ከጅምሩ ” ስልታዊ እንጂ ከልብ የታሰበ የፖለቲካ ውሳኔ አይደልም” የተባለለት ድርድር ጊዜ የትጨበጠ ነገር ሳይሰማበት አራት ወራትን አሳልፏል። ዋና የተባሉት ፓርቲዎች የተለዩት ድርድር ያሰባስባቸው ድርጅቶች ታሪካቸውና የመሪዎቹ የፖለቲካ ጨዋታ ከሕዝብ የተሰወረ ባለመሆኑ ድርድሩ ሳይጀመር ” የከሸፈ ” ሲሉ ብዙዎች በተለያዩ መድረኮች አጣጥለውታል። ያም ሆኖ ግን እነ አቶ ትግስቱ፣ እነ አየለ ጫሚሶን፣ እነ ተስፋዬ ቶሎሳን፣ እና ሌሎችን አካቶ የድርድር ጉዞ የጀመረው ኢህአዴግ የሚናገረው የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት መቁረጡን ነው።

የጀርመን ሬዲዮ የሚከተለውን ዘግቧል

አራት ወር ሆኖትም ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ገና-ሥለ ድርድር ከመደራደር ወይም በሥነ-ሥርዓታዊ ጉዳዮች ላይ ከመወያየት ያለፈ ቀጥታ ድርድር አልጀመሩም።ዋናዉን ድርድር የሚጀምሩበትንም ሆነ አጠቃላይ ድርድሩ የሚጠናቀቅበትን ወቅት አልወሰኑም።ወስነዉም ከሆነ በይፋ አላስታወቁም።በአራት ወሩ ሁለት ትላልቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርድሩ ወጥተዋል

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከ22 ተቃዋሚዎቹ ጋር ባለፈዉ የካቲት የጀመረዉ ዉይይት ወይም ድርድር ሞቅ-ቀዝቀዝ እያለ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።የኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ሥርዓት በሕዝባዊ ተቃዉሞ በመናጋቱ ሠበብ የተጀመረዉ ድርድር ገና ከጅምሩ ድጋፍ፤ ተቃዉሞ፤ ጥርጣሬና ቀቢፀ-ተስፋ አልተለየዉም። የደጋፊ-ተቃዋሚ፤ የተጠራጣሪ-ቀቢፀ ተስፈኞቹ ሰበብ ምክንያት በርግጥ ብዙ ነዉ።በጥቅሉ ግን ደጋፊዎቹ፤ ልዩነትን በዉይይት ማጥበብ፤ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓትን ለመገንባት ድርድሩ ጠቃሚ ነዉ ባዮች ናቸዉ። ድርድሩን የተቃወሙት ወገኖች ለመቃዉሟቸዉ ከሚያቀርቡት ምክንያት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚመለከታቸዉ ኢትዮጵያዉን በሙሉ (ከዉጪም-ከዉስጥም) ሳይጋበዙ የሚደረግ ድርድር የኢትዮጵያን ችግር አይፈታም የሚለዉ ምናልባት ዋናዉ ነበር።በድርድሩ መሳተፍ የሚገባቸዉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንደታሰሩ፤ ጋዜጠኞች፤ የመብት ተሟጋቾች፤ ፍትሕ እንዲከበር አደባባይ የወጡ ወጣቶች እስር ቤት ታጉረዉ የሚደረግ ድርድር የገዢዉን ፓርቲ አገዛዝ ከማረጋገጥ ያለፈ ዉጤት የለዉም ባዮች ነበሩ።ናቸዉም።

የተጠራጣሪዎቹ ምክንያት በሁለቱ መሐል የሚወድቅ ነዉ።የገዢዉ ፓርቲ ባለሥልጣናት ድርድሩ «የፖለቲካ ምሕዳሩን  ይበልጥ ለማስፋት» የሚል ዓላማ እንዳለዉ ገለፁዉ፤ ተቃዋሚዎቻቸዉ ደግፈዉት።ድርድሩን ጀመሩ-ቀጠሉትም።እስካሁን እንደ ደጋፊዎቹ የበጎ ዉጤት-ፍንጭ ሳያሳይ፤ እንደተቃዋሚዎቹ ጨርሶ ሳይቋረጥ ድንበር-ገተር እያለ  የተጠራጣሪዎቹን እምነት እና ምክንያት እያጠናከረ ቀጥሏል።አራት ወር ሆኖትም ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ገና-ሥለ ድርድር ከመደራደር ወይም በሥነ-ሥርዓታዊ ጉዳዮች ላይ ከመወያየት ያለፈ ቀጥታ ድርድር አልጀመሩም።ዋናዉን ድርድር የሚጀምሩበትንም ሆነ አጠቃላይ ድርድሩ የሚጠናቀቅበትን ወቅት አልወሰኑም።ወስነዉም ከሆነ በይፋ አላስታወቁም።በአራት ወሩ ሁለት ትላልቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርድሩ ወጥተዋል።ለምን? አብረን እንጠይቃለን።

ነጋሽ መሐመድ  ልደት አበበ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *