በህዝብ ተቃውሞና ግፊት በቢሸፍቱ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ በቅርቡ የተዘጋው የአህያ ቄራ ኢንቨስትመንት ከመዘጋቱ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም የካሳ ክፍያ የማይኖር መሆኑን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሉሉ አለሙ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል። ባለፉት ዓምስት ወራት ህዝቡ የአህያ ቄራው ከባህሉ፣ ከወጉና ከሃይማኖቱ ጋር የማይሄድ መሆኑን በመግለፅ በየመድረኩ እንዲዘጋጅ ሲያሳስብ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ከዚሁ ጋር በተያያዘው ቻይናዊው ባለሀብት የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን እንዲቀይሩ በከተማው አስተዳደር በኩል በተደጋጋሚ ምክር የተለገሳቸው ቢሆንም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ኢንቨስትመንቱ እንዲቆም የተደረገ መሆኑን አቶ ሉሉ ለሰንደቅ በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል። ለባለሀብቱ በመንግስት በኩል አማራጭ እድል የተሰጠ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው ከዚህ ውጭ ግን ኢንቨስትመንቱ በመቋረጡ የሚሰጥ ካሳ የማይኖር መሆኑን አመልክተዋል። የከተማ አስተዳደሩም እርምጃውን የወሰደው የህዝቡን ተደጋጋሚ ጥያቄ በመስማትና በማክበር መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሉሉ፤ በወቅቱ ህዝቡ ጥያቄው ካለመመለሱ ጋር በተያያዘ ቄራውን ለማውደም ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲደረጉ የቆዩ እንደነበር ገልፀዋል።

በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የቢሾፍቱ ከተማ የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የሺእመቤት ግንዳባ የአህያ ቄራው በአንድ ቻይናዊ ባለሀብት ወደ ስራ ገብቶ የነበረ ኩባንያ መሆኑን አስታውሰው በ34 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ ብር ካፒታል የተቋቋመ ኢንቨስትመንት እንደነበር ጨምረው ገልፀዋል። ቄራው በ2004 ዓ.ም ፈቃድ የተሰጠው መሆኑን ገልፀው፤ወደ ስራ ገብቶ እርድ የጀመረው ደግሞ በቀን ከ2 መቶ እስከ 3 መቶ የሚደርሱ አህዮችን እርድ ይፈፅም እንደነበር አስታውሰዋል። ህብረተሰቡ ባለፈው በኦሮሚያ ተቀስቅሶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ቄራውን በእሳት ለማቃጠል ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ገልፀው ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሁለት ሰዎች ህይወት እስከመጥፋት መድረሱንም ገልፀውልናል። ከዚያ በኋላም ቢሆን ቄራውን ለማውድም ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየቱም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ አህዮች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ቁጥር ኢትዮጵያ በአህያ ብዛት በዓለም የአንደኛ ደረጃን እንድትይዝ ያደረጋት መሆኑን ከዚህ ቀደም ዶንኪ ሳኩቻሪ ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ በአህዮች እና በበቅሎዎች ደህንነት ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ጭምር አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።

ሰንደቅ ጋዜጣ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *