• “አህያ ሲጠፋ እህል ማን ሊሸከም ነው? ሴት?!”
  • የአህያ ሥጋና ቆዳ ንግድ እንደ ህገወጡ የአውራሪስ ቀንድ ንግድ እንዳይሆን ተሰግቷል

“አህያ ልባችን ነው። አህያ ህልውናችን ነው። አህያ ቤተሰባችን ነው። አህያ ውለታውና ተግባሩ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ገዢዎቻችንም ቢሆኑ የአህያን ጥቅም በአግባቡ ያውቁታል። በበረሃ ሁሉን ችሎ እዚህ ያደረሳቸው አህያ ነው። እናም ጉዳዩ ከወሬ በላይ ነውና በሰከነ መልኩ ለማሰብ ፍላጎቱ ካለ ጊዜው ገናነው” ሲሉ የቱሉ ቦሎው ነዋሪ ይናገራሉ።

የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ያናገራቸው የቱሉ ቦሎ ነዋሪ እህል ነጋዴ ናቸው። እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ጉዳይ የሚደመደመው በጥያቄ ነው። እንዲህ ይላሉ “አህያ ሲመናመን ከገጠር ማን ተሸክሞ ወደ ገበያ ያመጣ? ያው የፈረደባት ሴት በወገቧ ልትሸከም?”

ለወትሮው “ሴት፣ የሴቶች መብት፣ የሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር …” በሚል ተቋቁመው በጾታ ስም ንግድ ከሚያካሂዱት ተቋማት ይህ ጉዳይ አለመነሳቱ ከፍተኛ ትዝብትን የጣለ ጉዳይ ሆኗል። በባልና ሚስት ጉዳይ ተንደርድረው በመግባት ፍቺን የሚያውጁት የሴት ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ማህበራት የአህያ እርድ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታውን ሳይሆን የችግሩን አሳሳቢነት እንኳን ለመጠቆም አለመሞከራቸው አሳፋሪ እንደሆነ ለዘጋቢያችን የጠቆሙት አሉ።

አህያ ለመግዛት ያቀዱና የቤት ውስጥ ጣጣቸውን ለማቃለል ያሰቡ እንዴት ነው ከቻይና ጋር ተወዳድረው የሚገዙት? የገጠሪቱ ኢትዮጵያ፣ በተለይም ኢህአዴግ የሚምልበትና 80 በመቶ ይሆናል የሚባለው አርሶ አደር በአህያ ከመጫን ወደ ጫንቃው እንዲዛወር፣ ሴቷም በጀርባዋ ወደመሸከም “እንድታድግ” መፍረድ አግባብ ነው? ይህ ጥያቄ ምላሽ ያስፈልገዋል። ለዛሬው “ሰባት ሚሊዮን አህያ አለን” የሚለው አስተሳሰብ መልስ እንደማይሆን ከወዲሁ እየጠቆምን፣ ጉዳዩን ችግሩ ካጋጠማቸው አገሮች ተመክሮ አንጻር እንየው። ቻይና በዓመት አራት ሚሊዮን የአህያ ሌጦ ትፈልጋለችና ኮታውን መሙላት የኢህአዴግ ተግባር ሊሆን ነው ማለት ነው።

የአፍሪካን አምባገነኖች በሚፈልጉት ጥቅም፣ ወንበራቸው እንዳይንገዳገድ እየረዳችና እየደለልች ሃብት የምትዘርፈው ቻይና የአህያ ፍላጎቷን ለማሟላት የተጠናከረ እንቅስቃሴ ላይ ነች። በዚሁ የዝርፊያ ተግባራቸው የተለያዩ አገራትን ረግጠዋል። እንዳሰቡትም አድርገዋል። በስተመጨረሻ ችግሩ ሊጋፉት የሚችሉት ባለመሆኑ ከተለያዩ የምዕራብና ሰሜን አፍሪካ አገራት ተባረሩ። የአህያ እርድ ንግድ የጣፈጣቸው ቻይናውያን በምትኩ ዓይናቸውን ወደ ምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ተክለዋል።

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

በራሷ ምድር የአህያ ፍላጎት መጨመርና የአቅርቦቱ መቀነስ ያሳሰባት ቻይና ጉዳዩ የአፍሪካ አህዮች ላይ ትኩረት እንድታደርግ አስገድዷታል። እኤአ በ1990ዎቹ 11 ሚሊዮን የነበረው የቻይና አህዮች ቁጥር በ2013 ወደ 6 ሚሊዮን ማጋደሉን የአገሪቱ የእንስሳት ዓመታዊ መጽሐፍ ያስረዳል። በዚህም የተነሳ በቀላሉ የሚደለሉትን የአፍሪካ አገሮች ተጠግቶ ማለቡ አማራጭ የሌለው በመሆኑ ቻይና ከዘመተችባቸው አገሮች መካከል በህገወጥ አህያ ንግድ የተጠለፈችው ደቡብ አፍሪካ ትጠቀሳለች።

በደቡብ አፍሪካ በአህያዎች ላይ የተካሄደው ህገወጥ እርምጃ ዜጎችን እያሳሰበ መጥቷል። አንዳንዶች “ንግዱ በህጋዊ መልክ ይካሄድ” ሲሉ ሌሎች ግን “በህጋዊ መንገድ ቢካሄድም ህገወጡን ንግድ ማስቆም አይቻልም” ሲሉ ይከራከራሉ።

ከሸኮናው እስከ ቆዳው በቻይናውያን ዘንድ የሚፈለገው አህያ በደቡብ አፍሪካ ዋጋው ከ30 ዶላር ወደ 160 ዶላር አሻቅቧል። ይህ ትርፋማ ንግድ የሳባቸው ህገወጥ ነጋዴዎች በቻይናውያን አስተባባሪነት በየቦታው የሚያገኙትን አህያዎች እየሸጡ ነዋሪውን ችግር ውስጥ መክተታቸውን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። “በዚህ አካባቢ አህዮች በነጻነት ይመላለሱ ነበር። አሁን ግን ምንም አህያ የማይታይበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚለው ደቡብ አፍሪካዊው የሞጎሳኒ መንደር ነዋሪ ነው። “እዚህ አካባቢ ያለነው ሰዎች የአህያ ሥጋ አንበላም፤ እንደሚታወቀው በአካባቢው ሥራ የለም፤ አህያ ያለው ግን ሠርቶ መብላት ይችል ነበር” በማለት ሌላኛው የመንደሩ ነዋሪ ለጃፓን ታይምስ ይናገራል።

የአህያ ዘራፊዎቹ ዋንኛ ትኩረታቸው ቆዳው ላይ ነው። ቻይና የአህያ ቆዳ በመቀቀል “ኢጂኣኦ” የተባለ ሙልጭልጭ መሳይ “ጄላቲን” ትሠራለች። ይህንንም በተለያዩ መድሃኒቶች ውስጥ በመጨመር ለደም ዝውውር፣ ሰውነትን ከበሽታ ለመከላከል፣ የራስ ማዞር፣ የዕንቅልፍ ዕጦትን፣ ሳል፣ የወር አበባ አለመስተካከልን ለመከላከልና ለማከም ይጠቀሙበታል። ሸኮናውም እንዲሁ ይኸው ሙልጭልጭ ጄላቲን የሚሠራበት ሲሆን ሥጋው ከከብት ሥጋ ይልቅ ጠቀሜታ አለው በሚል ቻይናውያኑ የአህያ ሥጋ በርገርና ወጥ በመሥራት ይመገቡታል። “ኢጂኣኦ” በመድኃኒት ውስጥ ካለው ጥቅም በተጨማሪ በሙቅ መጠጦች ውስጥ ሲጨመር ቶሎ ስለሚቀልጥ አብሮ ይጠጣል፤ ከኦቾሎኒ ምግቦች ጋር ተቀላቅሎም እንደ ሻይ (ቡና) ቁርስ ይቀርባል።

ቻይና ዴይሊ እንደሚለው ከሆነ፤ ቻይና በያመቱ 5ሺህ ቶን “ኢጂኣኦ” የምታመርት ሲሆን ለዚህም 4 ሚሊዮን የአህያ ሌጦ ያስፈልጋታል። ይህ የቻይና ፍላጎት በአህያ ስርቆትና ወንጀል መበራከት ህይወታቸውን ያቃወሰው ደቡብ አፍሪካውያኑ “አንድ የሆነ ነገር ካልተደረገ ልክ የአውራሪስ ቀንድ በህገወጥ መንገድ መሸጡ ያስከተለብን ዓይነት ቀውስ አሁን ደግሞ በአህያ ሌጦ ፍላጎት ተመሳሳይ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው” ይላሉ። ይህ ሁኔታ ለቻይናውያኑን በህጋዊ መንገድ የአህያ ቄራ እንዲከፍቱ መንገዱን የጠረገላቸው ይመስላል።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ጃፓን ታይምስ እንደዘገበው፤ ከጥቂት ወራት በፊት በጆሐንስበርግ ፖሊስ ከ5ሺህ በላይ የአህያ ሌጦ በቁጥጥር ሥር አውሏል። በአንድ ወቅት የአንዲት መሸታ ቤት ባለቤት ከሆነ ቻይናዊ ጊቢ ውስጥ በርካታ የአህያ ቆዳ መገኘቱን የፖሊስ ዘገባን የጠቀሰው ዜና ያስረዳል።

ሕገወጡን ንግድ ለመቆጣጠር በሚል ደቡብ አፍሪካ ወደ ህጋዊ የአህያ ንግድ ሥርዓት ለመግባት እየተንደረደረች ትገኛለች። አጎራባች የሆነችው ቦትስዋና በህጋዊ መልኩ የአህያ ውጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ወደ ቻይና ጀምራለች። ናሚቢያ ደግሞ የቻይናን የአህያ ገበያ ፍላጎት ለማሟላት ቄራ ግንባታ ላይ ነች። በስልት የተቀነባበረው ህገወጥ ንግዱ የፈጠረው ቀውስ ህጋዊ ዕውቅናን አስገኝቷል። “ከቀውስ ውስጥ ሥርዓት” ይሏል ይህ ነው።

በተቃራኒው በአህያ ንግድ ላይ በህጋዊ መልኩ ተሰማርተው የነበሩ የምዕራብና ሰሜን አፍሪካ አገራት በንግዱ ላይ ዕቀባ አድርገዋል። ቡርኪናፋሶ ማንኛውም ወደ ኢስያ የሚደረግ የአህያ ሥጋና ሌጦ ላይ ዕገዳ አድርጋለች። ባለፉት ሦስት ወራት ቡርኪናፋሶ 18ሺህ አህዮችን ለዓለምአቀፍ ንግድ ስታቀርብ ይህ አኻዝ ካለፈው ዓመት በአንድ ሺህ የጨመረ መሆኑ ታውቋል።

የኒጀር መንግሥት በበኩሉ በአገሪቱ ክልል ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውንም የአህያ እርድ አቅቧል። እኤአ በ2015 27ሺህ ብቻ የነበረው የአህያ ኤክስፖርት በያዝነው ዓመት በ200 እጅ ያህል በማደግ 80ሺህ አህዮች በቁማቸው ለኤክስፖርት መላካቸውን ቢቢሲ አፍሪካ ዘግቧል። በኒጀር የአንድ አህያ ዋጋ ከ34 ዶላር ወደ 147ዶላር ማደጉ የነዋሪውን ህይወት አቃውሷል። አህያን ለመጓጓዣ የሚጠቀሙት ገበሬዎችና ነጋዴዎች የዋጋ ንረቱ በቂ አህያ እንዳይኖራቸው ከማድረግ በተጨማሪ በሚያቀርቡት ምርት ላይ ተጽዕኖ አሳደሯል።

በምዕራብና ሰሜን አፍሪካ የተደረገው ዕቀባ ያሳሰባት ቻይና ፊቷን ወደ ምስራቅና ደቡባዊ የአፍሪካ አገራት አዙራለች። በናሚቢያና በቦትስዋና በህጋዊ መልኩ ፍላጎቷን እያረካች ካለችበት ሁኔታ በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካም እንዲሁ የአህያ ማረጃ ቄራዎችን እያቋቋመች ትገኛለች።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

በኬኒያ ሁለት የአህያ ቄራዎች በቀን እስከ 400 አህዮችን ያርዳሉ። ቆዳና ሥጋቸውን ለገበያ ያቀርባሉ። ባለቤቶቹ እንደሚሉት የአህያ ማርቢያና ማደለቢያም አዘጋጅተዋል። ሆኖም እያረቡ ማረዱ በቂ ስላልሆነ ከጎረቤት አገራት እስከ ታንዛኒያ የዘለቀ የአህያ አቅራቢዎችን መስመር ዘርግተዋል። ቻይናዊው ባለቤት እንደሚሉት በቀን ከ400 እስከ 600 አህዮች አንዱ በ77 ዶላር ሒሳብ ይቀርቡላቸዋል።

ለጥቂት መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል ከፍተዋል የሚባሉት ቄራዎች የሚያርዷቸው አህዮች ጉዳይ አንዳንድ የኬኒያ መንግሥት ባለሥልጣናትን እጅጉን አሳስቧል። በታረዱት ልክ የሚተካ አህያ ከሌለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀውስ እንደሚከሰት ስማቸው ያልገለጹ ምንጭ ለዴይሊ ኔሽን ተናግረዋል። ሆኖም ከተለያዩ ምንጮች የሚሰማው መረጃ እንደሚያመለክተው በኬኒያ ቅርብ ጊዜያት ውስጥ ተጨማሪ ቄራዎች እንደሚከፈቱ ነው።

ለአገር ውስጥ ፍጆታ ገና ባይቀርብም ኬኒያ እኤአ በ1999 የአህያ ሥጋ መብላት እንደሚቻል በሕግ ፈቅዳለች።

በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ በመቶ የሚቆጠሩ አህዮች ባለቤት የሆኑ ሃብታሞች አሉ። እነዚህ ባለሃብቶች የአህያ ሾፌር ቀጥረው ነው የሚያሰሩት። በግላቸውም አህያ ገዘተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ የቀን ሰራተኞችም አሉ። አንድ ላይ ሲደመር ችግሩ የሚፈጥረው ማህበራዊ ቀውስ የሰፋ ነው። ጎተራ ያለ አህያ አይሞላም። ማሳ ላይ ያለ ክምር ያለ አህያ አይነሳም። የገጠሩ ህዝብ አስፈጭቶ፣ ሸምቶና ሸጦ ወደ ደሳሳ ጎጆው የሚመለሰው በአህያ ነው። ሲራራ ነጋዴውም እንዲሁ። አህያ ትራንስፖርት ነው። የውሃ ጋሪ የሚስበው አህያ ነው። …

የአህያ ቄራ መከፈቱ ጉዳይ በበርካታው ሲወራ የሰነበተ ጉዳይ ቢሆንም የአህያ ማረጃ እስከመክፈት ሲደረስ በተለይ የሃይማኖት ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው የመደገፍ ያህል እንደሆነባቸው አንዳንዶች አስተያየት ሲሰጡ ተሰምተዋል።

ከላይ የቱሉቦሎው ነዋሪ እንዳሉት አህያ ለኢትዮጵያውያን ላባቸው፣ ህይወታቸው ነው። ምናልባት ህወሃት “የአህያውን ዘመን አልፌዋለሁና አይመለከተኝም” ካላለ!! “ደሳለኝ” ብለው የሚያቆላምጡት አህያ እንዳልነበራቸው አህያ እንዲጠፋ መቃብሩን ኦሮሚያ ላይ ተከሉ!! ልክ እንደ ሰይጣን ህወሃትም ወዳጅ የለውም!

goolgule.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *