“Our true nationality is mankind.”H.G.

በፈረሰችው የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ “ፓትርያርኩ” የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን አሳሰቡ

“የሕዝበ ክርስቲያኑ ሮሮ ተባብሶ አቅጣጫውን ከመለወጡ በፊት ፍትሕ ርትዕ የተሞላበት ዳኝነት ይታይ” /ፓትርያርኩ/

–    “ይዞታ በስጦታ ተገኘ በሚል ብቻ ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ አይችልም” /የከንቲባው ጽ/ቤት/

–    ደብሩ፣ በወረዳው ሥራ አስፈጻሚ እና የደንብ ማስከበር ሓላፊዎች ላይ ክስ መሠረተ

 aaderiba.jpg

በአዲስ አበባ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12፣ አባዶ ቁጥር 1 እየተባለ በሚጠራውአካባቢ የተሠራችው፣ የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፥ ድፍረት በተመላበት ኃይልና ሥልጣን፣ በወረዳው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት እንደፈረሰች ፓትርያርኩ የጠቀሱ ሲኾን፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያሰማው ሮሮ ተባብሶ አቅጣጫውን ከመለወጡ በፊት፦ ፍትሕ ርትዕ የተሞላበት ዳኝነት ታይቶ፣ የፈረሰው ተጠግኖ፣ የጎደለው ተሟልቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል አመራር ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍ ከንቲባ ድሪባ ኩማን አሳሰቡ።

የደብሩ ይዞታና ግንባታ፣ ሕገ ወጥ ነው፤ በሚል ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትፈርስ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የይግባኝ ቅሬታ ቀርቦበት እንዳይፈጸም ታግዶና በቀጠሮ ላይ እያለ፣ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በሚያሳዝን ኹኔታ፣ ታቦተ ሕጉ ያለበት መቃኞ ቤተ ክርስቲያን በመፍረሱ፥ ንዋያተ ቅድሳት ተመዝብሯል፤ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንም የድፍረት ሥራ ተፈጽሞባቸዋል፤” ብለዋል ፓትርያርኩ፣ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ ለከንቲባው በጻፉት ደብዳቤ።

የከተማው አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ ሳይታወቅና ጉዳዩ በቀጠሮ ላይ እያለ፣ በወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሠራተኞች የተፈጸመው ድርጊት፣ አፍራሽ ተልእኮ ያለውና ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት መኾኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ “ለሕግ የበላይነት ትኩረት አለመስጠትን ያመለክታል፤” ሲሉም ተችተዋል።

ምእመናን ከመንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይርቁ፣ በየአቅራቢያቸው ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት ቤተ ክርስቲያን እያቋቋሙ፣ ከርቀት ጉዞ በመታደግ የሥራ ተነሣሽነት እንዲኖራቸው ማስቻል፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሀገራዊ ልማት ባላት አስተዋፅኦ ኅብረተሰቡን የምትደግፈበት አገልግሎትዋ እንደኾነ ፓትርያርኩ አስገንዝበዋል።

ይኹንና መንግሥት ለዜጎች ባመቻቸው የየካ አባዶ ቁ.1 ኮንዶሚኒየም አካባቢ፣ ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች በተሰጠ ሕጋዊ ይዞታ ላይ ተሠርታ ላለፉት አራት ወራት አገልግሎት ስትሰጥ የቆየችው የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፣ ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል በመፍረሷሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያሰማው ሮሮ ተባብሶ አቅጣጫውን ከመለወጡ በፊት ፍትሕ ርትእ የተሞላበት ዳኝነት እንዲታይ፣ ፓትርያርኩ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል። “የፈረሰው ተጠግኖ፣ የጎደለው ተሟልቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል አመራር” ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍላቸውም ከንቲባውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም አሳስበዋል።

ፓትርያርኩ ለጻፉት ማሳሰቢያ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ በከንቲባው ጽ/ቤት በኩል ምላሽ እንደተሰጣቸው የጠቀሱት የደብሩ ካህናትና ምእመናን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ግንባታ ሕገ ወጥ እንደኾነና ቤተ ክርስቲያን ሊባል እንደማይችል፤ ይዞታው ከግለሰቦች የተላለፈበት የስጦታ ውልም፣ በውልና ማስረጃ ያልተረጋገጠ በመኾኑ ተቀባይነት እንደሌለው በሓላፊው በኩል እንደተነገራቸው አስታውቀዋል። አክለውም፣ የፈረሰችውን የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በወረዳው በቅርቡ ከተሠሩ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋራ በተያያዘ፣ በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ አዘጋጅነት በቅርቡ የተካሔደው የሽልማት መርሐ ግብር ተገቢ እንዳልነበረ ሓላፊው መተቸታቸውን ተናግረዋል፤ የይዞታ መብት በስጦታ ተገኘ በሚል ብቻ ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ እንደማይችልና የከተማውን ማስተር ፕላን በጠበቀ መልኩ ከሚመለከተው የከተማው አስተዳደር አካል ጋራ በመነጋገር የግንባታ ፈቃድ አስቀድሞ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተገልጾልናል፤ ብለዋል።

ነገር ግን፣ ማሳሰቢያው የተጻፈው በቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ እንደመኾኑና ባለአድራሻውም የከተማው ከንቲባ እንደመኾናቸው ጉዳዩ ደረጃውን ጠብቆ ምላሽ ሊሰጠው ይገባ እንደነበር ቅሬታቸው የገለጹት ካህናቱና ምእመናኑ፣ በጽ/ቤቱ የተስተናገዱበት ኹኔታ “ክብረ ነክ ነው፤” ሲሉ አማርረዋል፤ “እናንተን ማስተናገድ አይገባኝም፤ ውጡ እንዲያውም” መባላቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ ከይዞታና ከግንባታ ሕጋዊነት ጋራ በተያያዘ የፈረሰችው የየካ አባዶ ደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፥ ለይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ አለመከበር ተጠያቂዎች ናቸው ባላቸው፦ የወረዳ 12 የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሓላፊ፣ የአስተዳደሩ ሥራ አስፈጻሚ ሓላፊና በሌላ ሠራተኛ ላይ ክሥ መመሥረቱ ታውቋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትፈርስ በሥር ፍ/ቤት የተላለፈው ውሳኔ ላይ፣ በደብሩ የቀረበው የይግባኝ ቅሬታ ተመርመሮ ትእዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ተፈጻሚ እንዳይኾን የታዘዘበትን እያሳየናቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ማፍረሳቸው፣ የሕግ የበላይነትን አለማረጋገጥ፣ ሕጉና መናቅ ነው፤ ይላሉ፣ የደብሩ ካህናትና ምእመናን። ችሎቱ፣ የተከሣሾችን መልስ ለመስማት፣ ለሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. መቅጠሩ ተገልጿል።

http://www.sendeknewspaper.com

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0