Asefa chebo(ሚያዚያ 27 2009 ዓ.ም)፡- ሚያዚያ 27 ታሪካዊ ቀን ናት ፤ ከሰባት አስርት ዓመታት በፊት ከፋሺስት ጣሊያን ወረራ በኋላ ሀገር ነጻነቷን ያወጀችበት ሕዝብ እንደ ሕዝብ ደስ የተሰኝበት ቀን ናት ፤ የዛኔ በስደት የነበሩት ንጉሥ ከስደት መልስ ሀገራቸው የገቡበት ቀን ነው ፤ ዛሬ ግን በደርግ ዘመነ መንግሥት በጽሑፋቸው ለአስር ዓመት ከስድስት ወር በማዕከላዊ ካሳለፉ በኋላ በዘመነ ኢሕአዴግ የ16 ዓመት እስር የተፈረደባቸው ፤ ላለፉት 25 ዓመታት በስደት በሀገረ አሜሪካ ሕይወታቸውን የገፉት የሦስት ልጆች እና የዘጠኝ የልጅ ልጆች አባት ፤ ሀገራቸውን ለማቅናት እድሜ ዘመናቸው ሲወጡ ሲወርዱ ፤ ሀገሬን ….. ሀገሬን እያሉ ሞታቸው ከስደት ሀገር ከወደ ዳላስ የተሰማው አንጋፋው ጎምቱ ጸሐፊ ፤ የሕግ ባለሙያ ፤ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ፖለቲከኛና ምሁር የአቶ አሰፋ ጫቦ ስርዓተ ቀብር የተከናወነበት ቀን ነበር፡፡

አቶ አሰፋ ኢትዮጵያ ሀገራቸውን ፤ ጨንቻ የትውልድ አካባቢያቸውን ለማየት እንደጓጉ መሞታቸው እጅጉን ያሳዝናል ፤ እኚህን የሀገር አድባር የሆኑ ሰው የመጨረሻ ሽኝታቸውን ለማከናወን በርካታ ሰው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ተገኝቶ ነበር ፤ ሻለቃ ፍቅረስላሴ ወግደረስ ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፤ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፤ በርካታ የሀገር ውስጥ(የመንግሥት ጋዜጠኞች አልተመለከትኩም) እና የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች …. በዘመነ ኢሕአዴግ ተወልደው እና አድረገው የእሳቸው ጽሑፍ ያነበቡ ወጣቶች ፤ ከትውልድ አካባቢያቸው ከጋሞ ጎፋ ፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና በእሳቸው እድሜ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ስነ-ስርዓቱን ለመታደም በቅተዋል ፤ በርካታ የቤት መኪኖች እና ከገሞ ጎፋ በቀጥታ ስርዓተ ቀብራቸው ላይ ለመካፈል የመጡ በብሔረሰቡን አልባሳት የደመቁ ሰዎች በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል ፡፡ አቶ አሰፋ ‹‹አልቅሳችሁ እንዳትቀብሩኝ ፤ በገሞ ስርዓት ጨፍራችሁ ፤ እንደ ካህናት አሸብሽባችሁ›› ቅበሩኝ ባሉት ስርዓት በቦታው ላይ ስገኝ የማህበረሰቡ አባላት በደመቀ አልባሳት አጊጠው አንድ ከፍተኛ  የማሕበረሰቡ አባል በሚሸኝበት ስርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ በራፍ ላይ ተገኝተው  እያቅራሩ እና እየጨፈሩ ነበር ፤ በዚህ ሰዓትም በካቴድራሉ አውደ ምህረት ላይ ዲያቆን ሆነው ያገለገሉባት ቤተክርስቲያን የ‹ተስፋ ገብርኤል›ን ጸሎተ ፍትሀት እና ጸሎት እያከናወነች ነበር፡፡

Image may contain: 1 person, standing and outdoor

አባቶች ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሕይወት ታሪካቸው ሊነበብ አንባቢው ድምጽ ማጉያውን ከአባቶች ሲቀበል ጉም ያዘለውና ሰማይ ለ15 ደቂቃ ዝናብ አውርዷል ፤ ሰማይም ሀዘኑን የገለጸ ይመስል ነበር ፤  በዝናቡ ምክንያት አባቶች ለቀብር የመጣው ሰው ቤተክርስቲያን ተከፍቶ ጫማቸውን አውልቀው እንዲገቡ ፍቃድ ሰጥተዋል ፤ በመቀጠልም አሰፋን እጅግ በሚገልጽ መልኩ የተጻፈው የሕይወት ታሪክ በአውደ ምህረት ላይ ተነቧል፡፡ በሕይወት ታሪኩ ላይ አሰፋ ለአንድ ጓደኛው ነገረ የተባለው ታሪክ አስደማሚ ነበር…… ‹‹ ዝሆን በቀን ሦስት ኩንታል ያህል ሳር የመብላት አቅም አለው ፤ የዝሆን ጥርስ ይህን ሁሉ ሲፈጭ ጥርሱ በተፈጥሮ ራሱን ይተካል ፤ ዝሆን ወደ እድሜው መጨረሻ ላይ ጥርሱ ራሱን በማይተካበት እድሜ ላይ ሲደርስ ደመ ነፍሱ ወደ ሞት እየሄደ መሆኑን ይነግረዋል ፤ እርሱም ወደተወለደበት ቀዬ በመመለስ ከወገኖቹ ዘንድ የመጨረሻውን ረፍቱን ለማየት በመቀላቀል ያርፋል ፤ ከዚህ ዝሆን ጋር የሚዛመዱ ሁሉም በመምጣት ይህን እረፍቱ የቀረበን ዝሆን እየዞሩ የመጨረሻ ሽኝት ያደርጉለታል ፤ ዝሆኑም በስተመጨረሻ ያርፋል›› በማለት እርሱም የመጨረሻ ስንብቱ ሥሩ ከተመዘዘበት ከገሞ ጎፋ ፤ እሱን የሚያውቁት እሱም የሚያውቃቸው ሰዎች ዘንድ እንዲደረግ በምሳሌ ተናግሮ ነበር ፤ ዛሬም የምንወደው እና የሚወደን አቶ አሰፋን ከአሁን በኋላ ጽሑፉን ጽፎ ላያስነብበን ፤ ሀሳቡን ላያካፍለን ሸኝነው፡፡

የሕይወት ታሪክ ተነቦ ካለቀ በኋላ አስከሬኑ አውደ ምህረት ላይ የመጨረሻውን ስንብት ሦስት ጊዜ ካሳለሙት በኋላ ወደ ተዘጋጀለት ማረፊያ አመራ፤ ሳጥኑ እጅግ እንደሚከብድ የሚታወቀው ቀብር አስፈጻሚዎች ፊታቸው ሲታይ ነው ፤ አሰፋ ሀሳቡ ለአምባገነኖች ከዚህ በላይ እንደሚከብድ ማን በነገራቸው!!! ፤ በዚህ ወቅት እመቤት (ብቸኛ ሴት ልጁ) አሰፋን ለሚያውቀው እጅግ ውስጥን የሚረብሽና እንባን የሚያራጭ ቃላት እተናገረች ታለቅስ ነበር ‹‹ አሴ እረፈው… አሁን እረፈው ፤ ታሳሪው ስደተኛ አባቴ እረፈው ፤ አሁን እረፍ ፤ አሴ በቃ ዝም አልክ … በቃ…..በቃ… ›› አንድ ትልቅ የቀዬው ተወላጅ የኃይለሥላሴን ፤ የመንግሥቱን እና የመለስ ዜናዊን ስም መሀል መሀል በማስገባት ከቋንቋቸው ጋር በመቀየት ሀዘናቸውን ሲገልጹ ነበር( ትርጉሙን ማወቅ አልቻልኩም)… በክብር የአሰፋ ቻቦ አስከሬን ወደተዘጋጀለት ኪስ ሳጥን አመራ ፤ መንገዱ በመኪና በመሙላቱ ማቋረጡ አስቸጋሪ ነበር ፤ በካቴድራሉ በስተቀኝ በኩል ህዳር 14  1967 በግፍ በደርግ የተገደሉ የኃይለስላሴ ባለስልጣናትን በጎን ትቶ ከግቢው በመውጣት ካቴድራሉ ባሰራው አዳራሽ አመራ ፤ በጊዜው በአዳራሹ የሰርግ ስነ ስርዓት ለማከናወን ተጋባዥ እንግዶች ጸአዳ ልብስ ለብሰው ወደ አዳራሽ እየገቡ ነበር ፤ አቶ አሰፋ ደግሞ እጅግ ለደከመላት በአይነ ሕሊናው ተሰውራ ለማታውቀው ፤ በሕልሙ ለምትመላለስበት ፤ ከየትም ሀገር ጋር ለማያወዳድራት ውብ ለሆነችው ፤ እስራቷን ሽልማት አድርጎ ለተቀበላት ፤ እስከ እለተ ሞቱ ለሚወዳት ሀገሩ ‹‹ኢትዮጵያ›› ደክሞ ሊያርፍ ወደ አዳራሹ የታችኛው ክፍል እያመራ ነበር ፤ ሰርገኞቹ አቶ አሰፋን አከበሩት ዝምም አሉ ፤ አሰፋን በገሞ ባሕላዊ ልብስ ፤ በጥቁር ልብስ እና በሰርገኞች ጸአዳ በሆነ ልብስ በለበሱ ተሸኝ ፤ እኛም አሰፋን ይዘን ከዘላለማዊ ማረፊያው ገባን ፤ በርካታ (60×60) የሆኑ አስከሬን ማሰረፊያ ኪሶች ውስጥ በስተቀኝ በኩል ስምንተኛው column አራተኛው ረድፍ ላይ የሳጥን ቁጥ 104 ላይ አሳረፍነው ፡፡ ሳጥኑን ወደ ኪሱ ለማስገባት ቀብር አስፈጻማቹ ቢሞክሩም እንደ ሀገሩ ማረፊያ ቀዳዳዋ እምቢ አለች ፤ በሦስት ሆነው እጅግ ገፍተው ወደ ኪሱ ሳጥኑን አስገቡት ፤ አሰፋ በሕይወት እያለ ሀገሩ ለመግባት እጅግ ይፈልግ ነበር ፤ በስተመጨረሻ ግን ለሰው ዘር የማይቀረው ሞት ገፍቶ ሀገሩ ላይ አሳረፈው ፤ በዚህ ሰዓት እመቤት እጅግ እያለቀሰች ነበር ፤ ሰዎችም ተይ ሊሏት ሲሞክሩ ፤ የቅርብ ሰዎች ደግሞ ‹ተዋት ታልቅስ› ብለው ሰዎችን ገለል አደረጉላት ፤ ሁኔታውን ላይ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታዎች ነበሩ ፤ እኛስ ዛሬ ለአሰፋ ካላለቀስን መቼ ልናለቅስ ኖሯል?.. እሱ በሕይወት እያለ ‹አልቅሳችሁ እንዳትቀብሩኝ› ቢልም እኛ ግን ስላደረገው ሥራ ሁሉ ፤ ስለወጣው ፤ ስለወረደው ፤ ስለታሰረው ፤ ስለተሰደደው ፤ በስደት ላይ ሳለ ስለብቸኝነት ሕይወቱ …ሁሌም ሀገሬን ..ሀገሬን …ሀገሬን ማለቱን እያስታወስን አልቅሰን ቀበርነው …

ወንድማቸው ‹፣እኔ ለአሰፋ አላለቅስም ፤ ይህን ሁሉ ልጅ ወልዶ ነው የሞተው ፤ እኔ እናንተን በማየቴ ደስተኛ ነኝ ..አላለቅስም›› ብለዋል ፡፡ በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የመጡትን ሁላ በደከመ የሀዘን ድምጽ እጃቸውን ወደ ላይ በማድረግ አመስግነዋል ፤ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም በስተመጨረሻ ላይ ዘመድ አዝማድ ጋር በመጠጋት ‹‹አሰፋን እኛ ነው ያጣነው›› በማለት ተናግረዋል ፤ ሻለቃ ፍቅረ ስላሴ ወግደረስም  ቤተሰቦችን አጽንተዋል ፤ የውጭ ጋዜጠኞች ወደፊት በአሰፋ የሕይወት ታሪክ ላይ ዘጋቢ ነገር ለመስራት በማሰብ የቤተሰቦችን ስልክ ቁጥሮች ሲቀበሉ ፤ የቀድሞ ‹‹ጦቢያ›› ላይ ሲጽፉ የነበሩ ጋዜጠኞችም በወቅቱ ራሳቸውን ለቤተሰብ በማስተዋወቅ ሲያጽናኑ ነበር፡፡

አሰፋ ሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ፤ ፍትህ የሚከበርባት ፤ ፍትህ ርትዕ የነገሰባት ፤ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረባት ሀገር እንድትሆን የቻለውን ያህል ጡብን ከሲሚንቶ እያገናኝ ሀገር ለመገንባት ጥሯል ፤ ከጸጉር የሚበዙ ጠላቶች እያሉት ‹እኔ ጠላት የለኝም› ብሏል ፤ ጋሞነቱ ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር ሳይጋጩ አብሮ እስከ ሕልፈቱ ድረስ አዝልቋቸዋል ፤

ጋሽ አሴ ሦስት መንግሥታትን ከተማሪነታቸው ጊዜ አንስቶ ተመልክቷል ፤ ለሁሉም ውስጡ ያመነበትን ለሀር ለወገን ለሕዝብ የሚጠቅመውን አካሔድ በቃል በጽሑፍ አመላክቷል ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት በጀመረበት ወቅት ቀን ቀን በትምህርት ማታ ማታ ደግሞ በሲቪል አቪኤሽን ባለስልጣን የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ አገልግሏል ፤ ሀገርን በመወከል አለም አቀፍ ካሉ የትምህርት ተቋማት ጋር በመወዳደር ከንጉሡ ሥጦታ ተበርክቶለታል ፤ የወጡበት ማሕበረሰብን ወግ ልማድና ባሕል ከኢትዮጵያዊነት ጋር አንድ በማድረግ አንዱ ከአንዱን ሳይውጥበት ጋሞነትን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር በማድረግ ስለ ሀገሩ ብዙ ጽፏል ፤ ተናግሯል ፤ ሀሳብ አካፍሏል፡፡ እንዲህ ብሎ ኖረ ‹‹..እኔ ጋሞ ነኝ፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሁለቱ ተጣልተው ለማሥታረቅ ተቀምጬ አላውቅም፡፡›› ዛሬ ግን የመጨረሻ ቀን ደርሶ ወደማያልፈው የሰው ልጆች ሁላ መጨረሻ የሆነውን የሞት ጽዋ በመጎንጨት እስከ ሞት ሀገሩን ታምኗት  ላይመለስ ጋሽ አሴ አልፏል፡፡ አንድ ሰው እንዲህ አለ ‹‹ሰውየው ያገር ታቦት፤ የታሪክ ፅላት ነው፡፡››

እንደ ግንበኛ ጡብን ከሲሚንቶ በማገናኝት የአቶ አሰፋ ጫቦን ማረፊያ የconcrete ሳጥን በር የመጨረሻዋን ጡብ በማቀበል በመንበር ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እንዲህ አድርገን ሸኝተነዋል..፡፡

ዛሬ አዝኛለሁ…

ከአክሊሉ ሀብተወልድ

Photo 1 and 2  Guangul Teshager J  Fb.

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *