መግባቢያ!

የሀገረ-ኢትዮጵያ የእውቀት አደባባይ በአስፈሪ ዝምታ ተውጧል። ምሁራኖቻችን ከህዝባዊ ተዋፅኦ አፈግፍገዋል። የአደባባይ ምሁራን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በመናመን ላይ ባሉ ብርቅዬ የዱር እንሰሳት መመሰል ከጀመረ ዓመታት አልፈዋል። ቁጥራቸው የበዛ ምሁራን አገዛዙ በፈጠረው የጥቅመኝነት ፖለቲካ ጥላ ስር መጠለል ምርጫቸው ሆኗል። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ የባዕድ አገር ስደትን መርጠዋል። ሕዝባዊ መድረኮቻችንን ፋይዳ ቢስ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችና በተዛቡ የታሪክ ትርክቶች፤ በዘውጋዊ አጥርና አገራዊ ከፍታን መፍጠር በማይችሉ ሙግቶች ተውጠዋል። ዕድሮችና የመረዳጃ ማህበራት ሳይቀር ዘውጋዊ ቅርጽ (አጥር) ሰርተዋል።

አገሪቱ ለገባችበት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ቅርቃርና ለማህበራዊ ችግሮቻችን መፍትሔ ይሰጣሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የፖለቲካ ልሂቃን አገሪቱን ለአራት አስር ዓመታት ክፉኛ የናጣትን “የብሔር ጥያቄ” በማንገብ ወደ ማንነት ቅርጫታቸው በመጠቃለላቸው፤ የአገራዊ ችግር ባህሩን በማሻገር ወደ አርነት ከፍታ የሚያወጡን ሙሴዎች መምጫ ጊዜን እንደ ምፅአት ቀን የማይታወቅ አድርጐታል። በአናቱም አገዛዙ ከቀን ወደ ቀን አምባገነናዊ አገዛዝን በምልዐት መተግበር በመጀመሩ የጓዳ እንጂ የአደባባይ ፖለቲከኞችና ሕዝባዊ ተቆርቋሪነት ያደረባቸው ምሁራን ከፖለቲካ አፀዱ ተመናምነዋል። “አለን” የሚሉን ፖለቲከኞች የጓዳ ገመናቸውን መሸፈን አቅቷቸው በየአደባባዩ መዘላለፍ የሰርክ ተግባራቸው ሆኗል።

በርግጥ ለዘር ያህል የሚሆኑ ጥቂት የአደባባይ ምሁራን አሉ። ከትላትን እስከ ዛሬ መሰረታዊ ግባቸውን ያልሳቱ፤ የዚህችን አገር የውድቀትና የስኬት ታሪኮች መርምረው የደረሱበትን ድምዳሜ ካለ ፍርሃት ወደ አገሪቱ የእውቀት አደባባይ የሚያወጡ፤ የዘመን ዕንቁዎች አሉ። ክፋቱ ከጠመዝማዛው የኢትዮጵያ ታሪክ ቋጠሮ እና ከብዝሃነታችን አኳያ የጥቂት ለዛውም በጣት በሚቆጠሩ የአደባባይ ምሁራን ተሳትፎ ብቻ አገዛዙ ያነበረውን የሴራ ፖለቲካ ሰንሰለት ለመበጣጠስ አለመቻሉ ነው።

የምሁራኑ ከአደባባይ መራቅና አገዛዙ በተጠና መንገድ የፈጠረው አገራዊ ድብርት በጋራ ተጋምደው ወደ ቁልቁለት መንገድ ያንደረድሩን ጀምረዋል። እንደ አገርም ከፍታው ርቆናል። ያም ሆኖ የአገዛዙን ቅጥፈትና የለየለት አምባገነንነት ካለ ፍርሃት የሚተቹ ምሁራን ለዘር ያህል አሉ። በዚህ ፅሁፍ “ለሥልጣን እውነትን የመናገር” ግዴታን በበቂ ሁኔታ እየተወጣ ስላለው ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በጥቂቱ እናነሳለን። የመስፍንን ትሩፋቶችና አካዳሚያዊ ተዋፅኦዎች በአንድ ፅሁፍ ማብራራት የሚቻል አይደለም። ግና ስለመስፍን የአደባባይ ምሁርነት አብዝተን እናወራለን። እውነታውንም ለትውልድ እናካፍላለን። የወደደ የመስፍንን የትውልድ ዋርካነት አስተውሎ ይጠለል፤ ያልወደደም ከመስፍን ፅናትንና ብርታትን ይማር!!

መስፍን ትልቁ ሰው!

በኤሌክትሮኒክስና በህትመት ሚዲያው (መፅሐፍትን ሳንረሳ) ስለ ግለሰቦች የሚናገሩና የሚጻፉ ፅሁፎች እንደተናጋሪው ወይም እንደ ፀሐፊው የዕድሜ ደረጃ፣ የግል ቀረቤታ፣ አመለካከት ወዘተ የተነሳ “አንተ” ወይም “አንቱ” ሊባል ይችላል። የዚህ ፅሁፍ  አዘጋጅ  ለፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ካለው ቅርበት፣ ፍቅር፣ አድናቆትና ከበሬታ የተነሳ “አንተ” እያለ ለመጥራት ወዷል፤ ማዕረጉንም በአገር በቀሉ “የኔታ” ተክቶታል። (እንደ እውነቱ ከሆነ የዕውቀት አባት “አንተ” ሲባል፣ ከጥልቅ ከበሬታ ጋር መሆኑን ልብ ይሏል።)

ከግላዊ ጥቅም በዘለለ በርከት ያሉ አካዳሚያዊ የምርምር ሥራዎችን የሰራ፣ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ሕዝባዊ
ተዋፅኦዎች የራሱን አሻራ ማሳረፍ የቻለና፣ የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር አብላጫ የዕድሜ ዘመኑን ያሳለፈ፣ ዛሬም በእርጅና ዘመኑ የሚያምንበት ሃሳብ በአደባባይ የሚናገር (የሚፅፍ) ብርቱ ሰው የኔታ መስፍን ወ/ማርያም!

የእኔን ዘመን አምላጭ ትውልድ ሳይጠየፍና ሳይንቅ ምሁራዊና አባታዊ ተግሳፁን “በአስተዋይ ገላማጭነት” ወደ ትውልዱ ማድረስ የቻለው ይህ የዘመን ዕንቁ ያመነበትን ነገር በአደባባይ በመናገር ወደር የሌለው ኢትዮጵያዊ የአደባባይ ምሁር ነው። የመስፍንን ትጋትና አይደክሜነት ያስተዋሉ የዘመን ተጋሪዎቹም ሆኑ ተከታዮቹ በአንድ ድምፅ “የማይዳፈን ጩኽት፤ የማይከሽፍ ተስፋ ባለቤት” ይሉታል።

ዲያቆን፣ ጂኦግራፈር፣ ፈላስፋ፣ ሕዝባዊ ታሪክ ፀሃፊ፣ ገጣሚ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ . . . የሆነው የኔታ መስፍን ከአስራ ስድስት በላይ የምርምር መፅሐፍቶችን በማሳተም፤ በድርቅ ፣ ረሃብና መልከዓ ምድር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ በርከት ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በአለም አቀፍ ጆርናሎችና ዩኒቨርሲቲዎች በማቅረብ፣ ባለፉት አምስት አስርታት ውስጥ ለረዥም ጊዜያት በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች በአምደኝነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በማህበራዊ ድረገጽ (ፌስቡክ) ጭምር በመሳተፍ አገራዊ እሴትን በሚጨምሩ ፅሁፎቹ ያደፈውን ለማንፃት፣ የጎበጠውን ለማቃናት፤ የተናደውን ለመካብ፤ . . . በአያሌው የደከመ፤ የነፃው ፕሬስ ግብዓተ መሬት ከመከናወኑ በፊት የነፃው ፕሬስን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም የማህበራዊ ድረገጽ የቴክኖሎጂ በረከትን ለአገራዊ ግንባታ በማዋልና አገዛዙን በሃሳብ በመሞገት ከዕድሜ ዘመኑ አኳያ የእርሱን ያህል የታገለና የደከመ የአደባባይ ምሁር መኖሩ ያጠራጥራል።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

የፊታችን ሰኞ ሚያዚያ 16 ቀን 2009 ዓም 87 ዓመት የልደት በዓሉን የሚያከብረው ሞጋቹ ምሁር፣ ብዙዎች ሊገፉትና ሊወጡት የማይቻል የሚመስለውን የህይወት ውጣ ውረድ አሳልፏል። ከትላንት እስከ ዛሬ በማይጣረሱ መሰረታዊ ግቦቹና ከብረት በምናነጽረው ሥነ-ምግባሩ ለዜጐች ሰብዓዊ መብት መከበር፣ እኩልነት፣ ፍትህና ዘላቂ ሰላም በአይበገሬነት መታገል ችሏል። መስፍን ኢትዮጵያዊ ወገኖቹን በዘውግ መነፅር ሳይሆን በዜግነት ማዕቀፍ የሚመለከት የመርህ ሰው ነው።

የኔታ መስፍን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን በምስራቁ (ህንድ)ና በምዕራቡ (አሜሪካ) አለም እንደ መስራቱ የታሪክ አተያዩና አረዳዱን ከፃፋቸው መፅሃፍት አኳያ ስንመረምር ሰውዬው አንዳችም የውጭው አለም ተፅዕኖ የሌለበት፤ ነጮቹ በቀደዱለት ቦይ ለመፍሰስ የማይዳዳው ምሁር እንደሆነ እንረዳለን። አድርባይነትና ወላዋይነት ከመስፍን ስብዕና ጋር ተዛምዶ እንደሌላቸው እና ሰውየው ለእውነት የሚሰጠውን ዋጋ ለማሳየት “ባህል፣ ሥልጣንና አገዛዝ በኢትዮጵያ” እንዲሁም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኙት መፅሃፍቶቹ ይዘት (በይበልጥ) መረዳት ይቻላል።

የመስፍን የአካዳሚ ስራዎች በድርቅ፣ ረሃብ፣ የመሬት አስተዳደር፣ ካርታ ሥራ፣ . . .  ወዘተ ዙሪያ የሚያተኩሩ የበሰሉ ሥራዎች ናቸው። በነገራችን ላይ በአገሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጂኦግራፊ መማሪያና አጋዥ መፅሐፍቶች የመስፍንን የምርምር ሥራዎች ቀዳሚ ማጣቀሻ ያደረጉ ናቸው። መስፍን ከአካዳሚያ ሚናው በተጨማሪ በአገራዊ ጉዳዮች የሚያተኩሩ በምርምር የተደገፉ ሥራዎችንም የ(ሚ)ሰራ የአደባባይ ምሁር ነው። “አደጋ ያንዣበበት የአፍሪቃ ቀንድ ስጋት” በሚለው መፅሃፉ ስለ ሽብርተኝነትና የርስ በርስ ጦርነት ያነሳቸው ጭብጦች አለም አቀፋዊ ተሞክሮ ያላቸው ተጨባጭ ስጋቶች ሆነው እናገኛቸዋለን።

የኔታ መስፍን በመፅሃፍቶቹ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ትላንትን መነሻ ያደረጉ፣ ዛሬን በቅጡ የፈተሹና ለነገ መውጫ ጫፎችን የሚጠቁሙ የምርምር ስራዎች ናቸው። ከልክ በላይ የተወጠረው የዘውግ ፖለቲካ እንደ አገር የሚያስከትለውን ችግር፣ የመሬት ፖሊሲውን ክሹፍነት፣ የህወሓትን የጠቅላይ ዝግ አምባገነናዊ አገዛዝና በትግራይ ህዝብ ስም መነገዱ ለትግራዋያን የሚያመጣውን የነገ ዕዳ . . . ወዘተ የተመለከቱ ጉዳዮች በየጊዜው ባሳተማቸው መፅሃፍቶቹ የተነበያቸው በስጋት ያስቀመጣቸው ችግሮች ሲቀርቡና (ሲደርሱ) እንጂ ሲርቁን አላየንም።

በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተነሱት ተደጋጋሚ ህዝባዊ አመፆች ህወሓት በሁለቱ ክልል ህዝብ ላይ መንግስታዊ ፍጅት ሲፈፅም፣ ድርጊቱን ኮንኖ ተቃውሞ ያሰማ (አገር ቤት ያለ) የአደባባይ ምሁር አልታየም፤ ከየኔታ መስፍን ወ/ማርያም በስተቀር!! “የወያኔ አገዛዝና የኢትዮጵያ ወደፊት” በሚል ርዕስ በመስከረም 2ዐዐ9 ዓም በማህበራዊ ድረ-ገፆች ለውይይት ያቀረበው 22 ገጽ ፅሁፍ የያዘውን ጭብጥና አገራዊ ፋይዳ ስናስተውል የሰውየውን ብርቱነትና ልበ ሙሉነት እንድንረዳ ተጨማሪ ዕድል ይሰጠናል።

በርግጥ የመስፍንን አካዳሚያዊ ሥራዎችና ሕዝባዊ ተዋፅኦ እንዲሁም በህወሓት አገዛዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከብዙ ውጣ ውረድና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በመስፍን ፕሬዝዳንትነት የተመራውን ኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ) ለማቋቋም የከፈለውን መስዋዕትነት፤ እንዲሁም ባለፉት ሁለት አገዛዞች እንደ ምሁር የተጫወተውን ሚና በዚህች ፅሁፍ ማብራራት የሚቻል አይደለም። ይልቁንስ መስፍን ላመነበት ነገር መሰጠቱንና የጉልበተኞችን ሥልጣን በብዕሩና በአንደበቱ በመሞገቱ የደረሰበትን ፈተና ለማሳያነት ያህል በአዲስ ንዑስ ርዕስ እናያለን።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

እውነትና እውቀት ብዙ ዋጋ ያስከፍላሉ!

የኔታ መስፍን በብዕሩና በአንደበቱ አገዛዙን በመሞገቱ ዛቻና ግሳፄው ከገዢው ኃይል ብቻ አልመጣበትም፤ የአገዛዙን መቀጠል አብዝተው ይመኙ ከነበሩት አቡነ ጳውሎስ ጭምር ዘለፋ ደርሶበት ነበር።

“. . .  በጣም የሚያስከፋ ፣ የሚዘገንንና የሚያስለቅስ የሥልጣን መባለግ አለ። አንድ ጊዜ አንድ ጓደኛዬ ሊቀ ጳጳሱ ሊያነጋግሩህ ይፈልጋሉ አለኝና አብረን ሄደን። እጅ ነስተን ተሳልመን ቁጭ አልን።  . .  . ብፁህ አባታችን ግሳፄ ጀመሩ . . . ‹ብዙ ትናገራለህ፣ ምን እንደምትናገር፤ ለማን እንደምትናገር ማሰብ አለብህ!› በማለት ተራ ለፍላፊ አስመሰሉኝ። እሳቸው ሲናገሩ ቦግ ብለው ይታዩኝ የነበሩት መስቀሎች እያነሱብኝ። ሄደው በመጨረሻም ጠፉብኝ ። በሃሳቤ አንድ የማውቀውና ግን ለሰው ነግሬው የማላውቀው ነገር ትዝ አለኝ። ሲቃ ያዘኝ ጥርሴን ብነክስ፣ ሰውነቴን ባፈራግጥ በዓይኔ ላይ ባንዴ የተከመረው የእንባ ጎርፍ ሊታገድ አልቻለም። መነፅሬን አውልቄ በመሃረቤ ዓይኖቼን ይዤ ተንሰቀሰቅኩ። የሚደንቀው ነገር አብሮኝ የነበረው ጓደኞዬ ከእኔው ጋር አለቀሰ። እስከ ዛሬ እሱ ያለቀሰበት ምክንያት አይገባኝም። ብፁዕ አባታችን ደንግጠው ዝም አሉ፤ ምናልባትም በተግሳፅ የሚያለቅስ ሞልቃቃ የሚል ሃሳብ አድሮባቸው ይሆናል።

“ለማንኛውም እንደ ምንም ራሴን ተቆጣጥሬ የማውቀውን ሁሉ ለእርሳቸው እንደመሰላቸው እንደማልናገር ለማስረዳት አንድ የሚዘገንን ታሪክ ነገርኳቸው። አንዲት የቸገራት ሴት የአስራ ስድስት ዓመት ልጇን አስከትላ አንድ ሚኒስተር ዘንድ ለደጅ ጥናት ትሄዳለች። ችግሯን ስትናገር ታለቅሳለች። ሚኒስትሩ ልጅቱን ወደ ፀሃፊዋ ጋር ይልክና ሴትዬዋን ለብቻዋ ያናግራል። ችግሯ በቀላሉ እንደሚፈታ ይገልፅላትና . . . ግን ልጅሽ ድንግል ከሆነች ፍቀጂልኝና ይላታል። ይህ ደግሞ ምናልባት ወደ መጨረሻው የሚጠጋ የሥልጣን ብልግና ነው። የብፁህ አባታችንን መስቀል ሳልሳለም፤ እሳቸውም ያሰቡት ሳይሳካላቸው እንባዬን እየጠረግሁ ወጣሁ . . .” (መስፍን ወ/ማርያም – ኢትዮጵያ ከየት ወዴት? ገጽ 59)

ይህ ከላይ የሰፈረው ምስል ከሳች ትረካ መሰፍን ያነገበውን የእውቀትና የእውነት ዋጋ ለሕዝብ በማድረሱ ካጋጠሙት ልብ የሚነኩና ቅስም ሰባሪ ኩነቶች አንዱ ነው። ግና መሰፍን እንዲህ ባለ ውረፋ፣ ለዚያውም ራሳቸውን  ከእግዚአብሔር በላይ ለቄሳር ያስገዙ ተብለው በአደባባይ ለሚተቹ አካላት በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ሰው አልነበረም። ለባለ ብረቶቹም እንደዛው።

ዛሬ ላይ አገዛዙ በንፅፅር ለአንድ በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጀ ማህበር ከሚሰጠው ድጋፍ እጅግ ባነሰ “የበጀት ድጋፍ” ለሚንቀሳቀሰው፤ በአናቱም የበጎ አድራጐት ድርጅትና ማህበራት ሕግ (አዋጅ ቁጥር 621/2001) የሚሉት እግረ-ሙቅ ህግ እያሽመደመደ ላለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በአሁኑ አጠራር የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) መመስረት፤ በምስረታ ወቅት የሁሉም ዜጐች አበርክቶ እንዲኖር በተለይም ከፆታ እኩልነትና የወጣቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አኳያ የከፈለው መስዋዕትነት እጅግ የላቀ ነው።

ከምስረታው በኋላ ደግሞ በሽግግር መንግስት ምስረታው ወቅት በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች፤ በተለይም በደቡብ ምዕራብና በምስራቅ ኢትዮጵያ በአማራ ላይ ሲፈፀሙ የነበሩ ጭፍጨፋዎችንና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ከነፃው ፕሬስ አባላት፣ ከወቅቱ ምሁራንና ከአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመሆን አገዛዙ ይፈፀም የነበረውን ድርጊት እንዲያቆምና ተጠያቂ እንዲሆን በአደባባይ መሞገት ችሏል። ጉዳዩንም በወቅቱ ለመለስ በግንባር በመቅረብ አስረድቷል። በርግጥ ከእያንዳንዱ ጭፍጨፋ ጀርባ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር እጅ ነበረበት። መስፍንና አገዛዙ ሆድና ጀርባ መሆን የጀመሩትም ከዚያ ግዜ ጀምሮ ነበር።

ለመስፍን ተሟጋችነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ አለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች በየጊዜው ዕውቅና ችረውታል። የአውሮፓ ህብረት በአለም አቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ መብት ጠበቃዎች በየጊዜው “Sakharov Prize” በሚል ለሚሰጠው ከፍተኛ ሽልማት እ.ኤ.አ በ2006 ለሽልማት ታጭቶ ነበር። አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያን የተመለከቱ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን መረጃ የሚያገኙት ከየኔታ መስፍን ነበር።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ለዕውቀት አድባሩ መስፍን የአደባባይ ምሁርነትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት የአገር ውስጥ ዩኒቨርስቲዎች የዕውቅና ሽልማት ለመስጠት ባይደፍሩም ከምዕራቡ አለም ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬትን ጨምሮ የተለዩ የዕውቅና ሽልማቶችን አግኝቷል። ከረፈደም ቢሆን ባሳለፍነው ወር የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) የኔታ መስፍን ወ/ማርያም ኢትዮጵያ ውስጥ ለዜጐች ሰብዓዊ መብት መከበር ለከፈለው ውድ ዋጋ ዕውቅና በመስጠት ሽልማት አበርክቶለትል። እስከዛሬ ድረስ የፃፋቸውን መፅሃፍትና የሰራቸውን የምርምር ስራዎች እንዲሁም በምዕራቡ አለም ውድ ዋጋ ሊያወጡ የሚችሉ ቤቱ ዉስጥ የነበሩ ሁለት የገብረ ክርስቶስ ደስታ ዝነኛ የስዕል ሥራዎችን ለሰመጉ የሃዋሳ ቤተ መፃህፍት በስጦታ አበርክቷል።

የዘመን ዕንቁው የኔታ መስፍን ወ/ማርያም የኢሰመጉ ፕሬዚዳንት በነበረበት ወቅት በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በወተርሉ፣ . . . በአማራ ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተከታትሎ በማስረጃ አስደግፎ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማጋለጥ በቀዳሚነት የተጋ ሰው ነው። በአንፃሩ ዛሬ ላይ አንድም ረብ ያለው ተግባር ማከናወን ያልጀመሩና ፖለቲካዊ መብቃት ላይ ያልደረሱ የአዲሱ አማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች መስፍን በየጊዜው የሚያነሳቸውን ሃሳቦች እየተከተሉ ብርቱውን ታጋይ በሚያሳዝን መልኩ በስድብ ሊያቃልሉት ሲሞክሩ መታየቱ አሳዛኝ ክስተት ነው። ነገሩ ከባዶነት በላይ ነዉ። በታወቀ “ምክንያት” በኦሮሞና በትግራይ አክራሪ የዘወግ ብሔርተኞች ዘንድ መስፍን እንደማይወደድ ግልፅ ነው። ይህም መሰረታዊ መነሾ እርሱ ለዘውግ ፖለቲካ ጽዩፍ በመሆኑ ለግራ ቀኙ ኃይል በሚሰጣቸው ግልፅ አስተያየቶች “ተሰደብን” የሚሉ፤ ዝናን እንጅ ትችትን መሸከም የማይችሉ የመንደር ፖለቲከኞች በመሆናቸው ነው። የሟች እህት ወንድሞቻቸዉን አስከሬን ፌስቡክ ላይ በመለጠፍ “አብዮተኛ” የሆኑ የሚመስላቸዉ ከብሄር ፖለቲካ አንቀልባ ላይ መውረድ የተሳናቸዉ ስሁት “ፖለቲከኞች” ከመስፍን ምልከታ እጅግ ቢለያዩ የሚገርም አይደለም።ገራሚዉ ነገር ስድብ የጡት ቋንቋቸዉ መሆኑ ነዉ።

የኔታ መሰፍን በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ጎዳና የቻለውን ያህል ከታገለ በኋላ ራሱን በይፋ ወደ ተቃውሞ ፖለቲካ ጐራ በመቀላቀሉ የደረሰበትን እንግልትና የእስር መከራ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተል ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው። የሰላማዊ ትግል ጀምበር ጨርሳ በጠለቀችባት ኢትዮጵያ፤ መስፍን ከፓርቲ ፖለቲካ ትግል ርቆ እንኳ ዛሬም ድረስ ተቃውሞውን በሰላ ሂስ፣ በምሁራዊ አንደበት ከመግሰጽ አልተቆጠበም። ከፖለቲካው ባሻገር የማህበረ – ባህል ጉዟችን የከተተንን ቅርቃር በአደባባይ የሚተቸው መስፍን ለአምስት አስርት ዓመታት በብቸኝነት በአደባባይ ሐሳቡን መግለጽ የቻለ የአደባባይ ምሁም አድርጎታል።

በመጨረሻም

አብዛኛዎቹ የቅድመ አብዮት (1966) እና የድህረ-አብዮት (ያ) ትውልድ አባላት ዛሬም ድረስ የገዛ ፍላጎታቸውን ማሸነፍ ባልቻሉበት የትንቅንቅ ዘመን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ኑሯቸውን በብህትወትና መሰል የአኗኗር ዘይቤ ጊዜያቸውን በሚገፉበት ወቅት፤ አይበገሬው መስፍን ወልደ ማርያም በ87 ዓመቱ ለእውነትና ለዕውቀት እንደቆመ በማስመስከሩ፣ የዘመን ዕንቁ! የትውልድ ዋርካ! የሚሉ ገላጭ ሃረጋት የእርሱን ዋጋ የሚያስረግጡ ይመስላል። ረጅም እድሜ እንዲኖር ያደረገውም ለእውነትና ለዕውቀት በመትጋቱ ይመስለኛል። በአምላክ ቸርነት ገናም ይኖራል።

ይህ ትውልድ ከየኔታ መስፍን ወ/ማርያም የአቋም አዕማዶች ጋር ተስማማም አልተስማማም፤ ከእርሱ ጠንካራ ስብዕና ብዙ የሚቀዱ ልምዶች እንዳሉ ግን ማወቅ ግድ ይለዋል። በልዩነት ውስጥ እንኳ ለእውነትና ለእውቀት የሚያሳየው ትጋት የሚወደድ ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ፤ የትኛው የአገሪቱ ምሁር ይሆን በ87 ዓመቱ ሀሳቡን የሚገልፅበት ነፃ ፕሬስ ቢያጣ በማህበራዊ ሚዲያ ሃሳቡን በነፃነት የሚያጋራ? በርግጥም የኔታ መስፍን ወ/ማርያም የዘመን ዕንቁ! የትውልድ ዋርካ ነው! ያስተዋለ ወደ ዋርካው ይጠጋ። የእውቀት ግቡ ነፃነት ነውና!!!

ፕሮፍ እንኳን ተወልድክ! አንተ የመርህ ሰው፣ የህገ-ኅልዮት አማኝ ነህና አከብርሃለሁ። ተምሬብሃለሁ። ገናም እማርብሃለሁ።

ይህ ነው የዘመኔ ዕንቁ!! የኔታ መስፍን!! የቅኔ ጌታ!! የዕውቀት ገበታ!!

goolgule.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *