በፌደራል መንግስት የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የተሰራጨውን ለማለት ነው – “…መተላለፉን አላውቅም። የሕግ ረቂቅ የማውጣት ስልጣኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሆኑም፣ በእኛ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሰጠው አስተያየት የለም ”

ኦሮሚያ ማግኘት የሚገባትን ልዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ተመሳሳይ ጉዳዮች አስመልክቶ ክልሉ አዘጋጅቶ አቀረበ የተባለው ሰነድ ” ሃሰት ነው ” በሚል ኢ ኤን ኤን የሚባለው የኢህአዴግ አዲስ የቴሌቪሽን ፐሮግራም ቢያሰራጭም ጉዳዩ ማንን ማመን እንደሚቻል ግራ እያገባ መሆኑ እየተጠቆመ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማን ተጠሪነት ከፌደራል ነጥቆ ለኦሮሚያ የሚሰጠው፣ ኦሮሞ የሆነ ብቻ በከልሉ ያለመፈናቀል መብት የሚያጎናጽፈው እና የከተማዋ አስተዳደር እያለ ኦህዴድ ተጨማሪ የተቆጣጣሪ ምክር ቤት እንዲሰይም የሚፈቅደው ዝርዘር ህግ ሃሰተኛና የፈጠራ ቢሆንም፣ አንዳንድ ወገኖች ማስተባበያውን አልተቀበሉትም።

ያወዛገበው ረቂቅ አዋጅ ሰነድ “ሃሰተኛ ነው” ተባለ፤ “የሰውን ስሜት ለመለካት የተደረገ ነው”

 ክልሉ ቃል በቃል ሰነዱን እኔ አዘጋጀሁት ወይም አላዘጋጀሁትም በሚል ምላሽ ባይሰጥም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ሰነድ አዘጋጀቶ መቅረቡን በይፋ ተናግሯል። ሰነዱ በኦሮሚያ ላለው የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ይሁን አይሁን ወደፊት የሚታወቅ ቢሆንም፣ አዲስ አበባ በሶስት አካላት እንድትተዳደር ማሰብ እብደት እንደሆነ ግን ከወዲሁ እየተጠቆመ ነው። ብዙ ህገ መንግስቱን የሚጻረሩ ጉዳዮችም አሉበት።

ይም ሆነ ይህ ጉዳዩ ያለቀለትና ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ እንደሆነ የሚጠቁም የስርዓቱ ቅርብ ሰዎች፣ መጠነኛ አለመግባባት ከመኖሩ ሌላ ሰነዱ በቅርቡ በይፋ ለፓርላማ እንደሚቀርብ እምነታቸው ነው።

ለሁሉም ግን ሰንደቅ የሚከተለውን ዘግቧል።

በኢፌዲሪ ሕገመንግሥት መሠረት ኦሮሚያ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ያለውን ጥቅም በተመለከተ የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዝርዝር ሠነዱን ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን ክልሉ ማረጋገጫ ሰጠ። ሆኖም በማኅበራዊ ድረገጾች ስለተሰራጨው ሠነድ ጉዳይ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስተባብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ “የኦሕዴድ ሥራ አስፈፃሚ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ በሕገመንግስቱ በተቀመጠው አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የልዩ ጥቅም አተገባበርን በተመለከተ መካተት አለባቸው ያሏቸውን፤ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ዘርዝረው ለሚመለከተው አካል አስተላልፈዋል። እስከዚህ ድረስ የሚታወቅ ነገር አለ” ብለዋል።

Related stories   የቀንጢቻ ታንታለም ማውጫ እየተዘረፈ ነው

“የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገመንግስታዊ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጥናትሰነድ ነው እየተባለ በመገናኛ ብዙሃን እና በማሕበራዊ ድረ ገፆች ተለቋል። ይህንን የጥናት ሰነድ ወይም በአንዳንዶች ረቂቅ ሰነድ ተብሎ ስለተዘገበው ጉዳይ በክልሉ የሚታወቅ ነገር አለ? ወይም በክልሉ ነው የተዘጋጀው? ወይም በዚሁ ጉዳይ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ አዲሱ በሰጡት ምላሽ፣ “ወደኋላ ሄጄ የተዘጋጀው የጥናት ሰነድ ነው …ረቂቅ ሰነድ ነው ..እንትን ነው ስለሚባለው የማውቀው ነገር የለም። ረቂቅ ሰነድ የተባለውም እንዴት በዚህ መልኩ ለአደባባይ እንደሚበቃ የምናውቀው ነገር የለም። እንዲሁም ኦሕዴድ ነው ያዘጋጀው… እገሌ ነው ያዘጋጀው ስለሚባሉት ነገሮች ቢሆኑም፣ ረቂቅ ሰነድ የማዘጋጀት ሥልጣን የእኛ የሥራ ድርሻዎች ባለመሆኑ አስተያየት ለመስጠት እንቸገራለን። ሕግ የሚያወጣው ሕግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል በመሆኑ፣ በእኛ በኩል የተለየ አስተያየት የምንሰጠው ነገር የለም።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

 ይህ የተሰራጨው ረቂቅ ሰነድ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተላልፏል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ነጥብ ላይ ምን ይላሉ? ላልናቸውም፣ “መተላለፉን አላውቅም። የሕግ ረቂቅ የማውጣት ስልጣኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሆኑም፣ በእኛ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሰጠው አስተያየት የለም።” ሲሉ አቶ አዲሱ አረጋ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *