• ኩባንያው 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሏል

በዳዊት እንደሻው

ሰርከም ሚኒራል የተባለው የእንግሊዝ የማዕድን ኩባንያ፣ የፖታሽ ማዕድን በአፋር ለማውጣት የሚያስችለውን ስምምነት ከማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና የሰርከም ሚኒራል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብራድ ሚልስ በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ ዓርብ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ተፈራርመዋል፡፡

ከፊርማው ሥነ ሥርዓት በኋላ ኩባንያው ሥራውን በሁለት ወራት ውስጥ ይጀምራል ተብሏል፡፡ ለኩባንያው የተሰጠው የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን የማውጣት ፈቃድ ለሃያ ዓመት ፀንቶ የሚቆይ ሲሆን፣ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረት የፈቃድ ዕድሳት ጊዜ ከአሥር ዓመታት ላልበለጠ ጊዜ ሊታደስ ይችላል፡፡

ይህ የማዕድን የማውጣት ፈቃድ ኩባንያው በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢ በ365 ኪሎ ሜትር ካሬ ውስጥ የሚገኝ 4.9 ቢሊዮን ቶን የፖታሽ ማዕድን ላይ መብት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

ከፖታሽ ማዕድን ጋር በተያያዘ ሰርከም ሚኒራል ማዕድኑን የማውጣት ፈቃድ ያገኘ ሁለተኛው ኩባንያ ሆኗል፡፡ ከአሁን ቀደም አላና ፖታሽ የተባለው የካናዳ ኩባንያ ፈቃዱን አግኝቶ ነበር፡፡ በቅርቡም ያራ የተባለው ዓለም አቀፍ ኩባንያ የፖታሽ ማዕድን ለማውጣት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ጥያቄውም በመንግሥት እየታየ እንደሆን ተገልጿል፡፡ ያራ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸውን ማዳበሪያዎች ለብዙ ዓመታት ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በፖታሽ ላይ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዳሎል ብቻ 12 ቢሊዮን እስከ 14 ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ የፖታሽ ማዕድን አለ፡፡

ሰርከም ሚኒራል ከዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖታሽ ፍለጋ ላይ ነበረ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በዳሎል ጥናት እንዲያደርግ ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢው ላይ ማዕድኑን ማግኝት እንዳቻለ አሳውቆ ነበር፡፡

እስካሁን ባለው ቆይታ ኩባንያው ወደ 65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከአሁን በኋላ በአምስት ዓመት ውስጥ ፖታሽ ማምረት ይጀምራል ተብሏል፡፡

በአጠቃላይ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያወጣ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተነጋገረ እንደሆነ ኩባንያው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ሰርከም ሚኒራል በዓመት 2.75 ሚሊዮን ቶን ፖታሽ እንደሚያመርት፣ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋው ፖታሽ እንደሆነና ቀሪውን ፖታሽየም ሰልፌት ዳሎል ከሚገኘው ፕሮጀክቱ ያመርታል ተብሏል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ የፖታሽ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መቀነሱ ይታወሳል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት 570 ዶላር በቶን ሲሸጥ የነበረው በአሁኑ ጊዜ ወደ 214 ዶላር ወርዷል፡፡

ሰርከም ሚኒራል የሚያከናውነው ፕሮጀክት ከታጁራ ወደብ በ600 ኪሎ ሜትር ርቀት ይገኛል፡፡ ከፕሮጀክቱ እስከ ወደቡ የሚያገናኙ መንገዶችን ለመገንባት መንግሥት እየሠራበት አንደሆነ፣ በፊርማው ላይ የተገኙት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡

ከፕሮጀክቱ ጋራ የሚያገናኙ መንገዶችን ለመገንባት በቅርቡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የግንባታ ውል እንደተፈራረመ ይታወሳል፡፡

በዋናነት ኩባንያው የውጭ ገበያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ሊገነቡ ለታቀዱ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችም ፖታሽ ማቅረብ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

በቅርቡ የሞሮኮ መንግሥት በኢትዮጵያ የማደበሪያ ፋብሪካ በ3.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያቋቁም መግለጹ ይታወሳል፡፡ ፋብሪካው ሲጠናቀቅ በዓመት 3.7 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ያዩ የተባለው የማዳበሪያ ፋብሪካ በብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥር በግል ኩባንያዎች እየተገነባ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 300 ሺሕ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወደ አገር ውስጥ ተገዝተው በሚገቡ ማዳበሪያዎች ጥገኛ ለሆነው የኢትዮጵያ ገበያ፣ በመንግሥት በሺዎች ቶን መጠን ይቀርብለታል፡፡

Reporter Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *