….በዚህ የትግል ግለት ውስጥ የተወለደው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ትግሉን የመምራት፣ መረጃ የማቀብል፣ መረጃ የማሰራጨት ስራውን አጠነከረ። እነ ጁሃር መሐመድም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለተነሳው ህዝባዊ አመጽ የባለቤትነቱን መሪ ጨበጡ። የኦሮሞ ልሂቃን በአዲስ ሃይል የሚዲያ ዘመቻውን ተቀላቀሉ። ትግሉ ፍሞ ስለነበር የሽግግር ቻርተር እስከማርቀቅ ደረሱ። የውጩን የፖለቲካ ትግል እመራዋለሁ የሚለውን ግንቦት ሰባትን ወግድ ብለው በራሳቸው ሃይል ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን አወጁ። ከአማራው ትግል ጋር ለቀናት ተሳስሞ የነበረውን አግባብም አምክነው በራሳቸው የነጻ አውጪ ጀልባ ላይ ሆነው መቅዘፍ ያዙ….

OMN

አይኑን ለመታከም የሄደ አንድ ሰው የተለያየ መነጽር እየተደረገለት ይታየው እንደሆን ሲጠየቅ መልሱ ” አይታይም” የሚል ብቻ ነበር። በጣም በርካታ መነጽር ተከመረ። የሚሆነው ግን ሊገኝለት አልቻለም። በመጨረሻም ሃኪሙ ” ላንተ የሚሆን ህክምናና መነጽር እኛ ዘንድ የለም” ሲል አሰናበተው። አሁን አሁን ማንም ሆነ ማን ሻዕቢያ ዘንድ የሚወተፉ ሁሉ ይህንን ሰው ይመስሉኛል።
ከአንድ የኦነግ ከፍተኛ ሰው ከባልደረባዬ / ስሙን ያልጠቀስኩት ምን አልባት ደስ ካላለው ብዬ ነው/ ጋር ሆነን የመወያየት እድል አጋጥሞኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በወቅቱ ካነሳንላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና የዛሬው ጽሁፌ መነሻ በኤርትራ እና በኦነግ መካከል ያለውን ግንኙነት የተመለከተ ነበር። ግንኙነቱም ገና በሽግግሩ ጊዜ ሻዕቢያ ኦነግን ስለመሸጡ ነበር።
ጥያቄው ገና ሲነሳ ” ይብራራልኝ” ሲሉ ነበር ጥያቄውን በጥያቄ የመለሱት። ነገሩን አያውቁትም ከሚል ሳይሆን፣ የማብራራት ግዴታ ስላለብን የሚያውቁትን ጉዳይ አስረጂ ሆን። እናም መልሳቸው ” እንደዛ ነው ፤ ግን የራሳችንም ችግር ነበረበት …” ብለው አለፉት። ማየት የተሳነው ሰውዬ እንዳደረገው
አጭር ጭብጥ – ለማስታወስ ያህል
እንዲፍረከረክ የተደረገውን የቀድሞ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሃይል እና እንደ ባዕድ ሃይል እንዲበተን የተፈረደበትን ሰራዊት ከስር ከስር እያሰባሰበ ሃይሉን ያፈረጠመው ኦነግ “የፖለቲካ ተኩላነት” ጎድሎት እንጂ ህወሃትን በወራት ጊዜ ውስጥ ማንበርከክ የሚችልበት አጋጣሚና አቅም እንደነበረው የሚካድ አልነበረም። አንዛኛውን ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው ኦነግ ስለነበር ያሻውን አዋጅ አውጆ ከሽግግሩ ራሱን በማግለል ፍላጎቱን የማሳካት እድሉን እንዳበላሸ ብዙዎች ይስማማሉ።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ህወሃት እድሜ ለመግዛትና የመንግስትነት መዋቅሩን አስተካክሎ እስኪተክል በተለያዩ የቅድመ ድርድሮች ኦነግን እያስጋለበ ውስጥ ውስጡ ከረከረው። ባደረገውም ሆነ ባላደረግው እየከሰሰ ከህዝብ ጋር አጣላው። ሃጢያቱን እያገዘፈ ሚዲያ ላይ ያነጥፈው ያዘ። በፈጠራና በተቀነባበር ድራማና የወንጀል ትዕይንት አሳደፈው። ይህ ሁሉ ሲሆን መልኩንና አካሄዱን መርምሮ ፖለቲካዊ አክሮባት ከመጫወት ይልቅ አንቀላፋ። በስተመጨረሻ የተደገሰለትን ድግስ እንዲታደም ሻዕቢያ የግብዣ ካርድ ላከለት። ተቀበለና የግብዣውን ምንነትና ዓይነት ሳይረዳ ተነከረበት። ከዛ ብሁዋላ ኦነግ ታሪክ ሆነ። ልክ እንደ ዛሬው!! ዛሬ እንደደረሰበት ተበታትኖ እንደ ስፖርት ክለብ ቁጥር 1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5… ሆኖ ተበላለተ።
በወቅቱ የነበረው ግብዣ በሻዕቢያ አደራዳሪነት ኢህአዴግም ሆነ ኦነግ ሰራዊታቸውን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎ ማስገባት ነበር። ሰራዊቶቻቸውን ወደ ማሰልጠኛ አስገብተው መደራደር። ይህንን ሃላፊነት ኢሳያስ አፉወርቅ እንደሚወጡ ቃል ገቡ። የኦነግ አመራሮች ያፈረጠሙትን ሃይላቸውን አሰባስበው ወደ ማሰለጠኛ ማእከል አስገቡ። ኢህአዴግም ሃይሉን እንዳስገባ ተነገረ። በዚህ አፍዝ አደንግዝ ስምምነት መሰረት የኦነግ ሰራዊት በፈቃደኛነት እጅ የመስጠት ያህል እየተግተለተለ ካምፕ ገባ። በዛው በስልት ተከበበና የያዘውን ብረት ገቢ አደረገ። ከዛ ሰራዊቱ የበሬ መገዣ እየተሰጠው ወደ እርሻው ቢመለስ እንደሚያዋጣው ተሰብኮ ባዶ እጁን ወደ ቅዬው በየደረጃው ተመለሰ። በዛው የፈረጠመው የኦነግ ሃይል ሟሟ። ከዛ በሁዋላ የሚፈራ አለነበረምና ” ዘወር በል” ተባለ። አለቀ!!
ተመልሶ ሻዕቢያ ጉያ
እንደ ፊኛ የሟሸሸው ኦነግ በስልት ተፈታቶ ከወላለቀ በሁዋላ / እዚህ ላይ የኦነግን ሃይል ለማሳነስ ሳይሆን ሂደቱን በስዕላዊ መልኩ ለመግለጽ ታስቦ ነው፤ ኦነግ ማገገም የሚችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎችም እንደነበሩ የሚካድም አይደለም / እንደ ምናምንቴ ተግፈቶ ካገር ወጣ። እምብርቱ ላይ ሆኖ ያጣውን ድል በኤርትራ በኩል ዞሮ ለመቀበል ወስኖ የኢሳያስ ብብትና መዳፍ ስር ገባ። ከሂደትና ከስህተቱ ያለተማረው ኦነግ ኤርትራ ገብቶ የእገሌ፣ የእገሌ እየተባለ ክንፍና ቅርጹን ሲያሰፋ ከመመልከት ውጪ ትግሉ ውሃ የፈሰሰበት ሆነ።
እዛ የነበሩ እንደሚመሰክሩት የኦነግ ሰራዊት ኤርትራ ላይ ሆኖ እንኳን ተዋግቶ ኦሮሚያን ነጻ ሊያወጣ ለራሱም በግዞት የተያዘ መሆኑንን ነው። ለዚህም ይመስላል ኤርትራ ላይ የሚደረገው የትግል ዝግጅት አያዋጣም የሚሉ ሃይሎች ተነሱ። ትግሉ በኦሮሚያ ሜዳ ላይ አገር ቤት ሊሆን እንደሚገባው በማመን የተነሱት ሃይሎች ትኩረታቸውን አገር ቤት አድርገው በአጭር ጊዜ ያለውን መንግስት ናጡት። መናጥ ባቻ ሳይሆን አራዱት።
በዚህ የትግል ግለት ውስጥ የተወለደው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ትግሉን የመምራት፣ መረጃ የማቀብል፣ መረጃ የማሰራጨት ስራውን አጠነከረ። እነ ጁሃር መሐመድም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለተነሳው ህዝባዊ አመጽ የባለቤትነቱን መሪ ጨበጡ። የኦሮሞ ልሂቃን በአዲስ ሃይል የሚዲያ ዘመቻውን ተቀላቀሉ። ትግሉ ፍሞ ስለነበር የሽግግር ቻርተር እስከማርቀቅ ደረሱ። የውጩን የፖለቲካ ትግል እመራዋለሁ የሚለውን ግንቦት ሰባትን ወግድ ብለው በራሳቸው ሃይል ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን አወጁ። ከአማራው ትግል ጋር ለቀናት ተሳስሞ የነበረውን አግባብም አምክነው በራሳቸው የነጻ አውጪ ጀልባ ላይ ሆነው መቅዘፍ ያዙ። ከዛም በጥይት፣ በእስር፣ በዱላና በአስቸኳይ አዋጅ የፋመው ትግል ጋብ እንዲል ተደረገ። የከዳውን የኦህዴድ አመራርም ሙሉ በሙሉ ጠራርገው አበጠሩት። ኢህአዴጎች ያዋጣናል የሚሉትን ካደረጉ በሁዋላ ኦሮሚያን የኢኮኖሚ አብዮት እንደሚያናውጣት አበሰሩ… ብዙ ተባለ!!
የእነ ጁሃር ትግል አድጎ አንድ ደረጃ ይደርሳል ሲባል ዞሮ አስመራ ተገኘ። የሚገርመው አስመራ መገኘቱ ሳይሆን እንደሚዲያ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ሁለት ጠያቂዎች ኢሳያስ አፉወርቂ ቤት የሄዱበት ምክንያትና ያነሱዋቸው ጉዳዮች ናቸው።
መድረኩ ሆን ተብሎ የተመቻቸ ቢሆንም አንድ ራሱን ” ሚዲያ ” ብሎ የሚጠራ ክፍል፣ በዛ ሚዲያ በሚባለው ክፍል ውስጥ ወሬና መረጃ አቀብላለሁ የሚሉ ሰዎች አስመራ ድረስ ሲሄዱ ቢያንስ ጠረጴዛ ላይ ያሉትን ጉዳዮች አለማንሳታቸው መስቂያ ያደርጋቸዋል። ሻዕቢያ የኦሮሞ ልጆችን በግዞት ይዞ የቀን ሰራተኛ አድርጓቸዋል፤ የመወጣትና የመግባት ነጻነት የላቸውም፤ የቀን ሰራተኛ አድርጎ ስንዴ እየሰፈረ ይበዘብዛቸዋል፤ በቂ ህክምናና ክብካቤ ባይኖርም ትግሉ ከሁለት አስር ዓመት በላይ ባለበት የረገጠበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚሉትና ተመሳሳይ ጥያቄዎች በያንዳንዱ ኦሮሞ ልብና ጠረጴዛ ላይ ያሉ ያደባባይ ምላሽ የሚፈለጉ ጉዳዮች እንደሆኑ የሚካድ አይደለም።
ከዚህ ውጪ ስድ ንባብ እያነበቡ፣ እየተቁለጨለጩና እየሰገዱ ቅዠት ለቅሞ ለመምጣት እዛ ድረስ መሄዱ በራሱ አስፈላጊ መስሎም አይታየኝም። እንደውም እዛ በባርነት በተያዙት የኦሮሞ ልጆች ህይወትና መከራ ከመቀልድ የዘለለ ትርጉምም ሊሰጠው አይችልም።
“ሻዕቢያ የኦሮሞን ትግል፣ ወይም የመላው ኢትዮጵያዊያንን ትግል ለመደገፍ ቁርጥ ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ ትግሉ በፋመብት ወቅት ሁለት ብርጌድ ሰራዊት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ቢልክ፣ በቀናት ውስጥ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የነጻነት ተዋጊዎችን ማፍራትና ትግሉን በድል ማጠናቀቅ በትቻለ ነበር” ሲሉ አስተያየት የሰጡ ክፍሎች ያቀረቡትን ትንተና መከታተሉ እዚህ ላይ አስፈላጊ ሆኖ ይታየኛል።
እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ኤፍሬም ማዴቦ “በረሃ ወርደናል” ብለው በድርሰትና የፍቅር ደብዳቤ ይዘት ባለው መጣጥፍ የትግሉን የድል ሳንዱች ሲያስገመጡን ያዘነው ሳያነሰን ዛሬ የኦሮሞ አዲሱ ትውልድ ተመልሶ በዳውድ ኢብሳ ጫማ ውስጥ መቀርቀሩ ያሳፍራል። ብዙዎች ገና ዱሮ እንዳሉት ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ትግል የመርዳት ቁርጥ ሃሳብ የለውም። ይልቁኑም መደራደሪያ በማድረግ የዓላማው ማስፈጸሚያ ማድረግ እንጂ!! ለኦሮሞ ከአማራና በደም ከተሳሰራቸው ወገኖች ይልቅ ሻእቢያ እንዴትና በምን መስፈርት ቅርብ ሊሆን እንደሚችል ለዚህ ጸሃፊ ግልጽ አይደለም። ሊሆንለትም አይችልም።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ” ጦርነቱ ቆሟል” ተብሎ በግፍ መሳሪያውን እንዲፈታ ሲደረግ በገፍ በጅምላ የተጨፈጨፉት ወገኖች ደም ይጮሃል። እዚህ የደም ጎርፍ ውስጥ የኦሮሞ ልጆችም ነብስ አለ። እናም የእነሱም ደም ይጮሃል። ዛሬ ሻዕቢያ ደጅ እየሄዱም ሆነ ሄደው የሚያላዝኑና የትም ለማይደርሰው ትግል የሚያፈነደዱ “ጋዜጠኞች” ራሳቸውን ቢመረምሩ ደግ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። እውነቱን እየካዱ ኢሳያስ ለኢትዮጵያ አሳቢና ተቆርቋሪ እየተደረጉ የሚሰበኩ ስብከቶች ሁሉ መርዝ የመጋት ያህል እንደሆነ መረዳት ግድ ነው።
አሁን ፖለቲካው ውስጥ የሚገላበጡት የ ” ተራራውን አንቀጥቃጭ፣ ያ – ትውልድ” የሚባሉት የሚከስሙበት የተፈጥሮ ዘመን በጫፍ ነው። ህወሃት እንደሚመኘው ሳይሆን ከጥላቻ ወጥተው የሚነጋገሩ ትውልዶች በደጅ ቆመዋል። አንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ” የምንፈራው ይህ ከደጅ ያለውን መጪ ትውልድ ነው” እንዳሉት!! ለውጥ ያለውም እንዚህ ዘንድ እንጂ ከሌላ አካል አይሆንም። ይህን እውነት የምናይበት ጊዜ ቅርብ ነው። ህልመኛ አይደለሁም። ከውጭ ካለው ይልቅ ከውስጥ ያለው የማናጋት ሃይል እንዳለው አንካካድምና ሁላችንም እንመን። ሚዲያዎችም ቢያንስ ራሳቸውን ከቆሙና መረጃ የማስተላለፉን ስራ በወጉ ከቀጥሉ ከበቂ በላይ እንደሆነ ይሰማኛል። በዚህ እሳቤ ሁሉንም ሚዲያዎች ለመርዳት እሞክራለሁ። ቢቻል ቢሸለሙና ቢበረታቱ ይበልጥ ነጻ እየሆኑ የውስጡን ድማሚት ያፋፉታል፣ በየስርቻው ያለውም ውዝግብ ይቆማል የሚል የጸና እምነት አለኝ። በቀጣይ ስለሚዲያ የሚሰማኝን እላለሁ። ለዛሬው ግን እንደ አይን በሽተኛው ሰውዬ ከመሆን ይሰውረን። አለያ ልክ ሃህኪሙ ሰውየውን እንዳባረረው ህዝብ ቀይ ካርድ ይሰጣል። የዛኔ ይግባኝ የለም!!

Related stories   "የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን ላለመላክ የወሰነው የማይታዘዝና የማያጎበድድ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ነው"አንዳርጋቸው ፅጌ

ባሴ መኮንን –

ዝግጅት ክፍሉ – መጠነኛ የእርምት ስራ ከምስራታችን ውጪ ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው አመለካከት ብቻ ነው። ምላሽ መስጠት ለምትፈልጉ እናስተናግዳለን

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *