“Our true nationality is mankind.”H.G.

ተፈጥሮ ሲከዳ

የመዋዕለ ሕፃናት ተማሪዎች ከሚማሩበት ክፍል ውስጥ በአፏ እርሳሷን ይዛ ትጽፋለች፡፡ አንዳንዴ ከጎኗ ካሉ የክፍል ጓደኞቿ ጋር ትወያያለች፡፡ የትምህት ክፍለ ጊዜው እንግሊዘኛ ነበርና በአፏ የምትጽፈውን ለማየት ወደሷ ተጠጋን፡፡ የጽሑፍ አጣጣሏም ልቅም ያለ ነው፡፡ ደብተሯን አገላብጠን እንዳየነውም ስህተት የሚባል ነገር የለበትም፡፡ ደብተሯ ላይ የተሰጡ የመምህራን አስተያየቶች በሙሉ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባሉ ናቸው፡፡

የትምህርት ውጤቷን ለማየት ፈለግን መምህራኖቿ የፈተና ወረቀቷን በማሳየት እንዲተባበሩን ጠየቅን፡፡ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች ደፍናለች፡፡

የ11 ዓመቷ የአብሥራ ረታ እንደሌሎቹ የክፍል ጓደኞቿ ሙሉ አካሏ አይታዘዝላትም፡፡ በእጆቿ አትሠራም፣ በእግሮቿም አትንቀሳቀስም፡፡ የምትለብሰው፣ የምትመገበውና የምትፀዳዳው በሰው ድጋፍ ነው፡፡

በትምህርት ክፍሏ ውስጥ ጽሑፏን በአፏ ስታቀላጥፈው፣ እግሯ ጣቶች መሀል እርሳስ በማስገባት ደግሞ ሥዕል ትስላለች፡፡ በትምህርቷ እጅግ በጣም ጎበዝ ከሚባሉት የምትመደበው የአብሥራ፣ የወደፊት ትልሟም ፓይለት መሆን ነው፡፡

የአብሥራን ያገኘናት ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ ለእሷ በሚመጥን አንድ አነስተኛ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ስትማር ነው፡፡ በዚሁ መዋዕለ ሕፃናት የሁለተኛ ዓመት ኬጂ ተማሪ ናት፡፡ እናትና አባቷ ተለያይተዋል፡፡ እሷን ጨምሮ ሦስት እህቶቿ ከእናታቸው ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡

Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”

በአፏ እስክርቢቶ ጎርሳ መጻፍና በእግሯ ጣቶች እርሳስ ይዛ መሣል የለመደችው በእዚሁ መዋዕለ ሕፃናት ነው፡፡ ትምህርት ቤት እንደገባች መምህራኖቿ በዚህ መንገድ እንድትለማመድ እንዳበረታቷትና እርሷም እንደቀጠለችበት፣ በአሁኑ ጊዜም ጎበዝ ጸሐፊና ሠዓሊ ለመሆን እንደበቃች ትናገራለች፡፡

‹‹ድርጅቱ የምግብና የትምህርት ድጋፍ ያደርግልኛል፡፡ አንዳንድ በጎ አድራጊዎችም አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ ልብስና ጫማ ጣል ያደርጉልኛል፡፡ ቀጣይነት ያለው የትምህርት ዕድል ቢሰጡኝ ደስ ይለኛል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ግን ወደፊት ፓይለት የመሆን ሐሳብ አለኝ፤››› የምትለው የአብሥራ፣ ቀን ስትማር እንደምትውል፣ ቁርስ፣ ምሳ፣ መክሰስና እራት ከድርጅቱ እንደምትበላ፣ ማታ ላይ እናቷ ተሸክማ ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ ትናገራለች፡፡ ትምህርቷን በጣም እንደምትወድ፣ ለዚህም እናቷ እየተሸከመች በማመላለሷ እንደምታመሰግንም አክላለች፡፡

ወ/ሪት ዘውዴ ቢፍቱ የአብሥራ መምህርት ናት፡፡ እንደ መምህርቷ፣ የአብሥራ ከክፍል ጓደኞቿ ጋር ጥሩ መግባባትና ፍቅር አላት፡፡ በትምህርቷም በጣም ፈጣንና ጎበዝ ተማሪ ናት፡፡ የደረሰባትን የአካል ጉዳት በፀጋ ተቀብላ ብሩህ ተስፋ ሰንቃ የምትማርም ናት፡፡

Related stories   የትግራይ ክልል ባቀረበው ፍላጎት መሠረት የአፈር ማዳበሪያ መቶ በመቶ እንዲቀርብ መደረጉ ተገለጸ

ሁለተኛ የትምህርት አጋማሽ ላይ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ የአካባቢ ሳይንስና ሥዕል፣ ተፈትና ሁሉንም ፈተና ያለምንም ስህተት መሥራቷን ከፈተናዎቿ ወረቀቶች ላይ ለመረዳት ችለናል፡፡

ወ/ሮ ገነት አዱኛ የአብሥራ እናት ናቸው፡፡ በእርግዝናቸው ወራት፣ ወቅቱን እየጠበቁና ሳያቋርጡ ሕክምና ተቋም በመሄድ ክትትል ሲያደርጉ፣ በጽንሱም ሆነ በእሳቸው ጤንነት ላይ ምንም የሚያሠጋ ወይም የሚታይ ችግር እንደሌለ ሐኪሞቹ  ይነግሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የመውለጃቸው ጊዜ ደርሶ በሆስፒታል በቀዶ ሕክምና ሲገላገሉ ግን  የሕፃኗ እግሮችና እጆች እንደተጣጠፉ መወለዷን፤ ከዛም ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር እንደተባለችና ሐኪሞቹም ጭንቅላቷና ሆዷ መደበኛ ከሚባለው በላይ እንደሚያድጉ ነግረዋቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹ሐኪሞቹም ያሉት ሳይሆን ቀርቶ አዕምሮዋ ደህና በመሆኑ ይኼው ለትምህርት በቅታለች፤›› የሚሉት ወ/ሮ ገነት፣ ዛሬ ነገሮች ይስተካከሉ እንጂ ለልጃቸው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት (መዋዕለ ሕፃናት) ለማግኘት ያላንኳኳኩት በር እንዳልነበረ ይናገራሉ፡፡ ሁሉም ለእርሷ የሚሆን ክፍልና አስተማሪ የለንም በሚል ምክንያት ሊቀበሏት እንዳልቻሉ፣ በስተመጨረሻም ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ተቀብሏት አሁን ያለችበት ደረጃ ልትደርስ እንደቻለች ገልጸዋል፡፡

Related stories   ፋኦ በትግራይ ክልል ለአርሶ አደሮች የእህል ዝርያዎችን ማሰራጨትና እንስሳቶችን መከተብ ጀመረ

አብሥራ ሦስተኛ ልጃቸው ናት፡፡ መካከለኛዋ ልጃቸው ደግሞ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር በሚገኘው ፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ ስትማር፣ የሁሉም ታላቅ የሆነችው ግን ትምህርቷን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጣ ቤት እንደዋለች አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ገነት በድርጀቱ ውስጥ የአብሥራን የመሰሉ ሕፃናትን የመንከባከብ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ለዚህም በየወሩ 600 መቶ ብር ይከፈላቸዋል፡፡ የአብሥራን ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት፣ ከትምህርት መልስ ደግሞ ወደ ቤት የሚወስዱት ግማሹን መንገድ በታክሲ፣ የቀረውን ግማሽ ደግሞ አዝለው በእግር በመጓዝ ነው፡፡ ለትራንስፖርት ከሚያወጡት ገንዘብ ውስጥ ግማሹ በድርጅቱ በኩል ከፊሉ ደግሞ በራሳቸው ወጪ እንደሚሸፈን ነግረውናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይኼው የበጎ አድራጎት ማኅበር ከመጋቢት 17 ቀን እስከ መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የቆየ የፍቅር ሳምንት አካሂዷል፡፡

Reporter Amharic

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0