Skip to content

ኢቲቪ መቼ ነጻ ይወጣል? ” ብሔረሰቦችን አንቋሿል” በሚል የቴዲ ቃለ ምልልስ ታገደ!!

የኢትዮጵያ ወቀታዊ ሁኔታ እንደሚያሳስበው የሚገልጸውና በጥበብ ስራው የህንኑ ስጋት ለመጥረግ የተነሳው ቴዎድሮስ ካሳሁን / ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንግዳ ሆኖ እንደሚቀርብ ማስታወቂያ ከተሰራ በሁዋላ ህዝብ በጉጉት ሲጠብቅ ዝግጅቱ መሰረዙ ተሰማ። ዝግጀቱ እንዳይተላለፍ ማን እንደከለከለና ለክልከላው በገሃድ የተሰጠ ምክንያት ግን የለም። በትክክል ስም መጥቀስ ባይቻልም ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪሽን እንዳይቀርብ የተወሰነው በግለሰቦች ውሳኔ እንደሆነ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከትናት በስቲያ ሁለት ደቂቃ የሚሆን የማስታወቂያ ቃለ ምልልስ በማሰማት ዛሬ እሁድ ህዝብ ሙሉውን ቃለ ምልልስ እንዲሰማ ቃል ተገብቶ ነበር። የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ቴዲ አፍሮ ቤት ድረስ በመሄድ ቃለ ምልልሱን አካሂደው ማስታወቂያ እስከለቀቁበት ሰዓት ድረስ የቴዲ አፍሮ ቃለ ምልልስ በተባለው ቀን እንደሚከሄድ እሙን ነበር። እንዲህ ያለው ቀጭን መመሪያ ወርዶ ዝግጅቱ ህዝብ ጆሮ እንዳይገባ ይደረጋል የሚል ግምትም እንዳልነበር ከአካባቢው ሰዎች ለመረዳት ችለናል።

እነዚሁ ክፍሎችና አንዳንድ ለኢቲቪ እጅግ ቅርብ የሆኑ እንዳሉት ቅዳሜ እለት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። ከብዙ ንትርክ በሁዋላ ቃለ ምልልሱ እንዲተላለፍ ስምምነት ተደርሶም ነበር። በስተመጨረሻ ግን ዋና እና ምክትል ስራ አስኪያጁ አገር ውስጥ ባለመኖራቸው ሃላፊነት መወሰድ የሚችልና፣ የወረደውን ቀጭን ትዕዛዝ መጋፈጥ የፈለጉ አልተግኙም። በስብሰባው ወቅት ቃለ ምልልሱ መተላለፍ የለበትም ያሉት ክፍሎች ” ብሔር ብሄረሰቦችን አንቋሿል” ሲሉ አቀንቃኙን ግራ በሚያጋባ መልኩ ቃኝተውታል።

እነዚህ ክፍሎች እንደዚህ ቢሉም ግን ቃለ ምልልሱ ተቆንጥሮ ማስታወቂያ ከተሰራ በሁዋላ ከፍተኛ ባለስልጣን መመሪያ በመስጠት ቃለ ምልልሱ እንዳይተላለፍ ማድረጋቸውን ነው።

ጌጡ ተመስገን በፌስ ቡክ ገጹ  ” እርማት!” በሚል ርዕስ ” የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ቃለ መጠይቅ በ #EBC እሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ አይቀርብም” ከማለቱ ውጪ ስለ ዘግጀቱ አለመተላለፍ ያለው ነገር የለም። እስከመቼም ቃለ ምልልሱ ሳየተላለፍ እንደሚቆይ አልተገለጸም።

ጌጡ ተመስገን  እርማት!  የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ቃለ መጠይቅ በ #EBC እሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ አይቀርብም።

*********

‹‹አንዳንድ ባለሥልጣናት የኮርፖሬሽኑን አመራሮች፣ ኤዲተሮችና ጋዜጠኞች በቀጥታ በስልክ፣ በጽሑፍ መልዕክት ዜናም ሆነ ፕሮግራም እንዳይሠራባቸው፣ እንዲቀር ወይም እንዲሻሻል የሚፈጥሩት ተፅዕኖ እንዳለ ይሰማል፤›› ሪፖርተር 

ይህ በተደረገበት ተመሳሳይ ቀን ሪፖረተር ፓርላማውን ጠቀሶ  በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አሰራር ላይ ጣልቃ የሚገቡ እጃቸውን እንዲሰበስቡ መወሰኑንን  አስነብቧል።

Related stories   የኢትዮጵያ “ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም” ተመስገን ትሩነህ

የኢትዮጵያ ብሬድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን (ኢቢሲ) የመረጃ አቀራረብ ሥርዓትን የተቸው ፓርላማው፣ በተቋሙ ሙያዊ ነፃነት ላይ በተለያየ መንገዶች ጣልቃ የሚገቡ አካላት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ፓርላማው ሚያዚያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድና ሥራ አስፈጻሚዎችን በመጥራት ተቋሙ የሕዝብ ድምፅ መሆን እንዳልቻለ፣ ከፍተኛ የንግድ ሥራ ላይ እንዳተኮረና በሥራ አስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት የሙያ ነፃነቱን ያጣ ተቋም እንደሆነ መገለጹም ይታወሳል።

በዚሁ ስብሰባ የፓርላማው የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በተቋሙ ላይ ፓርላማው ሊወስድ ስለሚገባው ዕርምጃ የውሳኔ ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብም ታዞ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቡን ይዞ ቀርቧል፡፡ በኮርፖሬሽኑ አሠራር ላይ በተለያዩ መንገዶች ጣልቃ የሚገቡ አካላት እጃቸውን እንዲሰበስቡ፣ ተቋሙ ለረዥም ዓመታት ከነበሩበት ችግሮች ተላቆ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አኳኋን እንዲወጣ በማለት ውሳኔውን አሳልፏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልገው ያመላከቱ ችግሮች መኖራቸው በምክር ቤቱ በመታመኑ የሚታዩትን የአመለካከት፣ የአሠራር፣ የአደረጃጀትና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት እንዲያስተካክል የአመራር ቦርዱ ጠንካራ የለውጥ አመራር ቡድን በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲገነባ ውሳኔ ላይ መድረሱን ሪፖርተር አመልክቷል።

ሪፖርተር ከሳምንት በፊት የሚከተለውን ዘግቦ ነበር

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

የፓርላማ አባላት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ሚዲያ መሆን አልቻለም አሉ

 * የመንግሥት ባለሥልጣናት በዘገባ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ ተብሏል  * ኮርፖሬሽኑ የቀረቡበትን ወቀሳዎች ተቀብሏል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የሥራ አፈጻጸም የቆመለትን ዓላማ የማይወክል፣ የሕዝብ ድምፅ ከመሆን ይልቅ በባለሥልጣናት የሚታዘዝ መሆኑን በመግለጽ የሰሉ ትችቶችን ሰነዘረ፡፡

ፓርላማው የኮርፖሬሽኑን የሥራ ኃላፊዎችንና የቦርድ አመራሮችን ሐሙስ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመጥራት ነው ትችቱን የሰነዘረው፡፡ ‹‹አንዳንድ ባለሥልጣናት የኮርፖሬሽኑን አመራሮች፣ ኤዲተሮችና ጋዜጠኞች በቀጥታ በስልክ፣ በጽሑፍ መልዕክት ዜናም ሆነ ፕሮግራም እንዳይሠራባቸው፣ እንዲቀር ወይም እንዲሻሻል የሚፈጥሩት ተፅዕኖ እንዳለ ይሰማል፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ አባል አቶ ተክሌ ተሰማ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ በተፅዕኖ በተጠለፉ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ላይም ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ አልማዝ መሰለ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፣ ‹‹የምክር ቤቱን ሥራዎች በተመለከተ አንዳንድ የክልል፣ የከተማ አስተዳደርና የግል ሚዲያ ተቋማት ሥነ ምግባርን በጠበቀና በተሟላ ሚዛን ሲዘግቡ የሕዝብ ሚዲያ የሚባለው ኢቢሲ ሥራዎች በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒነት የላቸውም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ብቻ የሚያጎሉና የኅብረተሰቡን ችግሮች የማይዳስሱ መሆናቸውን በማንሳት ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አቶ ጥላሁን ጅግሶ የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ኮርፖሬሽኑ ወደ ፓርላማ የሚልካቸው ጋዜጠኞች በተጻፈ የአስፈጻሚ ሪፖርት ብቻ ዘገባ የሚሠሩ፣ ፓርላማው አቅጣጫ ሰጠ ሳይሆን ሚኒስትሩ እንዲህ አሉ የሚያዘወትሩ፣ እውነታዎችን አዛብተው የሚያቀርቡ ናቸው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ ከሚተላለፈው ይዘት ይልቅ ማስታወቂያ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ፣ ማስታወቂያዎቹም አሰልቺ መሆናቸውን አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መኮንን የሚዲያ ተቋሙ ሕዝባዊ ኃላፊነት እንዳለበት፣ እንዲሁም በራሱ ገቢ መተዳደር ያለበት በመሆኑ የንግድ ፍላጎቱ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Related stories   ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ "ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል"

በወር 18 ሚሊዮን ብር የደመወዝ ወጪ ያለበት ተቋም መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህንን ወጪ ለመሸፈን ተቋሙ ወደ ንግድ እያዘነበለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓላማውን ለማሳካት ፈተና እንደሆነበት የጠቆሙት አቶ ሥዩም፣ ከዚህ ፈተና ለመውጣት መንግሥት የበጀት ድጎማ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት መኖሩን ሙሉ ለሙሉ ያመኑት አቶ ሥዩም ይህንን ችግር በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት ችግርን የተመለከተ ዘገባ በተሠራበት ወቅት የሜቴክ (የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን) የሥራ ኃላፊዎች በሜቴክ ስለተመረተ አውቶቡስ መስሏቸው እንደደወሉ አስታውሰዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችም ለባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት ምቹ ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛው ሠራተኛ እርስ በርሱ ለመጠፋፋት ጥረት የሚያደርግ፣ የራስ ጥቅም የበዛበትና ተቋማዊ የአስተሳሰብ አንድነት የሌለበት መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር ዘገባዎች ማለትም ‘እንደ አንድ ለአንድና አሳሽ’ በተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ፣ ‹‹ባለሥልጣናትን እንደዚህ አታፋጡ›› የሚል ወቀሳ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ጠንካራ ኤዲተር (አዘጋጅ) የሌለው ተቋም ነው ሲሉ በግልጽ አምነዋል፡፡ ‹‹ያሉን ኤዲተሮች ፕሮፌሽናል አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ድርጅቱ የቆመለትን መሪ መፈክር ‹‹የህዳሴና የብዝኃነት ድምፅ›› የሚለውን አይወክልም ብለዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ግልጽነት ካደነቁ በኋላ፣ ባቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት መንግሥት የበጀት ድጎማ ሊያደርግ እንደማይገባና ችግሩ የሪፎርም እንጂ የበጀት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ተቋሙ ፈርሶ በድጋሚ ይመስረት እስከማለት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ግን፣ ‹‹ችግሩን ሰምተን ብቻ የምንተወው አይደለም፡፡ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ ምክንያቱም ኮርፖሬሽኑ ተጠሪነቱ ለፓርላማው ነው፡፡ ስለዚህ የባህል፣ የቱሪዝምና የመገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሚቀጥለው ሳምንት የውሳኔ ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብ፤›› ሲሉ አዘዋል፡፡

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
Pope Francis Says He Will Try to Find Common Ground With Donald Trump

(ABOARD THE PAPAL PLANE) — Pope Francis says he won’t try to convince U.S. President Donald Trump to soften his...

Close