የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ  ድረስ መሰጠት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት ያላነሰ ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ግን ትምህርቱ በተማሪዎች ላይ ያመጣው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡ ትምህርቱ ሲታቀድ ብቁ፣ አገር ገንቢና በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር ታልሞ የነበረ ቢሆንም፣ የታለመለትን ግብ ሳይመታ ቀርቷል፡፡ የትምህርቱ ውድቀት ከምን የመነጨ ይሆን?

በዜግነት ግንባታና በሥነ ምግባር ላይ አተኩሮ በትምህርት ሚኒስቴርና በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት የተሠራ ሲሆን፣ የጥናቱ ዓላማም ትምህርቱ መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተማሪዎች ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? የታሰበውን ያህል ነው ወይ? ለውጥ ካልታየ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? ለሚሉት ጉዳዮች ምላሽ ለማግኘትና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነበር፡፡

በጥናቱ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና የሱማሌ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተካተቱ ሲሆን፣ ያካለላቸው የትምህርት ደረጃዎችም ከአምስተኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ነው፡፡

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪው አቶ ሔኖክ ሥዩም አሰፋ እንደሚሉት፣ ትምህርቱ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ተብሎ ይሰጥ እንጂ አብዛኛው ትኩረቱ በዜግነት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ለሥነ ምግባር የተሰጠው ትኩረት አናሳ ስለመሆኑም ለ11ኛ ክፍል ለሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት በዓመቱ የተሰጠው ክፍለ ጊዜ 95 ሆኖ ከእነዚህ ሥነ ምግባር ነክ ጉዳዮችን ለማስተማር የተመደበው ክፍለ ጊዜ ሁለት መሆኑን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ይህ ከይዘት አንፃር ለሥነ ምግባር በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው ያሳያል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ለሥነ ምግባር ትምህርት ትኩረት ካለመሰጠቱም በተጨማሪ ተማሪዎችን በሥነ ምግባር የሚያንፅ ይዘት የለውም፡፡

ከአምስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚሰጠው ትምህርት ድግግሞሽ ያለበት መሆኑ ሌላው ክፍተት ሲሆን፣ ይህም ለተማሪዎቹም ሆነ ለመምህራኑ አሰልቺ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ትምህርቱ 11 እሴቶች ሲኖሩት፣ አንዳንዱ እሴት ከክፍል ክፍል ሰፋ ሲል፣ አንዳንዴ ደግሞ ራሱ የሚደገምበት ጊዜ ተስተውሏል፡፡

ትምህርቱ የታለመው አገሩን ገንቢ በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር ቢሆንም፣ በመጽሐፉ ላይ ያለው አቀራረብና መምህራን የሚያስተምሩበት መንገድ ዓላማውን ሊያስጠብቅ በሚችል መንገድ አይደለም፡፡ መምህራኑ እንደማንኛውም ትምህርት ዕውቀት ላይ መሠረት አድርገው ያስተምራሉ እንጂ ይህ ትምህርት የተማሪዎች የዜግነትና የሥነ ምግባር ቀረፃ ነው ብለው ትምህርቱ በሚፈልገው ትኩረት ልክና ክህሎት በሚያበለፅግ መልኩ የማያስተምሩ መሆኑም ታውቋል፡፡ ተማሪዎችም ትምህርቱን የሚማሩት ፈተና ለማለፍ እንጂ እንደ ሕይወት ክህሎት ከመቁጠር አንፃር አይደለም፡፡

የሥርዓተ ትምህርቱ አተገባበር ወጥ አለመሆን ሌላው ችግር ነው፡፡ ይህ በተለይ በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ ታይቷል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ሒደቱ በምን መልኩ መተግበር እንዳለበት ደረጃ ያወጣ ቢሆንም፣ ወጥ የሆነ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ የለም፡፡ አንዳንድ የሥነ ዜጋ ትምህርት መምህራን የሚያስመርቁ ኮሌጆችም ሕገ መንግሥት ነክ ጉዳዮችን አያስተምሩም፡፡ ሆኖም በቂ ክህሎት ይዘው ያልወጡ መምህራን፣ ሕገ መንግሥት እንዲያስተምሩ ይጠበቃል፡፡

የሥነ ዜጋንና ሥነ ምግባር ትምህርትን የሚያስተምሩ መምህራን የታሪክ፣ የጂኦግራፊ ወይም የቋንቋ ተማሪዎች ናቸው፣ ይህም ችግር ፈጥሯል በሚል ከጥናቱ ቀድሞ በነበረ መድረክ የተወሳ ሲሆን፣ ጥናቱም በዘርፉ ከተመረቁ መምህራን እጥረት ጋር አያይዞ እንደ ክፍተት አስቀምጦታል፡፡ በዘርፉ የተመረቁ መምህራን ቢኖሩም ትምህርቱን ከሕይወት ክህሎት ጋር አያይዘውና ለዜጎችና አገር ግንባታ ሒደት ዋና ምሰሶ አድርገው የማየት ችግርም ተስተውሏል፡፡

ከተለያየ ትምህርት መጥተው ሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር እንዲያስተምሩ የሚመደቡ መምህራን ምን ያህል ፍላጎት አላቸው? ብቃትስ? የሚለው ሳይታይም እንዲያስተምሩ ይገደዳሉ፡፡ እንደምሳሌ የተነሳውም፣ አንድ የጂኦግራፊ መምህር በሳምንት መያዝ የሚገባው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ካልሞላ ክፍለ ጊዜውን ለመሙላት ሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር እንዲያስተምር ይደረጋል፡፡ ይህም ተገቢ ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚያሳይ ነው፡፡

በአመራሩ፣ በመምህሩ፣ ሌሎች ትምህርቶችን በሚያስተምሩ መምህራን፣ በተማሪዎችና በኅብረተሰቡ ዘንድ ለትምህርቱ ያለው አመለካከትም ችግር አለበት፡፡ በጥናቱ እንደታየው፣ አንዳንድ መምህራን ትምህርቱን የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርገው ይወስዱታል፡፡ አንዳንዶቹ የገዢው ፓርቲ ጭልጥ ያሉ ደጋፊዎች ይሆኑና የፓርቲውን አመለካከት ማስተማሪያ አድርገው ያንን ይሰብካሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በተቃራኒ ጎራ ሆነው የገዢውን ፓርቲ የሚያጥላሉና የሌላ አስተሳሰብና የግል ፖለቲካ አጀንዳን የሚያራምዱ አሉ፡፡ በአመራሩ አካባቢ መምህራንን የሌላ ፓርቲ ሐሳብ አራማጆችና ተማሪዎችን የሚያነሳሱ አድርጎ የማየት ችግሮችም አሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ደግሞ መምህራኑን የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አመለካከት አራማጆች አድርጎ ያያቸዋል፡፡ በዚህም የዘርፉ መምህራን ከሁሉም ያጡ መሆናቸው ታይቷል፡፡

ለምን ይህ ተከሰተ፣ ስንል የጠየቅናቸው አቶ ሔኖክ፣ የትምህርቱን ይዘት ባዩበት ወቅት ለአገራዊ ጉዳዮች ብዙ ትኩረት ያልሰጠ፣ ንድፈ ሐሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ፣ በአገራችን ታሪካዊ ጉዳዮችና ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ብዙም ያላተኮረና ጠቅለል ያለ ነገር ይዞ የአገርን ጉዳይ የዘነጋ፣ ድግግሞሽ የበዛበትና ምሳሌዎቹም የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች መሆናቸው እንደ ምክንያት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል፡፡

የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ከትምህርት ጥራት ማስጠበቂያዎች አንዱ ፓኬጅ ቢሆንም፣ ይህን የሚመጥን አወቃቀርና ሥርዓት አልተዘረጋለትም፡፡ ለዚህም በትምህርት ሚኒስቴር የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርትን የሚከታተል አደረጃጀት አለመኖሩ፣ የሚመራው በሥርዓተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ሥር በአንድ ኤክስፐርት መሆኑ፣ በክልሎችም አንድ፣ አንድ ሰው ብቻ መመደቡና በዞንና በወረዳ ደረጃዎች ምንም ተወካይ አለመኖሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡

የዜገችን ሥነ ምግባር የመገንባት ሒደት ብዙ አካላትን የሚያሳትፍ ቢሆንም፣ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ተማሪዎችን በአሉታዊ መንገድ ሊቀርፁ በሚችሉ በርካታ ምክንያቶች የተከበቡ ትምህርት ቤቶችና ተቋማት ባሉበት ሁኔታ አዎንታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ ትምህርት ቤቶችን ከውጫዊም ሆነ ከውስጣዊ አሉታዊ ተፅዕኖ ነፃ ያወጣ የለም፡፡ ከዓመታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች የተማሪዎች ሥነ ምግባር እየጠፋ ነው በሚል በተደጋጋሚ ቢነገርም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሏል፡፡ በምርምር ተቋሙ የተሠራው ጥናትም ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነፅ ሥራው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እዚህ ግባ የማይባል እንደነበር ጠቁሟል፡፡

በትምህርት ቤት የተማሪዎች ዜግነትና ሥነ ምግባር ጉዳይ ትምህርቱን ለሚያስተምረው መምህር የተተወ ነው፡፡ በተማሪዎች ዘንድ ጉድለት ሲታይ ጣት የሚቀሰረውም በመምህሩ ላይ ነው፡፡ በትምህርት ቤት የወላጅ፣ መምህርና ተማሪዎች ኮሚቴ ቢኖርም፣ ከአስተዳደራዊና ትምህርት ነክ ጉዳዮች ውጭ የሥነ ምግባር ጉዳይ አጀንዳቸው አይደለም፡፡  ወላጆችም ስለልጆቻቸው የትምህርት ቤት ውሎ የማወቅ ፍላጎታቸው አናሳ ነው፡፡

መገናኛ ብዙኃን ያላቸው ተፅዕኖ ከባድ ቢሆንም፣ በሥነ ምግባር ላይ የሚጫወቱት ሚና ከሚጠበቀው ያነሰ ሆኖ በጥናቱ ተገኝቷል፡፡ በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ማሠራጨት ማኅበራዊ ኃላፊነት ቢሆንም፣ ክፍተት ታይቷል፡፡ በጽሑፍም ሆነ በድምጽና ምስል የሚተላለፉ ጉዳዮች ከሥነ ምግባር አንፃር የሚያሳድሩት ተፅዕኖም በሚፈለገው መጠን ሲፈተሽ አይታይም፡፡ ይልቁንም የወጣቶችን ሥነ ምግባር የሚፈታተኑ አንዳንድ ፕሮግራሞች ይተላለፋሉ፡፡

ከሥነ ምግባር አንፃር ኩረጃ አንገብጋቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተለይ ስምንተኛ፣ አሥረኛና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች ላይ የአካባቢ መስተዳድሮች፣ የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን፣ መምህራን፣ ወላጆችና ፈታኞች ተደራጅተው የሚሠሩትና ሥር እየሰደደ የመጣ ችግር ሆኗል፡፡ ጥቂት ቢሆንም መምህራን ለተማሪዎች መልካም አርዓያ ሆነው አለመገኘት፣ ጠጥተው መምጣትና ከትምህርት ቤት ውጪ በተማሪዎቻቸው ፊትና አብረውም ጫት የሚቅሙ፣ ሴት ተማሪዎችን የሚተነኩሱ፣ ውጤት ላይ በሃይማኖትና በአካባቢ ተሳስረው አድልኦ የሚፈጽሙ ተስተውለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ ሒደት ምቹ ናቸው ወይ? ለተማሪዎች ብቁ የትምህርት መረጃ ያቀርባሉ ወይ? ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ደስ ብሏቸው ራሳቸውን በሚገነቡበት ሁኔታ እንዲያሳልፉ ምቹ ናቸው ወይ? ሲባልም፣ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች እነዚህን አሟልተው አልተገኙም፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያለው ሁኔታ ነው፡፡

 የተማሪዎችን ጊዜ የሚሻሙ፣ ወደ ሱስ የሚስቡ ሁኔታዎች በየትምህርት ቤቱ ደጃፎች መታየት፣ ተማሪዎችም የዚህ ሰለባ መሆን ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ጥናቱም ትምህር ቤቶች በቁማርና በሺሻ ቤቶች እንዲሁም በጫት መቃሚያዎች የተከበቡ ቢሆንም፣ እነዚህን ለማዘጋት በደረገ ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሴት ተማሪዎችን እየደለሉና በችግሮቻቸው እየገቡ ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግ እንደችግር ተነስቶ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ችግሩ አይሎ ለሴት ተማሪዎች ምግብና መጠጥ በነፃ በማቅረብ ሀብታም ወንዶችን በሴት ተማሪዎቹ መሳብ ተጀምሯል፡፡ አቶ ሐኖክ እንደሚሉትም፣ የጥናታቸው ግኝት ይህንን አመላክቷል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ሴት ተማሪዎች በሳምንት ሁለት ቀን ተመርጦ በነፃ የሚጋበዙበት፣ በነፃ መጠጥና ምግብ የሚቀርብበት ሆቴል ድርጅት በጥናቱ ታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዓላማም ሀብታም ወንዶችን በሴቶቹ አማካይነት መሳብ ነው፡፡

ጥናቱ እንደ አጠቃላይ ያስቀመጠውም፣ ከአሥር ዓመት በላይ ያስቆጠረውና ከአምስተኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚሰጠው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ውጤት አለማሳየቱን ነው፡፡

ይህ ምን ያመላክታል?

የሥነ ዜጋ ትምህርቱ ተማሪዎች ስለዜግነት ያላቸውን ግንዛቤ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ከፍ አድርጓል፡፡ ተሟጋች ዜጋ ለመፍጠርም አስችሏል፡፡ ነገር ግን መብት የመጠየቅን ያህል፣ ግዴታ መኖሩን መገንዘብ ላይ ክፍተት አለ፡፡ መብቱን ያወቀ ግዴታውን የዘነጋ ግማሽ ጐፈሬ ዓይነት ተማሪ ተፈጥሯል፡፡ ኃላፊነትን ለመውሰድ ዳተኛ የሆነና በኃላፊነት መንፈስ ብዙም የማይንቀሳቀስ ተማሪ ከመፍጠሩም አንፃር ትምህርቱ ውጤት አላመጣም ማለት ይቻላል፡፡

ትምህርቱ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት የታቀደ ቢሆንም፣ የጥናቱ ውጤት ያሳየው ያልተዘራውን እንደማጨድ ነው፡፡ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ዜጋ ማፍራት ተብሎ የተቀመጠውና አብዛኞቹ ዓላማዎችም አልተሳኩም፡፡ ተማሪዎች በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ብሔራዊ ፈተና ላይ ትልቅ ውጤት የሚያስመዘግቡ ቢሆንም፣ መሬት ወርዶ በተግባር አይታይም፡፡

ምን መደረግ አለበት?

የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ዓላማውን ማሳካት በሚችልበት መልኩ ሊከለስ ይገባዋል የሚለው የጥናቱ የመፍትሔ ሐሳብ ነው፡፡ ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ ከንድፈ ሐሳብ በዘለለ ክህሎት የሚዳብርበት፣ መምህራን ሥልጠና ማግኘት የሚችሉበት እንዲሆንም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ትምህርቱን የሚመራ በቂ መዋቅር ማዘጋጀት ጥናቱ መደረግ አለባቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ ሲሆን፣ ከዚህ በተለየ መልኩ ደግሞ ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደጨረሱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት (National Service) መስጠት የሚችሉበት ሥርዓት ቢዘረጋ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ብሔራዊ አገልግሎ ለዜግነትና ለሥነ ምግባር ግንባታው ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎም ይታመናል፡፡

ምሕረት ሞገስ’s blog  ሪፖርተር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *