የባቢሎን አነሳስና አወዳደቅ፤ የከተሜነት ፈተናና “መዘዝ”

• የባቢሎን ስልጣኔና የባቢሎን ቋንቋ፤ “ሃጥያት እና ቅጣት” ናቸው?
• ቴክኖሎጂ መፍጠር፣ ከተማ መመሥረትና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ መገንባት፣ ሃጥያት ነው?

ከአዳምና ከሔዋን አስገራሚ ታሪክ፣ መጨረሻው አላማረም። ዓለምን ከዳር ዳር ወደሚያናውጥ ምዕራፍ ነው የሚሸጋገረው። የሕይወት ዘርን ሁሉ እንዳልነበረ የሚጠፋ ትልቅ መዓት ዓለምን ያጥለቀልቃል። የሰው ልጅ ታሪክም፣ እንደ አዲስ ‘ሀ’ ተብሎ ይጀመራል – በጨለማ ተውጦ የነበረውን ዓለም ወገግ የሚያደርግ፣ የእውቀትና የስልጣኔ ብርሃን የሚለኮስበት ዘመን፣ ‘1’ ተብሎ እንዲመዘገብ ብቅ ይላል።
በጎርፍ ማግስት፣… ሁሉም ነገር ኦና በሆነበት ወቅት፣ በራሳቸው አእምሮና እውቀት የሚተማመኑ ሰዎች፣ የአፈርን፣ የውኃን እና የእሳትን ምንነት መርምረው፤ በጠንካራ አላማ፣ አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ ፈጥረው ለስኬት ሲነሳሱ ይታያችሁ።
“ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንጥበሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው።… ኑ ለራሳችን ከተማ እንሥራ። ጫፉ እስከ ሰማይ የሚደርስ ሕንፃ እንሥራ፤ …ስማችንን እናስጠራው አሉ።” (ዘፍጥረት ምዕ10)
በአእምሮውና በእውቀት ላይ ተማምነው፣ የራሳቸውን ኑሮ በራሳቸው ምርጫና ጥረት ለመምራት፣… በራዕይ እና በአላማ ከፍ ከፍ ለሚሉበት፣ በፈጠራ እና በጥረት ወደ ስኬት የሚገሰግሱበት፣ የጀግንነት ቅዱስ ሰብዕናን የሚቀዳጁበት፣ አዲስ የስልጣኔ ታሪክ  ተከፈተ። አሳዛኙ ነገር፣ ይህ የእውቀት፣ የብልፅግናና የጀግንነት ዘመን፣ ብዙም ሳይቆይ በአጭሩ ተቀጭቷል። ብሩህ የስልጣኔ ጅምር፣ ብልጭ ብሎ ተመልሶ ድርግም ብሎ ጠፋ። ለምን? እስቲ ከመነሻው እንጀምር። መነሻው የአዳም ታሪክ ነው (ማለትም፣ እስከ ኖህ ድረስ የሚዘልቀው የአዳም ትውልድ ታሪክ)። “የሰው ልጅ ቀደምት ታሪክ” ብለን ልንሰይመውም እንችላለን።
የቀደምት ሰዎች ዘመን፣ ብዙም ጉልህ ታሪክ ያልተሰራበት ዘመን እንደሆነ፣ መጽሐፉ ይጠቁማል። እንዴት በሉ። ከሁለት ሺ በላይ ዓመታትን በሚሸፍነው ረዥም ዘመን ቢሆንም፤ የአዳምና የሔዋን ታሪክን ተከትሎ የሚመጣው ትልቁ ክስተት… የኖህ ታሪክ ነው። ከመነሻው ዘልሎ መደምደሚያው ላይ እንደመድረስ ነው። በሌላ አነጋገር፤ የቀደምት ሰዎች ታሪክ ማብቂያና ወደ አዲስ ታሪክ መሸጋገሪያ ነው – ኖህ። ከገጠርና ከእርሻ በተጨማሪ፣ ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ወደ ከተማ ምስረታና ወደ ሕንፃ ግንባታ መሸጋገሪያ!
ከዚያ በፊት ግን፣ አንዲት አጭር ትረካ አለች።

ከብት አርቢ እና አራሽ ገበሬ…
አዎ፣ ከኖህ በፊት፣ የአቤል እና የቃየን ታሪክን መጥቀስ ይቻላል። እንስሳት አርቢ የነበረው አቤል፣ በአራሽ ገበሬው በቃየን እንደተገደለ ይጠቅሳል – ዘፍጥረት ምዕ.4። በአንድ በኩል የግድያ ወንጀልን የሚተርክ ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በስደት ላይ የተመሠተው የከብት አርቢዎች አኗኗርን ለመቀየር የተደረገ የሰው ልጅ ግብግብን ለማሳየት የሚሞክር ይመስላል። የአራሽ ገበሬ አኗኗርን ለመቀለስ፣… በአንድ ቦታ አካባቢውን አልምቶና አሳምሮ ለመኖር የሚያስችል የእርሻ ስራ ተጀመረ እንደማለት ነው።
በእርግጥ፣ ቃየን፣ ከእርሻ በተጨማሪ፣ ከተሜነትንም ለመጀመር ሞካክሯል። ግን ከተሜነትን ከመቅመስ ያለፈ፣ የሚረባ ታሪክ አልሰራም። እንዲያውም፣ በአጠቃላይ የቃየን እና የልጆቹ ሕይወት፣ ገና ከውጥኑ በከንቱ እንደቀረና ከታሪክ መዝገብ እንደተሰረዘ ነው የሚቆጠረው። ትረካውን ተመልከቱ። ዘፍጥረት ምዕ.4፣ አዳምና ሔዋን፣ ቃየንን እንደወለዱ በመግለፅ ነው የሚጀምረው። ቃየን በተራው ማንን እንደወለደ፣ ከዚያም፣ የልጅ ልጅ እያለ፣… እስከ ሰባት ትውልድ ይዘረዝራል… “አዳም፣ ቃየን፣ ሄኖሕ፣ እይራድ፣ ሜኤል፣ ማቱሣኤል፣…” (ይሄኛው ማቱሣኤል፣ በረዥም እድሜ ሪከርድ የበጠሰው ሰውዬ አይደለም። ሌላ ነው። ለነገሩ፣ ከዚህ ጎን ለጎን፣ ሌሎች የሥም ምስስሎሾችም አሉ – ግርምትን የሚፈጥሩ)። ለማንኛውም፣ ከማቱሣኤል በኋላ የሚመጣው ላሜሕ ነው። እሱም በተራው፣ ልጆችን ይወልድና… ይወልድና… ከዚያ በኋላ ምንም የለም። በቃ፤ የቃየን የትውልድ ታሪክ፣ እዚያው ተንጠልጥሎ ይቀራል።
የመጽሐፉ ትረካ ወደ ምዕራፍ 5 ሲሸጋገር፤ የአዳም፣ የቃየን እና የልጅ ልጆችን ታሪክ ትቶ፤ በሌላ ይተካዋል። ወደ ኋላ ወደ አዳም እና ወደ ሔዋን ተመልሶ ታሪኩን እንደ አዲስ ይጀምረዋል። አዳምና ሔዋን፣… ሴትን ወለዱ። ሴትም ሄኖስን ወለደ… እያለ የትውልድ ሐረግ ይዘረዝራል… ሄኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤል፣ ያሬድ፣ ሄኖክ፣ ማቱሳላህ፣ ላሜሕ፣ ከዚያም ኖህ በማለት እስከ 10ኛ ትውልድ ይደርሳል።
እዚህ ላይ፣ ሁለት ነገሮችን ልብ እንበል።
አንደኛ፣ እንደ አዲስ በተተረከው የትውልድ ሐረግ ላይ የተዘረዘሩትን ስሞች ተመልከቱ። ቀደም ሲል በቃየን በኩል የተዘረዘሩትንም ሥሞች እዩ። ላሜሕ እና ላሜሕ፣…  ማቱሣኤል እና ማቱሳላህ፣… እይራድ እና ያሬድ፣… ሜኤል እና መላልኤል፣ ይመሳሰላሉ። በቃየን በኩል የጠቀሰው ሄኖሕ ደግሞ፤ ከሄኖስ፣ ከሄኖክ እና ከኖህ ጋር… ተቀራራቢ ድምፅ አለው። በእርግጥ የሰዎቹ ሥም ተቀራራቢ ስለሆነ፣ “አንዱ የትውልድ ሐረግ፣ የሌላው ግልባጭ ነው” ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል። ቢሆንም ግን፣… እንደገና ተደግሞ የተጻፈ እንደሚመስል አይካድም።
ሁለተኛው ነጥብ፣ “የአዳም የትውልድ ታሪክ”፣ ኖህ ላይ ሲደርስ፣ በጅምር ማብቃቱ ያስገርማል። ኖህ ልጅ እስኪወልድ ድረስ ያለው ዘመን ብቻ ነው፣ “የአዳም የትውልድ መዝገብ” ተብሎ የተዘረዘረው። ለምን?
ዘፍጥረት ምዕ5፤ “የአዳምን የትውልድ መጽሐፍ ይህ ነው” በማለት፣ ትረካውን እንደገና “ሀ” ብሎ ሲጀምር፤… “አዳም” ማለት “ቀደምት ሰዎች” ማለት እንደሆነ ይጠቁማል። ስለዚህ፤ “የሰው ልጅ መነሻ የትውልድ መዝገብ ይህ ነው” ብለን ልናነብበው እንችላለን።
“የአዳም  የትውልድ መጽሐፍ (የሰው ልጅ መነሻ ታሪክ) ይህ ነው። እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረ ቀን፣ በእግዚአብሔር ምሳሌ ሠራው። ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም… አዳም ብሎ ጠራቸው።”
ከዚያስ? ያው ቃየን ከትውልድ መዝገብ ውስጥ ተሰርዟል። አሁን በሌላ አዲስ የትውልድ ሐረግ ተተክቷል። ታዲያ፣ አዲሱ ትረካ፣… የልጅ እና የልጅ ልጆችን ሥም ብቻ ሳይሆን፣ እድሜያቸውን አንድ በአንድ ዘርዝሯል። ከትውልድ ትውልድ፣ ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖህ ድረስ፣ የእያንዳንዱ ሰው እድሜ ተተርኳል። ታዲያ በደፈናው አይደለም እድሜያቸው የተጻፈው። በስንት እድሜያቸው ልጅ እንደወለዱ፣ ከዚያ ለስንት ዓመት እንደኖሩ፣ በመጨረሻም በስንት እድሜያቸው እንደሞቱ ተዘርዝሯል።
“አዳምም 230 ዓመት ኖረ። ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ፤ ሥሙንም ሴት ብሎ ጠራው። …ሴትን ከወለደ በኋላ የኖረው 700 ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። …የኖረበት ዘመን ሁሉ 930 ዓመት ሆነ፤ ሞተም።”…
“ታሪኬ ባጭሩ” እንደሚሉት ዓይነት ነው። በዚሁ የአጻጻፍ ቅርጽ፣ የአሥር ሰዎች “ታሪኬ ባጭሩ” ቁጭ ቁጭ ብሏል።
መቼም፤ የእድሜያቸው ርዝመት ለጉድ ነው፤ አብዛኞቹ ከዘጠኝ መቶ ዓመት በላይ አስቆጥረዋል። ከፍተኛው የማቱሣላህ ነው – 969 ዓመት።
የመጀመሪያ ልጅ የሚወልዱትም 150 ዓመት ካለፋቸው በኋላ ነው። ኖህ ደግሞ፣ በ500 ዓመቱ ነው ልጅ የሚወልደው። ልክ እዚህች ላይ፣ ትረካው ያበቃል።
በቃ፤ የአዳም የትውልድ ታሪክ ይሄው ነው። የሰው ልጅ መነሻ ታሪክ ተፈፀመ። በ2156 ዓመታት ተጠናቀቀ።

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

ልዩ ቁጥር – 2156!!
ይሄ ቁጥር፣ እንደ ግረየም ሃንኩክ ለመሳሰሉ ጸሐፊዎች፣… ቁጭ ብድግ የሚያስብል አስደናቂ ቁጥር ነው።
አንዱን ዓመት “በ12 ወራት” እንደምነክፈለው ሁሉ፣ እነ ግረየም ሐንኩክ ደግሞ፣ ጠቅላላ የታሪክ ኡደትን “በ12 ሑረት” ይከፍሉታል። አንድ የታሪክ ኡደት፣ 25ሺ ዓመት ገደማ ነው። precession ይሉታል የአስትሮኖሚ ሳይንቲስቶች። እቅጩን ሲናገሩም፣ 25,868 ዓመታትን እንደሚሸፍን ይገልፃሉ።
ይሄንን ነው ለ12 ሑረቶች የሚከፍሉት (የዓመት ወር ሳይሆን የታሪክ ወር እንደማለት ቁጠሩት)። አስትሮሎጂ ላይ ለ12 ምሕዋር ተከፋፍሎ የምናየው የዞዲያክ ኡደትም ከዚህ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም።
እንግዲህ፣ አስትሮሎጂውን ወደ ጎን እንተወውና፣ በሳይንስ ስሌት፣ አንድ ሑረት ስንት ዓመታትን ይሸፍናል ብለን እንጠይቅ?
አንድ ሑረት፣ 2155.67 ዓመታትን ይሸፍናል። ማለትም 2156 ዓመታት!
እሺ። የሰው ልጅ መነሻ ታሪክ ይህ ነው ተብለው በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ላይ የተዘረዘሩት ዓመታት ሲደመሩ፣ ስንት ሆኑ?
2156 ዓመታት – የሰው ልጅ መነሻ ታሪክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ልንለው እንችላለን።
አስገራሚ ግጥጥሞሽ! ሊሆን ይችላል።
ለማንኛውም፣ የሰው ልጅ ቀደምት ታሪክ ተጠናቀቀ – በ2156 ዓመታት። የቀደምት ሰዎች የታሪክ መዝገብ ተዘጋ። አንድ የታሪክ ምዕራፍ ተፈፀመ፤ ወደ ሌላ ምዕራፍ ሊሸጋገር።
ነውጠኛ የታሪክ ሽግግር
እነ ግረይም ሐንኩክ፣ የኖህ አይነት ታሪኮችን ከአስትሮኖሚ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ የሚያምኑ ከምር ነው። ሌሎችንም ለማሳመን፣ ከሳይንስ ጋር እየቀላቀሉ ሃሳባቸውን ለማሳመር ይሞክራሉ። እንደነሱ አባባል ከሆነ፣ 2156 ዓመታትን ያቀፈ አንድ የታሪክ ምዕራፍ፣ አንድ የታሪክ ወር፣ አንድ ሑረት ሲጠናቀቅ፣… ነባሩ ታሪክ ያበቃለትና በሌላ ይተካል። አንዱ ታሪክ አርጅቶ፣ ሌላ እንደ አዲስ ይወለዳል።
እንዲህ ሲናገሩት ቀላል ይመስላል። ግን አይደለም። አንድ የታሪክ ምዕራፍ እንዴት እንደሚያበቃና ሌላ ምዕራፍ እንዴት እንደሚከፈት ለማሳየት፣ እነ ሐንኩክ የሚያቀርቡትን ምሳሌ መታዘብ ትችላላችሁ።
የነ አዳም ትውልድ፣… ማለትም የቀደምት ሰዎች ታሪክ ተጠናቀቆ ወደ ሌላ የተሸጋገረው እንዴት ነው? ታይቶ በማይታወቅ እልቂት! አለምን ከዳር ዳር በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ!
ሸለቆና ተራራውን ሁሉ በውሃ ሙላት ተውጦ፣ ነፍስ ያለው ሁሉ ሰምጦ አለቀ – የኖህ መርከብ ውስጥ ከተጠለሉት በስተቀር። ይሄ፣ ምሳሌያዊ አነጋገር ካልሆነ፣… በጣም ይዘገንናል። እነ ሐንኩክ እንደሚሉት፣ በእውን የተከሰተ እልቂት ከሆነ ግን፣ ዘግናኝነቱ በምንም ሊገለፅ አይችልም። አሳዛኝ፣ አስጨናቂ፣ ዘግናኝ ታሪኮች ሁሉ ቢደማመሩ እንኳ፤ ከዚያ የኖህ ዘመን እልቂት ጋር ሊስተካከሉ አይችሉም።
እንደ ምሳሌያዊ ትረካ ቆጥረን፣ አንድ የታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ፣ ሌላ ተከፈተ ብለን መቀጠል እንችላለን። ወይም ደግሞ፣ “ለዘመናት የተጠራቀመ የሰዎች ስህተት፣ ድክመትና ጥፋት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገዘፈና እየተቆለለ ይቆይና፣ የሆነ ጊዜ ላይ ጎርፍ ሆኖ አገር ምድሩን ያጥለቀልቃል፤ የሕይወት ዘርንም ይጠፋል” የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ትረካ ነው ብለን ልንረዳው እንችላለን።
የቁጥሩ ነገርስ? 2156?
እንግዲህ፣ የቀደምት ሰዎች ታሪክ፣ ኖህ ልጆችን እስኪወልድ ድረስ የነበሩ ዘመናት፣ ተመልሰው ላይመጡ ተዘግቷዋል – በ2156 ዓመታት የአዳም መዝገብ እንዲህ ከተዘጋ በኋላ፣ 100 ቆይቶ ዓለም በውኃ ሙላት፣ በጎርፍና በእልቂት ተጥለቀለቀች። ሁለቱን በመደመር ይመስላል፤ አለቃ ታየ፣ የጎርፍ እልቂት የተከሰተው በ2256 ዓመት እንደሆነ የሚገልፁት (የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ገፅ 6-7)።
በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በአማርኛ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተዘረዘሩት የነ አዳም እድሜዎችን በመደመርም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል (ዘፍጥረት ምዕራፍ አምስትን ይመልከቱ)።
ግረየም ሐንኩክ ደግሞ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ ቃል በቃል ከተቆጠረ፣ እስከ ጎርፍ ጥፋት ድረስ ያለው ጊዜ 2242 ዓመት እንደሚሆን ይገልፃል (Graham Hancock፣ FINGERPRINTS OF THE GODS ገፅ 369)። በሌላ አነጋገር፣ የአዳም የታሪክ ዘመን 2142 ዓመታት ይሆናል ማለት ነው። በአማርኛው መፅሐፍ ቅዱስ ከተዘረዘሩት ዓመታት ጋር ይቀራረባል።
በእግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ላይ የምናገኘው ትረካ ግን ከዚህ ይለያል። በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ላይ ከአዳም እስከ ኖህ ድረስ የተዘረዘሩት ዓመታት፣ 1565 ናቸው።
ግን፤ ዋናው ጉዳይ ያለው፣ ቁጥሮቹ ላይ አይመስለኝም። በኖህ ዙሪያ ከተተረኩት ታሪኮች መካከል፣ ትልቁን ቁምነገር የምናገኘው፣ ከጎርፍ ጥፋት በኋላ በተፈጠረው አዲስ ክስተት ነው – በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ።
በእርግጥ፣ ከጎርፍ ትረካ በኋላ የሚመጣው፣… የኖህ ልጆች የትውልድ ታሪክ ነው። ሌላ ሰው ሁሉ ከምድር ስለጠፋ፣ የኖህ ልጆች ታሪክ ማለት፣ “እንደ አዲስ የተጀመረ የሰው ልጆች ታሪክ” እንደማለት ነው። ያው፣ በደረቁ፣ የኖህ ልጆች፣ ሴም፣ ያፌትና ካም፣ በየፊናቸው እነማንን እንደወለዱ፣ ከዚያም የልጅ ልጆችን… እያለ የትውልድ ሐረግ ይዘረዝራል – አምስት ትውልድ ድረስ። እነዚሁ የኖህ ልጆች በየአቅጣጫው ተከፋፍለው በተለያዩ ቦታዎች እንደሰፈሩና፤ ብዙ ቋንቋዎች እንደተፈጠሩም ተጠቃቅሷል። አንዳንዶቹ ከተሞችን መስርተዋል፤ ኃያል ጦረኛም ሆነዋል ሲል ይተርካል። “የኖኅ የልጆቹ ነገዶች እንደ ትውልዳቸው በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። አሕዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከእነዚህ ተከፋፈሉ” በማለትም ትረካውን ይዘጋል – ዘፍጥረት ምዕ. 10።
ምዕራፍ 11 ሲጀምር ግን፣ ሌላ አስገራሚ ታሪክ ይዞ ይመጣል – ዝነኛው የባቢሎን ግንብ ታሪክን ያስነብበናል።

Related stories   ኢትዮጵያን የምታለቅሰው በ"መሪዎቿና በውድ ልጆቿ" ነውና !! ጆሮ ያለው ይስማ!!

ዝነኛው የባቢሎን ግንብ ታሪክ
“የባቢሎን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ አስገራሚ ታሪክ” ብንለው ይሻላል። የሰው ልጆች፣ በየአቅጣጫ ወደተለያዩ የምድሪቱ አካባቢዎች ተበትነው የሰፈሩትና የተለያዩ ቋንቋዎች የተፈጠሩት፣ ከዚህ የባቢሎን ሕንፃ ጋር በተገናኘ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃል – ትረካው።
ከጎርፍ በኋላ፣ እንደ አዲስ በተጀመረው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ የመጀመሪያው ትልቁ ስራ የባቢሎን ሕንፃ ነው ማለት ይቻላል። አንድ ቋንቋ ብቻ ይናገሩ የነበሩት የዘመኑ ሰዎች፣… የግንባታ ቴክኖሎጂን በመፍጠር፣ የመጀመሪያዋን ከተማ መሰረቱ። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃም ገነቡ። ይሄኔ፣ እግዚአብሔር መጥቶ፣ በቋንቋ እንዳይግባቡ፤ ከተማውንና ሕንፃውን ትተው እንዲበታተኑ አደረገ። ለምን?
በብዙዎች አስተሳሰብ፣ ነገርዬው “ቅጣት” ነው። ቅጣት? ምን አጠፉ?
በቋንቋ መግባባት፣ ቴክኖሎጂ መፍጥር፣ ከተማ መመሥረት፣ ሕንፃ መገንባት፣… ይሄ ሃጥያት ነው? ወንጀል ነው? ውግዘትና ቅጣት ይገባቸዋል?
አዎ የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ አስተሳሰብ ከሄድን፣ የሃጥያትና የወንጀል ትርጉም ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የባቢሎን ቋንቋ፣ የባቢሎን ግንብና የባቢሎን ሕንፃ፣… ምናልባት የጥፋትና የቅጣት ታሪክ ባይሆንስ? ደግሞም አይመስልም። እስቲ እናየዋለን።

Related stories   ኢትዮጵያን የምታለቅሰው በ"መሪዎቿና በውድ ልጆቿ" ነውና !! ጆሮ ያለው ይስማ!!

አዲስ አድማስ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *