ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ንግግር

” … ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ድረስ ታሪኩን መለስ ብለን ብንመለከት በሰው ዘር ላይ ግዛታቸውን ለመዘርጋት፣ ሰውን ባካልም ሆነ በመንፈስ ለመግዛት፣ ሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ሲታገሉ እናያለን፡፡ ከነዚህ አንዱ የሀይለኞች፣ ያጥቂዎች፣ የጦር ኃይል፣ ሁለተኛው የደራሲያን የብእር ኃይል ናቸው፡፡

“የጦር ኃይል በየጊዜው፣ በየቦታው የሚነሱ ኃይለኞች ሰራዊት አደራጅተው፣ የጦር መሳሪያ አከማችተው፣ ሰውን እየጨቆኑ ለግል ድሎታቸውና ፍላጎታቸው አገልጋይ የሚያደርጉበት እውር ሀይል ነው፡፡ የብእር  ኃይል በየጊዜው በየቦታው የሚነሱ ታላላቅ ደራሲያን ከስው ተለይተው፣ ከብእርና ከወረቀታቸው ጋር በየቤታቸው ተዘግተው፣ ምስጢረ ፍጥረትን እየመረመሩ፣ አዳዲስ ነገር እየፈጠሩ፣ ሰውን ከድንቁርና ሰንሰለት ተፈትቶ፣ ከእንሰሳ ባህርያት ጠርቶ፣ የመንፈስና የአካል ነጻነት አግኝቶ፣ ስርአት ያለው ህብረተሰብ መስርቶ፣ ፈጣሪ ከፍጥረት ሁሉ አልቆ ሲፈጥረው ለመደበለት ከፍተኛ ማእረግ ብቁ እንዲሆን የሚያደርገው ብሩህ ኃይል ነው፡፡

“እነዚህ ሁለት ተቃራኒ ኃይሎች በሚያደርጉት ትግል ምንም እንኩዋ ለጊዜው ጨቁዋኙ የጦር ኃይል ድል አድራጊ ቢመስል በመጨረሻ የእውነተኛው ድል አድራጊ የብእር ኃይል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የጦር ኃይል አስገዳጅ፣ የብእር ኃይል አስረጂ እንደመሆናቸው መጠን በማስገደድ የተመሰረተ እድሜው ማጠሩ፣ በማስረዳትና በማስወደድ የተመሰረተ ለሁልጊዜ መኖሩ የማያጠራጥር ነው፡፡ ለዚህም ኃይለኞች በጦር ኃይል የመሰረቱት ግዛት አንድ ባንድ እየፈረሰ፣ ያወጁት ትእዛዝ እየተደረመሰ፣ ዛሬ ዓለም የተቀበለው  ደራሲያን በየጊዜው ያወጁት የሃይማኖት፣ ያስተዳደርና የፍርድ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ስራት መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል”፡፡“… የጦር ኃይል … እና የብእር ኃይል …” ሃዲስ አለማየሁ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *