Skip to content

የቆሼ አደጋ ተጎጂዎች “መንግሥት ለቃሉ ሙሉ በሙሉ ታማኝ አልሆነም “

ከ130 ሰዎች በላይ ሕይወትን የቀጠፈው የቆሼ አደጋ ሁለት ወራት ቢያልፉትም፣ እስካሁን ድረስ ቃል የተገባው ዕርዳታ እንዳልደረሳቸው በአደጋው ተጎጂ የሆኑ ግለሰቦች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

አደጋው በተከሰተ ማግሥት ማለትም መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በነበሩ ሁለትና ሦስት ሳምንታት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ዕርዳታ እንደሚሰጡ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ከመንግሥትና ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ተቋማት፣ እንዲሁም ከባለሀብቶች ወደ 75 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብር ማሰባሰብ ተችሎ ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤተሰቦቻቸውን በሕይወት ላጡ ተጎጂዎች አሥር ሺሕ ብር ለቀብር ማስፈጸሚያ፣ እንደሁም ቤታቸውን ላጡ ሕጋዊ ተከራዮችና ባለንብረቶች ለሆኑ ቤተሰቦች የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም ሳይት የስቱዲዮ ቤት ማስረከቡን አስታውቆ ነበር፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቤተሰቦች እንደሚሉት ግን ለ54 ቤተሰቦች ቃል የተገቡት ቤቶች እስካሁን አልተሰጡም፡፡

ሪፖርተር ሥፍራው ድረስ ሄዶ እንዳረጋገጠው እነዚህ ተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ድረስ በኮልፌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው መጠለያ ማዕከል፣ ወይም በተለምዶ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

የሪፖርተር ጋዜጠኞች ባደረጉት ጉብኝት እነዚህ ቤተሰቦች በመጠለያ ጣቢያው ፖሊስ ተመድቦላቸው ሲወጡና ሲገቡ ስማቸውን አስመዝግበው ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በእዚህ መጠለያ ብቻ 98 ያህል ተጎጂ ቤተሰቦች ይኖራሉ፡፡

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?

ሪፖርተር ካነጋገራቸው ተጎጂ ቤተሰቦች መካከል ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ የሰባት ወር ሕፃን እናት ትገኝበታለች፡፡ እሷ እንደምትለው እስካሁን ምንም ዓይነት የገንዘብ ዕርዳታ አልተሰጣቸውም፡፡ ሌሎች ተያያዥ ዕርዳታዎችም እየቀነሱ ነው ብላለች፡፡

አደጋው በደረሰ ማግሥት ምግብ በቀን ሦስት ጊዜ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ምሳና እራት ብቻ በየቀኑ ከ9፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት አንድ ላይ እንደሚመጣላቸው፣ ቁርስ ግን ከጊዜ በኋላ እንደቀረ ትናገራለች፡፡

ይህንንም ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡ ግለሰቧ በምትኖርበት የመጠለያ ጣቢያ አንደኛው ክፍል ብቻ ወደ 22 የሚጠጉ ቤተሰቦች እናቶች፣ አባቶችና እንዲሁም ሕፃናት ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 12 ያህሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነው፡፡ ከአሁን በፊት አራስ ለሆኑ እናቶች ለሕፃናት ንፅህና መጠበቂያ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች ይመጡ እንደነበር፣ አሁን ግን መቆማቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተጎጂዎች ገልጸዋል፡፡

‹‹ሌላው ቢቀር ነፃ ሕክምና ስናገኝ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሄደን ተጎጂዎች መሆናችንን ገልጸን አገልግሎት ስንጠይቅ እንኳን አያምኑንም፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤት ተሰጥቶን ጥሩ ሕይወት እንደጀመርን ነው ሰዎች የሚያስቡት፤›› ሲሉ አንድ ተጎጂ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

Related stories   በምናለሽ ተራ ገበያ – ከሰኞ እስከ እሁድ

ሪፖርተር ሥፍራው ድረስ ሄዶ እንዳረጋገጠው የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም ሳይት በከንቲባ ድሪባ ኩማ የተላለፉት ቤቶች ገና ተሠርተው አልተጠናቀቁም፡፡ ማንም ገና እንዳልገባባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው አደጋው ከተከሰተ ከሳምንታት በኋላ ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ያሉ ነገር ግን በአደጋው እንደገና ሊጠቁ ይችላሉ የተባሉ ግለሰቦች ከቦታው ተነስተው ነበር፡፡ ከእዚህ ጋር በተያያዘ ግማሽ የሚሆኑት ቆሼ አቅራቢያ የተሠሩ የመንግሥት ቤቶችን እንዲወስዱ የተደረጉ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ አስኮ የሚገኝ ቤት እንደሠፈሩ ማወቅ ተችሏል፡፡ ከእዚህ ውስጥ ቆሼ አቅራቢያ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የሠፈሩት እስካሁን ለቤቶቹ ሕጋዊ ውል እንደሌላቸውና መብራትም ገና እንዳልገባላቸው ማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው ገንዘብ ይሰጣል ተብሎ ቃል የተገባው ነው፡፡ ተጎጂዎቹ የባንክ አካውንት እንዲከፍቱ ቢደረግም፣ እስካሁን የገባላቸው ገንዘብ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕጋዊ ይዞታ ለነበራቸው 14 አባወራዎች፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ውስጥ 175 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ ተመስገን መኮንን የተባሉ ግለሰብ በቆሼ ስምንት ዓመታት እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ በአደጋው ስድስት ቤተሰቦቻቸውን በሕይወት እንዳጡ የሚናገሩት አቶ ተመስገን፣ እስካሁን ያገኙት ምንም ዓይነት ምትክ ቦታ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ

‹‹በጣም ተቸግረናል፡፡ ገንዘብም አልተሰጠንም፡፡ ምግብ የምበላው ጓደኞቼ እየጋበዙኝ ነው፤›› ሲሉ አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አደጋው ከደረሰበት ቆሼ አቅራቢያ ያሉ ለአደጋ ተጋላጭ ቤተሰቦች እንዲነሱ መደረጉ ቢታወቅም፣ አሁንም ድረስ ቦታው ላይ የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ መመልከት ችሏል፡፡

አደጋው ከደረሰበት ቦታ ያልተነሱ አሥር ያህል አባወራዎች እንዳሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ግለሰቦች ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እኛ ተጎጂ ስላልሆንን ምንም የተደረገልን ዕርዳታ የለም፤›› ሲሉ በአካባቢው ነዋሪ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ ራድያ መሐመድ ይናገራሉ፡፡

ከአሁን አሁን አዲስ ነገር ይመጣል በማለት በደንብ ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳልቻሉ ተጎጂዎች ይናገራሉ፡፡

ጉዳዩ ባለው ውስብስብነት ምክንያት የማጣራቱ ሥራ ጊዜ እንደፈጀና አሁን ግን ሥራው እየተጠናቀቀ መሆኑን፣ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የአዲስ አበባ ከተማ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አንድ የሥራ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ትክክለኛውን ከአጭበርባሪው መለየት አለብን፤›› ሲሉ ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነስረዲን ሙሐመድ በበኩላቸው፣ ‹‹ባለን መረጃ መሠረት ሕጋዊ ለሆኑት ገንዘብ ተሰጥቷል፤››

ሪፖርተር አማርኛ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
ቴዎድሮስ አድሃኖም – ካልተመረጡ እምነታቸው በሆነው የጎሳ ፖለቲካ የመጀመሪያው ሰለባ ሆነው ይመዘገባሉ!!

የኢትዮጵያ ሃኪሞች ማህበር ሊቀመንበር ዶክተር ገመቺስ ማሞ ዶከተር ቴዎድሮስ አደሃኖምን በሚያወድሰው ንግግራቸው ወቅት ኮሌራን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ " መንግስትን ጠይቁ"...

Close