትም እንዲሁ ነው። ስብከቱ ልክ እንደ ሃይማኖት ቤቱ ድህነት ተኮር ነው። ” በቀን ሶስቴ ትበላላችሁ” ብለው ነው የጀመሩት።”ዋና ጠላታችን ድህነት ነው ድባቅ እነከተዋለን” ብለው አስቃዡን። አሁን ጥሩ ደሃ መሆን ሲያቅት ” ስራ እንሰጥሃለን፣ በቢሊዮን ብሮች በጀት ይዘንልሃል”  ማለት ተጀመረ። ደሃን በድህነቱ ማማለል። ክቡር የሆነውን ሰው በሆዱ ማታለል። አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ባናቱ እየተነሱ ቃል መግባት። በእቅድ የሌለን ነገር ማወጅ። ሲያቅት ” ከረፋን፣ በሰብስን፣ ገማን፣ ተሃድሶ፣ ግምገማ፣ ….. ” በማለት አባላትን ማባረር። ተመልሶ ጭቃ!! ከዚህ በላይ መመረዝ የለም።

ያበደው ይህንን የሚለው ለወቀሳ አይደልም። በበዙ መልኩ ተበክለናል። ቀናነት ተስኖናል። ቀናዎችን በማግለል ቦታ አሳጥተናቸዋል። ፍሬ ያላቸውን ወገኖች ገፍተን ረብ የሌለው ጉዳይ ላይ እንገብራለን። ከእድሜ፣ ከስህተት፣ ከተሞከሮ መማር አቅቶናል። ከቆሸሸ አስተሳሰብ ጋር ተጋብተን እየኖርን ” ቆሼ ሰፈር ቆሻሻ ለተደረመሰባቸው እናለቀሳለን”

ያበደው ዝም አለ። ራሱንም፣ አካባቢውንም ቃኘ። ጠኔ እየገረፈን ነው። ችጋር ምንም የማያውቁ ህጻናትን እየበላቸው ነው። እናት የሚቃትት ልጇን አቅፋ የነጠፈውን “ጡት” አፉ በመወተፍ …  ወደሞት የሚሮጡ ወገኖች ገጠውና ገርጥተው እያየን ነው። ዓለም ይህንን ጉዳችንን እያየ… በየድረ ገጹ እየተለመነልን ነው። ያም ሆኖ አልሆነም። ይኸው ግማሽ ምዕተ ዓመት በእርጥባን ላይ ነን።  ድህነቱ ቤቱን በላያችን ላይ ሰርቶብናል። የሚቀንስ ነገር የለም። እየባሰብን ነው…… አንድም የምንኮራበት ነገር የለም። ከመራብ በላይ አስነዋሪ ነገር የለም። የእኛ ረሃብ በዛ። የህሊናና የልቡና ረሃባቸን ጠነከረ። ትል በሚኖርበት ብስባሽ ውስጥ ኖረን ከሞትን በሁዋላ አሁንም አፋችንን እንከፍታለን። ያበደው ተንቆራጠጠ። የሚደርገው ጠፋው።

አገሪቱ ቢዘረዘር የማያልቅ ጣጣ ውስጥ ወደቃ እያቃሰተች ነው። የማይተዋወቁ ተፋቅረው ሲኖሩ እኛ ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክመን በጎሳ እንባለለን። በቋንቋ እንወዛገባለን። በዘር ተቧድነን እንሞሻለቃለን። ጠኔ የሚጨፈጭፈን አንሶ … ያበደው እንባው አይኑንን ሞላው። ሆድ ባሰው። መቼ እንደ ሰለጠነ ሰው …. አሁን የሚያስፈለገው ……..

ያበደው ዘለለ። ተቆናጥሮ ተነሳ። ምራቁን ጢቅ አደረገ። እንደ ልማዱ ” አዋጅ አዋጅ” ለማለት ቃጣው ። ሃይሉን ሰበሰበና አዋጁን እያውጀ …. ወደድንም ጠላንም ተበክለናል። በቅዠት የ60 ዎቹ ትውልዶች የነደፉት ስትራቴጂ ድምሩ ክሽፈት ነው። ያ- ትውልድ እያላችሁ አትመጻደቁ። ያ – ትውልድ ቋንቋው ደም ነው። ከዚህ ኡደት የሚያወጡን መሪዎች ያስፈልጉናል። የደም ፖለቲካ ይቁም። ዳቦ ዳቦ ዳቦ ዳቦ ዳቦ…. እንዴት እንደምንበላ እንምከር። ድህነት ተኮር ስብከት ይቁም። ድህነት ላይ የተንጠለጠሉ ስብከቶች በቃን።  በድህነት ስም ንግድ የቂም። ህይወታችንንም፣ ቤትችንንም፣ ኑሯችንንም የምንመራው ራሳቸን ነንና ድህነትን የስልጣን፣ የገቢና የኑሮ ስልታችሁ ያደረጋችሁ ተው!! እናንተ “አያገባንም” ብላችሁ የተቀመጣችሁ፣ ስትሞክሩ ሰሚ ያጣችሁ፣ እያወቃችሁ ዝም ያላችሁ፣ ተነሱ!! የተጥቀላላችሁበትን ሽል ስበሩ… እናንተ የምድሪቱ መደሃኔት ትሆኑ ዘንድ በድህነት ስብከት ላይ ተነሱ…..

ያበደው አመመው። ረጋ ማለት አለበት። አፍቃሪዋን የማታውቅ፣ ሲያፈቅራት ስትግደረደር የነበረች፣ ታግሶ ታግሶ ከተለያት በሁዋላ ልትቆጣጠር የምትሞክር ሴት ታሪክ ትዝ አለው። እሷን እያሰበ ከገባበት ሃዘን ለመውጣት ታገለ። ቦሰና ይህችን ባለ ታሪክ ” የዞሮባት” ስትል ታዝንላታለች። የተለያት ጓደኛዋ ግን መታከም አለባት ባይ ነው። ዋይ ዋይ ተለያየን ዋጋ የለውም። አፍቃሪንም ለማወቅ አቅም ያስፈለጋል። አለበልዚያ በነጋ ቁጥር እንደ ፌስ ቡክ ትግትግ / ቻት ህይወት በቅዠት ይጠቃለላል። አለያም ሎተሪ ይደርስና…. አሁን ያበደው ቦሰና ጎን ነው። ደጎል ደብሮታል። መናፈስ ይፈልጋል። እዚህ ደጎል ከሰው በላይ መብት አለው። ሰላም ሁኑ!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *