• ህወሃት/ኢህአዴግ በንፁሐን ደም ላይ ማላገጡን ቀጥሏል!!

በኢትዮጵያ ለሩብ ክፍለ ዘመን የተከማቸው የግፍ አገዛዝ  በምሬት የታጀበ ህዝባዊ አመጽ አስነስቷል። ህዝባዊ አመጽ ደግሞ ለኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ባይሆንም በአገሪቱ ዉስጥ በሁለንተናዊ ዘርፍ ተጽዕኖ መፍጠር ከሚችሉት ሁለቱ ክልሎች (የኦሮሞና የአማራ፤ የደቡብ ኮንሶንና ጌዴኦን ተቃውሞዎች ሳንዘነጋ) ተከታታይነት ባለው መልኩ የአገዛዙን ማህበራዊ መሰረት በሚንድ ሁኔታ አመጽ መቀስቀሱ ይህኛዉን ክስተት የተለየ ያድርገዋል።

በዚህ ህዝባዊ አመፅ ህወሃት ከበረሃ የሽምቅ ባህሪው በተሻገረ የ“መንግስት” ባህሪ የሌለው መሆኑን ለወዳጅ ጠላቶቹ ያስመሰከረበትን መንግስታዊ ፍጅት በዜጎች ላይ ፈጽሟል። በገዛ ዜጎቹ ላይ የከፈተውን ጦርነትና ጅምላ እስር ዘግይቶም ቢሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥም ህጋዊ ሽፋን ሲሰጠው ታይቷል። ድርጊቱንም “ስኬታማ” ሲል ገምግሟል።

http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2015/01/tplfs-election-board.jpg

በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተነሱት ህዝባዊ አመፆች የወዲያው ምክንያቶች (immediate causes) የተለያዩ ቢሆኑም፤ የሁለቱም ክልሎች አመጽ መሠረታዊ ምክንያቶች (root causes) ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። ለወትሮው የዘውግ ፖለቲካ ማቀጣጠያ የሆነው የታሪክ ተቃርኖ ወደጎን ተገፍቶ “ደምህ ደሜ ነው” በሚል ስሜት የሁለቱ ክልል ተወላጆች በአንድ ድምጽ፤ በህዳጣን የፖለቲካ ቡድን አንገዛም በማለት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት ንዲሁም ማህበራዊ ጥያቄዎችን ያነገበ በመሆኑ የአመጹን መሠረታዊ ምክንያት ተወራራሽነትና ተመሳስሎሽ ያመለክታል። ይሄው አመጽ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮችን ሥነ ልቦና ያናጋ፤ አገዛዙ “ቆምኩበት” የሚለዉን ማህበራዊ መሰረት በመናዱ በትግራይ ተወላጆች የበላይነት በሚመራው የጸጥታና የደህንነት ኃይሉ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ እንዲቀር በማድረግ፤ የአገዛዙ የደደቢት ልክፍት የሆነውን ምህረት የለሽ የጭካኔ ተግባራቱን አደባባይ ያወጣ፤ አገሪቱ በታሪኳ ካስተናገደቻቸው መንግስታዊ ፍጅቶች አይረሴ ኩነት ሆኖ ተመዝግቧል።

ህወሃት/ኢህአዴግ ከተራዘመው የአገዛዝ ዘመኑ እንደ 2008 እና 2009 ዓ.ም ተፈትኖ  የሚያውቅ አይመስልም። በኦሮሚያ ክልል መነሻውን የመሬት ባለቤትነት ባደረገ መልኩ  የተቀላቀለው ምሬት አዘል ህዝባዊ አመጽ ከህዳር 2008ዓም ጀምሮ በክልሉ ካሉ 17 ዞኖች ውስጥ በ15 ዞኖች፣ 91 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በተፈራራቂነት መቀጠሉ የአገዛዙ ራስ ምታት ሲሆን ታይቷል። ሐምሌ 05/2008 ዓም ጎንደር ከተማ ላይ የወልቃይት  አማራ ማንነት ጥያቄን መነሻ አርጎ የተከሰተው ብረት አካል ህዝባዊ አመጽ በአማራ ክልል 5 ዞኖች 55 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተፈጥረው ህዝባዊ አመጽ ማነቃቂያ ሆኖ አገልግሏል። በደቡብ ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ በኮንሶ የልዩ ዞን ጥያቄን፣ በጌዲዮ ዞንም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት ጥያቄዎችን መነሻ ያድርጉ ህዝባዊ አመፆች በሰፊው ታይቷል

በተለይም ከሐምሌ/2008 እስከ መስከረም/2009 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ሦስት ወራት በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከአገዛዙ የፀጥታ ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች ጎዳናው ላይ ወድቀዋል። ቤት ውስጥ እንዳሉ በቡድን የጦር መሳሪያ ጥቃት ደርሶባቸው የሞቱ፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸው፣ ታፍነው የተወሰዱና የደረሱበት የማይታወቅ ዜጎች ቁጥር ከግምት በላይ ነው። በአገዛዙ የኃይል እመቃና መንግስታዊ ፍጅት የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ቤት ይቁጠራቸው።

ለወራት ያህል ተራዛሚነቱን ባሳየው ህዝባዊ አመጽ የህወሃት/ኢህአዴግ የፀጥታ ኃይሎች የቡድን የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በነፍስ ወከፍ ክላሽንኮሽና የእጅ ቦንብ በመታገዝ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ እልቂት እንዳደረሱ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በአደባባይ ያጋለጡት ጉዳይ ነው። የአገዛዙ “አይዞህ” ባይ ድርጎ ሰፋሪ ምዕራባውያን በፖለቲካና ደህንነት አታሼዎቻቸው በኩል ያረጋገጡት እውነታም ነው። ምንም እንኳን ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚያደረጉትን ጉዞ እንዲሰርዙ መግለጫ ከማውጣት የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ሲያድርጉ ባይስተዋልም። አገራቱ ያደረጉትን የጉዞ ክልከላ ተከትሎ የአገሪቱ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ራቁቱን በመቅረቱ ከውጭ ንግዱ ማሽቆልቆል ጋር ተደምሮ የምንዛሬ ድርቀቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሽመድመዱ ተጽዕኖው ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ የሚታይ ነው

መንግስታዊ ፍጅቱን በሪፖርት ማፅደቅ . . .

ከላይ በተመለከተው አገራዊ ቀውስና መንግስታዊ ፍጅት የከረመችው ኢትዮጵያ፤ አገዛዙ በገዛ ዜጎቹ ላይ የፈፀመውን መንግስታዊ ፍጅት “ተገቢነቱንና ህጋዊነቱን” በህወሃቱ አዲሱ ገ/እግዚአብሔር የሚመራው የ“ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ከዚህ በኋላ ኢሰመኮ)” “መርምሬ ደረሰኩበት” በሚል በሪፖርቱ የአገዛዙን ድርጊት አፅድቆታል።

http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2015/01/addisu-g-election-board.jpg

ኢትዮጵያን ረግጦ እየገዛ ያለው አገዛዝ በበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ አማካይነት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ገለልተኛ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት በአዋጁ ቀርዳጅነት ተሽመድምደው ከአገሪቱ እንዲወጡ ተገፍተዋል። አገር በቀል ገለልተኛ ተቋማት ፍፁም ተቀብረዋል። አቅም አላቸው የሚባሉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የአገዛዙን ይሁንታ በማጣታቸው በአገር ቤት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ተገትተዋል። ከዚህ መርዘኛ አዋጅ መፅደቅ በኋላ አገዛዙ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የሚመጣበትን ጫና ለመቋቋምና በየጊዜው የሚፈፅማቸውን የአደባባይ ጭፍጨፋዎች “ተገቢነትና ህጋዊነት” በህዝባዊ ኑፋቄ ሪፖርቱ የሚያፀድቅበት ኢሰመኮ እንዲቋቋም ተደርጓል። የዚህ ህወሃታዊ ውገና (ክንፍ) መሪ ደግሞ የ2007 አገራዊ ግን የብቻ ቅርጫ (“ምርጫ” ላለማለት) 100% ለህወሃት/ኢህአደግና አጋሮቹ ያስረከበው “የምርጫ ቦርድ” ምክትል ፕሬዚዳንት የነበረው ህወሃቱ ቴክኖክራት አዲሱ ገ/እግዚአብሔር ነው።

በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ያማሞቶ ስለ አዲሱ ገ/እግዚአብሔርና ይመራው ስለነበረው ምርጫ ቦርድ ይህንን ማለታቸው ይታወሳል

“… ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር እንደሆነ እና ተቃዋሚዎች አስገራሚ ውጤት በምርጫው ላይ ካሳዩ በኋላ (የመራጮችን) ድምጽ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢህአዴግ) እንዳስረከበ ተቃዋሚ (ፓርቲዎች) አጥብቀው ይከስሳሉ፡፡ ከዚያ ወዲህ አዲስ ቦርድ የተሰየመ ቢሆንም ተቃዋሚዎች ግን አሁንም ትችታቸውን አላቆሙም፡፡ የቅንጅትን ስም እና ምልክት ፍጹም ለማይገባቸውና ለኢትዮጵያ መንግሥት የቅርብ ወዳጆች ለሆኑት ፖለቲከኞች ማስረከቡ ምርጫ ቦርድ ከአድልዎ የነጻ አለመሆኑ ላይ ያሉትን ጥርጣሬዎች እንደገና እንዲቀጣጠል አድርጓል፡፡ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር አዲሱ በቅርቡ ለዩኤስኤይድ ከፍተኛ የዴሞክራሲ አማካሪና የቀድሞ የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር (ስሙ እንዳይወጣ በጥብቅ የተከለከለ) ምርጫ ቦርድ “ቅንጅትን ለመግደል” ወስኖ እንደነበር መናገሩ እነዚህን ጥርጣሬዎች እርግጠኛ ያደርጋቸዋል፡፡ (የአዲግራት ተወላጅ የሆነው) (ዶ/ር አዲሱ የትግሬ የፖለቲካ ሳይቲስት ሲሆን የምርጫ ቦርድ “ፈጣሪና አድራጊ” እንደሆነ በሰፊው ይታመናል)፡፡ ባለፈው ሳምንት ምርጫ ቦርድ የወሰደው ውሳኔ (የቅንጅትን ስምና ምልክት ለቅጥረኞቹ መስጠቱ) ይህንኑ (ቅንጅትን የመግደሉን ዕቅድ) የሚያረጋግጥ ነው፡፡ . . . (ሹልክዓምድ (ዊኪሊክስ) ላይ የወጣውን ሙሉ መረጃ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል 15 ዞኖች (91 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች)፣ በደቡብ ክልል፤ ግርምት በሚጭር መልኩ ሰፊ እልቂት የደረሰበትን የኮንሶን ግጭት በመዝለል በጌዲኦ ዞን (6 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች) ብቻ የደረሰውን ግጭት “መርምሬለሁ” በሚል ሪፖርቱን ለህወሓት /ኢህአዴግ ፓርላማ አቅርቧል።

ሪፖርቱ ተዘጋጅቶ ይወጣል የተባለው የዛሬ ዓመት ነበር፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በወቅቱ “ህወሃት ራሱን በራሱ ሸንጎ አስገምግሞ የእጁን ደም ሊያጸዳ ነው፤ የኮሚሽኑ ሪፖርት በኢህአዴግ ጽ/ቤት መሰራቱ ተጠቆመ” በሚል ርዕስ ባስነበበው ዜና ዘገባው እንዲሰራ ያስገደደው ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት (ሒውማን ራይትስ ዎች) የህወሃትን ግድያ የሚያጋልጥ ዳጎስ ያለ ሪፖርት እንደሚያወጣ በመነገሩ መሆኑን ዘግቦ ነበር፡፡ የዓለምአቀፉ ድርጅት ዘገባ ከወጣም በኋላ ህወሃት ተስፋ የሰጠውን ዘገባ ለሕዝብ ይፋ እንዲደርግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ጌታቸው ረዳ የአፈቀላጤነቱን ሥልጣን ይዞ በነበረበት ወቅት ከዓለምአቀፉ ድርጅት ተወካይ ፊሊክስ ሆርን ጋር አልጃዚራ ላይ በቀረበበት ጊዜ ጥያቄው በግልጽ ተነግሮት መልስ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡ ከዚያ በማስከተልም በያዝነው ዓመት የህዳር ወር የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ለወርቅነህ ገበየሁ ነገዎ “በጽሁፍ የታተመ በእርግጥ ካለ ይፋ አድርጉት” በማለት የውትወታ ደብዳቤ መላኩ ይታወሳል (የጎልጉልን ዜና ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)፡፡

“የተወሰደው እርምጃ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ነው” እያለ ይፋ ባልሆነ ሪፖርት መግለጫ ሲሰጥ የቆየው ህወሃት/ኢህአዴግና “ኢሰመኮ” በፈጠራ መረጃዎች አምጦ የወለደውን ዘገባ ይፋ አውጥቷል፡፡ በ171 ገፆች የተወጠረው የኢሰመኮ ሪፖርት በሦስቱም ክልሎች የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተ “የተጎጅ ቤተሰቦችንና መንግስታዊ አካላትን በማነጋገር” የተዘጋጀ መሆኑን የህወሓቱ አዲሱ ገ/እግዚአብሔር በሪፖርቱ አመልክቷል። ቀድሞውንም የገለልተኝነት ጥያቄ የሚነሳበት ይሄው ድርጅት ህወሃታዊ ውገናውን በሚያስረግጥ መልኩ ሪፖርቱን አቅርቧል። አገዛዙ በዜጐቹ ላይ የፈፀመውን መንግስታዊ ፍጅት “ህጋዊና ተመጣጣኝ ነበሩ” በማለትም አጋርነቱን በድጋሚ አስመስክሯል።

ሪፖርቱ፡- የኦሮሚያን አመፅ በተመለከተ

በምስራቅ አርሲ፣ በባሌ፣ በምዕራብ ጉጂና በጉጂ ዞኖች በጦር መሳሪያ የተደገፈ ውጊያ እንደነበረ የሚጠቅሰው ሪፖርት፤ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በሶዶ፣ በአዳአ በርጋ፣ በሜታ ሮቢ፣ በደንቢ በተመሳሳይ በጦር መሳሪያ የተደገፈ ግጭት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር የነበረ በመሆኑ “በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደው ዕርምጃ ሕግን የተከተለ፣ ተመጣጣኝና ተገቢ ነበር” በማለት በሪፖርቱ ለህወሃት ያለውን ድጋፍ አሳይቷል።

ይሄው ሪፖርት በምዕራብ አርሲ፣ ሻሸመኔና አርሲ ነገሌ ውጊያ የተካሄደባቸው ቦታዎች በመሆናቸው “የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ መሆኑን” ይገልፃል። አገዛዙ በዜጎቹ ላይ የፈፀመውን መንግስታዊ ፍጅት “ተገቢ ነበር” የሚለው ይሄው ድርጅት ሚዛናዊ ሪፖርት ያቀረበ ለማስመሰል “በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 እስረኞች ሊያመልጡ ሲሞክሩ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ህግን ያልተከተለ፣ አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ያልነበረ” በማለት ይገልፀዋል። ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓም ዕለተ ቅዳሜ “በባሌ ዞን ሮቤ ከተማና በራይቱ ወረዳ የተካሄደው ሠላማዊ ሰልፍ ላይ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ተመጣጣኝ አልነበረም” የሚለው ሐሳዊ ሪፖርቱ፤ በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በአወዳይ ከተማ በአጋዚ ወታደሮች በተከፈተው ተኩስ “28 ሰዎች መሞታቸውን” ይጠቅሳል። በተመሳሳይ መልኩ በምስራቅ ወለጋ በነቀምቴ “12 ሰዎች ህግን ባልተከተለና ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ መገደላቸው ተገቢ አይደለም” ሲል በሪፖርቱ ይገልፃል።

በአጠቃላይ በዚህ ህወሃታዊ ድርጅት የተዘጋጀው ሐሳዊ ሪፖርት “ሚዛናዊ ነው” እንዲባልለት በብዙ መርዛማ ቅመሞች ተለውሶ ቀርቧል። ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓም በ15 የኦሮሚያ ዞኖች በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ መፈክር ይዘው በወጡ ወጣቶች ላይ የተኩስ እሩምታ በመክፈት በአንድ ቀን ብቻ 125 ዜጎች መገደላቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮች በጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀው ነበር። የኢሰመኮ ሪፖርት ግን የአገዛዙን መንግስታዊ ፍጅትና አረመኔያዊ ተግባር “ህጋዊና ተመጣጣኝ ነበር” በሚል ሊያፀድቀው ይሞክራል። “ጥልቅ ተሃድሶ  ላይ ነኝ” የሚለው አገዛዝ፤ በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ ሪፖርት እንዲወጣ ማድረጉ ካለፈ ታሪኩ ባለመማር ዛሬም በዜጎች ደም ላይ የሚያላግጥ ኃላፊነት የጎደለው አገዛዝ መሆኑን ይጠቁማል በማለት ዘገባውን የተከታተሉ ይናገራሉ።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

የኦሮሞን ባህላዊ ዕሴት ፍፁም በሚንድና በሚያዋርድ መልኩ በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ላይ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር በተሰበሰቡ የኦሮሞ ልጆችና ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎች ላይ በጭስ ቦምብና በተኩስ እሩምታ በታጀበ ምህረት የለሽ ድርጊት ከ250 በላይ ዜጎች ህይወታቸው እንዳለፈ፤ ከ1000 በላይ ዜጎች ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወስ ነው። ሪፖርቱ ይህን አሰቃቂ መንግስታዊ ፍጅት ፍፁም በመካድ አደጋው “በክልሉና በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዝላልነት የተፈጠረ ነው። በዓሉ እንዳይከበር አስቀድመዉ መከልከል ይችሉ ነበር” በማለት የህወሃትን የአደባባይ ሐጢያት ሊያነፃ ተፍጨርጭሯል። “የአደጋው አባባሽ” በሚል ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ኦኤምኤን፣ እና ሌሎችን የሚዲያ አውታሮችንና የፖለቲካ ድርጅቶችን ተጠያቂ ለማድረግም ሲሞክር ተስተውሏል።

እንደ ህወሓቱ ኢሰመኮ ሪፖርት “በኦሮሚያ ክልል ከሐምሌ/2008 እስከ መስከረም 2009 ዓም በተካሄደው ሁከት 462 ሲቪሎች ሲገደሉ 33 የፀጥታ አስከባሪዎች ህይወታቸው አልፏል። ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በክልሉ ወድሟል” በማለት ይገልፃል። በህወሃት የበላይ ሹማምንቶች ይሁንታ የወጣው ይሄው ሪፖርት የድርጅቱን በደም የጨቀዩ እጆች ለማንፃት የሟቾችን ቁጥር በአስር እጥፍ እና ከዚያ በሚልቅ መልኩ በመቀነስ ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ፡- የአማራ ክልል አመፅን በተመለከተ

ለአመታት በዘለቀው የዘር ማፅዳትና የግፍ አገዛዝ የብሔርተኝነት ቅርፁን መያዝ የጀመረው የአማራ ብሔርተኝነት፤ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄን መነሻው በማድረግ ተቃውሞው ወደ ከረረ ህዝባዊ አመፅ ማደጉ የሚታወስ ነው። በተቃውሞው የመጀመሪያ ጊዜያት ለአብነት ነሐሴ 01/2008 ዓም በባህርዳር ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ “የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት” ይፋ ባደረገው ሪፖርት 82 ዜጎች በአንድ ቀን ህይወታቸው ሲያልፍ ከ140 በላይ ዜጎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የባነር መፈክሮችንና የአገሪቱን የቀደመ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው በወጡ ዜጐች ላይ የተኩስ እሩምታ በመክፈት ጎዳናውን በደም ያጨቀዩት የፀጥታ ኃይሎች፤ ከዚህ ክስተት በኋላ ተቃውሞው ወደ በረታ ብረት አከል ህዝባዊ አመፅ ማደጉ ይታወሳል።

ሪፖርቱ በአማራ ክልል በአምስት ዞኖችና በሃምሳ አምስት ወረዳዎች በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ “110 ሲቪሎች ሲገደሉ፣ 30 የፀጥታ ኃይሎች መሞታቸውን” ይገልፃል። የአካል ጉዳትን በተመለከተ ይሄው ሪፖርት “276 ሲቪሎችና 100 የፀጥታ አስከባሪዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል” ይለናል። ሪፖርቱ በአማራ ክልል የታዩ ግጭቶችን ልክ እንደ ኦሮሚያ ክልል “ተመጣጣኝ” እና “ተመጣጣኝ ያልሆኑ እርምጃዎች” በሚል በሁለት ይከፍለዋል። መንግስታዊ ፍጅቱን “ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች” በሚል ማሻሻያ የሚገልፀው ይሄው ሪፖርት፤ በጐንደር አዘዞ፣ ደንቢያ፣ ወንበራ፣ ደባርቅ፣ ደብረታቦር፣ ስማዳ፣ እንጅባራና ዳንግላ ላይ የተፈፀሙ ግድያዎችን ተመጣጣኝ አልነበሩም ይላል። በአንፃሩ ነሐሴ 01/2008 ዓም ባህርዳር ከተማ ላይ በነበረው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ አገዛዙ የፈፀመውን መንግስታዊ ፍጅት በሪፖርቱ ውስጥ አላካተተውም። በአንድ ቀን 82 ሰላማዊ ሰልፈኞች የተገደሉበትን መንግስታዊ ፍጅት በሪፖርቱ የተገለጸ ነገር የለም። በሪፖርቱ ላይ “ተመጣጣኝ ያልሆነ ግድያ ተፈፀመባቸው” በሚል የተገለፁ ከተሞች/ወረዳዎች ላይ ለተከሰቱ ግጭቶች ቀደም ሲል ባህርዳር ከተማ ላይ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ አገዛዙ የፈፀመው መንግስታዊ ፍጅት ህዝባዊ ቁጣ ለመፈጠሩ የባህርዳሩ ፍጅት ቀስቃሽ እንደነበር ይታወሳል።

ኢሰመኮ በዘገባው “ተመጣጣኝና ህጋዊ ግድያ” በሚል የገለፀው መንግስታዊ ፍጅት፤ ሐምሌ 04/2008 ምሽት ጀምሮ እስከ ሐምሌ 05/2008 የሌሊቱ አጋማሽ ድረስ የዘለቀው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበሩ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱና የከተማውና አካባቢዉ ህዝብ (ህዝባዊ ጦር) ለአፈና ከመጣው የፌዴራል ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይልና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዘዞ ምድብተኛ 24 ክፍለ ጦር የተመረጡ የመከላከያ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር የተደረገውን ጦርነት ነው። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የዓይን ምስክሮች እንደሚናገሩት “የመንግስት ኃይሎች መትረየስና ዲሽቃን የመሳሰሉ የቡድን የጦር መሳሪያዎችን በዕለቱ ውጊያ ተጠቅመዋል” ይላሉ። በአንፃሩ ኮሌኔል ደመቀ ዘውዱና የከተማው ህዝባዊ ጦር ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችሏቸዉን የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎችን” መጠቀማቸውን አይሸሽጉም።

ይህ በሆነበት ሁኔታ በዕለቱ “12 የፀጥታ ኃላፊዎችና አራት ሲቪሎች መገደላቸውን፣ በማረሚያ ቤት የተወሰደው ዕርምጃም ህግን የተከተለ ነው” በማለት በውገና ሪፖርቱ የአገዛዙ የፀጥታ ኃይሎች በቡድን የጦር መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃታቸውን “ተገቢነት” በማፅደቅ፤ የህዝቡን ተከላካይነት በሪፖርቱ “ኮንኗል”።

በተለየ መልኩ ከሐምሌ 05/2008 ጀምሮ ጎንደር ከተማና በሰሜን ጐንደር ስር ባሉ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በአገዛዙ የፀጥታ ኃይሎች ላይ የደረሰውና የሚደርሰው የሞትና የአካል ጉዳት መጠን 10፣ 20፣ . . . በሚል መቆጠር ካቆመ ቆየት ብሏል። ጥቃቱ እየጨመረና እየተባባሰ በመምጣቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ኃይሎች እየረገፉ እንደሆነ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አገዛዙ በፀጥታ ኃይሉ ላይ የደረሰበትን ጉዳትም ሆነ በአደባባይ የፈጃቸውን ዜጐች ቁጥር በአስር እጥፍ ቀንሶ በኢሰመኮ በኩል ሪፖርት ማውጣቱ መንግስታዊ ፍጅቱን “በተመጣጣኝና ህጋዊነት” ሥም ለማፅደቅና ኪሳራውን በቀላሉ በመግለፅ “እኔም ተጐጂ ነበርኩ” ለማለት ያለመ ነው።

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ሪፖርቱ የኮንሶን ጭፍጨፋ በመዝለል የጌዲኦ ዞንን ጉዳይ ለይቶ ስለማንሳቱ

በ2008 ዓም የኮንሶ የልዩ ዞን ጥያቄ በተወላጆች አስተባባሪነት በሰላማዊ ሰልፍ ተቀጣጥሎ ቀርቦ ነበር። ቀላሉ ጉዳይ እየተወሳሰበ በመሄዱ አገዛዙ መዉሰድ በጀመራቸዉ የኃይል እርምጃዎች በርከት ያሉ የአካባቢዉ ተወላጆች እንደሞቱ የሚታወስ ነዉ። በዚህ የተነሳ ከታህሳስ 2008 ጀምሮ በኮንሶ ልዩ ወረዳ መደበኛ የመንግስት ተቋማት ለሰባት ወራት ያህል ተዘግተው ነበር። የአካባቢው የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ አልባ ሆነው መቀመጣቸውና ተቋማቱ በአመፅ ከጥቅም ውጪ መሆናቸው እያነጋገረም ነበር። በነዚህ ወራት በደረሰው ግጭት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ በኮንሶ ተወላጆች ላይ የከፋ ጭፍጨፋ አድርሰው የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ በኢሰመኮ ሪፖርት ሆን ተብሎ አልተካተተም። የኢሰመኮ ሪፖርት ከሐምሌ/2008 እስከ መስከረም/2009 ድረስ ያለውን ግጭት ብቻ የሚያጠቃልል ነዉ ቢባል እንኳ የኮንሶ ግጭት እስከ መስከረም 2009 ድረስ ቀጥሎ ነበር።

ከዚህ ተጻራሪ በሆነ መልኩ ሪፖርቱ በደቡብ ክልል ከተነሱ ግጭቶች የጌዴኦ ዞንን ብቻ አካቷል። እንደ ዘገባው “በጌዲኦ ዞን አራት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት 34 ሰዎች ተገድለዋል” ይላል። “በ178 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል” በሚለው ይሄው ሪፖርት፤ “ከጌዴኦ ብሔር ዉጪ ያሉ 8450 ተለያዮ ብሔሮች አባላት ከቀያቸዉ ተፈናቅለዋል” በማለት ይገልጻል። “ስር የሰደዱ የመልካም አስተደደር ችግሮችና ሥራ አጥነት” የግጭቶቹ መነሻዎች ነበሩ የሚል ከፖለቲካ የራቀ ምክንያት ይሰጣል።

የሪፖርቱ ፖለቲካዊ መዶሻነት!

በህወሃቱ አዲሱ ገ/እግዚአብሔር የሚመራው ኢሰመኮ በኩል ይፋ የተደረገው ሪፖርት ሦስት የተጠኑ ፖለቲካዊ ዓላማዎችን የያዘ ይመስላል። የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ዓላማ የተባበሩት መንግስታትና የአዉሮፓ ህብረትን ጨምሮ ዓለምአቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በገለልተኛ ወገን “እንመርምር” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። ለእነዚህ ዓለምአቀፍ ተቋማት በጎ ምላሽ የነፈገው ህወሃት “በራሳችን ነፃና ገለልተኛ ተቋም ጉዳዩን ማጣራት ችለናል” የሚል መልዕክት ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ማስተላለፍ ተቀዳሚ የፖለቲካ ዓላማው ነው። በሪፖርቱ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ “ተመጣጣኝ የሆነ” እና “ተመጣጣኝ ያልሆነ ግድያ” እያለ የዘረዘራቸው ጉዳዮች ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በሐሳዊነት የቀረቡ መደለያዎች ናቸው።

ሁለተኛው የሪፖርቱ ፖለቲካዊ ዓላማ በተለይ መልኩ በሁለቱ ክልሎች (ኦሮሚያና አማራ) ያሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮችን፤ ንቁ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ሞጋች ወጣቶችን በድጋሚ ለማጥቃት ያለመ ይመስላል። ለአብነት “በኦሮሚያ ክልል ሁከትና ብጥብጥ እንደሚነሳ እየታወቀ ዕርምጃ ባልወሰዱ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በህግ እንዲጠየቁ” የሚለው የሪፖርቱ ክፍል አሁንም ኦህዴድ ቤት ተጨማሪ ድርጅታዊ ማፅዳት እንደሚኖር ሪፖርቱ ይጠቁማል። ምናልባትም እነዚህን በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከኦነግና ከኦኤምኤን ጋር በማዛመድ የ“ሽብርተኝነት” ወጥመድ በህወሃት ሰዎች ተጠምዶ ሊሆን ይችላል። ሌላው በአመራሮቹና አባላቶቹ እስርና ግድያ መዋቅሩ የፈራረሰው ኦፌኮ ከእስር የተረፉ አመራሮቹ የግጭቱ አባባሽ ነበሩ በሚል በሪፖርቱ መፈረጃቸው የሪፖርቱን ፖለቲካዊ መዶሻነት ያመለክታል። ይህ መሰሉ ፍረጃ በአማራ ክልል ለታየው ግጭት በተመሳሳይ መልኩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የፀጥታ ዘርፍ አባላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ሪፖርቱ አፅኖት ሰጥቷል። ነሐሴ 01/2008ዓም በባህርዳር ከተማ በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ የሟቾችን ቁጥር ከመግለጽ የተቆጠበዉ ሪፖርቱ፤ “በሰልፉ ለደረሰዉ ሰብዓዊና የንብረት ዉድመት ሰማያዊ ፓርቲ ተጠያቂ ነዉ” በማለት ይወነጅላል። ሪፖርቱ በሁለቱ ክልሎ የታዩትን ህዝባዊ እምቢተኝነቶች ለማፈንና በብአዴንና በኦህዴድ ውስጥ በተለይም በመካከለኛ አመራሩ የታየውን አፈንጋጭነት በ“ተጠያቂነት” ስም ለመድፈቅ የተቀባበለ ፖለቲካዊ መዶሻ ነው።

ሦስተኛው የሪፖርቱ ፖለቲካዊ ዓላማ ህወሓት ለወጣበት ዘውግ የበላይነትና ልዕልና የሚተጋ ቡድን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለ ጉዳይ ነው። በሪፖርቱ እንደተመለከተው “በአማራ ክልል ብሔር ተኮር ጥቃት በመካሄዱ 11,678 የትግራይ ተወላጆች ተፈናቅለዋል” ይላል። በሪፖርቱ ምክረ ሃሳብም የክልሉ መንግስት “ለተፈናቃዮች ተገቢ ካሳ ሊከፍልና መልሶ ሊያቋቁማቸዉ ይገባል” በሚል ጥብቅና ቁሟል። ከዚህ ቀደም አማራ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ በምስራቅ፣ ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለዓመታት ከኖሩበት ቦታ ለተፈናቀሉ ዜጎች ቀርቶ ካሳ አጥጋቢ ምላሽ ባልተሰጠበት ሁኔታ፤ ግጭቱን በመፍራት ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳይደርስባቸው የቀደመ ተግባራቸዉ አስፈርቷቸዉ ለሸሹ የትግራይ ተወላጆች “ካሳ ይከፈል” የሚለው ሙግት፤ ትግራዋያንን ከበዳይነት በማንፃት ተበዳይ አድርጐ በማቅረብ በአገሪቱ ያለውን የብሔር የበላይነት በአደባባይ ለማስተባበል የታቀደ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ሪፖርት ነው እንዲባል ያደርገዋል።

ሪፖርቱ በግጭት ወቅት የታሰሩትን፣ የደረሱበት ያልታወቁ ዜጐችን ጉዳይ የተመለከተ ዘገባ ካለማካተቱ በላይ ከሲቪልም ሆነ ከፀጥታ ኃይሉ የሞቱና የተጎዱ ዜጎችን ቁጥር በአስር እጥፍና ከዚያ በላይ በመቀነሰ የቀረበ አህዛዊ መረጃ ነው። ህወሃታዊ ውገና የታየበት ይሄው ሪፖርት የአገዛዙን መንግስታዊ ፍጅት በማፅደቅ ተደምድሟል። ይህ ሪፖርት ለህዝቡ ተጨማሪ አመፅ መቀስቀሻ ደወል ሲሆን፤ ለትግራይ ተወላጆች ደግሞ ተጨማሪ የነገ የደም ዕዳ አመላካች ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ለጎልጉል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

goolgule.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *