ለኪነጥበብ ቅርበት በነበረው ቤተሰብ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡  አባቱ አቶ ካሳሁን ገርማሞ ታዋቂ ጋዜጠኛ፤ የዘፈን ግጥም ደራሲና የመድረክ መሪ ነበሩ።  ‹‹ሙዚቃ ህይወቴ›› የተሰኘው ዘፈኑን ለአባቱ  መታሰቢያ አድርጎ ሰርቶላቸዋል። እናቱ ወይዘሮ ጥላዬ አራጌ ደግሞ  በዳንስ ሙያ ያሳለፉ ኩሩ ኢትዮጵያዊ የቤት እመቤት ናቸው፡፡
በሙሉ ስሙ ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ ተብሎ ቢጠራም፣ የሚታወቀው ቴዲ አፍሮ በተሰኘው የመድረክ ስሙ ነው፡፡ ስያሜው ራሱ ከመሰረተውና ከሚያስተዳድረው “አፍሮ ሳውንድ” የሙዚቃ ባንድ ጋር ተያይዞ የተፈጠረለት ነው፡፡
በሙዚቃ  ሙያ ከተሰማራ ከ15 ዓመታት በላይ  ሆኖታል፡፡ ከድምፃዊነቱ በተጨማሪ የዘፈን ግጥምና የዜማ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ታሪክ አዋቂ፤ በጎ አድራጊና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ነው። ከሙዚቃ መሳርያዎች ኪ-ቦርድን ከመጫወቱም በላይ የተለያዩ አኩስቲክ የሙዚቃ መሳርያዎችን በመጫወት በመድረክ ላይ ባንዶቹን አጅቦ የመስራት ልዩ ተሰጥኦ አለው፡፡
በአልበሞቹ ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ፤ በመላው ዓለም በርካታ ኮንሰርቶች በመስራት፤ በአገር ውስጥ ኮንሰርቶች ከፍተኛ ታዳሚዎችን በመሰብሰብ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍተኛውን ክፍያ በማግኘትና አዳዲስ የስኬት ክብረ-ወሰኖችን በማስመዝገብ በኢትዮጵያ ቀዳሚው ድምጻዊ ነው፡፡
ትልልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፤ ”የአፍሪካ ሬጌ ሙዚቃ ንጉስ” እያሉ ያሞካሹታል፡፡ በእንግሊዙ ቢቢሲ፤ በቻይናው ሲሲቲቪ፤ በአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት፤ በሙዚቃ ስኬቱ ላይ ሰፋ ያሉ ዘገባዎች ተሰርተውለታል። በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በተፅእኖ ፈጣሪነት ከሚጠቀሱ ሙዚቀኞች ተርታ ይሰለፋል፡፡
ከትዳር አጋሩ አምለሰት ሙጬ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት ‹‹አላምን›› ለተሰኘ ሙዚቃው ቪድዮ በሚሰራበት  ወቅት የሜክአፕ አርቲስቱ በሆነችበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከጋብቻቸው በፊት ያሰረላት የቃልኪዳን ቀለበት፣ 750ሺ ብር እንደሚያወጣ የተወሳ ሲሆን ሰርጋቸው በመላው ዓለም ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ነበር፡፡  በትዳር ህይወታቸው 6 ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
የፊልም ባለሙያ፤ ፀሃፊና ተዋናይት የሆነችው አምለሰት ሙጬ፤ በ”ወይዘሪት ኢትዮጵያ” የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የነበረች ሲሆን   በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ የሃይስኩል ጣፋጭ ወጎችን በአዝናኝ አቀራረብ ትፅፍ ነበር፡፡  በሰይፉ ፋንታሁን “ይፈለጋል” ፊልም እና በሌሎች የአማርኛ ፊልሞች ላይ በመተወን የምትታወቅ  ሲሆን “ስለ ፍቅር” የተሰኘ አስቂኝ የፍቅር ፊልም ደርሳ ፕሮዲዩስ አድርጋለች፡፡ በኒውዮርክ የፊልም አካዳሚ የተማረችው አምለሰት፤ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፊልም የሰራች ሲሆን በአንድ ወቅት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ህይወት ዙሪያ  ዶክመንተሪ ፊልም እየሰራች መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
ቴዲ አፍሮ፤ በሙዚቃ ስራዎቹ በተለይ በኢትዮጵያዊ ማንነት፤ በሰብዓዊነት፤ በአንድነትና በፍቅር ዙርያ አተኩሮ በመስራትም ልዩ ከበሬታ ተቀዳጅቷል። ለሚሰራቸው ዘፈኖች፣ ለሚፅፋቸው ድርሰቶች ከፍተኛ ምርምርና ጥናት በማድረግ ትጋቱ ይደነቃል፡፡ በእያንዳንዱ  አልበሙ፣ ታላላቅ ሰዎችን የሚዘክሩ ታሪካዊ የሙዚቃ ስራዎችን ያበረክታል። ለአፄ ኃይለስላሴ፤ ለቦብ ማርሌይ፤ ለታዋቂዎቹ አትሌቶች ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ፣ ለአፄ ምኒልክ፤ ለእቴጌ ጣይቱ… ሌሎችም–
ከሙዚቃው ባሻገር የግጥም መፅሃፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡  የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የልብ አድናቂ ሲሆን፤ የስነ ጽሁፍ ችሎታውንና አስተሳሰቡን እንደቀየረለት በአንድ ወቅት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ‹‹ጥቁር ሰው›› በሚለው አልበሙ ይህን አድናቆቱን በሚያረጋግጥ መንገድ፣ በባለቅኔው የግጥም ንባብ በመታጀብ፣ ምርጥ ሙዚቃ መስራቱ  ይታወቃል፡፡
በአጠቃላይ 7 አልበሞችን  በካሴት፤ በሲዲ፤ በዲቪዲና በቪሲዲ በመስራት ለገበያ አቅርቧል፡፡
በአልበሞቹ አሳታሚነት አብረውት ከሰሩ አሳታሚዎች መካከል  ናሆም ሪከርድስ ዋናው ተጠቃሽ ቢሆንም፤ ከኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን እና ከአዲካ ሪከርድስ ጋርም ያሳተማቸው አልበሞችም አሉት፡፡ የመጀመርያ የስቱዲዮ አልበሙ ‹‹አቦጊዳ›› በሚል ርእስ በ1993 ዓ. ም  በናሆም ሪከርድስ የታተመው ነበር፡፡
በ1996 ዓ. ም ላይ በኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን የተሰራው ‹‹ታሪክ ተሰራ›› አስገራሚ ተሰጥኦውን ካሳየባቸው ነጠላ ዜማዎች የሚጠቀሰው ነው፡፡  ‹‹ታሪክ ተሰራ›› በኢትዮጵያ የ10ሺ ሜትር ጀግና አትሌቶች የቡድን ስራ በመማረክ፣ በአንድ ሌሊት ተሰርቶ በማግስቱ በኤፍኤም ሬድዮ በመለቀቅ፣ ከፍተኛ አድናቆትን  ያተረፈ ነጠላ ዜማ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በ1997 ዓም ላይ 3ኛው የስቱዲዮ አልበም ‹‹ያስተሰርያል›› በሚል ርዕስ በናሆም ሬከርድስ ለመታተም በቅቷል። ይህ አልበም በጥቂት ወራት ሁለቴ ለመታተም የበቃ ሲሆን፤ ከሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሰራጭቶ ክብረወሰን እንዳስመዘገበም ይገለፃል፡፡
በ1998 ዓም ‹‹ቤስት ኮሌክሽን ናሆም ቮሊውም 14›› በሚል በናሆም ሪከርድስ አሳታሚነት፣ በተለያዩ ጊዜያት የሰራቸው ነጠላ ዜማዎች ተሰባስበውበት፣ 4ኛው አልበም ለገበያ ቀርቧል፡፡
‹‹ጥቁር ሰው›› በሚለው አልበሙ በአሳታሚው አዲካ ሬከርድስ 4.6 ሚሊዮን ብር የተከፈለው ቴዲ አፍሮ፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።  በመጀመርያው እትም በቴፕ ካሴት 300ሺ፣ በሲዲ 50 ሺ ቅጂዎች መሸጡና  ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቱ ድምጻዊውን በድርብርብ  ክብረወሰኖች ያደምቀዋል፡፡ “ጥቁር ሰው” ለተሰኘው  ዘፈኑ የሙዚቃ ቪድዮ ለመስራት ከ500ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ፣ በወቅቱ ለአንድ የሙዚቃ ቪዲዮ ከፍተኛውን ገንዘብ ያወጣ ድምጻዊ ለመሆን በቅቷል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጣቸው ነጠላ ዜማዎቹም ስኬታማ ነው፡፡ ነጠላ ዜማ ሲያወጣ አገር ይንቀጠቀጣል፤ ይቅበጠበጣል፤ አቧራ ይነሳል፡፡ ይህ ደግሞ በሙዚቃ ያለውን  የላቀ  ብቃት  የሚያረጋግጥ ነው፡፡
በመኪና ሰው ገጭቶ በመግደል ክስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ፣  የ6 ዓመት እስርና የ18ሺ ብር ቅጣት ተላልፎበት ነበር፡፡ ይግባኝ ተጠይቆ እስሩ ወደ ሁለት ዓመት ወርዶለታል።  በወንጀሉ ተጠርጥሮ ከተያዘበት ዕለት አንስቶ 482 ቀናትን በወህኒ ቤት ካሳለፈ በኋላ በአመክሮ ሊፈታ  ችሏል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከኢትዮጵያ ዝነኛ ሙዚቀኞች የሚስተካከለው የለም። በፌስቡክ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወዳጆች አሉት፡፡ በትዊተር ገፁ ከ3ሺ በላይ ተከታታዮችን አፍርቷል፡፡ በዩቲውብ የተጫኑ ከ145ሺ በላይ የሙዚቃ ቪድዮች፤ ቃለምልልሶች፤ ቅንብሮች፤ ዘገባዎችና  ተያያዥ መረጃዎች አሉት፡፡ በርካታ የዩቲውብ ቪዲዮቹ፤ ከሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኙ ሲሆኑ ብዙዎቹን  የሙዚቃ ቪዲዮዎች፤ የኮንሰርት ትእይንቶች፤ ቃለምልልሶች እና ሌሎች ጉዳዮች በዩ ቲውብ በአማካይ ከ10 እስከ 100ሺ ተመልካቾች ይጎበኟቸዋል። በአድናቂዎቹ አማካኝነት በስሙ፤ በስራዎቹና ሌሎች በሚሰጡት ልዩ ልዩ ማዕረጎች የተከፈቱ በርካታ የፌስቡክ ገፆችም ይገኛሉ፡፡ http://www.teddyafromuzika.com በአሁኑ ጊዜ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድረገፁ ነው፡፡
በ1991 ዓም ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከወጡ ሙዚቀኞች ጋር ላስታስ ባንድን አብሮ መስርቷል፡፡ ባንዱንም በበላይነት በመቆጣጠርና በመምራትም ትልቅ ድርሻና ሃላፊነትም ነበረው:: ከላስታስ በኋላ አቦጊዳ ባንድን ማናጀሩ ከነበረው ታዋቂው አዲስ ገሠሠ፤ በታዋቂው ዳሎል ባንድ ከሰሩ ሙዚቀኞች በመቀናጀት ሊመሰርት ችሏል፡፡ በዋናነት ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆኑ ከ5 እስከ 7 ሙዚቀኞችን በአባልነት ያሰባስበው አቦጊዳ፤ ቴዲ አፍሮን በማጀብ  በኢትዮጵያ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ኮንሰርቶችን አቅርቧል።  በባንዱ የሚሰሩት ሙዚቀኞች ዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው የሬጌ ሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ሰርተዋል፡፡  ከአንጋፋ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር በመስራት ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፡፡
የመጀመርያው ኮንሰርቱን የሰራው በፈረንጆቹ 2003፣ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀበት ወቅት ነበር፡፡ በ2005፣ የቦብ ማርሌይ 60ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኮንሰርት በተዘጋጀበት ወቅት፣ የዝግጅቱን መክፈቻ ሙዚቃዎች  የማቅረብ ማዕረግ አግኝቷል፡፡
ከአገር ውጭ በመላው አለም በአፍሪካ፤ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በአውስትራልያ እና በመካከለኛው ምስራቅ በመዘዋወር በ40 ትልልቅ ከተሞች ኮንሰርቶችን አቅርቧል። በተለይ በፈረንጆቹ 2006፣ ለአስር ወራት በቆየ  “ወደ አገር ቤት” በሚል ስያሜ በተዘጋጀ ኮንሰርት 33 የዓለም ከተሞችን አዳርሷል፡፡ በ2009፣ ከእስር  ከተፈታ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተዘጋጀ ኮንሰርት ሙዚቃዎቹን ሲያቀርብ፣ ከ60ሺ በላይ ታዳሚዎችን አግኝቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያቀርባቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች በአማካይ እስከ 15ሺ ዶላር እንደሚከፈለውም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኔዘርላንድ ኩባንያ ሄኒከን ከሚያስተዳድረው በደሌ ቢራ ጋር በመሆን  በመላ አገሪቱ በመዘዋወር “የፍቅር ጉዞ” በሚል ርእስ ለሚያቀርባቸው ኮንሰርቶቹ, 25 ሚ.ብር ተመድቦ ሊሰራ ተዘጋጅቶ  ነበር። በኢንተርኔት በተካሄደ የተቃውሞ ዘመቻ፣ ከ20ሺ በላይ ሰዎች በሰበሰቡት ድምጽ፣  ኮንሰርቶቹ ቢሰረዙም በውሉ  መሰረት 4.5 ሚ. ብር ተከፍሎታል፡፡
አንጋፋው ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ እና ቦብ ማርሌይ አርአያዎቹ ናቸው፡፡
በበጎ አድራጎት ስራዎቹም ይታወቃል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት በመስራት፤ ለአበበች ጎበና የህፃናት ማሳደጊያ እና ለአካል ጉዳተኞች ማህበር የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም በሱዳን ታስሮ ለነበር ኤርትራዊ  700ሺ ብር ዋስትና በመክፈል የሰራቸው ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ታሪክ በህይወት እያለ መፅሃፍ የታተመለት  ብቸኛው ድምፃዊም ነው፡፡ ‹‹የቴዲ አፍሮ ታላቅነት ሚስጥር›› በሚል ርእስ የህይወት ታሪኩን የሚዳስስ መፅሃፍ ያዘጋጀው አቤል ዘነበ  የተባለ ፀሃፊ ሲሆን “አብዮታዊ ሙዚቀኛ” ብሎታል፡፡
በካናዳ ፣ዊንፔግ ከተማ “ የትውልዱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ና አርአያ” ለሆኑ ባለሙያዎች  የሚሰጠውን ሽልማት የተሸለመው የ40ኛ ዓመት ልደቱን ባከበረበት እለት ነው፡፡  በ2016 የኮራ አዋርድ ላይ በምርጥ ዝነኛ ድምጻዊ (LEGENDARY AWARD) ዘርፍ ታጭቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2014 ፣ ብራዚል ላስተናገደችው 20ኛው የዓለም  እግር ኳስ ዋንጫ፣ ዘፈን እንዲሰሩ  በውድድሩ ዋና ስፖንሰር በኮካኮላ ኩባንያ ከተመረጡ የዓለም ሙዚቀኞች አንዱ ነበር፡፡   ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም በወከለ የሙዚቃ ስራው ተደንቋል፡፡

ምስጋና አዲስ አድማስ – ፎቶ ከአምለሰት ሙጬ ፌስ ቡክ የተወሰደ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *