• በኦሮሚያ በሦስት ዞኖች ብቻ 241 ት/ቤቶች ተዘግተዋል፤ 114,751 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል!
  • በቦረናና በጉጂ ዞኖች 127,010 ከብቶች በዘንድሮው ድርቅ ሞተዋል!

ድርቅ ከፍ ሲልም ችጋርና ረሃብ ለኢትዮጵያ ተጠባቂ የስጋት ምንጭ ሆነው እንደቀጠሉ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ካሳለፍነው አስከፊ የርስ በርስ እና ከጐረቤት አገራት ጋር ከተደረጉ ጦርነቶች ጐን ለጐን ድርቅ፣ ችጋር፣ ረሃብ ሌላኛው የኢትዮጵያ አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በቀደሙት ጊዜያት በየአስር ዓመታት ልዩነት ኢትዮጵያን በሰፊው ይጐበኛት የነበረው ድርቅ፤ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገሪቱን ደጋግሞ ሲያጠቃና የከፋ ማኅበራዊ ቀውስ ሲያስከትል ታይቷል፡፡

በተራዛሚው ጦርነት ፍፃሜ ማግስት በአገሪቱ የተከሰተው የ1988 ዓም ድርቅ የአማራ፣ የሶማሌ፣ የአፋር እና ከፊል የኦሮሚያ አካባቢዎችን ክፉኛ አጥቅቷቸው እንዳለፈ ይታወሳል፡፡ የጦርነት ፍፃሜ የድርሻ ክፍያ የብቻ ተቋዳሽ የሆነው ህወሃት፤ ለድርቁ ይህ ነው የሚባል ትኩረት ባይሰጥም በለጋሽ አገራት ርብርብ ድርቁ ያስከተለውን ረሃብ መሻገር ተችሎ ነበር፡፡ ይሁንና ድርቁ ካስከተላቸው ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ማገገም ሳይቻል በአራት ዓመታት ልዩነት አገሪቱ ላይ የከፋ ድርቅ ድጋሚ ተከሰተ፡፡ ለዜጎች ሞትና ስደት መንስኤ የሆነው ይሄው ድርቅ በወቅቱ ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት የተነሳ ትኩረት የተነፈገው በመሆኑ ያደረሰው ሰብዓዊ ጥፋትና ማኅበራዊ ኪሳራ በቀላሉ የሚገለፅ አልነበረም፡፡ ምናልባትም ህወሃት ማዕከላዊ መንግሥቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ለዜጎቹ ስቃይ ደንታ ቢስ መሆኑን ለዓለም ህዝብ በአደባባይ ያሳየበት ክስተት የ1992 ዓም ድርቅ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡

ሞትና ስደትን ካስከተለው ድርቅ በኋላ፤ ሟቹ መለስ ባልተገራ አንደበቱ የራሱን ድርጅት “ገምተናል” “በስብሰናል” በሚል “ተሃድሶ” አደረኩ አለ፡፡ በርግጥ “መበስበስ”ና “መግማታቸው”ን በመለስ በኩል የነገሩን ከአስከፊው ድርቅ መንስኤና ውጤት አኳያ ሳይሆን፤ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት አስታኮ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ የራሳቸውን ዘውግ የበላይነት ማስቀጠል በሚቻልበት ስልታዊ አካሄድ ዙሪያ ልዩነታቸው ጎልቶ በመውጣቱ ነበር፡፡

የሆነው ሆኖ ከ1993ቱ “ተሃድሶ” በኋላ የተከለሰ የግብርና ፖሊሲ፣ ውሃ ማቆር፣ የመስኖ ልማት፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ መንደር ማሰባሰብ … የሚሉ የአፍ ዲስኩሮችና የመለስ ግለሰባዊ ስሜቶች “ፖሊሲ” ተብለው ማቅረባቸው ቀጠለ፡፡ ተዘቅዝቆ የተተከለን ችግኝ በሪፖርት የሚያፀድቁት የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች በሚያስተላልፉት የተጋገረ ሪፖርት “የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ ነው” በሚል በቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ተጠምዶ የነበረው መለስ በ2001 ዓም በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ 14 ሚሊዮን ዜጎች ለረሃብ መዳረግቸውን ሊደብቀን ቢሞክርም አልተሳካለትም፡፡ መለስና የሥልጣን አሽከሮቹ በወቅቱ የሰብዓዊና የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሚያወጡትን ሪፖርት የኒዮ-ሊበራሎች ተላላኪ ተቋማት ዘገባ አድርጐ ማጣጣል መገለጫቸው ነበር፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ በአመራር ድክመቱና በፖሊሲ ክሽፈቶቹ የሚፈጠሩ አውዳሚ ችግሮችን ሰበብ ፈለጎ አንዱ ላይ መለጠፍ ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ በአገሪቱ በየጊዜው የሚከሰተውን ድርቅ ቢቻል ወደ ግልና ዓለምአቀፍ ሚዲያ እንዳይደርስ ማፈን፤ ካልሆነም ችግሩን ከተፈጥሮ ክስተት ጋር ብቻ ማያያዝ እና አቃሎ ማውራት መገለጫው ሆኗል፡፡ አገሪቱ በተደጋጋሚ በድርቅ መጠቃቷ፤ ድርቁ ከትኩረት ማነስ ወደ ረሃብ የማደጉ ሁነት የህወሓት ታላቅ ውድቀት ምልክት ቢሆንም፤ ድርጅቱ ራሱንም ሆነ አገሪቱን ለመፈተሽ አቅሙም ሞራሉም አልነበረውም፤ እስካሁንም የለውም፡፡ የዚህ ውጤት ዛሬም ድረስ ድርቅ የኢትዮጵያ ተጠባቂ ስጋት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ (ጸደይ፣ በጋ፣ መኽርና ክረምት እንደምንለው ሁሉ ድርቅም የአገሪቱ ተፈራራቂ የወቅት አካል ሆኗል)፡፡

የአደጋ ግምገማ፣ የቀዳሚ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የንብረት (መሬት) ባለቤትነት ጉዳይ፣ የዴሞክራሲ ተጠያቂነት፣ የገበያ ማረጋጊያ ስልቶች (ፖሊሲዎች)፣ የክልሎች ፍትሃዊ የበጀት ድልድል፣ አካባቢያዊ ሃብት ላይ የተመረኮዘ የፖሊሲ አዋጪነት ጥናት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ወሳኝ መንግስታዊ አሰራሮች ተቀብረው በአንፃሩ ለአንድ ዘውግ የበላይነት የሚተጋ ወታደራዊ ኃይልን የጨበጠ ቡድን ሙስናና ብልሹ አሰራርን መገለጫው ባደረገበት ሁኔታ ከፖለቲካ-ኢኮኖሚ የፖሊሲ ክሽፈቶች አኳያ ድርቅን ተከትሎ የምግብ እጥረት መከሰቱ ብሎም ትኩረት እስካልተሰጠው ድረስ ድርቁ ወደ ረሃብ ማደጉ የማይቀር ይሆናል፡፡

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ማዕከላዊ መንግስቱን በከልካይ የለሸ ወታደራዊ የኃይል ሚዛን የተቆጣጠሩት የህወሓት ሹማምንት በአደባባይ ባመኑት መረጃ መሰረት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ አመታት አስተናግዳው የማታውቀው መጠነ ሰፊ ድርቅ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት አጥቅቷታል፡፡ በቀደሙት ሁለት ዓመታት ድርቁ ከጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስተቀር የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የገጠር ቀበሌዎችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል፡፡ በትግራይ ክልል ታየ የተባለውን ድርቅ (ለፕሮፖጋንዳ ማመጣጠኛ የዋለ ነው በሚል) ለማመን ቢቸግረን እንኳ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች (ገጠራማ ቦታዎች) ድርቁ የከፋ ማህበራዊ ጠባሳ አሳርፏል፡፡ በርከት ያሉ የቁም እንስሳቶች አልቀዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን እስከማዘጋት የደረሰ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጐች፣ ትምህርት ለማቋረጥ የተገደዱ ታዳጊዎች፣ ከብቶቻቸው በየሜዳው ያለቁባቸው አርብቶ አደሮች ህይወት መጎሳቆል፣ አልሚ ምግብ አጥተው ከተገማች ኪሎ በታች የሆኑ ከሲታ ህፃናትና  እናቶች፣ … የድርቁ አስገዳጅነት ያስከተላቸው ማህበራዊ ቀውሶች ናቸው፡፡

በድህረ-ደርግ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1988፣ 1992፣ 2001 እና ከ2007 እስከ አሁን ድረስ (2009) ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በተራዛሚነት ድርቅ ከተፈራረቀባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች አንዱ ኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ኦሮሚያ ክልል በቆዳ ስፋቱ ቀዳሚ ክልል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ኃይል አቅም ለልማት ማስተባበር የሚያስችል ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራርና ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለመኖሩ ዛሬም ድረስ በአገራዊ የምርት ክምችት መመከት የሚቻለው ድርቅ ወደ አስከፊ የምግብ ዕጥረት (ረሃብ) እያደገ ይገኛል፡፡

አረንጓዴው ድርቅ በኦሮሚያ

ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞንን ጨምሮ 17 ዞኖች አሉት፡፡ 2007 ዓም ድርቁ ሲከሰት ከ17 ዞኖች 9 ዞኖች በድርቁ የተጐዱ ነበር፡፡ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት (2007 – 2009) በተራዛሚነት ያለማቋረጥ የተጐዱ ዞኖች ደግሞ 5 ናቸው፡፡ ባሌ ዞን (ሁለት ከተማ አስተዳደርና 18 ወረዳዎች ያሉት)፣ ቦረና ዞን (2 ከተማ አስተዳደርና 12 ወረዳዎች ያሉት)፣ ጉጂ ዞን (2 ከተማ አስተዳደርና 12 ወረዳዎች ያሉት)፣ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን (4 ከተማ አስተዳደርና 15 ወረዳዎች ያሉት) ፣ ምዕራብ አርሲ (3 ከተማ አስተዳደርና 9 ወረዳዎች አሉት) በድምሩ በ5 ዞኖች፤ 13 ከተማ አስተዳደሮች እና 66 ወረዳዎች በተራዛሚው ድርቅ ተጠቂ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር በመስከረም ወር አደረኩት ባለው የቅድመ ድጋፍ ጥናት በክልሉ 3.8 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ምግብ ደራሽ ፈላጊዎች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ ይሁንና ድርቁ በተራዛሚነት ካካለላቸው የዞኖች ስፋትና በቅርቡ ከሶማሌ ክልል አርብቶ አደሮች ጋር በተፈጠረው ግጭት የተነሳ የግጭት ተፈናቃዮች የተረጂዎችን ቁጥር እንደጨመረው በክልሉ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ “በአንፃሩ በከተሞች መጠነኛ የንግድ እንቅስቃስዎች የሚስተዋል ቢሆንም በገጠሩ ክፍል ድርቁ የከፋ ጉዳት አድርሷል” የሚሉን የጎልጉል የመረጃ አቀባዮች “ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር የሚዋሰኑት የኦሮሚያ ዞኖች (ጉጂ፣ ቦረና፣ ባሌና ምስራቅ ሐረርጌ) የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል” ይላሉ፡፡ ድርቁ ባስከተለው የምግብ ዕጥረት የተነሳ በተፈጠረው የተፈጥሮ ሃብት ቅርምት የሁለቱ ከልል አርብቶ አደሮች በጦር መሳሪያ የተደገፈ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የሚጠቁሙት የጎልጉል የአካባቢው ምንጮች፤ ግጭቱ በቀዳሚነት የተቀሰቀሰባቸው ቦታዎች በምስራቅ ሐረርጌ “ጭራቅሰን” ወረዳ በመቀጠልም “ሚዮም ሙሉቤ” እና “ቁምቢ” የተባሉ ወረዳዎች ላይ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ “እነዚህ ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ በምስራቅ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ነዋሪዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ‹የእርዳታ ማዕከል› በሚል በተቋቋሙ ቦታዎች ተጠልለው ይገኛሉ” የሚሉን የጎልጉል ምንጮች፤ በዕርዳታ ማዕከሎች ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት መኖሩን ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ተላላፊ በሽታዎች ተጨማሪ ፈተና ሆነዋል፡፡

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

የኦሮሚያ ክልል “መንግስት” ሊቋቋመው ያልቻለው የተላላፊ በሽታዎች ስጋት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተከስቷል፡፡ በየዕርዳታ ማዕከሎቹ የህክምና ድጋፍ ለማድረግ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት ማጋጠሙን የሚገልጹ የጎልጉል መረጃ አቀባዮች “የሌሎች ክልሎችን የህክምና ባለሙያዎችን ድጋፍ መጠቀም እንደአማራጭ ተጥዟል” ይላሉ፡፡ ከአማራና ከትግራይ ክልል የተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች ድርቁ የከፋ ጉዳት ባደረሰባቸው ዞኖች በመገኝት ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውንም የአገሪቱ ህወሓታዊ የሚዲያ ውጤቶች ይፋ ያደረጉት ጉዳይ ነው፡፡

እንደመረጃ ምንጮች  “በኦሮሚያ ክልል 5 ዞኖች በተራዛሚነት ቀጥሎ ባለው ድርቅ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን ለመርዳት እየተሄደበት ያለው የዕርዳታ መንገድ የድርቁን አስከፊነት በቅጡ ያልተረዳ አካሄድ ነው” ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ “በወር 14 ኪሎ ስንዴ እና ሁለት ሊትር ዘይት በቤተሰብ ደረጃ እየቀረበ፣ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለበት ሁኔታ፤ ድርቁን መቋቋም የማይታሰብ ነው” በማለት በማረጃ ያስረዳሉ፡፡ ከሁሉ በላይ አስጊ ሆኖ ያለው በዕርዳታ ማዕከሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የድርቅና የግጭት ተፈናቃዮች የተጠለሉ በመሆኑ እየታዩ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች መሆናቸውን የጎልጉል የአካባቢው ምንጮች  ይጠቁማሉ፡፡

ከሌሎች ክልሎች ለፖለቲካ ፍጆታ የሚላኩ 20 እና 30 የህክምና ባለሙያዎች በየዕርዳታው ማዕክሉ የተከሰተውን የአተት በሸታ ለመቆጣጠር በቂ እንዳልሆኑ የሚገልጹት የጎልጉል ምንጮች፤ ማዕከላዊው አገዛዝ በጤና ሚኒስቴር በኩል  በርከት ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ዕርዳታ ማዕከሎችና ንዑስ ጣቢያዎች  በመላክ  የህክምና ድጋፍ ማድረና ካልጀመረ በተላላፊ በሸታዎች የዜጎች  ህይወት ሊያልፍ  እንደሚችል የስጋት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይሁንና ኦሮሚያን የመበቀል ስሜቱ ገና ያልበረደ እንደሆነ በሚያሳብቅ መልኩ ማዕከላዊ “መንግስቱን” በበላይነት የተቆጣጠረዉ ህወሓት፤ በኦሮሚያ  አምስት ዞኖች በተራዛሚ ለተከሰተው ድርቅ የረባ ሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ  አልታየም፡፡

“ፀሐይ በምዕራብ ወጣች” እንደማለት ያለ የማይታመን ዜና ቢሆንም  የትግራይ ክልል ለኦሮሚያ ክልል የዕርዳታ እህልና የህክምና ባለሙያዎች በመላክ “ድጋፍ” ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ወተት እንደውሃ ሊፈልቅበት  ከሚችለው የቦረና ምድር ከመቀሌ የተጫነ ስንዴ ተራግፎበታል፡፡ ዜናው ክልሉን “እየመራሁት ነው” ለሚለው ኦህዴድ ብቻ ሳይሆን ለኦሮሞ ህዝብም የአደባባይ ስድብ ነው በማለት ጉዳዩን የሚከታተሉ ይናገራሉ፡፡ ድርቁ በተራዛሚነት  የቀጠለባቸው በተለይም ጉጂና ቦረና ዞን አካባቢያዊ ሃብት ላይ ያተኮረ የአዋጭነት ፖሊሲ ጥናት ተደርጎ በአካባቢው ያለውን የቁም  እንሰሳት ሃበት ለሥጋ እና ለወተት ልማት ማቀነባበሪያነት ለማዋል የሚያስችል የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጥ ለኦህዴድ ከተፈቀደለት መስመር በላይ አልፎ እንደመጫወት ያለድፍረት ነውና ከጥይት እና ከአሰቃቂ እስር  የተረፈዉ የኦሮሞ ህዝብ በረሃብ እንዲረግፍ ተፈርዶበታል፡፡ ለጊዜው ፍርዱ በጉጂና በቦረና ከብቶች ላይ ተፈፃሚ ሆኗል፡፡

ከ2007 ዓም ጀምሮ በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ እጥረት በታየባቸው ጉጂ እና ቦረና ዞኖች ያሉ አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው ቀርቶ ራሳቸውን ለመመገብ ተስኗቸዉ አስከፊ የችጋር ጊዜያትን እያሳለፉ ይገኛል፡፡ በሁለቱ የአርብቶ አደር ዞኖች በ2009 ዓ.ም ብቻ 127,010 የቁም እንሰሳቶች እንደሞቱ በክልሉ ከእንሰሳት ጥበቃና እንክብካቤ ጋር በተያያዘ ከሚሰሩ የግብረሰናይ ድርጅት ሠራተኞች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ መረጃ እየተጠናቀረ በነበረበት (መጋቢት ሁለተኛ ሳምንት 2009 ዓ.ም) ወቅት በሁለቱም ዞኖች የቁም እንሰሳት ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው በአማካይ ከ75% – 90% የሽያጭ ዋጋ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡

ለአብነት በቦረና ዞን “ቡሌ ሆራ” እና “ዳግዳ ዳዋ” ወረዳዎች ያለውን የእንሰሳት ዋጋ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-

እንሰሳት ከድርቁ በፊት  የነበረበት የሸያጭ ዋጋ ድርቁ በተከሰተበት በአሁኑ ወቅት ያለዋጋ የገበያ ልዩነት
በሬ 12,000 -16,000 ብር 3,000 – 5,000 75% – 68%
ላም 7,ዐዐዐ – 11, 000  ብር 2,000 – 3,500 71% – 68 % 
ፍየል 1,100 – 2200 ብር 120 – 180 89% – 92%
Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ከዚህ በላይ የተጠናቀረው መረጃ በቦረና ዞን በሁለት ወረዳዎች ያለውን የቁም እንሰሳት የሽያጭ ዋጋ በአማካይ ደረጃ የቀረበ ቢሆንም፤ ድርቁ ባጠቃቸው  በጉጂ፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ያለው የቁም የእንሰሳት የሽያጭ ዋጋ ከዚህ ብዙም የተለየ እንዳልሆነ የጎልጉል የአካባቢው ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

“እንሰሳቱ በመኖ እጥረት የተነሳ እጅግ የተጎሳቆሉ በመሆናቸው የሸያጭ ዋጋቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ አነስተኛ ሊሆን ችሏል”  የሚሉት የመረጃ ሰዎቻችን፤ በቦረና ዞን ውሰጥ “አሬሮ”፣ “ተልተሌ”፣ እና “ዲሎ” ወረዳዎች በነፍስ ወከፍ እስከ 123 ከብቶች የሞቱባቸው አርብቶ አደሮች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህን አርብቶ አደሮች በምን ሁኔታ መልሶ ማቋቋም እንደሚቻል ግራ የገባቸዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሰራተኞች “ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን በሰፊው ሊዘረጋ ይገባል” ይላሉ፡፡ በአንፃሩ  “አገሪቱ በሁለት አኻዝ የሚቆጠር እድገት እንድታስመዘግብ አደረኳት” የሚለን ህወሓት፤ ለድርቁ ባሳየው ቸልተኝነት አርብቶ አደሮች ከቀያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር ባዶ እጃቸውን እንዲቀሩና የተላላፊ በሽታ ተጠቂ  እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል!

የድርቁ አስከፊ ጉዳት (ተጽዕኖ) በርከት ያሉ ትምህርት ቤቶችን እስከማዘጋት ደርሷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ
ሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኘው  የተባበሩት መንግሥታት የዕርዳታና የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅት (UNPOCHA)  “Ethiopia፡ Activities and Resource Gap for Closed schools in Drought Affected Areas of Oromia and Somalia Regions” (በኢትዮጵያ ድርቅ  በተጠቁ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች በተዘጉ ት/ቤቶች ያለው የእንቅስቃሴና የሃብት ክፍተት) በሚል ባወጣው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል በድርቅ በተጎዱ ዞኖች 141 ት/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ 44,751 ተማሪዎች ትምህርታቸውን  አቋርጠዋል፡፡

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት ይህን ሪፖርት ይፋ ካደረገ በኋላ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች በተፈጥሮ ሃብት  ቅርምት በተነሳ ግጭት በድንበር አካባቢ የሚኖሩ 35,000 አባወራዎች የግጭት ተፈናቃይ ሆነዋል፡፡ አራት የኦሮሚያ ዞኖች ከሶማሌ ክልል ጋር ይዋሰናሉ፡፡ በእነዚህ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ከግጭት ጋር በተያያዘ 94 ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ እንደተዘጉ በክልሉ የግብረሰናይ ድርጅቶች አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በድርቁና በድንበር አዋሳኝ ቦታዎች በተነሱ ግጭቶች የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ቁጥር በድምሩ 241 ደርሰዋል፡፡ 114,751 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ ከድርቅና የግጭት ተፈናቃዮች ውስጥ 76,000 ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት (ዕድሜቸዉ ከ6-7 የሚገመት) ይገኙበታል፡፡

በአምስት የኦሮሚያ ዞኖች ተራዛሚነቱን እያሳየ ያለው ድርቅ የከፋ ማህበራዊ ቀውስ እያደረሰ ይገኛል፡፡ ኦሮሚያ የኢትዮጵያ የምግብ እጥረት መገለጫ  ሆናለች፡፡ የረሃብ ሰለባ የሆኑ ወላጆች ህፃናት ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ አልሚ ምግብ ህልም ሆኖባቸዋል፡፡ በዕርዳታ ማዕከሎች  ተላላፊ በሽታዎች ተጨማሪ ስጋት ሆነዋል፡፡ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና የሌሊት ልብስ (ብርድ ልብስ) ዛሬም ድረስ የተፈናቃዮች ቀዳሚ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዓለምአቀፉ  ማህበረሰብ  በሚፈለገው መልኩ የእርዳታ እጁን ሲዘረጋ አልታየም፡፡

በህወሓት  የበላይነት የሚዘወረው ማዕከላዊ አገዛዝ “መንግሥትነቱን” ዘንግቶታል፡፡ ለአንድ ዘውግ የበላይነት ብቻ መትጋት የመንግስት ሚና አድርገው ቀጥለውበታል፡፡ በርግጥ በኦሮሚያም ሆነ በቀሪዉ የኢትዮጵያ ክፍል ድርቅንና ረሃብን መሻገር እንዲቻል ገዢነቱን የዘነጋውን ሥልጣን አምላኪውንና የኢኮኖሚ በዝባዡን ህወሓትንና አሽከሮቹን ከነ ማህበራዊ መሰረታቸው መናድ ብቸኛ አማራጭ ነው በማለት ለሁኔታው ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይናገራሉ፡፡ ድርቅና ረሃብ ለቀደሙት የኢትዮጵያ ገዥዎች   መውደቅ ምክንያት እንደሆነው ሁሉ ክስተቱ ዛሬም መደገሙ የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ ከተለያዩ ወገኖች ሲነገር ይሰማል፡፡ (የተወሰኑትን ፎቶዎች ያገኘነው እዚህ ላይ ነው)

goolgule.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *