“ወራሪው የኢጣሊያ ሰራዊት የአገራችንን ሉዓላዊነት በተዳፈረበት ወቅት በአራቱም አቅጣጫ የኢትዮጵያን ድንበር ለመጠበቅ የተዘጋጀ ጦር አልነበረም፤ የወታደራዊ መሰረተ ልማቶችም እንዲሁ፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይም በምስራቁና በደቡብ ምስራቁ የኢትዮጵያ ድንበር የባሰ ነበር፤ እናም ፋታ የማይሰጠውን የኢጣሊያኖች ጥቃት የሚመክት ሃይል በአስቸኳይ ማደራጀት ነበረባት፤ኢትዮጵያ ይህን የሚያስተባብርና ድንበሯን ከጠላት የሚታደግ የቁርጥ ቀን ልጅ ትፈልግ ነበር፡፡ የጀግና መካን ሆና የማታውቀው ኢትዮጵያ፤ ለጥሪዋ ፈጣን ምላሻቸውን የሰጡ ታላላቅ ጀግኖች ለማግኘት አልተቸገረችም። በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ በሶስት አቅጣጫ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ የገባውን የፋሺስት ሀይል ለመፋለም ከፊት የቀደሙት በምዕራብ በኩል ግራዝማች መኩሪያ ተሰማ፣ በመሃል ግንባር ደጃዝማች በላቸው፣ በምስራቅ ግንባር ደግሞ ቆራጡ ጦረኛ ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ታላላቅ የጦር አዝማቾች መካከል በቆራጥነታችውና በውጊያ ጽናታቸው በይበልጥ ስማቸው የሚነሳው አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ናቸው። ግራዝማች አፈወርቅ በኮሎኔል ማቲሊ እየተመራ በምስራቅ በኩል የገባውን የፋሺስት ወራሪ ሀይል የመመከት ታላቅ ሀላፊነት ሲወስዱ እድሜአቸው ገና 29 ብቻ ነበር፡፡

ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት በጊዜው አጠራር የሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ልዩ ስሙ አቃቂ በሰቃ በሚባለው አካባቢ በ1898 ዓ.ም ተወለዱ፤ ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስም በባህላዊው የትምህርት ስርዓት አልፈው መሰረታዊ ዕውቀትን አግኝተዋል፡፡ በስራ ህይወታቸው በመጀመሪያ በምስለኔነት፣ በኋላም የጅግጅጋ አውራጃ አስተዳዳሪ ነበሩ፤ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ደግሞ የቆራሄ አውራጃ አስተዳዳሪና የጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ግራዝማች አፈወርቅ ወይዘሮ ተዋበች ካሴ ከተባሉ ሴት ጋር በትዳር ተጣምረው አምስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
ግራዝማች አፈወርቅ የጊዜውን ታላቅ አገራዊ ሀላፊነት እንደወሰዱ፣ ውለው ሳያድሩ ነበር ወደትግበራ የገቡት፤ በዚህም በጥቂት ጊዜያት በርካታ ምሽጎችን በመገንባት ጠላትን ለመመከት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ፡፡ በኦጋዴን ወታደራዊ ካምፖችን የመመስረቱን ስራ የጀመሩት ገርለጎቢ በሚባል ቦታ ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት በኋላም በቀብሪደሃር ላይ ጠንካራ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ችለዋል፡፡ የቆራሄው አንበሳ አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ጠንካራ ምሽጎችን ከመገንባት ባለፈ የወታደራዊ ስለላ መረብ አደራጅተው ነበር። በዚህም የጠላትን የውጊያ ዕቅዶችን ቀድመው በመረዳት በተደጋጋሚ የፋሺስትን ጥቃት ለማክሸፍ ችለዋል፡፡ የኢጣሊያ ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ወታደሩ ምግብና ውሃ የሚያገኝበትን መንገድ መቁረጥ ነበር፤ ነገር ግን ግራዝማች አፈወርቅ ጠንካራ የሶማሌ ሰላዮች የነበራቸው በመሆኑ አልሰመረለትም። የፋሺስት ጦር ከተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራ በኋላ ተሳክቶለት አዶ፣ ዳኖት እና መርሲን የመሸገው የኢትዮጵያ ወታደር በውሃ እጦት እንዲቸገር ለማድረግ ቻለ፤ሰራዊቱም አካባቢውን ለመልቀቅ ተገደደ፡፡ ፋሺስት ግስጋሴውን ቀጥሎም በአጭር ጊዜ ገርለጎቢ፣ ታፈረና ሸላቦ ከተሞችን ተቆጣጠረ፤ ግስጋሴውንም የግራዝማች አፈወርቅ ጦር ጠንካራ ይዞታ ወደነበረው ወደ ቆራሄይ አደረገ፡፡
በአፈወርቅ ወልደ ሰማያት አመራርነት የተገነባው የቆራሄ ምሽግ፣ ጠላት ወደ መሃል አገር የሚያደርገውን ግስጋሴ የማስቆም ግዳጅ ነበረው፡፡ ቆራሄይ የመሸገው የኢትዮጵያ ጦር በትጥቅም በስንቅም ከኢጣሊያ ጦር ጋር ፈጽሞ አይመጣጠንም፡፡ በስድስት ክፍለ ጦሮች የተደራጀው የጠላት ጦር 150 ካሚዮኖች፣አራት ታላላቅ መድፎች፣ ዘጠኝ ታንኮችና 30 ብረት ለበስ መኪናዎች የታጠቀ ሲሆን በርካታ ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችም የእግረኛውን ጦር ለማገዝ ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአንጻሩ የወገን ጦር አራት መትረየስና 40 አውቶማቲክ ጠመንጃ ብቻ ነበረው፤ ስንቁም ጭብጥ በሶ ነበር፡፡
የኢጣሊያ ጦር በጦሩ ዋና ሰፈር በቆራሄ በየጊዜው የአውሮፕላን ድብደባ ያደርግ ነበር፡፡ አፈወርቅ ወልደሰማያት ግን የጠላትን ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ከምንም አይቆጥራቸውም፤ይልቅስ ይዝናኑባቸዋል ማለት ይቀላል፡፡ የወቅቱን ሁኔታ ሚስተር እስቴር የተባለ እንግሊዛዊ በግል ማስታወሻው ያሰፈረውን ጠቅሶ ጳውሎስ ኞኞ ‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት› በተሰኘው መጽሀፉ እንዳስነበበን፡-
‹‹…………ቆራሄ በየጊዜው በአውሮፕላን ቦምብ ይደበደባል፡፡ ከሚወድቀው ቦምብ ቢላዋ እየሰሩ ስለሚጠቀሙበት አፈወርቅ ስጋ የሚበሉት ከቦምብ ፍንጣሪ በተሰራ ቢላዋ ነው፡፡‘…….. ስለዚህ ነገር አፈወርቅ ሲያጫውቱኝ ይሄ ቦምብ ጩኸቱ ያደነቁረናል እንጂ መንካት አይነካንም፡፡ እኛም እንዲህ እንዲህ እየሰራን እንጠቀምበታለን ብለውኛል፡፡’ ›› ሲል አስፍሯል፡፡
ፋሺስት ያለውን የዘመናዊ መሳሪያ አቅም አሟጦ ቢጠቀምም የቆራሄይ ምሽግ ግን በቀላሉ ሊደፈር አልቻለም፡፡ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እስከ አፍንጫው ታጥቆ ለነበረው የኢጣሊያ ሰራዊት ፈተና የሆነው የግራዝማች አፈወርቅ ጦር ጥንካሬ ምንጭ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪው ጉዳይ የአፈወርቅ ድንቅ የውጊያ የአመራር ጥበብና ጀግንነት ነው፤ በወታደሮቻቸው ላይ የገነቡት የመንፈስ ጥንካሬና ሞራልም ሌላው ለወገን ጦር ጥንካሬን ያላበሰ ሁነት ነው፡፡ ግራዝማች አፈወርቅ በየዕለቱ ወታደሮቻቸውን ሰብስበው እንዲህ ይሏቸው ነበር፡-
‹‹………..አብረን እንደበላን አብረን እንሙት እንጂ እኔን ጥለሀ የት ትሄዳለህ?! በሰላሙ ቀን ከወደድከኝ በዚህች ቀውጢ ቀን ብቻዬን ትተኸኝ እንደማትሄድ አውቃለሁ። እንደምትወዱኝ እወዳችኋሃለኁ፡፡ በሰላሙ ጊዜ ጭብጦ በሶ ተካፍለን አብረን በልተን አሁን እንዴት ይርበናል?! ስንቄን አካፍዬ እንዳበላሁህ የመከራዬም ተካፋይ ሁነኝ፡፡ አፈወርቅ እጁን ለጠላት አይሰጥም፡፡ አንተም አፈወርቅ ነህና የተቀደሰ እጅህን ላልተቀደሰ ጠላት አትሰጥም›› ይሉ ነበር፡፡
ስንቅና ትጥቁ እየተመናመነ፣ በጠላት ተከቦ ለነበረው ወታደር ስንቁም፣ ትጥቁም እነዚህ የግራዝማች አፈወርቅ ቃላት ነበሩ፡፡ ዕለት በዕለት ጥቃቱን እያፋፋመ የመጣው የፋሺስት ሀይልን በጽናት ይቋቋም ዘንድ ያስቻለውም ይኸው መልዕክት ነበር፡፡
የፋሺስት ኃይልም ተጠናክሮ ቀጥሎ ጥቅምት 23 ቀን 1928 ዓ.ም 20 አውሮፕላኖች በቆራሄይ አየር ላይ እየተመላለሱ የቦምብ ዝናብ ሲያወረዱ ዋሉ፡፡ የወገን ጦር ምንም ያህል የሞራል ጥንካሬ ቢኖረውም የኢጣሊያን ጦር የማያቋርጥ የጥቃት ዘመቻ ለመመከት አቅም አነሰው፡፡ በተለይም ወታደሩ የውሃ አቅርቦት ስለተቋረጠበት እጅግ ደከመ፡፡ ግራዝማች አፈወርቅም ከምሽጋቸው ሆነው በየአቅጣጫው የሚመጣውን የአውሮፕላን ኦርሊከናቸውን እያዘዋወሩ በሚተኩሱበት ጊዜ በቦምብ እግራቸውን ተመቱ፤ቁስሉ ከባድ ቢሆንም እጅ አልሰጡም፡፡ 220 ኪሎ ሜትር ከሚርቀው ከደገሀቡር የቀይ መስቀል የህክምና ቡድን ቁስላቸውን ለመታከም ወደዚያ ቢሄዱ ወታደሩ ሁሉ እንደሚከተላቸው ስለሚያውቁ እምቢ አሉ፡፡ አጠገባቸው ያሉ ወታደሮች እንግዲያው ምሽግ አግብተን ከዚያ ይተኙ ቢላቸው እሰዋለሁ እንጂ እንዲህ ያለውን ነገር አላደርገውም፤ ከዚህ ሆኜ እታኮሳለሁ ብለው መለሱ፡፡ አፈወርቅ ክፉኛ የቆሰለ እግራቸውን እየጎተቱ ኦርሊከናቸውን ይተኩሱ ነበር፡፡

ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም ጠላት ጥቃቱን አጠናክሮ በመቀጠል፣ በቆራሄ ምሽግ ላይ ከባድ ድብደባ አደረገ፡፡ አልበገር ባዩ አፈወርቅ ግን እጅ አልሰጡም፤እንደተለመደው ከተኙበት እየተንፏቀቁ ተነሱ፤ እጆቻቸውም የተለመደውን ስራ ሊሰሩ ኦርሊከኑን ጨበጡ፤ አሁን ግን እኒያ አልበገር ባይ፣ ቆራጥ የጦር መሪ የሆነላቸው አይመስልም፡፡ ያንን ቅጽበት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሀፊ ጳውሎስ ኞኞ፤ ‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት› በተሰኘው መጽሀፉ እንደሚከተለው አስፍሮታል፡-
‹‹ ……….የአፈወርቅ ኦርሊከን ዝም አላለም፡፡ አፈወርቅ ጥቂት ቆይቶ ደከመ፤ እጆቹ ዝለው መሬት ላይ ወደቁ፡፡ ከተመታ ጀምሮ ከቁስሉ ደም ይወርድ ነበር፤ ኦርሊከኑ ላይ ድፍት ብሎ የዛሉት እጆቹ መሬት ሲነኩ የቁስሉ ደም ቆመ››
ብዙም አልቆየ፣ የቆራሄው አንበሳ አፈወርቅ ወልደሰማያት እስትንፋስ የማቆሙ ዜና ከኦጋዴን በረሃ ተሰማ፡፡ ጥቅምት 28 ቀን 1928 ዓ.ም ለመላው ኢትዮጵያዊ መርዶ፤ ለፋሺስት ደግሞ የምስራች ሆነ፡፡ ደጃዝማች አፈወርቅ ከተሰዉ በኋላ የፋሺስት ጦር የሚያቆመው አልተገኘም፤ በጥቂት ጊዜያትም የቀብሪደሃር፣ ደገሃቡርና የጅግጅጋ ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡
የአገር ህልውና አደጋ በወደቀበት በዚያ ቀውጢ ወቅት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ፤ ህዝቡ በጽናት የአገሩን ሉዓላዊነት እንዳያስደፍር ለማነሳሳት ተንቀሳቅሰዋል፤ ከዚህም አንዱ ለአረንጋዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ አርማ ክብርና ሞገስ ሲሉ በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት የተዋደቁትን አርበኞችን መዘከር ነበር፡፡ በዚህም ግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት በጀግንነት በተሰዉ በ14ኛው ቀን የደጃዝማችነት ማዕረግ በክብር ሰጥተዋቸዋል፤ አስከሬናቸው ባረፈበት ደገሃቡር ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተውም የመታሰቢያ ሀውልት አኑረውላቸዋል፡፡ በንጉሰ ነገስቱ ትዕዛዝ በጅግጅጋ ከተማ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል በስማቸው እንዲሰየም ተደርጎ ነበር፡፡ ለደጃዝማች አፈወርቅ መታሰቢያነት የተሰራ ሀውልት በጅግጅጋ ከተማ እምብርት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ቆሞ ይገኝ ነበር፣ ነገር ግን በመንግስት ለውጡ ወቅት በከተማው በተፈጠረ ግርግር እንደፈረሰ ይነገራል፡፡”

#ክብር ለጀግኖቻችን

Frew Getachew  FB.

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *