ስምንት እግሯን እየጎተተች በበሩ ቀዳዳ ስትገባ አየኋት፡፡ ወትሮም ለነፍሳት አልደነግጥም፡፡ እየጮህኩ አልሮጥም፡፡ በአንዱ እጄ ወደ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እየደወልኩ በሌላኛው ያገኘሁትን ቁስ አልወረውርም፡፡ እስካልነኩኝ እስካልጎዱኝ ድረስ አሳድጄ ለመግደል አልሞክርም … 50 እግር ስታይ ከዙ ያመለጠ አንበሳ እንዳየ የምትደነብር እና … ለቢንቢ ‘እሽሽሽ’ መባል አንሷት መግደያ ወይም ፎጣ ነገር ይዞ ከአልጋ ወደ ወንበር የሚዘልን ሰው እንደማየት የሚያስቅ ምን ነገር አለ?
.
ሰዎች ከበላዮቻቸው ካሉ ጋር ብቻ ሳይሆን ከበታቾቻው ጋር ያላቸው የስልጣን ተዋረድ እና ግንኙነት ማንነታቸው ይመዘናል … አንዳንዶች የበላዮቻቸው እግር ስር የጣሉትን ክብር የበታቾቻውን አናት በመኮርኮም … በጩኸት በማሳቀቅና ጨፍልቆ በመግደል ሊያገኙት ይሞክራሉ … እነሱንም እንደ ቢንቢ መጨፍለቅ የሚችል አካል መኖሩን ይዘነጋሉ… አንድ ሱናሚ ወይም ቶርኒዶ በቂ አይደለም?
.
በእግሬ ስር ያለችን በረሮ ልገድላትና ላድናት እየቻልኩ በመጨፍለቅ ምን አይነት ጀብዱና የድል አድራጊነት ስሜት እንደሚገኝ አላውቅም፡፡ ከእኔ ጋር መስመር ላይ ብንገናኝ እንኳ… እዛ ሰባተኛ መኪኖች ባቡሩን እንደሚያሳልፉት ቆሜ በትህትና አሳልፋታለሁ እንጂ አልጨፈልቃትም … አዎ ከሞት ህይወት ይሻላል… እኔ ከህይወት ወገን ነኝ፡፡ አሁን ራሱ በቤቴ ወለል ላይ የምትንጎራደደውን ባለ ድር አልፈራኀትም… በነፃነት ዓይኔ እያየ ወለሉን አቋረጠች … እሷን ለመግደል ሳመነታ … ያጠፋችውን ጥፋት እና የበደለችኝን በደል ለማስታወስ ስሞክር (መቼም ሸረሪት ስለሆነች ብቻ አልገድላትም)… ከወንበሩ አራተኛ እግር ደረሰች …ጫማዬ ውስጥ ገብታ ወጣች … በመጋረጃው ተንጠላጠለች…መቅዘፍ ስትችል በእግሯ ምን አለፋት? ከሞቀ አልጋዬ መነሳት ደክሜ በዓይኔ ስከተላት ድሯን ተመኘሁ…መንሳፈፍ አማረኝ… እንደ እፉዬ ገላ… ነፍስ የሌላቸው፡ ነፋስ የሚገፋቸው የሚንሳፈፉ … ቦታ ሳይመርጡ እንደሚያርፉ …
.
ሰዎች የሸረሪትን ድር ለምን እንደሚጠርጉ አላውቅም፡፡ይህ የወፍ ጎጆን ኢላማ አድርገው ድንጋይ ውርወራ ከሚለማመዱ ስራ ፈት ማቲዎች ተግባር የተለየ አይደለም… ቆሻሻን የማያውቁ ሁሉ “ቆሻሻ” ነው ይሉታል፡፡ በየስርቻቸው በየአደባባዮቻቸው ቆሻሻ ጎዝጉዘው … እንደ እነሱ በድንጋይ ስላልታነፀ ብቻ ‘ቤት’ን ቆሻሻ ይላሉ … ድር ለሸረሪቷ ህልውናዋ ነው…ደግሞ ሲያምር ባለሙያ ያጠላለፈው ዳንቴል አይመስልም? ኑሮዋ እና ምግብ ማጥመጃዋ ይህን መበጣጠስ በአሳ አጥማጅነት ኑሮውን የመሰረተውን ሰው መረብ እንደ መበጣጠስ ቅጥ ያጣ ጭካኔ እና ራስ ወዳድነት ይመስለኛል፡፡ ቆይ ቆይ … ይህ ራሱ ጥሩ ምሳሌ አይደለም፡፡ ዓሳስ ለምን ይጠመዳል?

Teym Tsigereda Gonfa

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *