“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሕፃናት በጎዳና እና በትምህርት ቤት

ግርማ ሠይፉ ማሩወደፊት አዲስ አበባ እንዴት እንደምትሆን መገመት ከባድ ቢሆንም የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል ብለን ለምናም ሰዎች፤ ሳያገባቸው ገብተው አያገባችሁም የሚሉንን ንቀን በመተው፤ አንድ አንድ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል፡፡ እነዚህ የወደፊት አገር ተረካቢ የምንላቸው ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በየቀኑ በምመላለስበት ለገሐር፣ ብሔራዊ ቲያትር/መከላከያ መብራት ላይ፣ መስቀል አደባባይ፣ ወዘተ የምናያቸው ህፃናት ልጆች በዚህ ሁኔታ መኖራቸው እንዲያበቃና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኝ አንድ ቀን ተነስተው በከተማው ያለውን ህንፃና መኪና በድንጋይ ሲያወድሙ፣ እሳት ጭረው ሲለኩሱ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪ ከተማው የተስፋፋው ህፃናትን አዝሎ ልመና በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተናገደው፤ የሴቶችና ህፃናት ሚኒሰትር ቢሮ ባለበት ጎዳና ላይ ነው፡፡ በሰማቸው ሚኒሰትርም ይሁን ኤክስፐርት የሆኑ ሰዎች ይህ ጉዳይ እንደሌለ ቆጥረው በተንደላቀቀ መኪና ሲገቡና ሲወጡ ስራቸው ምን እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም፡፡

በአንድ ወቅት የቀደሞዋ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒሰትር በጉዲፈቻ ወደ ውጭ ስለሄዱት ህፃናት ጉዳይ ለመነጋገር ፈረንሳይ መሄዳቸውን አስታውሳለሁ፡፡ አፍንጫቸው ስር ቤንዚልና ማስተሸ እየሳቡ በጠራራ ፀሀይ ናላቸውን እያዞሩ የሚገኙትን ህፃናት ለመታደግ ግን አንድም የሚደረግ ነገር አይታይም፡፡ በዚህ ፅሁፌ ወቀሳ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄ አቅጣጫም ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡

1. በመንገድ ላይ የሚገኙ እድሚያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ በተለይ በቤንዚልና ማስትሽ ናላቸውን የሚያዞሩት ህፃናት እንደዚህ መሆን መብታቸው ሰለአልሆነ፣ በግዳጅ ወደ አንድ ማዕከል ገብተው ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቢ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ህፃናት በማሳደጊያ ወይም በጉዲፈቻ እንዲኖሩ ማመቻቸት በወረቀትም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለ (አንቀፅ 36)፤ እነዚህ ሕፃናት ምግብ፣ መጠለያ፣ ትምህርት የማግኘትና ጤናቸው የመጠበቅ መብት አላቸው፡፡ መንግሰት ይህን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
2. ሕፃናትን ለልመና መጠቀም ወንጀል ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ወላጅ እናትም ሆነ አባት ቢሆኑ ህፃናትን ለልመና ሲጠቀሙ ዝም ብሎ መመልከት፤ ይልቁንም ለእነዚህ ሰዎች ገንዘብ በመስጠት ማበረታታት ገደብ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ልጆቻቸውን መመገብ አልቻልንም ብለው በልመና ላይ የተሰማሩ ሰዎች፤ ልጆቻቸውን ተቀምተው ልጆቹ አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ የመንግሰት ግዴታው ይመስለኛል፡፡
የአረጋዊያን መጦሪያ እንደሚያስፈልግ ሁሉ የህፃናት ማሰደጊያ ቦታ መኖር የግድ ነው፡፡ የህፃናት ማሳደጊያ የመጨሻው አማራጭ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ሕፃናት በጎዳና ላይ በዚህ ሁኔታ ከሚኖሩ ግን መቶ በመቶ የተሻለው አማራጭ የህፃናት ማሰደጊያ ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ይህች አገር አቅም የላትም የሚባል ሰንካላ ሰበብ መቅረብ የለበትም፣ ስርዓት ተዘርግቶ ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ህፃናት ማቆያዎች በጉዲፈቻ ልጆች ማሳደግ ለሚፈልጉም ግለሰቦችም ሰርዓት ዘርግቶ ሊያስተናግድ ይችላል፡፡

ለማነኛውም ህፃናት ደህነነታቸው እንዲጠበቅ፣ ሕፃናትን መለመኛ የሚያደርጉ ወላጅ ተብዬዎች ደግሞ አደብ እንዲገዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ሆይ እነዚህ ልጆች ድንጋይ አንስተው፣ እሳት ጭረው ከመነሳታቸው በፊት ሳይቃጠል በቅጠል መባል ያለበት ይመስለኛል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ ፎቆች እየበቀሉ፣ ከስር ግን ህፃናት ከስብዕና ውጭ እየሆኑባት ያለች መሆኑን ለመረዳት ከላይ በገለፅለኳቸው ቦታዎች መገኘት በቂ ነው፡፡ ወዳጃችን ከበደ ካሣ በቅርቡ እንደተረዳው የባለስልጣኖቻችን መኪና ከውጭ እነርሱን እንዳናይ የሚጋርደ ቢሆንም፤ እነዚህን ልጆች ለማየት የሚጋርዳቸው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በትላንት ምሽት ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተሰፋዬ የሚመሩት የተማሪዎች መመገቢያ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ነበር፡፡ ይህ መድረክ የአድርባይ ማስታወቂያ ስራተኞችን ከማሳየት ባለፈ አንድም ፋይዳ አላገኘሁበት፡፡ በጣት ከሚቆጠሩት የግል ድርጅቶች ውጭ ከፍተኛውን ድጋፍ ያደረጉት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌ፣ መብራት ኃይል፣ የክልል መንግስታት፣ ወዘተ በአብዛኛው የመንግሰት ተቋሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ያለምንም ተጨማሪ እዩልኝ ሰሙልኝ ሊያድርጉ የሚችሉት የህዝብ ሀብት ባለቤቶች ናቸው፡፡ መንግሰት የሚያስተዳድራቸው፡፡ ሰለዚህ ኢትዮጵያ አገራችን እነዚህን ልጆች አብልታ ማስተማር ትችላለች የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ የግሎቹ ድጋፍ ሊያደርጉበት የሚችሉበት እድል ሊመቻች ይገባል፡፡ ለማነኛውም ትላንት ለምግብ ገንዘብ የተሰበሰበላቸው ከወላጆች ወይም ከአሰዳጊዎች ጋር ሆነው ምግብ ሳይበሉ በትምህርት ገበታ ለሚገኙት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ከላይ በመግቢያ ያነሳኋቸው ሕፃናት ልጆች ከዚህ በከፋ ደረጃ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በበሩ ላይ ያሉትን ልጆች ቢታደግ የበለጠ ያስመሰግነዋል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ፡፡ ይህ ሁሉ የምለው መንግስት ካለ ብዬ ነው…….
“የሕፃናት ጉዳይ ሁሉንም ይመለከታል – ከሠይጣን በስተቀር!!!”

ግርማ ሠይፉ ማሩ

0Shares
0