” አንዱ መላ ምት ግንቦት ሰባት ከሻእቢያ እየተፋታ ነው የሚለው ነው “

ጠንቋይና አፖለቲከኛ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። ሁለቱም ተገልጋያቸውን ለማምታታት የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየርን ተክነውበታል።
ውበታል።isaiasኢሳያስ አፈወርቂ በዚህኛው – የኦሮሚያ መዲያ ኔትወርክ ገለጸቸው ራሳቸውን ሳይቀይሩ ሌላውን ለመቀየር የተነሱ ግብዝ ነው የሆኑት።

ይህ “ቃለ-ምልልስም” አንድ አላማ አለው። አላማውን ለማወቅ ቃላቶችን መሰንጠቅም አያስፈልግም። ግልጽ ነው።   ‘ብዙ ስላልተሰራበት’ መልዕክቱ የተጠበቀውን አላማ የመታ አይመስልም።  ቃለ-ምልልሱ የተደረገበት ወቅት፣ የተመረጠበት ሰዓት የሚሰጠን ግልጽ የሆነ ግን የተለየ ትርጉም  አለ።

ጠያቂዎቹ በሻዕቢያ ላይ የነበራቸው የፖለቲካ አቋም ከመቅጽበት መቀየሩ በራሱ የሂደቱን ግራጫ ምስል ያሳየናል።”ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል።” ይላሉ አበው።  እነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ መላ-ምቶችን መዘርዘሩ አስፈላጊ ባይሆንም (አንዱ መላ ምት ግንቦት ሰባት ከሻእቢያ እየተፋታ ነው የሚለው ነው)፣ ይህንን የፖለቲካ ሂሳብ ለመቀመር ግን ሮኬት ሳይንቲስት መሆን የሚጠበቅ አይደለም።

ነቢያት በቀየሱ ሐዋርያት ገሰገሱ ነውና ነገሩ፣ ዞሮ-ዞሮ ያለፈ ታሪክ ሲደገም ነው የምናየው። ከሻዕቢያ ጋር በፍቅር መውድቁ እጅግ ቀላል እንደሆነ ከበርካቶች አይተነዋል። ከባዱ ነገር አብሮ መቆየቱ እንደሆነም ተገንዝበናል። የሰው ልጅ አንዴ ይሸወዳል። ሁለቴ ለመሸወድ ራስን ማሳመን ግን ብልህነት አይደለም። “ወደ ፊት የምንራመድ ከሆነ ታሪክን መድገም ሳይሆን አዲስ ታሪክ መፍጠር አለብን።” ይሉናል ማሀተመ ጋንዲ።

ይህች ጎንበስ-ጎንበስ ታዲያ የቁቤው ትውልድ የአስመራን “ወዳጅነት” ፍለጋ ለመሆንዋ የፖለቲካ አቡጊዳን ለቆጠረ አዲስ አይሆንም። ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ በዋዜማ ራዲዮ የኦሮሞ ወጣቶች ትግል በአስመራ ስለሟሟቅ የተናገርውን ተከትሎ – ከቁቤው ትውልድ ውግዘት ደርሶበታል። ውግዘቱ ባይኖር ነበር ሚደንቀው። ውግዘቱ ወደ ተለመደው የአበቱታ ፊርማ ላለማደጉም ዋስትና የለም።

ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው በሚል ብሂል ብቻ ተነሳስተን ፖለቲካውን ባልተገራ ፈረስ መጋለብ መሞከር የከፋ አደጋም እንዳለው ሳይረዱት ቀርተው ሊሆን አይችልም። በዲፕሎማሲ ሀ-ሁ “ቋሚ ወዳጅ እና ቋሚ ጠላት የለም” ተብሎ ብቻ የቅርቡን ትዝታ ወዲያ ብለው፣ በብርሃን ፍጥነት የሚጓዙበት ጉዳይም አይደለም።  ከነዚህ ሁሉ ቀደም ብለው የሚወራረዱ ሂሳቦች ይኖራሉ። ለመቀበል በመጀመርያ መስጠት ግዴታ ነውና። ኢሳያስ አፈወርቂ ይህንን ሁሉ ለጽድቅ እየሰሩት እንዳልሆነ ሕጻን ልጅም አያጣውም።

ግና የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የቀረው “ብቸኛው አማራጭ የትጥቅ ትግል ነው።” እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በጦር ተደራጅተው ለአመታት አስመራ የመሸጉት ኦቦ ዳውድ ኢብሳን እብብታቸው ስር ሸጉጠው፤  ይልቁንም እነ ጃዋር መሃመድ እንደ ሸቀጥ የሚያዞሩትን የ”ኦሮሚያ አብዮት” ወደ አስመራ ለማስገባት መጣራቸው የሚደነቅ ነው።  ይህንን ለማድረግ  ቃል መግባታቸው “የፖለቲካ ዝሙት”  ብቻ ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ የምትካሄደዋ እያንዳንድዋ እንቅስቃሴ የአስመራ ይሁንታ እንዲኖራት የሚደረግ ሸፍጥም አለበት።

***

በኦሮሚያ ሜድያ ኔትወርክ የቀረበው ጉዳይ “ቃለ ምልልስ” ነው? ውይይት ነው?ወይንስ የኢሳያስ አፈወርቂ የአቋም መግለጫ?… የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳቱም ተገቢ ይመስላል። ጥያቄው ከመልሱ ሲረዝም፣ ጥያቄዎች ተጽፈው ቀርበው ሲነበቡ እና ጠያቂዎች ፈራ-ተባ እያሉ፤  አንዳንዴም በፈገግታ ሲናገሩ ከተጠያቂው ተሰጡትን የቤት ስራዎች መስራታቸውን ያሳብቃሉ።  በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ቃለ-ምልልስ ራሱን የቻለ ጥበብ እና አካሄድ አለው። ጠያቂው ከተጠያቂው በልጦ ካልተገኘና፣  ባላመነበት ጉዳይ ተጠያቂውን መሞገት ካልቻለ …ነገሩን ቃለ-ምልልስ ነው ልንለው ይከብደናል። ከጠያቂዎቹ (ገረሱ ቱፋ እና ደረጀ ሃዋዝ) የሚሰነዘሩት ጉዳዮች በሙሉ ስለ ኦሮሞ እና በኦሮሚያ የተቃኙ ናቸው። ኢሳያስ አፈወርቂ የሚሰጡት ምላሽ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ነው። ሁለቱ አልተጣጣሙም። ፕሬዝዳንቱ የሚጠየቁትን ሳይሆን ማስተላለፍ የፈለጉትን ነገር ነበር የሚናገሩት።

ህዝባዊ አመጹ የሃገሪቱን ፖለቲካ ለወራት እያናወጠው በነበረበት ግዜ፣ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ አስመራ ላይ ተኝተዋል። ሃገር ሲደበላለቅ፣ እሳቸው ልክ እንደ ሕጻን ልጅ ተጋድመው ከባድ እንቅልፍ ወስዷቸው ነበር። የሱናሚው ማዕበል ነበር ከዚያ ለ20 ዓመታት ክተኙበት ከባድ እንቅልፍ ቀስቅሶ ያነቃቸው። ከእንቅልፋቸውም ሲነቁ እንዲህ አሉ።

“ሕዝባዊ አመጹን እየመራሁ ያለሁት እኔ ነኝ!”

ይህ አነጋገራቸው ከፌስ ቡኩ አርበኛ ከጃዋር መሃመድ ጋር ገመድ ያጓትታቸው እንጂ ለወያኔ ግን ጃክፖት ነበር የሆነለት። ይህንን ማለታቸው፣ የኦሮሞን ወገን እንዲመታ ለወያኔ ቦንብ አቀበሉት። ያንን ግዙፍ የህዝብ ንቅናቄ የኦነግን ኩታ አልብሰውና በስልቻ ልክ አጥብበው ድባቅ እንዲመታ አደረጉት።

ኢሳያስ አፈወርቂን ገረሱ ቱፋ ስለ አመጹ ጠይቋቸው ሲመልሱ፤ “በዚያ የሱናሚ ማእበል ውስጥ የአንድም ፖለቲካ ድርጀት እጅ የለበትም። የሕዝብ በደል ለሁለት አስርተ አመታት ተጠራቀሞ በመጨረሻ ፈነዳ” ነበር ያሉት።

ይህንን በተናገሩ ግዜ በጉያቸው አንቀላፍቶ ለታሪክ ሽሚያ የነቃው ዳውድ ኢብሳ እጅግ አሳዘነኝ። እጉድጓድዋ ተደብቃ እንደምትቁለጨለጭ ትንሽ አይጥ መሰለኝ። ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ ኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር የተናገሩት በዚህ አላበቃም። ሰለ ድርጅቱ በተደጋጋሚ የሚናገሩት “የታሪክ ስህተት” ጉዳይም ያስደምማል። አንደኛው 20 ሺ የሚያህል የኦነግ ሰራዊት እሳቸው መርገምት ብለው ለሚጠሩት ወያኔ አስረክበው መፈርጠጣቸው። ይህ ታሪካዊ ስህተት አሁን ውጤቱ እየታየ ሰለሆነው ጉዳይ ሲሆን፤  ሁለተኛው ደግሞ የአማራ ሕዝብ ጨቁኗል እየተባለ የሚነገረው ፍጹም ሃሰት እንደሆነ በዚህ ገለጻቸው ማስረገጣቸው ነው። ልብ እንበል። ጠያቂዎቹ ጃዋር መሃመድ ከሚመራው የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ ናቸው።

ኢሳያስ አፈወርቂ “የገዥ ቡድን እንጂ የአማራ ጨቋኝ አልነበረም። ይህ የወያኔ ፈጠራ ነው። ይህ ዘራፊ ቡድን እንዲህ ካላደረገ መቆየት አይችልም።” ባይ ናቸው። አማራ የኦሮሞ ጠላት ሆኖ አያውቅም ከሚለው ተነስተእ፣   የአማራው ሕዝብ ሲጨቁን ነበር እየተባለ የሚነገረው ብሂል ስህተት እንደሆነ ሲናገሩ ለመጀመርያ ግዜ መሆኑ ነው። ለዚያውም በኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ።

ወያኔ ያጎረሳቸውን ሁሉ ሳያላምጡ ጥሬውን ውጠው፣  በትላንት ላይ ለተጠመዱት ሁሉ ይህ ትልቅ መልእክት ይመስላል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩበት ምክንያት ከጀርባ ቢጠናም፣  ምክንያቶች ቢደረደርም – ባይደረደርም፤  መራራው ሃቅ ከአንደበታቸው ወጥቷል። ለማመን እንጂ ላለማመን ምክንያት የሚፈልጉ የሜዲያው መልእክተኞችም በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን ከመምረጥ ውጭ አማራጭ የነበራቸው አይመስልም። ከጀግናው ጃገማ ኬሎ ይልቅ ጃዋርን ለሚያደንቅ ትውልድ፣  ከአቡነ ጴትሮስ ይልቅ ለሊበን ዋቆ የሚያጨበጭብ ትውልድ አልሰማ ብሎ እንጂ የታሪክ ምሁራንም የሚነግሩን ይህንን ሃቅ ነው።

በ1991 (እ.ኤ.አ) የሽግግር መንግስቱ ሲመሰረት ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ አኢዮጵያ ታሪክ ሲናገሩ፣ ይህንን ተረት-ተረት እዚያው ዩኒቨርሲቲያችሁ ጣሉት ነበር ያሉት።  በዚሁ ቃለ-ምልልሳቸውም የምንኮራባቸው ኢትዮጵያ እሴቶች፤ በተለይ ደግሞ ያሃገሪቱ የሶስት ሺ ዘመን ታሪክ ተረት-ተረት (ሚት) ነው ይሉናል። ኢትዮጵያ ታሪክ እንደሌላት የሚያሳየውን ማስረጃ ግን አሁንም አላሳዩንም።

ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር በሕዝባቸው ላይ ያደረሰው መከራ አሁንም ትምህርት የሰጣቸው አይመስልም። ላለፉት 25 አመታት በባርነት የተያዘውና ለስደት የተዳረገውን የኤርትራ ሕዝብ ችግር ችላ ብለው አሁንም ስለ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥነት ነው የሚናገሩት።

በመላው ኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ውስጥ የኤርትራ እጅ አለበት መባሉ ኢሳያስ አፈወርቂን አስቋቸዋል። ምላሻቸው ባሳቅ ብቻ አላበቃም፤  “ይህንን ባደረግነውና ደስ ባለን ነበር። ግን ሁኔታዎች እና የአቅም ጉዳይ ሆኖ አላደረግነውም።” ይላሉ። ካሁን በኋላ ግን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም በሚል ቅላጼ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የመብት ትግል የመደገፍ ግደታ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ለውጡ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኙት እንደሆነ ገልጸዋል።Isayas

በኢትዮጵያ የሚደረገውን የለውጥ ትግል አስመራ በምን መንገድ ለመደገፍ ማቀድዋ ግልጽ ባይሆንም “የትጥቅ ትግሉ” ከትብብሩ ፓኬት ውስጥ ለመውጣቱ ግን ጨረፍ አርገውታል።

የኤርትራ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለትጥቅ ትግሉ ድጋፍ አስቸጋሪ እንደነበርም ኢሳያስ ሳይናገሩ አለለፉም።  የሁኔታዎች አለመምቻቸት እና የአቅም ጉዳይም ድጋፍ እንዳይደረግ አስተዋጻኦ አድርገዋል ይላሉ አይቴ ኢሳያስ አፈወርቂ።

ስርዓቱን በጦር ለመፋለም የወሰኑ ሃይሎች ወደ አስመራ ያመሩት ኤርትራ በኮሪደርነት እንድታገለግላቸው ነበር። ጦርነት ፋይዳ የሌለው መሆኑን ኢሳያስ የሚነግሩን ከሆነ ታዲያ “ካሁን በኋላ ለመርዳት” ያሰቡት ምንድነው? ለጦርነት ካልሆነ ኤርትራ መግባቱ ለምን አስፈለገ?  ሰላማዊው ትግሉም የነሱን ቡራኬ ይሻል ማለት ነው?

ከዚህ ሁሉ የትጥቅ ትግል እና የጦርነት ወሬ በኋላ “ሁኔታዎች አላመቹምና፤ “የሽግግር መንግስት” እንደገና እንዲቋቋም ሃሳብ ሰጥተዋል።  “በ1991 ድል ተቀዳጅተናል። ያለምነው ነገር ግን ግቡን አልመታም። 25 ዓመት እንዲሁ ባክኗል፣ አሁን የምመክረው ሁሉም የሚሳተፍበት የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ነው።” ብለዋል። አዲዮስ!  ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ተከካም ተቦካ ትልቁ ዳቦ ግን እዚህ ላይ ሊጥ ሆነ!

– ክንፉ አሰፋ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *