ቴዎድሮስ ካሳሁን በአዲስ የሙዚቃ ስራው፥ ገበያውን እንደተለመደው፥ በቁጥጥር ውስጥ አውሎታል፡፡ ርዕሱ ‹ኢትዮጵያ› እንዲል፥ ያልተዳሰሱ ያልተነሱ የኢትዮጵያ ጉዳዮች አሉ ለማለት ያዳግታል። ‹‹ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ›› የምትለዋ የፍቅር እስከ መቃብር ትረካው ግን፥ ለእኔ ጎጃም እስከ መቃብር ሆናብኛለችና፥ ቴዲ አፍሮን በጎጃምኛ ስሙ፥ ቴዲ ጎፈር ብዬ ሰይሜ ጎጃም ላስመንነው ነው፡፡ በጎጃም አካባቢ፥ ፀጉሩን የሚያሳድግ ሁሉ ‹ፀጉሩን አጎፍሯል› ይባላልና፥ ቴዲ ጎፈር እንበለው። መልካም ምናኔ፡፡
‹‹ማሬ ማሬ
ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ ማር በንቧ ብዙ ድካምና ልፋት እንዲገኝ፤ ጎጃምም በልፋት በድካም ትገለፃለችና፡፡ የጎጃም ማሯ ትምህርቷና ጤፏ ናቸው፤ በብዙ ድካምና ውጣ ውረድ ገንዘብ ያደርጓቸዋል እንጂ በዋዛ አይቀመሱምና፡፡ ጎጃም ትምህርቷን ልቅሰም ቢሉ፥ ከውሻ ተናክሰው፣ አኮፋዳ ይዘው፣ ደበሎ ለብስውና እከክ ወርሰው፥ በጭንቅ፣ በመከራ ይማሩታል እንጂ፤ አይስ ክሬም እየላሱ፣ ጌም እየተጫወቱ፣ ባክ ባግ ቦርሳ አንግተው አይደለምና፡፡ ጤፍም በአይን ሲያይዋት ትናንሽ ናት እንጅ፥ ትንሽ አንጀትን የምታልብ ድካም ያለባት ሰብል ናት፡፡ መሬቱን ሁለት ሦስቴ ደጋግመው አርስው፣ አለስልሰው፤ ዘር ዘርተው፣ በከብረት አስደቅድቀው፤ ጉልጓሎ ጎልጉለው፣ አረም ሁለት ሦስቴ ታርሞ በብዙ ድካም አድጋ፣ አፍርታ፣ ታጭዳ፣ ተወቅታ ጎተራ ትገባለች እንጅ፤ እንደ ቡና እሸት እየለቀሙ ጎተራ አይከቷትም። ጎጃምማ ማር ናት የምትላስ ወለላ፡፡
ንጉስ ካሌብ ከንግስናው በፍቃዱ ወርዶ ቢመንን የገባው ጎጃም ጣና ገዳም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሰነፍ ተማሪ እየተባለ በተወለደበት አካባቢ ቢወቀስ ጎጃም ገብቶ የዜማ ሊቅ ሆነ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ የገዛ ወንድሞቹ እስከ እየሩሳሌም ቢያሳድዱት ጎጃም ገብቶ፣ በተማረው ጥበብ ሁሉንም አስከነዳቸውና የቅድስና ማዕረግን ተቀዳጅቶ ለዘመናት ምስክር የሚሆኑ ትክል ውቅር ህንፃ ቤተ ክርስቲያኖችን ቆርቁሮልን አልፏል፡፡ የአስራ ስድስተኛው ዘመን ፈላስፋችን ዘርዐ ያዕቆብ እንኳ በተከሰተው ችግር ተማርሮ ሊሰደድ የወደደው ወደ ጎጃም ነበር፤ ምንም እንኳ እንፍራነዝ የሌላ ሃገር መስሎት እንፍራን ሃብቱ ቤት ተጠለልኩ ቢለንም፡፡ ጎጃም ረቂቅ ቅኔ ናት!
‹‹የጸበል ዳር እንኮይ፤ ወንዝ ያወዛት ቅጠል›› የወንዝ ዳር እፀዋት ከልምላሜ፣ ከአበባ፣ ከፍሬ አይለዩም፤ አመት እስከ አመት ከሐመልማል አይታቀቡም፡፡ ሰብለ አለም በቤተሰቦቿ ቤት እንደ ጸበል ዳር እንኮይ፣ እንደ ወንዝ ዳር ቅጠል የፈካች ያማረች ጉብል ነበረች፡፡ ለቤተሰቦቿና ለአካባቢዋ ውበት የምትፈነጥቅ ስጋ ለበስ ሐመልማል፡፡
‹‹ብራናዬ አንቺ የልጅነቴ ቀለም፤
እኔ እንዳንቺ ያጠናሁት የለም››
በእርሷም ልጅነት በባልንጀሮቿም ልጅነት ውስጥ ከህሊና የማትለይ ማራኪ ቀለም፡፡ በልጅነት ዓይናችን ስንመለከት ሁሉም የልጅ ነገር ይሆናልና፤ በልጅነት ትውስታችን ዛሬም ጎጃም ልጅ ናት፡፡ ቀለሟ በህሊናችን ቀልሞ አልጠፋ ያለን የልጅነት መስፈሪያ መለኪያ፣ አለምን መመልከቻ መነጽር ያበጀንባት ብራናችን ጎጃም፡፡ እንደ ማንኩሳው ልጅ በዛብህ፡፡
‹‹ብራናዬ አንቺ የልጅነት ጓዴ
ተረሳሽ ወይ የሳት ዙሪያው ባንዴ››
‹‹ፍቅር የበዛባት ፈልቃ ከማንኩሳ፤
መንናለች ቢሉኝ ብጫ ልብስ ለብሳ››
ማሬ፣ ማሬ ሲላት፤ እንኮይ ሲላት፤ የልጅነት ቀለሜ፣ ጓዴ ሲላት የነበረችውን አሁን በመጠቅለያ ስሟ ‹‹ፍቅር የበዛባት›› ብሎ አመጣት፡፡ ሲማስንላት፣ ሲንገላታላት፣ ሲንከራተትላት የሚኖራት ጎጃሙን ፍቅሬ፣ ፍቅሬ እያለ ሊያሽኮረምማት ይከጅላል። ፍቅር በባህሪው መናኝ ነው፤ ሌላ ጠባይ አይስማማውም፤ ብቻውን ፍቅር ነው፡፡ ቴዲ ጎፈርም መንናለች ቢሉኝ ብጫ ልብስ ለብሳ›› ይላታል ፍቅሩን፤ መናኝ መሆኗን እንደ መርዶ ሁሉ ከሌሎች ነው የሚሰማው፤ ‹‹መንናለች ቢሉኝ›› ይለናልና። መናንያን ብጫ ልብስ ለብሰው፣ ያውም ወይባ ተጎናጽፈው ብርሃናዊ፣ መናኝ፣ ሰማያዊ መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ የቴዲ ፍቅሩ ወደ ጎጃም ያስመነነችው ብጫ/ወይባ አስለብሳ ነው፡፡ ሰብልዬ፣ ሰብልዬ እያለ ሲያንቆለጳጵሳት፤ ጎጃም ሰባተኛው ሰማይ ላይ ሰቀለችው፡፡ ‹‹ባሳደገኝ ደብር የስለት ልጅ ሆኜ፤ ካህን እንዴት ይፍታኝ ያንቺ እስረኛ ሆኜ›› እያለ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን የተባሉት ካህናት እንኳን የማላገኝበት ያንቺ ፍቅር የሰባተኛው ሰማይ መናኝ አድርጎኛል የሚለን ይመስላል፤ ቴዲ ጎፈር፡፡ ‹‹ሸዋ ተሩፋኤል›› ይልና በዘዴ አማላጁን ሩፋኤልን ይጠራል፤ ሩፋኤል ፈታሄ ማህጸን ነውና፡፡ ሴቶች በወሊድ ጊዜ ምጥ ሲበዛባቸው ማህጸናቸውን ፈትቶ በሰላም እንዲገላገሉ ያደርጋል፡፡ ቴዲ ጎፈር የጎጃም ፍቅር ጠንቶበት በጭንቅ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ሰቅሎታልና፤ ፈታሄ ማህጸን ሩፋኤል የሰማያትን ማህጸን እንዲፈታለት ይማጸነዋል፡፡
‹‹በጊዜ ተደፋ የቀለሙ ቀንዴ፤
የኔ ፊደል ማወቅ ካንቺ አዳነኝ እንዴ››
በድቁና ዘመኑ የጎጃም መኳንንትንና መሳፍንትን አፍ ያስከፈተው ጉብሉ በዛብህ፤ ባልታሰበ አጋጣሚ ፊደል እንዲያስተምራት በተሰጠችው ሰብለ የምትባል ምትሃታዊ ልጃገረድ አቅሉን ስቶ ጨርቁን ጥሎ አበደ፡፡ ‹‹ድጓ መማር መና፤ ማወቅስ ውሃ ዋና›› እንዳለው፣ የውሃ ሙላት ሚስቱን ሲወስድበት ታዛቢ እንደሆነው ደብተራ፤ የበዛብህ ቅኔ ማወቅ ከሰብለ ፍቅር ሊያስጥለው አልቻለም፡፡
‹‹ማሬ ማሬ ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት፣ በሙሴ ቃል ኢትዮጵያን የሚከበው ወንዝ የጎጃሙ ግዮን እንደሆነ ተጠቅሷል አይደል፡፡ ይሄው ግዮንም አይደል እንዴ ገነት ከሚያጠጡ አራት አፍላጋት አንዱ ነው የተባለ። ታዲያ ቴዲ ጎፈር፤ ጎጃምን ፍለጋ መንኖ ሰባተኛው ሰማይ አልወጣም የሚል አለ‘ንዴ? ይሄው በራሱ አንደበት እንዲህ ይለናል፡-
‹‹ማር ሲገባ ገዳም ድንጋይ ተንተርሶ፤
እዩት ጧፍ ገዳም ገባ ቢጫ ልብሱን ለብሶ››
ማር ባህሪ የተባለ ጎጃም ድንጋይ ትራሱ፣ ቅጠል ጉርሱ፣ ዳዋ ልብሱ ሆኖ ገዳም ሲገባ ቢያየው፤ እንዲሁም ማር ባህሪ የሆነች ሰብለ ወንጌል ፀብዐ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን ተቋቁማ ድንጋይ ተንተርሳ፣ ጤዛ ልሳ፣ ዳዋ ጥሳ ገዳም ገባች፤ የፍቅር ጧፍ የምሆን ቴዲ፤ ከማር ተለይቼ ጧፍ መሆን፣መኖር፣ መብራት መስጠት፣ ብርሃን መፈንጠቅ አይቻለኝምና ጎጃም መንኛለሁ ይለናል። ጧፉ ቴዲ ጎፈር፤ ወይባ ለብሼ ተከተልኩ እያለም አይደል እንዴ፡፡ ምስጢር ለማመስጠር ስፍራ አልበቃው ብሎ እየፏለለ ጎጃም ይገባል፤ ጧፉ ቴዲ፡፡
‹‹ማር ጧፉኔ፣
ማር ጧፉና፤
ማሬ ማሬ፣
ጎጃም ኖራ ማሬ››
‹‹ማር ጧፍ ሆኖ ገባ መቅደስ፤ ነዶ ሌሊት ጸሎት ሊያደርስ›› ማር የተባለው ፍቅር ማርኮኝ፤ ጧፍ የሆንኩት እኔ ቴዲ ተያይዘን መቅደስ ገባን፤ በፍቅር እሳታችን ሌሊት በተባለው ጥላቻ ላይ እንደ ጧፍ ነድደን የምህረትና የቸርነት ጸሎት ከሚደርስበት ሰባተኛው ሰማይ ገነት ገብተን ምልጃ እያቀረብን ነው የሚለን ይመስላል፤ የጎጃሙ መናኝ ቴዲ ጎፈር።
‹‹ሰብልዬ ሰብልዬ ሰብለ አለም ኧረ ቢጫው ቀለም፤ ሰብለ አለም ገባሽ ወይ ገዳም›› በጭንቅ፣ በምጥ፣ በጋር የተያዘ ሰው ህመሙን ቢደጋግም ቢደጋግም ቢጠራው የሚሻለው የሚድን ይመስለዋልና፤ ስሟን ጠርቶ አይጠግበውም፤ ሰብለ ጎጃሙን፡፡ አልያዝ አልጨበጥ ብትለው ‹‹ኧረ ገባሽ ወይ ገዳም›› ይላታል፡፡
‹‹ማሬ ማሬ ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ ጎጃሜ ጉብል ልጁን ሲወዳት ሰብለ ይላታል፡፡ መሬት አርሶ፣ ዘር ዘርቶ፣ አረም አርሞ እንደሚንከባከባት ሰብል ሁሉ ‹‹ሰብለ›› ይላታል የሚወዳት ልጁን፡፡ የሃዲስ አለማየሁ የ‹‹ፍቅር እስከ መቃብሯ›› ሰብለ እንዲህ ያለች ሰብል ናት (ሰመሬታ ሰብስቤ የምትባለውን የዩኒቨርሲቲ ጓደኛቸንን በምን እናስታውሳት ታዲያ በዚህ ካልሆነ)፡፡ የተደከመባት፣ የተንከራተቱላት፣ የሚመንኑላት፣ የመነነች ሰብል። ጎጃም ሲመንኑላት ትመንናለች፤ ስትመንን ይመንኑላታል፡፡ በምናኔ በብቸኝነት ተሰልቃ፣ ተደቁሳ፣ የምትጠፈጠፍ እንጎቻ ናት ጎጃም፡፡ ጎጃምን ይበሏታል እንጂ እሳቷን አይጋሯትም፡፡ ‹‹ማሬ ማሬ ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ ጎጃም ሽናሻ፣ አገው፣ ሻንቅላ፣ ዴንሳ፣ ስናን፣ ቀራንዮ፣ ጉንድ፣ ጮቄ፣ ሶማ፣ ባሶ፣ ጃዊ፣ ቻግኒ፣ ወንበራ፣ መተከል፣ ወይጦ፣ ደንቀዝ፣ እንፍራንዝም ናት። ‹‹ሳዋህድ ከኖርኩት ቅኔ ከደብተሬ፤ ተሸሎ ተገኜ ባላንዲሩ ገብሬ›› ጎጃም የባለዋሽንት ባላገር፣ የቅኔ፣ የቀለም ውህድ ሃገር መሆኗን ለማሳየት የኛው ቴዲ ጎፈር ስሪት፣ ንጥረ ነገራችንን እያወዳደረ፣ እያነጻጸረ ያሳየናል፡፡ ‹‹ለካ ሰው አይድንም በዖሪቱ ገድል፤ ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካደረገ ድል›› ይለናል፤ እርሱን ብቻ ሳይሆን ጎጃም፣ ፍቅር፣ ሰብለወንጌል ሁሉንም አሸንፋለችና።
‹‹አንቺ የፍቅር ጥጌ ወርቅነሽ በጣሙ፣
መምጣቴ ነው በቃ እኔ አቃተኝ አሁን፤
ሃዲስ አለም ሆነ ባንቺ ስል ወጋየሁ…›› ይላል ቴዲ፡፡
ሃዲስ ዓለም የማየት ወግ የሚያደርሰን የጨለማውን መገለጥ የንጋቱን ውጋግ የሚያሳየን መሲህ ከጎጃም ያገኘ እየመሰለው፡፡ የቴዲ የፍቅር ጌጡ ጎጃም ወርቅ ከነጣዕሙ የሚያጣጥምባት መሆኗን ያውቃልና፤ ቀድሞ ገና ቀጠሮ ያስይዛታል – ‹‹መምጣቴ ነው በቃ እኔ አቃተኝ አሁን›› እያለ፡፡ የመሲህ መምጫው በጭንቅ በመከራ ነውና፤ ጭንቅ መከራ የሚበዛባትን የጎጃም ማር ለመላስ፣ ከመሲኋ ጋር ቃል ለቃል ለመመላለስ የሚናፍቅ የሚሽቀዳደም ይመስላል፡፡ ‹‹የት ነበር ያረኩት ቀፎዬን ስል ኖሬ፤ ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ›› የክርስቶስን መወለድ በኮከብ ምልክትነት አውቀው ኮከቡ መንገድ እየመራቸው ቤተልሔም በግርግም ለተወለደው ህጻን እንደ ሰገዱ ሰብዐ ሰገሎች (ጎጃሜውን ዘርዐ ደሽትን ጨምሮ) ቴዲም ንብ ተከትሎ፣ ጎጃም ገብቶ የናፈቀውን መሢህ ያገኘ ይመስላል፡፡
ዊንተር ፓላስ የሚባል የሩሲያ አረቄ ያለ መለኪያ እየተቀዳልኝ፤ ከመነንኩበት ሃሳብ ስነቃ፣ ክለብ ዩጎቪያ ውስጥ መሆኔን ተረዳሁ፡፡ ጋባዥ ጓደኞቼ ከእነመኖሬም እረስተውኝ ዳንኪራቸውን እያስነኩት ነው፡፡ የሚዘፈነውም ዘፈን የጃኖ ባንዶች እንደ ሚዳቋ እየተዘለለ የሚናጡበት ነው። ምንድን ነው እዚህ ሃሳብ ውስጥ የከተተኝ፡፡ ምናልባት ቀን በተደጋጋሚ የቴዲ አፍሮ አዲሱ አልበምን ስንሰማ ስለቆየን ይሆናል፡፡ ጩጬው ጓደኛዬ ፊቱ በሙሉ ላብ በላብ ሆኖ እስክስታውን ይለዋል። ፊቱን ፀሐይ አስመስሎ ሌላኛው ጓደኛዬ ዝላዩን ያጦፋል። እንዳሻው የሚምነሸነሸው ሌላው ጓዴ ወለሉ ጠቦታል፡፡ እኔ በእኩለ ሌሊት መሲህ ከጎጃም እጠብቃለሁ፡፡
‹‹ሃዲስ አለም ሆነ ባንቺ ስል ወጋየሁ፤
የእድሌ ሆነና ባንቺ ተሰቃየሁ
ማር ጧፉኔ፣
ማር ጧፉና፤
ማሬ ማሬ፣
ጎጃም ኖራ ማሬ››

addisadmass

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *